Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለበዓላት በሚሠሩ ሙዚቃዎች ጎልተው የሚነሱት ማኅበረሰባዊ ፋይዳ ያላቸው ጉዳዮች ናቸው›› አማኑኤል ይልማ፣ የሙዚቃ ባለሙያ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹‹ወንድ ልጅ አበባ አየሽ ሆይ ብሎ ሲጨፍር ታዘብኩ›› እንዳሉት ሁሉ፣ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም መጥቢያ ለቴዲ አፍሮ በሠራው ‹‹አበባ አየሽ ሆይ›› ሥራ ይታወሳል፡፡ ብርሃኑ ተዘራና ማዲንጎ አፈወርቅ የተጣመሩበትን ‹‹አንበሳው አገሳን›› በዚያው ሰሞን በመድገም ትልቅ ዝናን አትርፏል፡፡ እንደ ‹‹ፔንዱለም›› ባሉ ፊልሞች ብቅ ብሎ ትወናን ሞክሯል፡፡ ብዙ ባሳለፈበት የሙዚቃ ዘርፍ ግን ከአስቴር አወቀ እስከ ኤፍሬም ታምሩና ከሌሎችም አንጋፋ ሙዚቀኞች ጋር በመሥራት ይታወቃል፡፡ እንደ ጃኪ ጎሲ ላሉ ወጣት ሙዚቀኞች ወደ ሕዝብ መቀላቀያ ሥራዎችን የሠራው ይህ የሙዚቃ ሰው በግጥም፣ በዜማና በሙዚቃ ቅንብሩ በቅርብ ዓመታት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ተጠቃሽ የሆኑ ሥራዎችን በመሥራት ይታወቃል፡፡ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ምሩቁ የሙዚቃ ሰው አማኑኤል ይልማ በቅርብ ጊዜ የወጣውን በየኛ የሴቶች የሙዚቃ ቡድን የተሠራውን ‹‹ሆ ብለን መጣን›› የሚል ተወዳጅ የበዓል ሙዚቃ ያበረከተም ነው፡፡ የበዓላት ሙዚቃዎችን በተመለከተ ሰፊ ትንተና የሰጠበት ከዮናስ አማረ ጋር ያደረገው ልዩ የበዓል ቆይታም እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- በዓላትና ሙዚቃ ለምን ጥብቅ ቁርኝት ፈጠሩ?

አማኑኤል፡- አብዛኞቹ በዓላቶቻችን ከሃይማኖት ጋር የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ በክርስትናው እምነት የጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ መወለድ ወይም ወደ ምድር መምጣትን፣ በምድር መመላለሱን፣ ስቅለቱን፣ ሞቱን፣ ትንሳዔውንና በስተመጨረሻም ማረጉን በተመለከተ ብዙ ትስስር ያላቸው በዓላት አሉ፡፡ የተሰቀለበት መስቀልና ጥምቀቱ በክርስትና በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጥብቅ የሚከበሩ መንፈሳዊ ክብረ በዓላት ናቸው፡፡ የሙዚቃው አንዱ መሠረታዊ ምንጭም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ከቅዱስ ያሬድ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ያሬድ በመንፈስ የተሰጡት ሦስት ዓይነት የዜማ መደቦች አሉ፡፡ ግዕዝ፣ እዝልና አራራይ ይባላሉ፡፡ ድፋት፣ ቅናት፣ ወዘተ እየተባለ አሥር የዜማ ክፍሎች ኖረውት ልክ እንደ ሙዚቃ ኖታ የተጻፈ፣ ለሙዚቃ መሠረት የሆነ ዕውቀት በውስጡ ያለው ነው፡፡ ይህ ሁሉ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ ዝማሬዎች መፍለቂያ ብቻ ሳይሆን፣ በሒደት ለዓለማዊ ሙዚቃዎችም መሠረት የጣለ ነው፡፡ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ ‹‹ቸርች ኤንድ ኢትዮጵያን ሚዩዚክ›› የሚባል ትምህርት ይሰጠን ነበር፡፡ ከዚያ ትምህርትም ሆነ ከልምድ የተረዳሁት በዓላትና ሙዚቃ የማይነጣጠሉ የሆኑት፣ የሙዚቃችን ምንጭ ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው በመሆኑ ነው፡፡

