በገነት ዓለሙ
ዓመቱን በሙሉ፣ ከዚያም በፊት ባለፉት አምስት ዓመታት በዘመነ ኢሕአዴግ ጊዜ ጭምር የኢትዮጵያን ‹‹ዴሞክራሲ›› ያጎደለው መንግሥታዊ አውታራት ነፃና ገለልተኛ ሆነው አለመዋቀራቸው፣ ይልቁንም የአንድ ቡድን፣ ወገን ወይም ፓርቲ ተቀፅላ የእሱ ሀብትና ንብረት ሆነው መደራጀታቸው ነው ስንል፣ ይህንን ስንታገል ለዚህ እንዲተጋ ስናበረታታ ኖረናል፡፡ በለውጡ ወቅት በዚህ ደረጃ ልዩነት ያሳዩ፣ እውነትም ‹‹ለውጥማ አለ›› የሚያሰኙ፣ የፈለገውን ያህል ቢጣጣሉና ቢዋደቁ እንኳን፣ ለውጡና ሪፎርሙ ለስሙ መጠሪያ የሰፋቸው ቁናዎች ማለት ያህል ክህደትና እምቢታ ቢኖር እንኳን ባለፈው አምስት ዓመት ፈርሰው የተሠሩ፣ አዲስ ሆነው የተወለዱ ተቋማት አሉን፡፡ እንደ ዓይን ብሌን የምንጠብቃቸው፣ የምንሳሳላቸው፣ እንዳሻቸው እንዳይሆኑ ጤንነታቸውን የምንጠብቅላቸው፣ የምንከታተላቸው ናቸው፡፡
ተሠርተው ያለቁ ግን አይደሉም፡፡ ‹‹መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ተመልሷል›› የተባለባቸው/የተባለላቸውም በጭራሽ አይደሉም፡፡ ገና ብዙ ቀሪ ሥራ፣ ቀሪ ጉዞና ዕርምጃ፣ መልሰን መላልሰን፣ ደግመን ደጋግመን፣ በ‹‹አረም›› ጭምር እንደገና የምንጎበኛቸው፣ ተከታይ፣ ተከታታይ ሥራ ያለባቸው ናቸው፡፡ እነዚህ መሻሻል የተደረገባቸው ተቋማት (ወይም ከእነዚህ መካከል ይባል እንደሆነም) የመከላከያ ሠራዊቱ/ኃይሉ፣ የምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ወዘተ ይገኙበታል፡፡ በተለይ የመከላከያ ኃይሉ ግንባታ ዴሞክራሲን በነፃና ገለልተኛ ተቋማት ላይ የመገንባት ሥራ የአገርን ህልውና ከማዳን ውስብስብ ሥራ ጋር በተደረበበት ቀውጢ ወቅት ጭምር የተፈጸመ ሥራ በመሆኑ ምናባዊ ሳይሆን፣ በተግባር የሚታይና የሚጨበጥ ማስረጃ የሚቀርብበትና የተሰጠበት ነው፡፡ ጥቅምት 23 እና 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ፕሪቶሪያ ላይ የተፈረመውና የፀናው ስምምነት፣ ሁለቱ ወገኖች ማለትም የፌዴራሉ መንግሥትና ሕወሓት ተስማምተው ተግባብተው፣ ተማምነው የተፈራረሙት ውል ብቻ ሳይሆን ከፍ ሲል ያልኩት ጉዳይ ማስረጃ ጭምር ነበር፡፡ እዚያ ውስጥ ስማቸው በቀጥታ የተነሱት በተለይም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ ሳይሆኑ አገር፣ ኢትዮጵያ ‹‹Vindicate›› የተደረገችበት፣ ‹‹ነፃ›› ነሽ የተባለችበት ምስክርነት ጭምር ነው፡፡
ይህ ፍርድ፣ ማስረጃና ምስክርነት ግን ለዚህ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ፍጥርጥርና ባህርይው የፍርድ አፈጻጸም ዕዳ ያለበት፣ የተፈጻሚነት ግዴታ ያስከተለ ምን ላይ ደረሰ? ምን ቀረ? የሚባል እንጂ በመስታወት ገብቶ ግድግዳ ላይ የሚሰቀል፣ አንገት ላይ የሚንጠለጠል አይደለም፡፡ የኒሻን ወይም የሜዳሊያ ሚናው ባይናቅም ዋናው ጉዳይ ግን ዴሞክራሲን የመገንባት ለብዙ ጊዜ ተወዝፎና ተሰነካክሎ የኖረው የአገር ተልዕኮና አደራ፣ የጥበብ መጀመርያ በነፃና ገለልተኛ ተቋማት መታነፅ ላይ መመሥረት ያለበት መሆኑን ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ (እንዲሁም ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ሁሉ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም፣ (እንዲሁም መላው የዴሞክራሲ ተቋማት) ለውጥና መሻሻል መታየት፣ መገምገም ያለበት ከዚህ አንፃር ነው፡፡ አንዴ ‹‹የተከተቡ››፣ የክትባት መርፌ ተወግተዋል ተብለው እንዳለቀላቸው የሚቆጠሩ አይደለም፡፡ በርቱ ገና ነው የሚባሉ፣ የሕዝብ፣ የሚዲያ፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ የሰላ ዓይንና ጠባቂነት ያለባቸው ጥሩ መጀመርያዎች ናቸው፡፡
በእነዚህ ተቋማት፣ በተለይም ከእነዚህም መካከል በአንዳንዶቹ አስደናቂ ለውጥ እየኮራንና አንዳንዴም እየተመካን፣ ወዲያውም ከሰላ (ክሪቲካል) ዓይንና ዕይታ ጋር በርቱ ግፉ ገና ነው እያልን መጪው ዓለምም ብሩህ ነው፣ ተስፋ ሰጪም ነው ብለን አንፅናና ነገር ደግሞ የሚዲያው ነገር ነው፡፡ ሚዲያው የእነዚህ የገለጽናቸውና ተስፋ ሰጪ ናቸው ያልናቸው ተቋማት የሰላ ዓይን ነው፡፡ የተቆጣጣሪዎች ተቆጣጣሪ፣ የጠባቂዎች ጠባቂ፣ የዓይኖቻችን ዓይን ናቸው፡፡ የሚገርመውና በዚያም ምክንያት ሲበዛ የሚያሳስበው ግን ሚዲያው ከሁሉም በላይ ደግሞ የመንግሥት ሚዲያው እዚህ ለውጥ፣ እዚህ ፈርሶ መሠራት ውስጥ፣ ከይስሙላና ከማስመሰያ ውጪ አለመግባቱ ነው፡፡ የመንግሥት ሚዲያዎችና ባለቤታቸው መንግሥት ራሱ፣ በተለይም በዚህ ጉዳይ ከራሳቸው የማይሰማ ድምፅ በስተቀር የሌላ ወገን ድምፅ አይሰሙም እንጂ፣ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29 በንዑስ ቁጥር (4) እና (5) የሚለውን ደጋግመን ተናግረናል፡፡
ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29 ከሌሎች መካከል 1) ለዴሞክራሲ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ሐሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ 2) በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል ይላል፡፡ ይህንን የሚለው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይህንን እንደሚል፣ ይህንን ሕገ መንግሥቱ እንደሚል አልሰማችሁም ወይ ብለን እኛም ደጋግመን ተናግረናል፣ ነግረናል፡፡ የሌላውንና ሌላ ሌላውን ትተን ስለመንግሥት ሚዲያ ብቻ እንነጋገር፡፡ ሕገ መንግሥቱ የዛሬ ሃያ ስምንት ዓመት የበላይ ሕጉ ከዛሬ ጀምሮ ፀና፣ ሪፐብሊክም አቋቋምኩ ሲል የዚህ ሕገ መንግሥታዊነትና ሪፐብሊክ ዋና ይዘት የሁሉም ለሕግ መገዛት (የመንግሥትንና የመንግሥት ሚዲያን ጨምሮ) በነፃና በገለልተኛ ተቋማት ላይ ዴሞክራሲን ማደላደል ነውና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በተለይ የጠቀስኳቸው የእነዚህ የዕለቱ (የመንግሥትና የመንግሥት ሚዲያ) አካላት አደራና ግዴታ የመንግሥትን ሚዲያ አመራር መለዋወጥ እንደገና አፍርሶ መሥራት ነው፡፡ ለምን? የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጎ አፍርሶ መሥራት መንግሥት ሚዲያና የባለቤቱ ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ የእኛም ጭምር፡፡ ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድና ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል ማለትማ የሁሉም ሚዲያዎች ግዴታ ነው፡፡ ታዲያ ጥያቄው ሚዲያው በተለይም የመንግሥት ሚዲያ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነት አገኘ ወይ? የተለያዩ አስተያየቶችን የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው ሆኖ የአደረጃጀትና የአመራር ለውጥ ተደርጎለታል ወይ? ይህንን ጥያቄ ካለፉት 28 የዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክም ሆነ አምስቱ የለውጥ ዓመታት አኳያ የደረሰበትን ‹‹ዕድገት›› ወይም ሌላ ነገር ባለበት መርገጥ፣ እየከፋ መምጣት ለመመልከት መጀመርያ ስያሜ እንነሳ፡፡ ስያሜው ወይም መጠሪያው ራሱ ሥውር፣ ወይም የውስጥ ለውስጥ ሳይሆን ግልጽ ግብግብና ትግል የተደረገበት ተራ ሳይሆን ይፋ/ኦፊሴል የሰነድ ማስረጃ ያለው ነው፡፡ የአገሪቱ የበላይ ሕግ፣ ሕገ መንግሥቱ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ ወይም በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ሚዲያ ሲል፣ በወቅቱም የነበረው የሚዲያ ባለቤትነት የሕግ ማዕቀፍና ከዚያም በኋላ የመጡት ‹‹የማሻሻያ›› ዕርምጃዎች ጭምር እንደሚሳዩት መነሻው የታወቀ ነው፡፡ የሚዲያ/የፕሬስ ባለቤትነትም ሆነ ሥራ በተለይም የብሮድካስት ሥራና ባለቤትነት ለመንግሥት ብቻ የተከለለ፣ ለግል የተከለከለ ነበር፡፡
በዚህ ማዕቀፍና ከባቢ ውስጥ፣ እንዲሁም ዴሞክራታይዜሽን ማለትና የፋሽን ዓይነት ልክና መልክ ያገኘው በዓለም የተስፋፋው ንቅናቄ የሚጠይቀው ማሻሻያና ለውጥ፣ ለግል የተከለከለውን ወይም ለመንግሥት ብቻ የተከለለውን የሚዲያ ባለቤትነትና ሥራ ለግሉ ዘርፍ ከመክፈት ጋር የመንግሥት ሚዲያንም ወደ ሕዝብ ሚዲያነት የመለወጥ፣ ትራንስፎርም የማድረግ፣ አፍርሶ የመሥራት ግዳጅንም ያካትታል፡፡ ዓለም አቀፋዊው የፕሬስና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት፣ የዩኒቨርሳል ሒዩማን ራይትስ ዲክላሬሽን የአንቀጽ 19 ድንጋጌ ድጋፍ ያለው ይህ ማሻሻያ ስቴት ሚዲያን ወደ ፐብሊክ ሚዲያ መለወጥን ይጠይቃል፡፡ በአጠቃላይ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 (5) ትርጉም ስቴት ሚዲያ ፐብሊክ ሚዲያ ይሆናል፣ ስቴት ሚዲያ ወደ ፐብሊክ ሚዲያነት ይለወጣል፣ ስቴት ሚዲያ ፐብሊክ ሚዲያ ሆኖ ፈርሶ ይሠራል ማለት ነው፡፡ የዚህ ትርጉምና አንድምታ ስሜት በሚነዝርና የቋንቋ ውበት ባለው የቃላት ጨዋታና አጭበርባሪ ሎጂክ ውስጥ ተድበስብሶ የሚቀር ወይም እዚያ አርፎ የሚተኛ አይደለም፡፡ በመላው ዓለም ያኔም አሁንም የሚታወቀው የዴሞክራታይዜሽን፣ በተለይም ሐሳብን