Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ከአሮጌ ዓመት ወደ አዲስ ዓመት ለመግባት ዋዜማ ላይ ሆኜ የበዓል ትዝታዎች ቢቀሰቀሱብኝ ይህንን ገጠመኝ ለመጻፍ ተነሳሁ፡፡ የዘመን መለወጫ በዓል ሁሌም በብሩህ ተስፋ የሚከበር ስለሆነ ለአዲስ ዓመት የሚተላለፉ የመልካም ምኞት መግለጫዎች፣ በዚህ ስሜት የተቃኙና ከዛሬ ይልቅ ነገን የሚያስናፍቁ ናቸው፡፡ በአደይ አበባ የሚያጌጠው መስከረም ሲጠባ የክረምቱ ዝናብ፣ ቅዝቃዜ፣ ጎርፍና የድብርት ስሜት ቦታውን ለነፋሻ አየርና ብቅ ጥልቅ እያለች ለሰስ አድርጋ ለምታሞቀው ፀሐይ ቦታውን ይለቃል፡፡ አዲስ ዓመት አዲስና ጥልቅ የሆነ ተስፋ ሰንቆ ከች ሲል ተማሪው፣ ሠራተኛው፣ ገበሬው፣ ነጋዴው፣ ብቻ ምን አለፋችሁ ሁሉም በመልካም መንፈስ ይነሳሳሉ፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ ሁላችንም ከአዲስ ዓመት ጋር የየራሳችን ገጠመኞች አሉን፡፡

የ1980 ዓ.ም. ክረምት ተገባዶ አዲሱ ዓመት ሲብት ቤተሰቦቼን ጥየቃ ከአዲስ አበባ ወደ አሰላ መሄድ ነበረብኝ፡፡ ያኔ ኢምፖርት ኤክስፖርት (ኢምፔክስ) ይባል የነበረ የመንግሥት ተቋም ውስጥ በጀማሪ ኤክስፐርትነት ተቀጥሬ መሥራት ከጀመርኩ አንድ ዓመት ሞልቶኝ ነበር፡፡ ለሥራ ጉዳይ አሰብ ከርሜ ስመለስ የአንድ ሳምንት ፈቃድ ወስጄ ነበር ወደ አሰላ ጉዞ የጀመርኩት፡፡ የተሳፈርኩበት አንበሳ አውቶቡስ ከአዲስ ከተማ መናኸሪያ ተነስቶ ቃሊቲ ፍተሻ ደርሰን ከአውቶቡሱ ወረድን፡፡ አንድ ልጅ እግር ቢጤ የቆምኩበት መጥቶ ሲጋራ ግዛ ይለኛል፡፡ ሲጋራ እንደማላጨስ ስነግረው፣ ‹‹ታድለህ የእዚህ አገር ሰው እኮ እንዳለ አጫሽ ነው…›› ሲለኝ፣ ‹‹ምን ይደረግ ብለህ ነው መንግሥት በአፉ አላስተነፍስ ሲለው በሳንባው ይተንፍስ እንጂ…›› እያሉ አንድ አዛውንት ድንገት ወሬያችን ውስጥ ገቡ፡፡

እኔም ልጁን ከዚህ በላይ ማስቆሙ ጠቀሜታ ስለሌለው አንድ እሽግ ማስቲካ በስሙኒ (ሃያ አምስት ሳንቲም) ገዝቼው ካሰናበትኩት በኋላ፣ ‹‹አባቴ ንግግርዎ ቅኔ አዘል ነው መሰል…›› ስላቸው፣ ‹‹የምን ቅኔ አመጣህ ወዳጄ፣ ይህ ሁሉ የምታየው አጫሽ…›› ብለው በጣታቸው ከአውቶቡስ ወደ ወረዱ ተሳፋሪዎች ሲያመለክቱ፣ ከሴቶቹ በስተቀር ሁሉም ለማለት እስኪቻል ድረስ በሲጋራ ጭስ ታጥነዋል፡፡ ፈታሾቹ ከውስጥና ከአውቶቡሱ አናት ላይ ወጥተው ሻንጣ ሲበረብሩ የእኛ ሰው ይህንን ትምባሆ ይምገዋል፡፡ ‹‹…ይህ ሁሉ የምታየው አጫሽ ወዶ መሰለህ እንዴ የሲጋራ ሱሰኛ የሆነው… በየእስር ቤቱ ታጉሮ ከርሞ እኮ ነው ከእነ ሱሱ የተለቀቀው…›› ሲሉኝ፣ በዘመነ ነጭና ቀይ ሽብር ከሞት የተረፉ ሰዎችን ጉዳይ እየተናገሩ መሆኑ ገባኝ፡፡

