Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉዛሬን እያሳጡን ያሉ የፖለቲካ ስንክሳሮቻችን

ዛሬን እያሳጡን ያሉ የፖለቲካ ስንክሳሮቻችን

ቀን:

በዳግም መርሻ

አገራችን ኢትዮጵያ በበርካታ ፈተና በተሞላበት ታሪካዊ ሒደት ያለፈች አገር ናት። ችግሮቿም መጠነ ሰፊና አድማስ ተሻጋሪ ናቸው። አገሪቱ ረዥም የመንግሥትነት ታሪክ ባለቤት ብትሆንም  በየዘመናቱ በውስጥና በውጭ ጠላቶቿ ያልተፈተነችበት ጊዜ የለም፡፡ ዘመናዊ ፖለቲካን ጀምረናል ከሚባልበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ፖለቲካው ጤናማ ሆኖ አያውቅም፡፡  ያለን ታሪክ በአብዛኛው የሥልጣን ሽኩቻ ታሪክ ነው፡፡ ያለን ታሪክ የጦርነትና የግጭት ታሪክ ነው። ነፍጥ አምላኪዎች ነን።

በተለያዩ ጊዜያት ሥልጣን ላይ ሲወጡ የነበሩ መሪዎች ሥልጣንን ማኅበረሰብን ወደ ተሻለ ቦታ ማድረሻ መሣሪያ አድርጎ ከማሰብ ይልቅ፣ ጤናማ ባልሆነ መንገድ ማዋላቸውና በአፈ ሙዝ ማመናቸው በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ እንዲያገነግን ምክንያት ሆኖ በተደጋጋሚ ታይቷል። ይህ ደግሞ በተለያዩ ጎራዎች   በተሠለፉ ዜጎች መካከል ሲፈጠሩ ለነበሩ፣ እስካሁንም ድረስ ለዘለቁ ግጭቶችና አለመግባባቶች  አንዱ መነሻ ሆኖ ሕዝባችንን ትልቅ ዋጋ አስከፍለውታል። 

በዚህ ላይ ደግሞ አግባብነት ባለው መንገድ ሳይፈቱ ከዘመን ወደ ዘመን እየተንከባለሉ የመጡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ስንክሳሮቻችን ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲያገኙ ባለመደረጉ አገሪቱ የቀደመ አኩሪ ታሪኳን የሚመጥን ዕድገት ሳይኖራት፣ ሕዝቡም የረባ ዕፎይታ ሳያገኝ አሁን የምንገኝበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።

በትውልድ ሽግግሮች የተፈጠሩት የፖለቲካ ቀውሶችና ውጥንቅጦች ረግበው ሕዝቡን  በላዩ ላይ ከተጫነው መከራና ሥቃይ ዕፎይ ከማሰኘት ይልቅ፣ ቀን በገፋ ቁጥር ችግሮቹ በይበልጥ ገዝፈውና ተወሳስበው ወደ ግጭትና መጠፋፋት እየወሰዱ የኢትዮጵያ ልጆች ደም በከንቱ እንዲፈስ፣ የወጣቶች ውድ ሕይወት እንዲቀጠፍ፣ በብዙ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች ያለ ልጅ፣  ያለ ጧሪና ቀባሪ እንዲቀሩና የእናቶች እንባ እንዲረግፍ ማድረጋቸው ጥሬ ሀቅ ነው። በዚህ ሁኔታ ሕዝቡ ተነግሮ የማያልቅ በርካታ ፍዳ ዓይቷል።

በማኅበረሰቡ ዘንድ ግጭት ያስከትላሉ ለሚባሉት የፍትሕ፣ የእኩልነት፣ የልማት፣ የሰብዓዊ መብት፣ የመልካም አስተዳደር፣ ወዘተ ጥያቄዎች  አፋጣኝና ፍትሐዊ ምላሽ ሳያገኙ መቅረት ወደ ብሶት አድጎ ሲከሰቱ የነበሩት ግጭቶች፣ ንትርኮችና አለመተማመኖች፣ መሳደድ፣ መገዳደል፣ ወዘተ የየወቅቱ ፖለቲካ ዋና መገለጫ ሆኖ  የአገሪቱ ዕድገት ወደኋላ እንዲጎተት ምክንያት ሆኗል። የዚህ ሁሉ መንስዔው ኋላቀር የፖለቲካ ባህላችን የወለደው  ከሕግ በላይ የመሆን ክፉ ልማድና  በአፈ ሙዝ የማመን አባዜ ነው። 

ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ሁላችንም የኖርንበት ሕይወትና የመጣንበት መንገድ የሚያሳየን ነገር ፖለቲካው፣ ‹‹የሰጡህን ብቻ ተቀበል›› በሚለው አምባገነናዊ  የአስተዳደር ዘይቤ የተቃኘ መሆኑን ነው። በተጨማሪም ፖለቲካችን የጥቂቶችን ፍላጎት ብቻ ይዞ የመሮጡ ነገር ያለና ዛሬም ድረስ ሊቆም ያልቻለ እውነት ነው። ፖለቲካችንን የወል ማድረግ ተስኖናል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሴራ፣ መጠላለፍና መገፋፋት፣ አለመተማመን፣ አለመደማመጥ፣ ከትብብር ይልቅ ሽኩቻ፣ መበቃቀል፣  ‹‹እኔ እበልጥ››፣ ‹‹እኔ እበልጥ›› ፉክክር፣ መሸናነፍ፣ መገዳደል፣ ሁሉን ነገር መቆጣጠር፣ ቃል አባይነት፣ ወዘተ ዋና ዋና መገለጫዎቹ ናቸው ማለት ይቻላል።  መቻቻልና መደማመጥ ባልተለመደበት በዘመነ ደርግ ፖለቲካ፣ ‹‹የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ሐዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ›› እንዲል ብሂሉ፣ ወንድም ወንድሙን ገድሎ ግዳይ እንደጣለ ጀግና  በ‹‹ፍየል ወጠጤ…›› ዜማ  ፉከራ የተፎከረበትን ጊዜ እንደ ዋዛ አልፈናል። 

በተለያዩ ጊዜያት የነበረው የፖለቲካ ሒደት በፈጠረው የአመለካከት (የርዕዮት ትርክት) ልዩነት ሰበብ በርካታ ዜጎች እንደ ጠላት ተፈርጀው ለእስር፣ ለእንግልትና ለግድያ ተዳርገዋል። የአንድ ቤተሰብ አባላት በአመለካከት ልዩነት ምክንያት ብቻ በጠላትነት ተፈራርጀው በነፍስ እስከ መፈላለግ ደርሰዋል። አገር የምትመካባቸው  በርካታ ምሁራን በየአደባባዩ በጥይት ተቆልተው፣ አገሪቱን እንደ ትውልድ ወደኋላ የጎተተ  ምሁር አልባ እንድትሆን አድርጓታል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ከስክነት የራቀው ፖለቲካ የሚያመጣው ጣጣና መዘዝ አስግቷቸው፣ ‹‹ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ››  በሚል ብሂል  ለአገራቸው  ፖለቲካ ባይተዋር ወይም የበዪ ተመልካች ሆነው እንዲቆዩ ተገደዋል። ይህ በማኅበረሰቡ ፖለቲካ ባህል ላይ እስካሁን ድረስ ያልሻረ መጥፎ ጠበሳ ጥሎ አልፏል፡፡ ይህንን ሁላችንም ማስቀረት እንችልና ይገባንም ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን  ፖለቲካውን ጨከን ብለን የጋራ ማድረግ አልቻልንም።

እንደምናውቀው አገራችን ኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ፣ አኩሪ ባህል፣ ታሪክና እሴቶች ባለቤት ናት፡፡ ሕዝቦቿ ከእነ ጉድለታቸው ተሳስበው፣ ተከባብረው፣  ተቻችለውና ተፈቃቅረው  ለዘመናት ሕይወትን በጋራ ኖረዋል፡፡ የወግ፣ የትውፊትና  የባህል ትስስራችንም ላይለያይ አንድ ሆኗል፡፡ አንዳችን ካንዳችን ተዛምደን ተጋምደናል። ከዚህ ጎን ለጎን ለዘመናት የተነሱብንን የውጭ ጠላቶች ዘር ጎሳ ሳይለያየን በጋራ ወኔ ድል አርገን መልሰናቸዋል። ወርቃማው የዓድዋ ድልን ጨምሮ የኦጋዴን፣  የካራማራ፣ ወዘተ የጦር ሜዳ ገድሎች በዘርና በጎሳ ሳንለያይ ድል ያስመዘገብንባቸው የጋራ እሴቶቻችን ማሳያ ናቸው።

