ከሁለት ቀናት በኋላ አሮጌ በምንለው 2015 ዓ.ም. የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ክዋኔዎች የተካሄዱበትና በርካታ ተግዳሮቶች የታዩበት ዓመት ነበር፡፡ ለተከታታይ ዓመት የአገሪቱ ትልቅ ችግር ሆኖ የቆየው የዋጋ ንረት በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም የአገሪቱ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖ ዓመቱ ተጠናቋል፡፡ ከወቅታዊ የአገሪቱ ዋጋ ንረት አኳያ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደገለጹትም፣ በ2015 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደር በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው ይኼው መረጋጋት ያልታየበት የዋጋ ንረት ነው፡፡
በተለይ እንደ ጤፍ፣ ስንዴና የመሳሰሉ ምርቶች በከፍተኛ ደረጃ ዋጋ ጭማሪ ያሳዩበት በ2015 በጀት ዓመት ነው፡፡ መስከረም 2015 መጀመርያ ላይ ከስድስት ሺሕ ብር በታች ይሸጥ የነበረ አንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ ለመጀመርያ ጊዜ ከ10 ሺሕ ብር በላይ ዋጋ ያወጣው በ2015 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህ የጤፍ ዋጋ በዓመቱ ማጠናቀቂያ የመጨረሻ ሳምንት ላይ ሲሆን፣ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ እስከ 15 ሺሕ ብር ሊደርስ መቻሉ፣ የዋጋ ጭማሪ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከዕጥፍ በላይ እንደደረሰ ያመለክታል፡፡
የስንዴ ገበያም በተመሳሳይ ከፍተኛ ዋጋ የተመዘገበበት ዓመት ይኼው 2015 ዓ.ም. ነው፡፡ ከፀጥታና አለመረጋጋት ጋር በተያያዙ የተፈጠሩ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችም የዋጋ ንረትን ከማባባስ ዓይነተኛ መሆኑን የሚጠቅሱት የኢኮኖሚው ባለሙያ አቶ አወት ተክኤ፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እንዳይስፋፉ ጭምር ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በ2015 በጀት ዓመት ለዋጋ ንረቱ መባባስ በተደጋጋሚ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች ባሻገር፣ መንግሥት የወሰዳቸው የፖሊሲ ዕርምጃዎች ለዋጋ ንረቱ አስተዋጽኦ የነበሩ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ የኢኮኖሚ የነዳጅ ጭማሪና ሌሎች የመንግሥት የፖሊሲ ውሳኔዎችም ለዋጋ ንረቱ የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደነበራቸው የሚያመለክቱት አቶ አወት፣ ይህ የዋጋ ንረት በቀጣይ ዓመትም እንዳይተላለፍ ለችግሩ መንስዔ የነበሩት፣ ለምሳሌ የፀጥታና ያለ መረጋጋቶች መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ውሳኔዎችን በአግባቡ መተግበር ለዋጋ ንረት መርገብ መፍትሔ ሊሆኑ ይገባል፡፡
የተንገራገጨው የወጪ ንግድ
በዓመቱ ውስጥ ዓበይት ኢኮኖሚዊ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አፈጻጸም አንዱ ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ የወጪ ንግድ በዕቅድ ልክ መከናወን ያልተቻለበት ነው፡፡ መንግሥት በ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት 5.4 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ዕቅድ የያዘ ቢሆንም፣ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ 3.9 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ይህም ከዕቅዱ አንፃር 25 በመቶ፣ እንዲሁም ከ2014 ዓ.ም. አፈጻጸም አንፃር ሲታይ ደግሞ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ዶላር ቅናሽ ያሳየበት ዓመት ነው፡፡
ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ የዓለም ገበያ ዋጋ መውረድ አንድ ምክንያት ቢሆንም፣ በአገር ውስጥ ካለው አለመረጋጋትና ብልሹ አሠራሮች፣ እንዲሁም በችግሮች የተተበተበው የግብይት ሥርዓቱ የወጪ ንግዱን በተያዘው ዕቅድ ደረጃ ማሳካት እንዳላስቻለም የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ የወጪ ንግድ ምርቶችን ከቦታ ቦታ ማዘዋወር አለመቻሉና በቂ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ባለመቻሉ የተፈጠረ ክፍተት መሆኑንም የሚገልጹ አሉ፡፡