ፈታሾቹ መታወቂያ እያዩና እየበረበሩ ማስገባት ሲጀምሩ፣ ‹‹ይኸውልህ ልጄ ሁለት ልጆቼ በዕድል ከግድያ ተርፈው በሕይወት አሉ፡፡ አንዱ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ተመርቆ ጥሩ ሥራ አለው፡፡ አንዱ ደግሞ ከመምህራን ማሠልጠኛ ተመርቆ አስተማሪ ነው፡፡ ምን ያደርጋል ታዲያ ሁለቱም ይህንን ትምባሆ ከንጋት እስከ ውድቅት እየማጉ ሰው አልመስል ብለዋል፡፡ ይህ እርኩስ ፖለቲካ ልጆቻችንን በመጥፎ ሱስ ሲበክል አገራችንን ደግሞ እያቀረናት ነው…›› እያሉኝ እኛም ተራችን ደርሶ ተፈትሸን አውቶቡሱ ውስጥ ገብተን ጉዞ ተጀመረ፡፡ ከአዛውንቱ ጋር መቀመጫችን የተለያየ በመሆኑ ወጋችንም በዚሁ አበቃ፡፡ አዛውንቱ ከተናገሩት ጋር ይገናኝ ወይም አይገናኝ ባላውቅም እኛ መሥሪያ ቤት በተለይ ወጣት ወንድ ሠራተኞች በብዛት አጫሽ ነበሩ፡፡ በእርግጥም ከማዕከላዊና ከከርቸሌ ተፈተው የተለቀቁም እንደነበሩ ግን አልዘነጋም፡፡

አሰላ ደርሼ ከእናቴ፣ ከአባቴ፣ ከእህት ወንድሞቼ፣ ከዘመዶቻችን፣ እንዲሁም ከወዳጅ ጎረቤቶቻችን ጋር የናፍቆት ጊዜዬን እያሳለፍኩ በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ሳከብር የተሰማኝ ደስታ ወደር የለውም፡፡ ከወንድሞቼና ከድሮ ጓደኞቼ ጋር ወጣ እያልን ቢራ ስንቀማምስ በየሆቴሉም ሆነ በየመንገዱ የአጫሹ ብዛት በጣም ብዙ ነበር፡፡ ዕድሜ ለእዚያ የቃሊቲ ሲጋራ ነጋዴ ብላቴና ይሁንና በተለየ ትኩረት አጫሾችን ሳያቸው፣ ከወንድሞቼና ከጓደኞቼ ጋርም ስለጉዳዩ ስንነጋገር የተገነዘብኩት የዘመነ ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር የጅምላ እስራት ውጤት መሆኑን ነው፡፡ በአዲስ አበባም ቢሆን ያኔ በመመርያ ተከልክሎ እንጂ አውቶቡስ፣ ታክሲ፣ ሲኒማ ቤት፣ ቴአትር ቤትም ሆነ የሕዝብ መሰባሰቢያ ቦታዎች ማጨስ የተለመደ ነበር፡፡

የበዓሉ ሰሞን እረፍቴ አልቆ ወደ አዲስ አበባ ልመለስ ሁለት ቀናት ሲቀሩኝ አባቴ በድንገት እንግዶች እንደሚጋብዝ ነገረን፡፡ ለመስተንግዶውም ሁለት የፍየል ሙክቶች አሳርዶ ነበር፡፡ አንዱን ለቁርጥና ለጥብስ፣ ሌላውን ለወጥና ለቅቅል ነበር ያሳረደው፡፡ ቀኑ ቅዳሜ ስለነበር ይመጣሉ ተብለው የሚጠበቁት እንግዶች ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ደረሱ፡፡ በካኪና በውኃ ሰማያዊ የኢሠፓ የደንብ ልብስ ሽክ ያሉ አሥር ያህል ወንዶችና ሴቶች ነበሩ የመጡት፡፡ ሁሉም የክፍለ ሀገሩ ኢሠፓ መሥሪያ ቤት ሹሞች ሲሆኑ፣ አባቴ ለምን እንደጋበዛቸው እስካሁን ድረስ አላውቅም፡፡ ሰዎቹ ገብተው ሰፊው ሳሎን ውስጥ የሚገኘው ትልቅ የመመገቢያ ጠረጴዛ ዙሪያ እንደተሰየሙ ቢራ፣ ጠጅ፣ ጠላ፣ አረቄ፣ ጂን፣ ውስኪ በየዓይነቱ ከፊታቸው ተደረደሩ፡፡