በተለይ በፆም ጊዜ በመሰንቆና በበገና ብዙ መንፈሳዊ ሙዚቃዎች ተሠርተዋል፡፡ እነ ዓለሙ አጋ በበገና ይጫወቱ ነበር፡፡ እንዲሁም እነ ዓለማየሁ ፋንታን በመሰንቆ እናስታውሳቸዋለን፡፡ ዘለሰኛ የምንለውን ጨምሮ ለፆም ወቅቶች የሚደመጡ የበገናና የመሰንቆ መንፈሳዊ ሙዚቃዎች ከጥንት እስከ ዛሬ አገልግሎት ላይ አሉ፡፡ የፆሙ ወቅት አልፎ በዓላት ሲመጡ ደግሞ የሙዚቃው ሥልት በዘመናዊ መንገድ የበዓላት ድግስ ማድመቂያ ሆኖ ይመጣል፡፡ በዓላትና ድግሶችን በልዩ ሁኔታ ለማድመቅ ተብለው የሚሠሩ ሙዚቃዎች ይኑሩ እንጂ፣ በኢትዮጵያ እያንዳንዱ የዕለት ተዕለት አኗኗር ባህላችን ሁሉ ከሙዚቃ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው፡፡ ሲታረስ፣ ሲዘራ፣ በደቦ ሲታጨድም ሆነ ሲወቃ ሙዚቃ አለ፡፡ ቤት ውስጥ ጉድ ጉዱ ሁሉ፣ ጌሾ ወቀጣው ወይም ልብስ ማጠቡና ምስር መልቀሙ ሁሉ በእንጉርጉሮና በዜማ ነው፡፡ ሕፃናት ሲያለቅሱ ማባበያው እሹሩሩ ዜማ ነው፡፡ የታዳጊዎች ጨዋታም በሙዚቃ ነው፡፡ እረኝነቱ ሁሉ በዋሽንት ዜማ ነው፡፡ ለለቅሶ ሳይቀር ሙሾ አለን፡፡ በኢትዮጵያ እያንዳንዱ የኑሮ እንቅስቃሴ ሙዚቃ የሚቀዳበት ነው፡፡ በዓላት ወይም ሠርግ ሲመጡ ጠብቆ መጨፈሩ ልዩ ቦታ ቢሰጠውም፣ በየገጠመኙ ግን ከሙዚቃ ጋር የተሳሰረ ሕይወት ነው የምንኖረው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በበዓላት ወቅት የሚሠሩ የሙዚቃ ሥራዎች ስሜት የሚቀሰቅሱና ፍፁም የማይረሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሥራዎች በዓላቱን በየዓመቱ የሚያስታውሱ ብቻ ሳይሆኑ፣ ፍፁም የሚነሽጡና ለየት ያለ ለዛ ያላቸው ናቸው፡፡ ይህ ከምን የመነጨ ነው?

አማኑኤል፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ለበዓላት ተብለው የሚሠሩ ሙዚቃዎች በሚያስገርም ሁኔታ ብዙዎቹ ተመሳሳይ ቅኝት የሚከተሉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ አራት ዓይነት የሙዚቃ ቅኝቶች እንዳላት ይታወቃል፡፡ እነሱም ባቲ፣ ትዝታ፣ አንቺ ሆዬና አምባሰል ናቸው፡፡ ከእነዚህ አራት የሙዚቃ ቅኝቶች መካከል ግን በሚያስገርም ሁኔታ አንቺ ሆዬ የሚባለው ቅኝት ነው ለኢትዮጵያ የበዓላትና የሠርግ ሙዚቃዎች መሠረት የሆነው፡፡ የያሬድ የዜማ መደቦች ለሙዚቃው የመጀመሪያ መሠረት ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ተወስኖ የቆየው መንፈሳዊ ዜማ ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ ወደ አዝማሪዎች ተሸጋገረ፡፡ ይህ ደግሞ የሙዚቃ ቅኝቶችን እየፈጠረ በሒደት አንቺ ሆዬ የሚባለው ለሠርግና ለበዓላት ዋና ማድመቂያ ሆኖ ተስፋፋ፡፡ አንቺ ሆዬ አሁን በየበዓላቱ የምናያቸው ዳቦው፣ ጠላው፣ ዶሮው፣ ቅርጫው፣ ድግሱና ጭፈራው ሁሉ ተዋሕዶ የሚቀርብባቸው ኦውዲዮ ቪዡዋል የሙዚቃ ሥራዎች የዚህ ሥልት ውጤቶች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የበዓላት ሙዚቃዎች ከሌሎች ሙዚቃዎች የሚለዩበት የሙዚቃ ጣዕም ምንድነው?

አማኑኤል፡– የበዓላት ሙዚቃዎች ሙዚቃዊ ለዛ ወደ ሠርግ ያደላ ነው፡፡ ሁለቱም የአንቺ ሆዬ ቅኝት ውጤቶች መሆናቸው እጅግ ያመሳስላቸዋል፡፡ ሰው ለይቶ ለማጣጣም ባይችል እንኳን ወደ ጆሮ ሲገቡ የሠርግ ሙዚቃ ዓይነት ቃና ነው ያላቸው፡፡ በዜማም ደረጃ አራራይ ከሚባለው የዜማ መደብ ውስጥ ነው ብዙ የበዓላት ሙዚቃዎች የሚመደቡት፡፡ አራራይ የማሳዘንና የተስፋ ስሜት የሚፈጥር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በበዓላት ወቅት የታመመ እንዲድን፣ ፍቅርና መተሳሰብ እንዲመጣ፣ የታሰረ እንዲፈታ፣ ጦርነትም እንዲቆም መልካም ምኞቶችን የሚያስተላልፉ ሙዚቃዎች ናቸው የሚደመጡት፡፡

ሪፖርተር፡- የበዓላት ሙዚቃዎች ዕድገት በኢትዮጵያ ምን ይመስላል?