ሆኖም ከላይ የጠቃቀስኳቸውን አብረውን ለዘመናት የቆዩትን በርካታ እሴቶች፣ ባህሎችና ትውፊቶቻችንን ያላሉብን የፖለቲካ ችግሮች ለማከም ተጠቅመንባቸዋል ብዬ አላስብም። ፊደል ቆጥረናል ተምረናል የሚሉት አብዛኞቹ የፖለቲካ ተዋንያን/ልሂቃን ሳይቀሩ ለዴሞክራሲ ባህል ባይተወር ናቸው።  እነሱ ዘንድ ዴሞክራሲ በቃል እንጂ በተግባር የለም። መወያየት፣ መነጋገር መመካከር፣ ወዘተ እንደ ግጭት መፍቻ መሣሪያ ከማሰብ ይልቅ እንደ ሽንፈት የመቁጠሩ ሁኔታ ተለምዷል። የዴሞክራሲ እሴቶች በሚፈለገው ሁኔታ አልዳበሩም። ይህ ደግሞ የምንፈልገውን ዓይነት ኅብረተሰብ ሊፈጥርልን አልቻለም። አሁን እያጨድን ያለነው የዚህን ፍሬ ነው።

አንዳንዴ ሳስበው ‹‹የኢትየጵያ ሕዝብ  ቅኔ ነው›› የሚለው አባባል በብዙ ሁኔታ እውነትነት አለው፡፡ ለምሳሌ በአንድ በኩል የተነሱብንን የውጭ ጠላቶች በጋራ መክተን አገርን ጠብቆ የማቆየት አኩሪ እሴት ሲኖረን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የራሳችን ጠላት እኛው፣ የራሳችን ፀሮች እኛው ሆነን እርስ በርስ የተጎዳዳንበት፣ የተገዳደልንበትና የተጠፋፋንበት ጊዜ መብዛቱ ያስገርማል። የውጭ ጠላትን በጋራ መክተን ያቆየነውን የነፃነታችንን ፍሬ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ የዜጎችን  ኑሮ ለማሻሻል፣ የመቻቻልና የመከባበር ባህልን ለመገንባት፣ ወዘተ አልተጠቀምንበትም። ይህ በእጅጉ ያሳዝናል፣ ያስቆጫልም።

በእኔ እምነት ያልተላቀቀን የድህነታችንና የኋላ ቀርነታችን ትልቁ ምክንያት በተለያዩ ሰበቦች የምናካሂዳቸው ደም አፋሳሽ ግጭቶችና ጦርነቶች ናቸው። ከዚህ ችግራችን አልተማርንም። እንዳልተማርን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየናቸው ያሉት ነገሮች በቂ ማሳያዎች ናቸው፡፡ 

አርባና ሃምሳ ዓመታት ሙሉ አንድ ዓይነት ስህተት እንዴት እንሳሳታለን? ከስህተታችን ትምህርት ወስደን እንዴት መሻሻል አቃተን? ዓለም ሁልጊዜም በለውጥ ሒደት ውስጥ ነች። ይኸውም ለከጨለምተኝነት ወደ ተስፈኝነት፣ ከአይቻልም ባይነት ወደ ይቻላል ባይነት፣ ከስሜታዊነት ወደ ምክንያታዊነት፣ ከኋላቀርነት ወደ ሥልጣኔ፣ ከድህነት ወደ ብልፅግና፣ ከአሮጌው ወደ አዲሱ ተስፋ፣ ከኋላቀር ወደ ተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት፣ ወዘተ የሚወስደን ጉዳይ (ጎዳና) ነው። ከዚህ አኳያ የዛሬው ፖለቲካ ከትናንቱ ካልተሻለ ምን ለውጥ አመጣን? ከመተባበር  ይልቅ  መገፈታተርን፣ ከመደጋገፍ ይልቅ መጠላለፍን፣ ከአብሮነት ይልቅ ልዩነትን ካራገብን ምን ዓይነት የአስተሳሰብ ወይም የባህሪ ለውጥ አመጣን? ትውልዱ የሚራገቡ ሐሰተኛ ትርክቶችን በሰከነ መንፈስና በብስለት ሳይፈትሽ ያንኑ ከደገመ ምኑን ወደፊት ተራመድን? የጀግንነት ውኃ ልክን ከጦር ዓውድማ፣ ከትጥቅ ትግል፣ ከመበቀቃቀል ጋር ብቻ የምናያይዝ ከሆነ ምኑን ጊዜ ተለወጠ?