በአንፃሩ ግን በ2015 በጀት ዓመት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መገኘቱን የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያሳወቀ ሲሆን፣ 269 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውም ታውቋል፡፡ እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ኤክስፖርት 148.3 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱንና በበጀት ዓመቱ ለ67 ሺሕ የሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩ የተለገጸበት ዓመት ነው፡፡ ከረሚታንስ የተገኘ ገቢን በተመለከተም በዓመቱ ከ3.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ፕሮግራምና የሚፈለገው 20 ቢሊዮን ዶላር
በ2015 በጀት ዓመት ዓበይት ኢኮኖሚያዊ ክንውኖች ተብለው ከሚጠቀሱ ውስጥ አዳዲስ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይዟል የተባለው ሁለተኛው አገር በቀል ኢኮኖሚ ፕሮግራም ዝግጅት መጠናቀቁና ከዚህ ጋር ተያይዞ ፕሪግራሙን ለማስፈጸም ዓለም አቀፍ ገንዘብ ተቋማት ጋር ድርድር የሚጀምር መሆኑ መገለጹ ነው፡፡ ይህንን ፕሮግራም ለማስፈጸምና ለመልሶ ማቋቋሚያ ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡ ይህንንም የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ድርድር የሚጀምር መሆኑ የተገለጸውም በዚህ ዓመት ነበር፡፡ መንግሥት በዚሁ ድርድር ከገንዘብ ድጋፉ ባሻገር፣ ሽግሽግ እንዳደረገበትም ጥያቄ የሚያቀርብበት ድርድር ለማካሄድ በአሁኑ ወቅት ዝግጅት እያደረገ ሲሆን፣ ይህንን ድጋፍ ለማግኘትም ትልቅ ተስፋ ያለ መሆኑ መገለጹም አይዘነጋም፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ለሪፖርተር ሲገለጹ እንደነበረው ደግሞ፣ የዚህ የገንዘብ ድጋፍ መገኘት የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ የሚለውጥ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ27.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዕዳ ያለበት ናት፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንደተሰማው የኢትዮጵያን ዕዳ ክፍያ ለአንድ ዓመት ለማራዘም ስምምነት ላይ መድረሱም አይዘነጋም፡፡ የዓለም ባንክ አዲሱ ፕሬዚዳንት ከተሾሙ በኋላ የመጀመርያ ጉዟቸውን ኢትዮጵያ በማድረግ፣ ከመንግሥት ጋር ያደረጉት ውይይትም ኢትዮጵያ ፍላጎቷን የማስረዳት ዕድል ያገኘችበት እንደሆነም ይታመናል፡፡ ፕሬዚዳንቱም በተለያዩ መስኮች ኢትዮጵያን ለመደገፍ ዝግጁ ስለመሆናቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የብሪክስ አባላት
በዓመቱ የመጨረሻ ወር ላይ ከተሰሙ አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መካከል ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን ውሳኔ መተላለፉ ነው፡፡ ከ40 በላይ ጥያቄ ካቀረቡ አገሮች መካከል የስድስቱን የአባልነት ጥያቄ ያፀደቀው ብሪክስ ኢትዮጵያን አንዷ ማድረጉ ለኢትዮጵያ እንደ መልካም ዕድል የታየ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ብሪክስ አባል አገር ሆና መመረጥ ታሪካዊ የሚባልና የዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት መሆኑም ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ዙሪያ የተለያዩ አመለካከቶች የሚንፀባረቁ ሲሆን፣ እንደ ቆስጠንጢኖስ በረሃ (ዶ/ር) ያሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በአባልነት መታቀፍ ጠቃሚ ቢሆንም፣ በዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን በኢትዮጵያ ብዙ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ነገሮች አሉ ይላሉ፡፡ በተለይ ሥር እየሰደደ ያለውን ሙስና መከላከልና የግል ዘርፉን እንዲጠናከር ማድረግ የግድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ሌላ የብሪክስ አባል አገሮች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያደርጉት የኢንቨስትመንት መጠን ስለሚያድግ ለዚህ ዝግጁ መሆኑ የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ሊያስገኝ ይችላል የሚለው ጉዳይ ላይ በተለየ አተያይ ያላቸው የኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ያሬድ ኃይለመስቀል፣ የብሪክስ ቡድን ከኢኮኖሚው በላይ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ምናልባትም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗም ከብሪክስ በተቃራኒ ያሉ አገሮች ጫና ያሳድሩባታል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ በእሳቸው እምነት የአፍሪካ የንግድ ቀጣና ስምምነት ላይ የበለጠ መሥራቷ አትራፊ ያደርጋታል ይላሉ፡፡
ዲጂታል ግብይት
በ2015 በጀት ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ እንዲተገበር ከተደረጉ ኢኮኖሚያዊና ዘመናዊ ክዋኔዎች መካከል የነዳጅ ግብይት በዲጂታል የክፍያ ዘዴ እንዲከናወን ተወስኖ በተግባር ላይ መዋሉ ነው፡፡ የዲጂታል የነዳጅ ግብይት ከተጀመረ አንስቶም ከ81 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት መፈጸም መቻሉ ታውቋል፡፡
መንግሥት የነዳጅ ግብይት በዘመናዊ የግብይት ዘዴ እንዲካሄድ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ፣ በአዲስ አበባ ከሚያዝያ 16 ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።
ነዳጅን በዲጂታል ግብይት መፈጸም መንግሥት በከፍተኛ ድጎማ የሚያስገባውን ነዳጅ ከብክነት ለመከላከል፣ ቀልጣፋና ጊዜ ቆጣቢ አገልግሎት ለመስጠት፣ እንዲሁም ለቁጥጥር አመቺ እንዲሆን በማሰብ የወሰነው ውሳኔ ነው፡፡ አገልግሎቱ በተጀመረበት የመጀመርያ ሳምንት የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢገጥመውም እያደር ግን መሻሻል እያሳየ የሄደ ስለመሆኑም መገንዘብ ይቻላል። በዚህ ግብይት ውስጥ በአሁኑ ወቅት ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ እየተሳተፉ ሲሆን፣ ከ30 በላይ ባንኮችና የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት በዚህ የነዳጅ ግብይት ሥርዓት ውስጥ ለመግባት አመልክተው ውሳኔ እየጠበቁ ነው፡፡
ከዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በ2015 በጀት ዓመት ከፍተኛ የሚባል ሥራ የተሠራበት ነው፡፡ በብዙ ባንኮች የገንዘብ ዝውውሮች እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአጠቃላይ የገንዘብ እንቅስቃሴው ከ64 በመቶ በላይ የሚሆነው በዚሁ የዲጂታል የክፍያ ዘዴ መከናወኑ በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡
የፋይናንስ ዘርፉ በ2015 ዓ.ም.
በተጠናቀቀው 2015 ከሌሎች ዘርፎች በተለየ የተለያዩ ክንዋኔዎች ያታዩበት ዘርፍ ቢኖር የፋይናንስ ዘርፉ ነው፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እንደ ቀደሙት ዓመታት ሁሉ ዕድገት በማስመዝገብ ቀጥሏል፡፡ የአገሩቱ ባንኮቹ ቁጥር ወደ 32 ያደገበት ሲሆን፣ እነዚህ ባንኮች በአጠቃላይና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ከ78 ቢሊዮን ብር በላይ ያተረፉበት ዓመት ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ ለየት ባለ ሁኔታ የትርፍ ምጣኔውን የቀነሰው መንግሥትታዊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡
ከባንኩ መረጃ መገንዘብ እንደሚቻለው የዘንድሮው (የ2015) በጀት ዓመት የትርፍ ምጣኔው ከቀዳሚው ዓመት በሰባት ቢሊዮን ብር ቀንሶ መገኘቱ ነው፡፡ ባንኩ በ2014 በጀት ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 27 ቢሊዮን ብር አትርፎ የነበረ ሲሆን፣ በ2015 ዓ.ም. ግን 20 ቢሊዮን ብር ማትረፉ የዘንድሮ አፈጻጸሙን ለየት አድርጎታል፡፡
የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውም ቢሆን በዋጋ ንረቱ ከፍተኛ ተግዳሮቶት ውስጥ ያለፈ ቢሆንም፣ ከ22.7 ቢሊዮን ብር በላይ ዓረቦን የሰበሰቡበት ዓመት ነበር፡፡
ይህም ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ ከ36.3 በመቶ ብልጫ ያለው ዓረቦን ማሰባሰብ የተቻለበት ዓመት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ታሪክ የዓረቦን መጠን ከፍተኛ የሚባል ዕድገት የተመዘገበበት ዓመት ነው፡፡
የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ዘንድሮ ከፍተኛ የዓረቦን ዕድገት የተመዘገበ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ካለው የዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ እያሻቀበ የመጣው የመለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋ ዕድገት ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ሁኔታ ከመጉዳቱም በላይ፣ አትራፊም ሆኖ ለመቀጠል አስቸጋሪ እንደሚሆን መግለጹም አይዘነጋም፡፡
ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ አንፃር በ2015 ዓ.ም. ሊጠቀሱ ከሚችሉት ክዋኔዎች መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ ገዥ የተሰየመበት ዓመት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ከአራት ዓመት በላይ ገዥ ሆነው ያገለገሉት ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ ምትክል አቶ ማሞ ምሕረቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው እንዲያገለግሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙበት ዓመት ነው፡፡
አዲሱ ገዥ ከተሾሙ በኋላ ባንኩ የተለያዩ መመርያዎች ያወጣ ሲሆን፣ የዋጋ ንረትን ተፅዕኖ ለመቀነስ ያወጣው የገንዘብ ፖሊሲ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ በዚህም ፖሊሲው ባንኮች የብድር ምጣኔ ዕድገት በ14 በመቶ እንዲገደብ ወስኗል፡፡ በውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ጋር በተያያዘም ላኪዎቹ ከሚያስገቡት የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶውን ብቻ እንዲጠቀሙ የሚደነግገው መመርያ ተሻሽሎ ወደ 40 በመቶ ከፍ እንዲል የተወሰነውም በዓመቱ መጠናቀቂያ አካባቢ ነው፡፡
ከዚህ ሌላ ለመጀመርያ ጊዜ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለተሽከርካሪ የሚያስከፍሉት አረቦን ዝቅተኛ ወለል በማስቀመጥ ተግባራዊ እንዲሆን የወሰነበትም ዓመት ነው፡፡
አነጋጋሪው ግብር
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የንብረት ግብር አካል ነው የተባለው የቤት ጣሪያና ግድግዳ ግብር ክፍያ ጉዳይ ተጠቃሽ ነው፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር ወስኖ ወደ ሥራ የገባው ይህ የግብር ዓይነት፣ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ጥያቄ ማስነሳቱም ይታወቃል፡፡ ሆኖም አስተዳደሩ በተቀመጠው ተመን መሠረት ግብሩ መከፈል አለበት ብሎ የቤት ባለቤቶች ክፍያውን እንዲከፍሉ እያደረገ ነው፡፡
ይህ የግብር ዓይነት ማመላከታቸው 800 ሺሕ የሚጠጋ ግብር ከፋይ እንዳሉም ተጠቁሟል፡፡ አስተዳደሩ ከዚህ የግብር ዓይነት ብቻ በዓመት ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኘለት ነው፡፡
የግብር ገቢ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች 450 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 442 ቢሊዮን ብር ማሳካት መቻሉን ገቢዎች ሚኒስቴር ገልጿል።
ከዚህ ከተሰበሰበው ግብር ውስጥ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች 183.9 ቢሊዮን ብር ታቅዶ 176 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉ ተጠቅሷል፡፡ በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ ሚኒስቴሩ 529 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡ በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ከ107 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ ገቢ ውስጥ ከታክስ 77.3 ቢሊዮን ብር፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 11.3 ቢሊዮን ብር፣ ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት 13.6 ቢሊዮን ብር ሲሰበስብ፣ ቀሪው ከሌሎች ዋና ዋና የገቢ ምንጮች የተሰበሰበ ነው ተብሏል፡፡ አስተዳደሩ የ2015 በጀት ዓመት የገቢ አፈጻጸም ከ2014 ጋር ሲነፃፀር የ37.83 ቢሊዮን ብር ወይም የ53.9 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ መረጃ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከካሽ ሬጅስተር ጋር በተያያዘ ችግር በፈጠሩ ከ6,600 በላይ ሰዎች ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን፣ ከ800 በላይ ሰዎች ደግሞ በሕግ ተጠያቂ አድርጌያለሁ ማለቱም ተገልጿል፡፡ የአስተዳደሩ የቀጣይ ዓመት (2016 በጀት ዓመት) ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱንም አስታውቋል።