አማኑኤል፡- የበዓላት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ዕድገት ከቴአትር ቤቶችና ኦርኬስትራዎች መስፋፋት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፡፡ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ በተስፋፉት የቴአትር ቤቶች፣ እንዲሁም በጦር ሠራዊትና በፖሊስ ውስጥ የተደራጁ የኪነ ጥበብ ቡድኖች ናቸው ሙዚቃችንን በዘመናዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች በሰፊው መሥራት የጀመሩት፡፡ አገር ፍቅር ቴአትር፣ ብሔራዊ ቴአትር፣ ራስ ቴአትርና ማዘጋጃ እያለ ነው ያደገው፡፡ ፖሊስ ኦርኬስትራ፣ ክብር ዘበኛ፣ ምድር ጦር እየተባለ በየመስኩ የተደራጁ የኪነ ጥበብ ቡድኖችም ነበሩ፡፡ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ቀደም ባሉ ጊዜያት ጀምሮ ለዘመናዊ ሙዚቃዎች መሠረት የሆኑ ሥራዎች መሠራት ጀምረው ነበር፡፡ ለምሳሌ እነ አሰፋ አባተና እነ ካሳ ተሰማ የሚጫወቷቸው ሥራዎች በቀዳሚነት ይነሳሉ፡፡

በአዝማሪዎች እየተስፋፋ የመጣው የሙዚቃ ሥራዎችን የማቅረብ ጥረት በዘመናዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች ወደ ተደራጁ ቴአትር ቤቶችና ኦርኬስትራዎች ተወራረሰ፡፡ በየቴአትር ቤቶቹ የሚቀርቡ የእነዚህ ሙዚቃ ቡድኖች የሙዚቃ ሥራዎች በሕዝቡ በጣም እየተወደዱ መጡ፡፡ በጊዜው በተለይ በዓላትን አስታከው ሁሉም የሙዚቃ ቡድኖች አዳዲስ ሥራዎችን ይዘው መምጣታቸው ተወዳጅ ነበር፡፡ በዓላትን በተለይም አዲስ ዓመትን እየጠበቁ በሙዚቃ መፎካከር ዘርፉን አሳድጎታል፡፡ በእነዚህ መድረኮች ይቀርቡ የነበሩ ለዓውደ ዓመት ተብለው የተሠሩ ሙዚቃዎችን ዛሬም ድረስ እንሰማቸዋለን፡፡ የእነ ዘሪቱ ጌታሁንና አስናቀች ወርቁ እንቁጣጣሽ ዛሬም ድረስ ተወዳጅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– አንቺ ሆዬ በተለየ ሁኔታ ለምን የበዓላት ማድመቂያ ሆነ?

አማኑኤል፡- ቅኝቱ በራሱ ኃይለኛ የሙዚቃ ስበት ያለው ነው፡፡ ገና ከመነሻው ዳን፣ ዳን፣ ዳ፣ ራ፣ ራ፣ ራ፣ ባም ባም፣ ባ፣ ራ፣ ራ፣ ም፣ እያለ ጨዋታው ሲጀምር ጆሮን ይይዛል፡፡ አ…ሂ…እያለ ሲገባ ደግሞ አብሮ ይዞህ በምቱ እየቀዘፈ ይወስድሃል፡፡ ወዲያው ነው የሠርግ የሚመስል ወይም የበዓል ቃና እንዳለው የምትለየው፡፡ አንቺ ሆዬ የበዓል ሙዚቃዎች መለያ ነው፡፡ ይህ ቅኝት ደግሞ በእነዚህ ሥራዎች ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረና እስካሁን የቀጠለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በበዓላት ሙዚቃ ዑደት ውስጥ ምንድነው እየተለወጠ፣ እየቀረ ወይም እየተጨመረ የመጣው ነገር?