የኢሠፓ ጓዶች በአባቴ አጋፋሪነትና በእናቴ ጋባዥነት ምሳቸውን እንዲያነሱ በክብር ተጠይቀው በየተራ እየተነሱ ከፍየል ቁርጡ፣ ከጥብሱ፣ ከወጡና ከቅቅሉ እየወሰዱ ተቀምጠው መመገብ ጀመሩ፡፡ ደጋግመው እየተነሱ ከአሰኛቸው እየወሰዱ በሚገባ በልተው መጠጥ ሲጀምሩ፣ ከመሀላቸው የሚያጨሱት ደግሞ ወደ በረንዳ ወጣ እያሉ ሱሳቸውን እያረኩ ነበር፡፡ መጠጡ እየተደጋገመ ጨዋታው ሲደራ አባቴ፣ ‹‹ጎበዝ ይኼ አጫሽነት በጣም በዛ እኮ ለምን አብዮታዊ መንግሥታችን አንድ መላ አይፈልግም…›› እያለ ሲስቅ፣ ከመሀላቸው እንደ አለቃ የሚከበረው ጓድ አጫሽ ባይሆንም፣ ‹‹ፓርቲያችን ዴሞክራሲያዊ መብት ስለማይጋፋ መንግሥት መከልከል አይችልም…›› ብሎ እሱም ሳቀና ነገሩ በዚህ ተዘጋ፡፡

ከስንትና ስንት ዓመታት በኋላ አምና ከአሜሪካ የመጣ የድሮ የመሥሪያ ቤት ጓደኛዬ ጋር ለአዲስ ዓመት ዋዜማ ምሽት አንድ ታዋቂ ክለብ ሄድን፡፡ ያኔ በእኛ ጉርምስና ዘመን ወንዶች በበላይነት ሲያቦኑት የነበረውን ሲጋራ፣ አሁን ሴቶቹ በእጥፍ አስከንድተው ሲምጉት ሳይ አዲስ ነገር ነው የሆነብኝ፡፡ እንኳን አሁንና በወጣትነቴም በጣም ወግ አጥባቂ ስለነበርኩ የምሽቱን ሕይወት ሳላውቅ ነበር ወደ ትዳር የገባሁት፡፡ ከአሜሪካ የመጣው ወዳጄም ሆነ ሌሎች በኋላ እንደነገሩኝ፣ በዚህ ዘመን ሴቶች በጣም እንደሚያጨሱና ከወንዶች እኩል ሆነዋል፡፡ በበዓሉ ዋዜማ ምሽት አንዲት ወጣት ቆንጆ ለጓደኞቿ፣ ‹‹የአዲሱ ዓመት ሪዞሉሽኔ ሲጋራ ማቆም ነው…›› ስትል ሲስቁባት ሰማሁ፡፡ እኔ ደግሞ ያኔ ጭልጥ ብዬ አንድ ትውልድን ያገዳደለውና ለስደት የዳረገው ፖለቲካ ትውልዱን ለሱስ መዳረጉን፣ ዛሬም እያገዳደለና እርስ በርስ እያሳደደ መሆኑን በቁጭት እያስታወስኩ፣ ‹‹አምላኬ ሆይ ከሱስ ብቻ ሳይሆን፣ አልላቀቅ ካለን ግጭትና ጥፋት አላቀን…›› እያልኩ ነበር፡፡ አሁንም እንደዚያ እያልኩ እየተማፀንኩ ነው፡፡

(ዘነበ መንገሻ፣ ከለቡ)    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...