የግዙፎቹ ኩባንያዎች ገቢ
በኢትዮጵያ የቢዝነስ ሥራዎች የመንግሥት ኩባንያዎችም የሚሳተፉበት ነው፡፡
ከፍተኛ ገቢና ትርፍ ካላቸው የአገራችን ትልቅ ኩባንያዎች ውስጥ በመንግሥት እጅ የሚገኙ ኩባንያዎች ከፊት ተርታ የሚሠለፉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ግዙፍ መንግሥታዊ ኩባንያዎች መካከል ዓመታዊ አፈጻጸማቸውን ካሳወቁት ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮም ይጠቀሳሉ፡፡
በኩባንያዎቹ ሪፖርት መሠረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጀት ዓመቱ 6.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንና ይህ የገቢ መጠንም ካለፈው ዓመት ሲነፃር የ20 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ 11 አዳዲስ የመንገደኞች አውሮፕላን በመረከብ አጠቃላይ የመንገደኞች አውሮፕላንን ከ140 በላይ ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው፣ በሌላ በኩል ሁለት የመንገደኛ አውሮፕላኖችን በምሕንድስና ወደ ጭነት በመቀየር የጭነት አውሮፕላኖችን ቁጥር 15 ማድረሱንም ገልጿል፡፡
አየር መንገዱ በጀት ዓመቱ 13.7 ሚሊዮን ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ መንገደኞችን እንዲሁም 723 ሺሕ ቶን ጭነት ማጓጓዙን ተናግረዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁሉ ኢትዮ ቴሌኮምም ከፍተኛ ገቢ ካስመዘገቡ የመንግሥት ተቋማት መካከል አንዱ ያደረገው በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከ75 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማሰባሰብ መቻሉ ነው፡፡
በ2014 በጀት ዓመት በ131 መሥሪያ ቤቶች ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ በወቅቱ ያልተወራረደና ያልተሰበሰበ ሒሳብ መኖሩ በኦዲት መረጋገጡን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታወቀ።
ያልተወራረደ ሒሳብ
በበጀት ዓመቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀረቡ ሪፖርቶች መካከል በጄኔራል ኦዲተር የቀረበው ይገኝበታል፡፡ በዚህ ሪፖርት ብዙዎችን ያነጋገረው ጉዳይ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብን በተመለከተ፣ ኦዲት በተደረጉ 131 መሥሪያ ቤቶች በጠቅላላው ከ15 ቢሊዮን 125 ሚሊዮን ብር በላይ በወቅቱ ያልተወራረደና ያልተሰበሰበ ሒሳብ መኖሩን አመልክቷል፡፡
በወቅቱ ያልተወራረደ ውዝፍ አለባቸው ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ የጤና ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስና የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ይገኙበታል፡፡
ከውጭ ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ከሚጠቀሱ አገሮች መካከል ቻይና አንዷ ናት፡፡ በኢትዮጵያ ከ1,800 በላይ የቻይና ኩባንያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህ ኩባንያዎች ከ4.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት ያላቸው ናቸው፡፡
ቻይና በቀጣይም ኢትዮጵያን በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች መደገፏን እንደምትቀጥል ጠቅሰው፣ ኩባንያዎችም የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ይሠራል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም፣ የ2015 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም በሚቀጥለው ዓመት የዓለም ዕድገት 1.4 እንደሚሆን ሲገምት፣ የኢትዮጵያ ዕድገት 6.4 እንደሚሆን ተንብዮ፣ በፈጣን ዕድገት ላይ ካሉ የዓለም አገሮች ተርታ አስቀምጧታልም ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ ስንዴን ጨምሮ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል። የዋጋ ንረት በዓለም ላይ ‹‹ወረርሽኝ›› ሆኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ሲሉ አስረድተዋል።
በመሆኑም ይህንን ዓለም አቀፍ ችግር ለመከላከልና ለመቋቋም የተለያዩ ተግባራትን መከናወናቸውን ጠቅሰው በማዳበሪያ፣ በነዳጅና በሌሎችም ላይ መንግሥት ድጎማ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በዚህም የዋጋ ግሽበቱን ከ37 በመቶ ወደ 30 ዝቅ ማድረግ መቻሉን አስታውሰው፣ በቀጣይም ለመቀነስና ለመቆጣጠር እንሠራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ ለውጡ ሲመጣ የዕዳ ጫና 59 በመቶ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን ላይ 38 በመቶ ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው፣ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ከ30 በመቶ በታች ለማድረስ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የፋይናንስ ተቋማትና ገቢዎች
የፋይናንስ ተቋማት በዚህ ዓመት ገጠመኝ ብለው ይፋ ካደረጓቸው ተግዳሮቶች መካከል የገቢዎች ሚኒስቴር ለካፒታል ማሳደጊያ የዋለ የትርፍ ድርሻ ላይ ታክስ እንዲከፍሉ ጥያቄ ያቀረበላቸው መሆኑ ነው፡፡ ሚኒስቴሩ ጥያቄውን ያቀረብኩት ሕጋዊ በሆነ መንገድ ነው ቢልም፣ የፋይናንስ ተቋማቱ ግን ለካፒታል ማሳደጊ የዋለ የትርፍ ድርሻ ላይ ታክስ መጠየቅ የለብንም በማለት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዳቸው ታውቋል፡፡ በገቢዎች ሚኒስቴር ለካፒታል ማሳደጊያ ስለመዋላቸው በሕግ በተደነገገው ድንጋጌ መሠረት መፈጸማቸውን ስለሚያመላክት ጥያቄው ትክክል በመሆኑ ሊከፍሉ ይገባል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና ዋጋ የጨመረበት ዓመት
በበጀት ዓመቱ በዋናነት ከሚጠቀሱ ተግዳሮች ባሻገር፣ እንደተግዳሮች መጠቀስ ካባቸው ውስጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከመ መምጣቱ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በወራት የሚቆጠር ጊዜ ወረፋ መጠበቅ ግድ ያለበት ዓመት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት ከእጥፍ በላይ ልዩነት ያሳየበትም ዓመት ነው፡፡
በጥቁር ገበያ ለመጀመርያ ጊዜ የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ ከ100 ብር በላይ መድረሱም ተጠቃሽ ነው፡፡ በዓመቱ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል 38 የሚሆኑ ምርቶች ወደ አገር እንዳይገቡና ለእነዚህም ምርቶች ባንኮች የውጭ ምንዛሪ እንዳይፈቅዱ የተወሰነባቸውም በዚህ ዓመት ነው፡፡
ለመንግሥት መግባት ያለበት ገንዘብም ሊከፈለን ይገባል በማለት በአቋሙ ፀንቷል፡፡ ከፋይናንስ ተቋማቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ገቢዎች ሚኒስቴር ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ከባንኮች ደግሞ በቢሊዮን የሚገመት የትርፍ ድርሻ ክፍፍል የታክስ ክፍያ ይጠብቃል፡፡
የተጨማሪ እሴት አዋጅ ረቂቅ
ከ20 ዓመታት በላይ ሥራ ላይ የነበረውን የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ለማሻሻል አዲስ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለውይይት የቀረበው በዚህ ዓመት ነው፡፡ አዳዲስ ድንጋጌዎችን የያዘውና እንደ ባንክና ኢንሹራንስ ያሉ ኩባንያዎች፣ እንዲሁም የቴሌኮም ኩባንያዎች ለሚሰጡት አገልግሎት ክፍያ ተጨማሪ እሴት ታክስ መሰብሰብ ግዴታ ስለመሆኑ የሚደነግገው ይህ ረቂቅ ብዙዎችን ያነጋገረ ቢሆንም፣ የረቂቁ ዝግጅት በመጠናቀቁ በአዲስ ዓመት ይፀድቃሉ ተብለው ከሚጠበቁ አዋጆች መካከል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ሲሚንቶ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በገበያ ውስጥ ከፍተኛ እጥረትና የዋጋ ጭማሪ ካሳዩ ምርቶች መካከል አንዱ ሲሚንቶ ነው፡፡ መንግሥት ይህንን የሲሚንቶ የተበላሸ የገበያ ሥርዓት ያስተካክልልኛል ያላቸውን ከአምስት በላይ የተለያዩ መመርያዎችንና ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን፣ አሁንም ገበያው ውስጥ ያለው ችግር ሳይፈታ ዓመቱ ተጠናቋል፡፡