አንድ መንግሥት ሄዶ ሌላው በተተካ ቁጥር ካለፉ ስህተቶች ተምረን በአግባቡ አልታረምንም፡፡ የተመላለስንበትን የተጣመመ መንገድ አቃንተን በሁሉም መስክ እንደ ሌሎች በርካታ አገሮች ማደግና መለወጥ ተስኖናል። በተለያዩ የታሪክ እጥፋቶች  የመጡ መሪዎች የገቡትን ቃል በማጠፍና አሳይተው በመንሳት (Missed Opportunity)    የታሰቡት ለውጦች ውጤት አልባ ሆነው ቀርተዋል፡፡ በአጭሩ ኢትዮጵያ ከአንድ የፖለቲካ አዙሪት ወደ ሌላው እየገባች ዜጎች ከዛሬ ነገ ይሻል ይሆን በሚል ተስፋ የሰቀቀን ኑሮ የሚገፉባት አገር መሆኗ የተለመደ ነገር ሆኗል። ላለፉት አርባና ሃምሳ ዓመታት የአገራችን ፖለቲካ ያሳየን ነገር ይህንኑ እውነታ ነው፡፡  ለእኔ የ‹‹እንዘጭ- እንቦጭ›› ፖለቲካ ሲባል ትርጉሙ ሌላ ሳይሆን እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ይመስለኛል።

እናም ፖለቲካው በኖረበት አዙሪት እንዲቀጥል ስለፈቀድንለት ጦሱ አሁንም አልለቅም ብሎናል፡፡ የሚያንገላታን ፖለቲካዊ ትብታብ አልበቃ ብሎ ተጋግዘንና ተደጋግፈን ያሳለፍነውን የጋራ ታሪክ ዘንግተን አሁን ደግሞ ለያዥ-ለገናዥ እያስቸገረ ላለ ብሔር ተኮር ፉክክር ተጋልጠን በመገፋፋትናና በመጠፋፋት ላይ ተጠምደናል፡፡ በጎራ ስም የመቧደን በሽታም ዋና መለያችን ከሆነ ሰነባብቷል። 

በተለይ ካለፉት አራትና አምስት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያዊ እሴታችንን የሚሸረሽሩና የቆየውን አብሮነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ በርካታ እኩይ ተግባራት ገጥመውናል። የባንዲራ ትርክት፣ የበዳይ ተበዳይ ትርክት፣ ልዩነትን የማጉላት ፖለቲካ፣ ጥላቻን ማቀንቀን፣ ወዘተ የየዕለቱ (Routine) የፖለቲካ ክሰተት መሆኑን ቀጥሏል። እነዚህ ሁኔታዎች በየቦታው ካለው ዱለታ፣ ፉከራ፣ መገፋፋት፣ ፉክክርና የመጠፋፋት እሳቤ፣ ወዘተ ጋር ተደማምረው አገርንና ሕዝብን ወደማያስፈልግ አቅጣጫ እየገፉ ነው።

በአሁኑ ጊዜ በነባሩ የፖለቲካ ችግራችን ላይ ተደርቦ ስንተኛም ሆነ ስንነሳ ለሥጋትና ለሰቀቀን እየዳረገን ያለው ዋና ጉዳይ ሐሰተኛ ትርክት ወይም የጥላቻ ንግግር ነው። አሁን አሁን በሕዝብ ውስጥ ችግር ሳይኖር ችግር እንዳለ አድርገው የሚያራግቡ፣ እንዲሁም ትናንት የነበሩ ትርክቶችን ከተገቢው በላይ በማጎን ማኅረሰቡን ለአመፅና ለብጥብጥ የሚያነሳሱ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ  አካላት  እየተበራከቱ መጥተዋል። ከትንሽ እስከ ትልቅ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ዲጂታልና መደበኛ ሚዲያን በመጠቀም የውሸት ትርክትና የጥላቻ ንግግር ፈብራኪ ሆኗል። ‹‹ልሂቁ›› አለኝ የሚለውን ጥያቄ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ አምጥቶ መወያየት አይደፍርም፡፡ መደማመጥ፣ መከባበር የለም፡፡ ይህ የተለመደ ክስተት (Trend) ከመሆኑ በሻገር ነውርነቱ እየቀረ መጥቷል፡፡