አማኑኤል፡– በነገራችን ላይ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ አንቺ ሆዬ ቅኝት ነው፡፡ ነጮቹ ሳይቀሩ ገና ሲሰሙት የሚደነግጡበት ሥልት ነው፡፡ ክሮማቲክ ስኬል እንለዋለን፡፡ በሙዚቃ ስኬል ውስጥ ግማሽ ግማሽ የሆኑ ኖቶችን እየረገጠ የሚሄድ ልዩ ውበት ያለው የሙዚቃ ቅኝት ነው፡፡ ይህ ቅኝት ማንም አገር የለውም፡፡ የውጭ አገር ሰዎች የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለማወቅ ሲመጡ ይህን ሥልት ገና እንደ ሰሙት ይገረማሉ፡፡ አሊያንስ እንዲሁም የጣሊያን ካልቸር በመሳሰሉ የውጭ አገሮች የባህል ማዕከላት ስንጫወተው የሚገጥመን የውጭ ዜጎች ስሜት የተለየ ነው፡፡

በበዓል ሙዚቃዎች ውስጥ በጊዜ ሒደት እየተለወጡ የመጡ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ብዙ መልዕክቶች ተቀይረዋል፡፡ ብዙ ዓይነት ክንውኖችም ተቀይረዋል፡፡ የቡሄ በዓል ሙዚቃ ለምሳሌ ከእነ ቡሄ ዳቦው፣ ጅራፉ፣ ዱላውና ጨዋታው ጋር ነበር የሚቀርበው፡፡ አሁን ግን ያን አታገኘውም፡፡ አሲናበል ገናዬ ከገና ጨዋታ ጋር ነበር ድሮ፡፡ አሁን ግን የገና ጨዋታም ሆነ ገበጣውና ሌላው ጨዋታ ላይኖር ይችላል፡፡ የበዓላት ሙዚቃዎች በየበዓላቱ የየራሳቸው አልባሳት፣ መዋቢያ፣ ጭፈራ ወይም ጨዋታ፣ ሙዚቃ መሣሪያ፣ አበባ፣ ቄጤማ፣ ምግብና መጠጥን ጨምሮ አብረዋቸው የሚሄዱ ልዩ መገለጫዎች አሏቸው፡፡

ወጣ ያለ ወይም ቀየር ያለ ነገር ጨምሮ የበዓላት ሙዚቃን መሥራት አንዳንዴ ሊወደድ ይችላል፡፡ ለምሳሌ እኔ ኢትዮጵያ ሚሊኒየም አበባ አየሽ ሆይን በወንድ ድምፅ ከቴዲ አፍሮ ጋር ሠርቼያለሁ፡፡ ሥራው እስካሁንም ተወዳጅ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የኛ ከሚባሉት አምስቱ ሴቶች ጋር የተለየ አበባ አየሽ ሆይን ይዤ ለመምጣትም ሞክሬያለሁ፡፡ በዚህ ሙዚቃ አበባ አየሽ ሆይን ድባብ ለወጥ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ‹‹ታየኝ ታየኝ አውዳመት ጭሱ… ሰላም ፍቅር ይላል መንፈሱ›› የሚል የአገር ሰላምን የሚሰብክ ስንኝ ለማስገባት ሞክሬያለሁ፡፡         

አንድ አሥር ዓመት ቢሆነውም የፋሲል ደሞዝን ዓውደ ዓመት ሠርቻለሁ፡፡ ከአቦነሽ ጋርም ሠርቻለሁ፡፡ በእኔ ስቱዲዮ ደረጃ እንኳን ብዙ የበዓል ሥራዎችን በዘመናዊ መንገድ ለመሥራት ተሞክሯል፡፡ የበዓል ሙዚቃ ሥራዎችን አዳዲስ ነገር እየጨመሩ ወይም ለወጥ እያደረጉ ማቅረቡ ባይከፋም፣ ነገር ግን መሠረታዊ ማንነቱን በለቀቀ መንገድ ባይቀርብ ይመረጣል፡፡ ብዙ ጊዜ የበዓል ሙዚቃ በግጥሙ፣ በዜማውና በምቱ ብቻ ሳይሆን በክዋኔውም በበዓሉ ዙሪያ የሚሽከረከርና የበዓል ድባብ የሚፈጥር ነው መሆን ያለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ የተዘፈነለት በዓል የትኛው ነው?

አማኑኤል፡- አዲስ ዓመት ነው ብዙ የተዘፈነለት፡፡ የአዲስ ዓመት በዓል ሁሉንም ወገን የሚያስማማ ገጽታ አለው፡፡ ከክረምት ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ አጋጣሚ ነው፡፡ ከረመ ከሚባለው ከክረምት ነው የምንወጣው፡፡ ክረምት ደግሞ የራሱ ድባብ ያለው ነው፡፡ ዝናብ፣ ጭጋግ፣ ብርዱ ሁሉ የሚስተናገድበት ክረምት አልፎ የሚያምር ልምላሜ ወዳለው አዲስ ዓመት ነው የምንገባው፡፡ አዲስ ዓመት የለመለመው የሚታጨድበት፣ የተዘራው የሚበላበት ወቅት መምጣቱን አብሳሪ ነውና ብዙ ተስፋና ደስታ ይዞ የሚመጣ ወቅት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ለአዲስ ዓመት በዓል ብዙ መልካም ምኞት ያላቸው ሙዚቃዎች ተሠርተዋል፡፡ ከአዲስ ዓመት ውጪ ሙዚቃ መነሻው ሃይማኖት እንደመሆኑ መጠን፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆኑ በሙስሊሞች በሚከበሩ በዓላት ወቅቶች ብዙ ዓይነት ሙዚቃዎች ተሠርተዋል፡፡ በሙስሊሞች ዘንድም ምንጫቸው መንፈሳዊ ምሥጋናና አገልግሎት የሆኑ ከመንዙማና ነሺዳ ጀምሮ በሰፊው የሚሠሩ ራሱን የቻለ ሥልት ያላቸው በዓላትን የሚያደምቁ ሥራዎች አሉ፡፡ ያም ቢሆን ግን በዓላትን ማድመቂያ ተብለው የሚሠሩ ሥራዎች በበዓላት ደስታና ድባብ ከመፍጠር ውጪ መንፈሳዊ መሠረታቸውን አይለቁም፡፡ ለምሳሌ መስቀልን የተመለከተ ዘፈን ከሆነ በዓሉ ደስ ይላል መተሳሰቡ ብሎ መስቀሉን ማንሳቱ አይቀርም፡፡ ገና ከሆነ የገና ስጦታው፣ መጠያየቁ ወይም የገና ጨዋታው ብሎ የክርስቶስን ውልደት ማስታወሱ የማይቀር ነው፡፡

ሃይማኖታዊ ገቢሮችን ወደ ዓለማዊ ዘፈን ማምጣት ከባድ ነው፡፡ መስቀል፣ ልደት፣ ጥምቀት፣ ትንሳዔ መንፈሳዊ መነሻ ያላቸው በመሆናቸው ወደ ዘፈን ላምጣቸው አትልም፡፡ በእነሱ ዙሪያ ያለውን የበዓል ድባብና ክዋኔ ግን በዘፈን ማንሳት ይቻላል፡፡ በዓል የሙዚቃ ማጠንጠኛው የበዓል ድባቡ ላይ የሚሽከረከር ቢሆንም፣ ተመልሶ ደግሞ መንፈሳዊ ማንነቱን ወይም ምንጩን መልቀቅ የለበትም፡፡ በዓል የሙዚቃዎች አንድ ዓይነትና ወጥነት ያላቸው የሚመስለን ለዚያ ነው፡፡ በአንድ ዓይነት ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ በመሆናቸው ከረዥም ጊዜ በፊት የተሠራውን ጭምር ዛሬም እንደ አዲስ ነው የምንሰማው፡፡ የጥላሁን ገሠሠ ሥራ ለዚህ ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡ ክረምት አልፎ በጋ፣ መስከረም ሲጠባ እያለ የዘፈነው ዘፈን ሁሌም ስሰማው ደስ ይለኛል፡፡ ስንሰማው አድገን እስካሁንም እየሰማነው ነው፡፡ ትልቅ የበዓል ዘፈን ነው፡፡ ለአዲስ ዓመት የተዘፈነ ቢሆንም፣ ነገር ግን ደግሞ በየዓውደ ዓመቱ የመደመጥ ለዛ አለው፡፡ አንዳንዴ ለአዲስ ዓመት የተዜሙ ዘፈኖች ይሆናሉ በሌሎችም በዓላት ዋና ማድመቂያ የሚሆኑት፡፡ ስለዚህ አዲስ ዓመት የብዙ ሙዚቃዎች መነሳሻ በዓል ሊባል ይችላል፡፡  

ሪፖርተር፡- የበዓል ሙዚቃዎችን በተለየ ዜማ መሥራት ለምን አልተቻለም? በውጭ የሙዚቃ ሥልቶች መሥራት ለምን አይቻልም? ለምሳሌ በራፕም ሆነ በሬጌ ሥልት ቢሠራ ምን ችግር አለው?

አማኑኤል፡- በጭራሽ አይሆንም፡፡ ከበዓል ቃናው ላውጣው ብትል አይቻልም፡፡ እንዲያውም የማሳሳት ነገር ሊፈጠር ይችላል፡፡ በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ ይባላል፡፡ ከገና ጨዋታና ከገና በዓል ጋር የተቆራኘው አሲና በል አሲና ገናዬ ሙዚቃ ከበዓሉ ጋር አብሮ የተፈጠረ ነው፡፡ ዛሬ ላውጣው ወይም ልቀይረው ብትል አይሆንም፡፡ እኔ የእነ አበበ መለሰና የይልማ ገብረአብ አድናቂ ነኝ፡፡ ከዚያ በፊትም ቢሆን የእነ ባህሩ ቃኜ አድናቂ ነኝ፡፡ ባህሉ አንደኛ አልተነካም፡፡ በዚያው መንገድ እየሠራን ብናሳድገው ምንም ችግር የለውም፡፡ የውጭ ሰዎች ጭምር የሚደነግጡበት አንቺ ሆዬ ቅኝት አለን፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥልት ኢትዮጵያን በሙዚቃ ወደፊትም የሚያሳድግ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ሀብት ማሳደግ እየተቻለ ወደ ራፕ ገብተን ብንሠራ ዞሮ ዞሮ የሰው ጌጥ አያደምቅ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ መንገድ የትም አይደርስም፡፡ በራሱ ሥልተ ምት ሙዚቃችን ቢያድግ የተሻለ ነው፡፡