በነፃ ከመግለጽና ከፕሬስ ነፃነት ጋር የተያያዘው ንቅናቄ፣ አፍሪካ አኅጉር ውስጥ ደግሞ ጋምቢያ ባንጁል ውስጥ ያለው የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብት ኮሚሽን ጭምር ያወጧቸው ደንቦች፣ መመርያዎች፣ ፍኖተ ካርታዎችና ሞዴል ሕጎች ይህንን ቋንቋ ውስጥ የተደበቀ፣ ቋንቋንና ስያሜን ተገን ያደረገ ማጭበርበሪያ/ማስመሰያ ያጋልጣሉ፡፡ ከስቴት ሚዲያነት ወደ ፐብሊክ ሚዲያነት መለወጥ ማለት ስም የመለወጥ፣ ‹‹የመንግሥት መባሌ ቀርቶ የሕዝብ ተብዬ ልጠራ›› ብሎ በገዛ እጅ መወሰን አለመሆኑን ደግመው ደጋግመው ይናገራሉ፡፡
ሚዲያ/የፕሬስ (ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን) ገና ሲጀምር አንስቶ በባለቤትነት ብቻ ሳይሆን፣ በተግባርም ማለት በሚሠሩት ሥራም የመንግሥት መሣሪያ ተደርገው የተቋቋሙና የተዋቀሩ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት የመረጃ ማከፋፈልና ማሠራጨት ሥርዓቱ የዕዝ ሰንሰለት በመንግሥት ሥራና አሠራር ውስጥ ከላይ ወደ ታች እንደተዋቀረ ዘልቋል፡፡ ይህንን በየዘመኑ የነበረውን የሚዲያ ዓይነት፣ በመንግሥት ተቆልፎ የተያዘውንና የኖረውን ከላይ ወደ ታች የሚታዘዘውን የመገናኛ ሥርዓት ተግባር የመንግሥት ተግባር አከናዋኝ፣ መሣሪያነቱንም የመንግሥት የምንለው ሥራው የፕሮፓጋንዳ ሆኖ ስለኖረ ነው፡፡ ይህ ለመንግሥት ለራሱ ጭምር ዛሬ ሳይሆን ትናንት በንጉሡ፣ በደርግ፣ በኢሕአዴግ ዘመንም ችግር ፈጥሮ ዓይተናል፡፡ ይሰለችና ለመንግሥት ወሬና ልፈፋ (እውነትም ወሬና ልፈፋ ለሆነውም፣ ነው ለሚባለውም) ጆሮውን አልሰጥም የሚል ሰው ይፈጥራል፡፡ ይህም ቁጥር እየበዛ፣ እየተባዛ የመንግሥትን ‹‹ወሬ›› ትርጉም ያሳጣል፣ ወደ ተቃውሞም ይለውጣል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ከዚህም በፊት የነበረ፣ አሁን ደግም ተጠናክሮና ልዩ ሆኖ የተፈጠሩ ግምቶች፣ አሉባልታዎች፣ ሹክሹክታዎችና የሴራ ወሬዎች የሚነገሩበት (ከመንግሥት ይፋ መረጃና ዜና ጎን ለጎን የሚኖር)፣ ድሮ ከአፍ ወደ ጆሮ የሚቀባበሉት፣ አሁን ደግሞ በሶሻል ሚዲያ ‹‹ይድረስ›› ብለው የሚነዙበት ሥርዓት እንዲገኝ ያደርጋል፡፡
የመንግሥትን ሚዲያ ወደ ሕዝብ ሚዲያ ለውጠናል ወይ? ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29 (4) እና (5) ይፈጸም ያለውን ትዕዛዝ ፈጽመናል ወይ? ይህንን ጥያቄ ራሱ የመንግሥት ሚዲያና ይህንን ሚዲያም፣ ሌሎችን ሚዲያዎች ሁሉም የሚቆጣጠረው ተቆጣጣሪ አካል በቀጥታና በግልጽ አይመልሱልንም፡፡ እንዲያውም መጀመርያ ቋንቋውን፣ የሥራ ቋንቋ የሆነውን ቋንቋውን ተገን አድርገው የቃላት ጂምናስቲክ መሥራት ውስጥ የማይገባ የማደናገር/የማደንዘዝ ሥራ ይሠራሉ፡፡