በዚህም ምክንያት እነዚህ አካላት የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የእኔ ብሔር አባል ነው የሚሉትን ማኅበረሰብ እንዳሻቸውና በፈለጉት አቅጣጫ በመጋለብ፣ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር እንዲጋጭና እንዲቃቃር ያደርጉታል። ዛሬም ምንም የፖለቲካ ዝንባሌ የሌለው ባተሌው ሕዝባችን የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ‹‹Displaced Anger›› አንዳንዴም ‹‹Misplaced Anger›› እንደሚሉት፣ የተዛባ ትርክትና ዋልታ ረገጥ የፅንፈኝነት  ስተሳሰብ የወለደው ቂም ማወራረጃ ሆኖ በአሰቃቂ ሁኔታ ይገደላል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ለወግ ማዕረግ ከበቁበት አካባቢ በግፍ ይፈናቀላሉ፣ ይሰደዳሉ። በዚህ ሰዓት ብዙ ሰዎች በሰቆቃና በፈተና ውስጥ እንዲኖሩ ተገደዋል። ነገን ማሰብ ከባድ ሆኗል። ይህ ሁኔታ የትም አላስኬደንም። እናም ብዙ ሰው ሳይሞት፣ ብዙ ደም ሳይፈስና ትውልድ ሳይጎዳ ከተሳሳተው ወደ ትክክለኛው መንገድ መመለስ አለብን። ዛሬ ላይ ሆነን በትናንት ትርክት መኖርን በቃ ልንለው ይገባል። እንደ ሩዋንዳ የመሳሰሉት አገሮችን መንገድ ተከትለን እኛም ይህን ታሪካችንን ልንዘጋ ግድ ይለናል።

ኢትዮጵያውያን ከሚያለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ነገሮች ይበዛሉ። ሕዝባችን ተዋዶና ተፈቃቅሮ የመኖር ችግር የለበትም፡፡ ይህ ዘመናትን ባስቆጠረው የታሪክ ሒደት በተግባር ታይቷል። ከጥንት ጀምሮ ያለው የአኗኗር ዘይቤያችን በራሱ ኅብረትና ትስስር እንዲኖረን የሚያስገድደን ነው። በግሌ ዋናው ችግር የፖለቲከኞች የሥልጣን ሽኩቻና የጥቅም ሽሚያ ነው ብዬ አምናለሁ። ሌላው ችግር ነው ብዬ የማስበው በታሪክ ሒደት የነበሩ ትርክቶቻችን በውስጣችን ተክለው ያኖሩት የሥነ ልቦና ችግር ወይም እውነታን የምናይበት ዓይን ነው። ይህ የሥነ ልቦና እንቅፋት መሰበር አለበት።

ያለንበትን ክፉ ጊዜ ለማለፍ የአቅጣጫና የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልገናል። ከመሪዎችም ሆነ ከሕዝቡ ከፍ ያለ አስተዋይነት ይጠበቃል። ያሉትን የእርስ በርስ ጥርጣሪዎች፣ ሥጋቶች፣ አለመተማመኖችና ውጥረቶችን ጋብ ማድረግ (Deescalate) ያስፈልጋል። አገርን ለማዳን የሥልጣን ሽኩቻው ልጓም ሊበጅለት ግድ ይላል፡፡

በአጠቃላይ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ አገረ መንግሥት ሊገነባ የሚችለው ሌሎች አገሮች ከደረሰባቸው ኪሳራ ተምሮ ለመነጋገር፣ ለመወያየትና ለመደራደር ዝግጁ ሆኖ በመገኘት እንጂ፣ የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር ነጋ ጠባ የኃይልና የግጭት መንገድን በመከተል እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። የኃይልና የግጭት አማራጭ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለው ውጤታማነት ከዜሮ በታች መሆኑን በተደጋጋሚ ዓይተነዋል። ውይይትንና ንግግርን ማስቀደም ያሉንን ልዩነቶች ፈትሸን አንድ የጋራ እውነት ላይ ለመድረስ ያስችለናል። ለዚህ ባህሉ አለን፣ ትውፊቱ አለን። የሚያስፈለገው ነገር ቢኖር እነዚህን እያሳደጉና እያጎለበቱ (Scale-up) ለችግሮቻችን ጥቅም ላይ ማዋል ነው። ያኔ የሚያታግለንን ለማሸነፍ መፃኢ ዕድላችንን ብሩህ ለማድረግ ዕድሉ ይኖረናል።

መልካም አዲስ ዓመት!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሕዝብ አስተያየት ጥናት ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው dagimmersha@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...