ለምሳሌ ቴዲ አፍሮ አበባ አየሽ ሆይን ዘፍኗል፡፡ ቤቱን የሠራሁት በችክችካ ነው፡፡ በዘፈኑ ላይ አንዳንድ ነገሮች ቢነሱም ሰው ግን ወዶታል፡፡ በግጥሙ ግን ሆ በል ክራሩ ሆ በል ማሲንቆ፣ ስታይ ሰው ታንቆ፣ እንዲሁም እንኳን አደረሰን ለአዲስ ዘመን ዘመን ጀመርነው ይኸው ታርቀን፣ እያለ አዲስ ሐሳብን በአበባ አየሽ ሆይ ሥልት ማምጣቱና ምቱም ለወጥ ማለቱ የተለየ ቃና ሰጥቶታል፡፡ ምቱ በሚያስጨፍርና ዘመናዊ ቅላፄ ባለው መንገድ ነው ሙዚቃው የተሠራው፡፡ ቢዮንሴ እዚህ መጥታ ትርዒት ባቀረበችበት ወቅት ስትጫወት ያየነው አጨፋፈር፣ በየክሊፖቿ ያየናቸው ሥልቶች ሁሉ የውጭዎቹ እንዲያውም ከእኛ ብዙ ነገር እንደሚፈልጉ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ የሰሜኑ አካባቢ ብቻ ሳይሆን የደቡቡ አገራችን ክፍል ሙዚቃዎችን ብንመለከት ብዙ ሀብት አለን፡፡ ያለንን ነገር ብናከብረውና ማንነቱን ሳያጣ የበለጠ አዘምነን ለመሥራት ብንሞክር የተሻለ ውጤት እናገኛለን፡፡ ዛሬ የባህል ልብሳችን ከአገር ቤት አልፎ በውጭ አገሮች ውድ ዋጋ እያወጣ ነው፡፡ ሸማኔው ልብሱን እንዳሳደገው እኛም ሙዚቃውን ብናሳድገው የተሻለ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ ብሔረሰቦች ውስጥ ራሳቸውን የቻሉ ልዩ ጣዕመ ዜማ ያላቸው ሙዚቃዎች አሉ፡፡ ብዙዎቹ በጣም ድምቅ ያሉ የበዓላት ሙዚቃዎች አሏቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል የመሥራት ዕድል የገጠመህ ይኖራልና ስለእነሱ የአንተን ሐሳብ ብታጋራን?

አማኑኤል፡- ሁሉም ለየራሳቸው አላቸው፡፡ አሸንዳ ለምሳሌ ልክ እንደ አበባ አየሽ ሆይ ሴቶች የሚጨፍሩበት በዓል ነው፡፡ ሙዚቃው፣ ግጥሙ፣ የሴቶቹ አለባበስና ውበት ስትመለከት ራሱን የቻለ ኢትዮጵያዊነትን ገላጭ ውብ ሙዚቃዊ ሀብት ነው፡፡ የሃላባ አካባቢ ባህልን ስትመለከት ደግሞ ሌላ ራሱን የቻለ ሙዚቃዊ ቃና ታገኛለህ፡፡ አረጋኸኝና ነዋይ ያሉበት ሥራ ከሃላባ ሙዚቀኞች ጋር ሠርቻለሁ፡፡

ይህ አጋጣሚ ስለሃላባና አካባቢው ብዙ ነገሮችን እንዳውቅ አድርጎኛል፡፡ ሄደህ ባህሉን፣ ጭፈራቸውን፣ እጅ አጨባጨባቸውን ሁሉ ብታይ በጣም ነው የምትገረመው፡፡ ሙዚቃዊ ቅላፄውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅኩት ቀርፀው አምጥተው አሰምተውኝ ነው፡፡ ስሠራው ልክ እንደማላውቀው የውጭ አገር ሙዚቃ ነው የሆነብኝ፡፡ ውስጡ ገብተህ ስታይ የሃላባ ባህል ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ትረዳለህ፡፡ በዚህ ሙዚቃ መነሻነት የቅርብ ሩቅ ሆኖ የኖረብንን ሃላባ ከተማን በደንብ አወቅኩ፡፡ የበርበሬ አገር ነው ሃላባ፡፡  