‹‹በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ›› ወይም ‹‹በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ›› ሚዲያ ሲባል የትኞቹን ነው፡፡ መንግሥታዊ የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 6/1984 የዚህን ትርጉም የሚነግረን ‹‹ከመንግሥት በጀት ተመድቦላቸው በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥር የሚተዳደሩ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ሥርጭትና የፕሬስ አገልግሎቶች ናቸው›› በማለት ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 533/1999 ደግሞ ‹‹ሕዝብን ለማስተማር፣ ለማሳወቅና ለማዝናናት በአገር አቀፍ ወይም በክልል የሚቋቋም፣ ተጠሪነቱም ለፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ወይም ለክልል ምክር ቤቶች የሆነ በሙሉ ወይም በከፊል የመንግሥት በጀት የተመደበለት የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን አገልግሎት…›› የመንግሥት ብሮድካስት አገልግሎት ይባላል፣ አለ፡፡ ይህን የ1999 ዓ.ም. የብሮድካስት አዋጅ የሻረው የ(መጋቢት) 2013 አዋጅ ‹‹በአገር አቀፍ ወይም በክልል ደረጃ በሕግ የተቋቋመ ተጠሪነቱም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ለክልል ምክር ቤት የሆነ፣ ሙሉ በሙሉ ወይም በአብዛኛው በመንግሥት በጀት የሚተዳደር ከመንግሥት ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የሕዝብ ጥቅምን የሚያረጋግጡ ይዘቶች በማዘጋጀት ለሕዝብ የማቅረብ ግዴታ ያለበት የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን አገልግሎት…›› የሕዝብ ብሮድካስት አገልግሎት ይባላል ብሎ አወጀ፡፡
የ1999 ዓ.ም. የብሮድካስት አዋጅ የመንግሥት ብሮድካስት አገልግሎት፣ የ2013 ዓ.ም. የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ (ቁጥር 1238) የሕዝብ ብሮድካስት አገልግሎት ብለው ተለያይተው የጠሩት የሚዲያ ዓይነት፣ የአዋጆቹ ትርጉም ይዘት እንደሚያሳየው ያንኑ አንድና ራሱን በተጠሪነቱም በበጀቱም የመንግሥት የሆነውን ሚዲያ ነው፡፡ እርግጥ ነው ይህ የሚዲያ ዓይነት አዋጅ ቁጥር 1238/ሚዲያ ሕጉ ውስጥ ሲተረጎም የተወሰነ የቃላት ማስተካከያ መደረጉን፣ እንዲሁም ‹‹…ከመንግሥት ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የሕዝብ ጥቅምን የሚያረጋግጡ ይዘቶች በማዘጋጀት ለሕዝብ የማቅረብ ግዴታ ያለበት›› የሚል ባህርይ ትርጉሙ ውስጥ መታከሉን እናያለን፡፡
የ1999 ዓ.ም. ሕግ የመንግሥት ያለውን የ2013 ዓ.ም. ሕግ የሕዝብ ያለውን ዕውን በዚህ ጊዜ ውስጥ ደግመን ደጋግመን እንደገለጽነው ስቴት ሚዲያ ወደ ፐብሊክ ሚዲያነት ተቀይሮ ነው? እንዳንል ወይም ሌላ ከ2010 ዓ.ም. በኋላ በመጣ ለውጥ እንዳናመካኝ በተባለው ጊዜ ውስጥ (በአዋጅ የመንግሥት ብሮድካስት የሚባለውን) የብሮድካስት ባለሥልጣን/አሁንና በኋላ የሚዲያ ባለሥልጣን ይህንን የሚዲያ ዓይነት የሕዝብ ነው፣ የመንግሥት ሳይሆን የሕዝብ ነው የሚል መመርያን የመሰለ የሕግ ዓይነት በማውጣት ጭምር የተደገፈ ትግል ሲያደርግ አናውቃለን (የ2012 ዓ.ም. የመገናኛ ፖሊሲ ራሱ ፐብሊክን ሕዝብ ብሎ እንደሚጠራው ይመለከቷል)፡፡
እዚህ ላይ ጠቡና ክርክሩ፣ ወይም ‹‹ጭቅጭቁ›› አማርኛ ፐብሊክን ምን ብሎ ይተረጉመዋል? ምንስ ብሎ ቢተረጉመው ይሻላል? አይደለም፡፡ አማርኛ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የውጭ አገር ቋንቋዎችም ይህ ችግር እንዳለባቸው ባለሙያዎች ሲነግሩን አውቃለሁ፡፡ አማርኛ ውስጥም ቢሆን ፐብሊክ አንዴ ሕዝብ (ለምሳሌ የሕዝብ ጤና ጥበቃ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት) ሌላ ጊዜ ደግሞ የመንግሥት (የመንግሥት ገንዘብ፣ የመንግሥት ዕዳ፣ የመንግሥት ግዥ) ሲባል እናውቃለን፡፡ ጥያቄው ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ፐብሊክ ሚዲያ ማለት ምን ተብሎ ቢተረጎም ነው የሚያምርበት? የመንግሥት ነው የሕዝብ? የሚለው የቃላት ጨዋታ ላይ ሳይሆን ዋናው ጭብጥ ላይ ነው፡፡ ዋናው ጭብጥ ደግሞ ስቴት ሚዲያን ወደ ፐብሊክ ሚዲያን የመለወጥ ዴሞክራሲን የሚመለከት፣ የዴሞክራሲ ጉዳይ የሚጠይቀው ለውጥና ትራንስፎሜሽን አለ፡፡ ይህንን የትራንስፎሜሽን ዓይነት፣ ልክ፣ መልክና ይዘት ሕገ መንግሥቱ የፕሬስ ‹‹የተቋምና የአሠራር ነፃነት››፣ ‹‹የተለያዩ አስያየቶችን የማስተናገድ ችሎታ›› ብሎ ጠቁሞታል፡፡
የአገራችን ሚዲያዎች፣ የመንግሥት ሚዲያዎች ሁሉም ዓይነት ዝንባሌዎች የሚብላሉባቸው ናቸው ወይ? ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29 (1) እና (2)፣ ‹‹ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፣ ማንኛውም ሰው ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው›› ይላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአዋጅ አለኝ የሚለው የተለያዩ አመለካከቶችና ዝንባሌዎች ገበያ የሚቀርቡበት ምኅዳር ለምሳሌ ኢቢሲ/ኢቲቪ ውስጥ አለ ወይ? ኢቢሲ መከራውን እያየ ያስመረቀውና አሁንም የሚያስተዋውቀው፣ የሚያስጎበኘው፣ እዩልኝ ስሙልኝ የሚለው ለውጥ ይህንን ትራንስፎሜሽን ዋናው ጉዳዩ፣ ዋናው ተልዕኮው፣ ዋናው አደራውና ግዳጁ ያደረገ ነው ወይ?
ደግመን ደጋግመን የጠቀስነው፣ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 በከፊል፣ እንዲሁም የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/1999ን በሙሉ የሻረው፣ ከመጋቢት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ (ቁጥር 1238/2011) ፐብሊክ ሰርቪስ ብሮድካስቲንግ፣ ከዚህ በፊት የነበረና ራሱ የተካው አቻ ሕግ/አዋጅ የመንግሥት ብሮድካስት አገልግሎት ብሎ ይጠራው የነበረውን በአዋጁ አንቀጽ 2/11 ‹‹የሕዝብ ብሮድካስት አገልግሎት›› ብሎ እንደገና ሰይሞታል፡፡ ይህንን የመሰለ ድንብርብሮሽና የዕውር ድንብር ዕርምጃ ውሳኔና ‹‹ለውጥ›› ውስጥም፣ አማርኛ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ፣ የአገር ሕግ ምንም ብሎ ጠራው ምን፣ የመንግሥት ሚዲያ አለው የሕዝብ (የመንግሥት ወይም የሕዝብ የሚል፣ መንግሥትና ሕዝብ በዚህ ረገድ ተወራራሽ ናቸው ብሎ የሚያምን ሌላም ‹‹አቋም›› አለ)፣ በየትኛውም ስም የሚጠራ የዚህ ዓይነት የብሮድካስት አገልግሎት፣ ‹‹…ከመንግሥት ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የሕዝብ ጥቅምን የሚያረጋግጡ ይዘቶች›› የማዘጋጀትና ለሕዝብ የማቅረብ ግዴታ ያለበት መሆኑ በሕግ ተደንግጓል፡፡
ኢትዮጵያን ያጎደላት ነገር ኢወገናዊ ወይም በሌላ አባባል ነፃና ገለልተኛ በሆኑ ተቋማት ላይ ዴሞክራሲን መገንባት አለመቻላችን፣ አልሆንልን ያለ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ዴሞክራሲን የመገንባት ነገር ብቻ አይደለም፡፡ የመጠፋፋትና የመጨራረስ ዕድልን የሚያመክንም ጉዳይ ነው፡፡ የመጠፋፋትና የመበታተን ዕድልን አምክነን ዴሞክራሲን የመቀዳጀት ዕድልን የምንይዝበት አስተማማኙ ጎዳና ትልቅ ትንሽ ሳይባል ተቋማትን ሁሉ፣ የአገሪቱ የመከላከያ ኃይል ከመናጋትና ከመፍረስ አደጋ ጋር ሳይገናኝ ወይም እዚህ ውስጥ ሳይፈታ፣ የአገር የመረጃና የደኅንነት አውታራትም የልማት ሀብቶቻችንን፣ የሕዝብን ደኅንነትና ሰላምን ነቅቶ ከመጠበቅ ለአንድ አፍታም ሳያቋርጥ ከገዥ የፖለቲካ ቡድን ታማኝነትና ደባል አገልጋይነት እንዲላቀቁ፣ በአጠቃላይም የተክለ መንግሥቱ (የስቴቱ) አውታራት ገለልተኛ ባህርይን እንዲጎናፀፉ በማድረግ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሚዲያ በተቋምነቱ የአሠራር የአመራር ነፃነት ይኖረዋል ሲል እዚህ ውስጥ የሚካተቱ መሆኑን ያሳያል፡፡
ከፖለቲካ ወገንተኛነት ይልቅ ለእውነት፣ ለሚዛናዊነት ለነባራዊነት ታማኝ የሆኑና በዚህ ምግባር አማካይነት ብልሽቶችንና ጉድለቶችን ከራሳቸው ቤት/ድርጅት/ሚዲያ ከመንግሥት ቤት እስከ ግል ተቋምነትና ፓርቲዎች ድረስ እየገላለጡ ለሕዝብ የሚያቀርቡ ሚዲያዎች የሚፈኩት እዚህ ለውጥ ውስጥ ሲገቡ ነው፡፡
ሕገ መንግሥቱና ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በተግባር እንዲሠራ፣ ለዚህም ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት በአግባቡ እንዲቋቋም፣ የሥርዓተ መንግሥቱ ወታደራዊና ሲቪል ቢሮክራሲ፣ ሚዲያው ጭምር ከፓርቲ ማጠንትና ሰንሰለት መለየት አለበት፡፡ መገናኛ ብዙኃን የሕዝብ ተባለ፣ የመንግሥት ከፓርቲ ገዥነት አስተዳዳሪነት ማጠንትና ሰንሰለት አልተቆራረጠም ማለት ፓርቲዎች ከባለጠመንጃነት አልተሰነባበቱም፣ ከአግላይነት አልወጡም፣ ከዴሞክራሲያዊ አሠራርና አደረጃጀት እሴቶች ጋር ገና አልተግባቡም እንደ ማለት ነው፡፡ ፓርቲዎችን ከባለጠመንጃነት እናላቅ እያልን በሥራ አስፈጻሚዎቻቸው፣ በአመራር ቦርድ አባሎቻቸው አማካይነት በፓርቲ አባላት ሰዎች እስከ መመራት የከፉትን፣ በሌሎች ተቆጣጣሪ አካላት አማካይነትም ፓርቲያዊ ጡት አባት ያላቸውን ሚዲያዎች ‹‹በርቱ ግፉ ገና ነው›› ማለት ይከብደናል፣ ያሳፍረዋልም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