ጥበብ ብዙ ነገር ሊሠራ ይችላል፡፡ ለወደፊቱ እሱ ሰላም ያድርጋት እንጂ አገራችን ሰላም ከሆነች ብዙ የጥበብ ሥራዎች ወጥተው እናያለን፡፡ እጅግ ብዙ ያልተነኩና የተደበቁ የጥበብ ሀብቶቻችን ገና ይወጣሉ፡፡ እንኳን ውጭ ሄደን የሌሎችን ሀብት ልንመኝ ቀርቶ ቢወጡ ለማመን የሚያቅቱ ብዙ የጥበብ ሀብቶች በጉያችን ሞልተዋል፡፡ የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ እንደሚታየው ነው፡፡ እነዚህን የተደበቁ የሙዚቃ ሀብቶች ለማውጣት ብዙ ልፋትና ጥረት ይጠይቃል፡፡ እነዚህን ሀብቶች ሳይጠፉ ሠርቶ በማስቀረት ለልጅ ልጆቻችን ለማውረስ ብዙ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ በሙዚቃ ማኅበሩ ሊሆን ይችላል እንደገናም በመንግሥት ብዙ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡

ለዚህ ደግሞ ሕዝብ ለሕዝብ የኪነ ጥበብ ሥራ ቀላል ምሳሌ ሊሆነን ይችላል፡፡ ያን ዓይነት መድረክ ከዚያ ወዲህ ሲሠራ ዓይተን አናውቅም፡፡ በኦሮሚኛ፣ በጉራጊኛ፣ በትግርኛ፣ በወላይትኛ ቅይጥ የሆነ የሙዚቃ ባህል የታየበት ትልቅ የሙዚቃ መድረክ ነበር፡፡ ብዙ የባህል ሙዚቃዎች በዓለም አቀፍ መድረክ ቀርቶ በአገር አቀፍ መድረኮችም ሳይወጡ እንደተሸፈኑ በዚያው በተፈጠሩበት አካባቢ ብቻ እየተጨፈረባቸው ነው የሚኖሩት፡፡ ሙዚቃችን ሰፊ ነው፣ ባህላችንም ሰፊ ነው፣ የበዓላት ሙዚቃዎቻችንም ብዙ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- እንቁጣጣሽ ሲመጣ እንደ ዘሪቱ ጌታሁን ያሉ የሠሯቸው እንቁጣጣሽ የሚሉ ሥራዎች በብዙዎች ጆሮ ያቃጭላሉ፡፡ አንዳንድ ሙዚቃዎች በልዩ ሁኔታ ከበዓላት ጋር ቁርኝት ይፈጥራሉ ማለት ነው?

አማኑኤል፡- እነዚህ ሙዚቃዎች እኛ ባልተፈጠርንበት ጊዜ የተሠሩ ቢሆንም እንኳን አሁንም ድረስ እንሰማቸዋለን፡፡ ይህ የሆነው በዋናነት ለበዓላቶቻችን በሚፈለገው ልክ ብዙ ሥራዎችን ስላልሠራን ነው፡፡ ሰው በቴዲ አፍሮ አበባ አየሽ ሆይ የሚጨፍረው ከራሱ ትውልድ ጋር የሚሄድ ስለሆነ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የቆዩ የበዓል ሙዚቃዎችን ደግመን ደጋግመን የምንሰማ ከሆነ፣ ከእነዚያ የተሻለ በጥራትም በቁጥርም አልተሠራም ማለት ነው፡፡  የበዓል ሙዚቃዎች ከበዓላት ጋር የተሰፉ ናቸው፡፡ ዶሮን፣ ቡናን ወይም ሽሮን ከኢትዮጵያዊያን ውስጥ ማውጣት እንደማይቻለው ሁሉ የበዓል ሙዚቃዎችንም ከበዓል መነጠል አይቻልም፡፡ እንቁጣጣሽ ለምሳሌ ሪከርዲንጉ ፈጠን ያለና በጣም ቆንጆ ዘፈን ነው፡፡ እነ ለማ ገብረ ሕይወትን ማንሳት እንችላለን፡፡ በጣም ከባድና ትልቅ ሥራ ሠርተው ያለፉ ናቸው፡፡ እነ ጥላሁን በወጡበት ጊዜ የተሠሩ ሥራዎችም ትልቅ ዋጋ አላቸው፡፡ ከዚያ በ1970ዎቹ በመጣው የእነ ሮሀ ባንድ አብዮት ደግሞ የተሠሩ አስደናቂ ሥራዎች አሉ፡፡      

አበጋዙና ሞገስ ተካ የተጠበቡበት የሐመልማል አባተ የበዓል ሥራ ከሕዝብ ውስጥ አይወጣም፡፡ ኤልያስ መልካ ከትዕግሥት በቀለ ጋር የሠራው የራሱ ዜማ የሆነው የበዓል ሙዚቃ በጣም ውብ ነው፡፡ ማንአልሞሽ ዲቦ የሠራችው የሙሉጌታ አባተ ውጤት ደግሞ በልዩ ሁኔታ ይነሳል፡፡ እነዚህን መሰል በየጊዜው የተሠሩ የሙዚቃ ሥራዎች በዓላትን እንዳንረሳ የሚያደርጉና ልዩ ትዝታ የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ እኛ እዚህ ስላለን እንጂ በውጭ በተለይም በዓረብ አገሮች፣ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ካናዳም ሆነ አውስትራሊያ ያሉ ወገኖቻችን ከእነዚህ ዘፈኖች ውጪ ብዙም መፅናኛ የላቸውም፡፡

በውጭ ሆድ በሚያስብስ ኑሮ እየኖሩ በዓል ሲመጣባቸው ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው የሚያደርጓቸው እነዚህን መሰል ሙዚቃዎች ናቸው፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ ሙዚቀኞች የማይደፍሩትን አልፈው እነ ታደሰ ዓለሙ ለትንሳዔ ሚሻ ሚሾን የመሰሉ ተወዳጅ ሥራዎች ሠርተዋል፡፡ ይሁኔ በላይ ደግሞ ለጥምቀት ቃና ዘገሊላ ልዩ ሥራ አበርክቷል፡፡ ይሁኔ ምናልባት ቃና ዘገሊላ በደማቁ የሚከበርበት አካባቢ ሰው ስለሆነና የሙዚቃ ደራሲውም ጎበዝ ስለሆነ፣ በአገርኛው የጎጃም ምት በጥሩ ሁኔታ የማይረሳ ሥራ አበርክቶልናል፡፡ በጊዜው በዓላትን የሚያስታውሱ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያዊነትን የሚያስታውሱ ሙዚቃዎች ባይኖሩ ኖሮ በዓላት ሊረሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሙዚቃዎች ባይኖሩ ኖሮ በዓላትን በምን ታከብር ነበር፡፡ የበዓል ሙዚቃዎች ትልቅ ማኅበራዊ ፋይዳ ነው ያላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የበዓል ሙዚቃዎች ውስጥ በብዛት የሚነሱ ጉዳዮች ምንድናቸው?

አማኑኤል፡- የበዓል ሙዚቃዎችን ሰፊ ግዛት የሚይዘው ቅድም እንዳነሳሁት አዲስ ዓመት ነው፡፡ በዚህ የአዲስ ዓመት ሙዚቃ የሚነሳው ትልቁ ነገር ተስፋ ነው፡፡ ከረሚ ከሚለው ክረምት ተወጥቶ የተዘራው ወደ የሚታጨድበት የምርት ዘመን የምንገባ በመሆኑ መልካም ምኞትም በዘፈኖች ይነሳል፡፡ የተዘራውን የምንበላበት እንዲሆን ከመመኘት ባለፈ ጦርነት ካለ ሰላም፣ የታመመ ካለ መዳን እንዲገኝ የሚሰበክበት ነው፡፡ በእነዚህ ሙዚቃዎች አካላዊ ውበትን የምትገልጽበት ሁኔታ ብዙም የለም፡፡

የእነዚህ ዘፈኖች ትኩረት በልቶ ጠጥቶ መዋል ብቻም አይደለም፡፡ ቤተሰብ መጠየቅ፣ የእናትና የአባት ምርቃት ማግኘት ጭምር ይነሳል፡፡ አንድነትን፣ መሰባሰብንና አብሮ መብላትን ጠንከር አድርገን የምናነሳበት ነው፡፡ ከአዲስ ዓመት ውጪ ባሉ በዓላትም ቢሆን ተመሳሳይ በጎ ነገሮችን የማነሳሳት ልምድ ነው ያለው፡፡ እንደ አሲና ገናዬ ወይም ሆያ ሆዬ ያሉ እንደወረደ የሚሠሩ ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ለበዓላት በሚሠሩ ሙዚቃዎች ጎልተው የሚነሱት ማኅበረሰባዊ ፋይዳ ያላቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ በእነዚህ የዓውደ ዓመት ሥራዎች ቅንድብሽ፣ ዓይንሽ፣ ዳሌሽ፣ ተረከዝሽ ወይም ወገብሽ እያሉ ለአካላዊ ውበት መቀኘት ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የመጣው ነባር ትውፊቱን ሳይለቅ በአዝማሪዎችና በሌሎች ተወራርሶ በመጣው የበዓል ሙዚቃ አሠራር ልማዳችን ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች