Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየበዓል ቀን ትጉኃን

የበዓል ቀን ትጉኃን

ቀን:

የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በበዓላት ቀናት አዕምሯቸውንም ሆነ አካላቸውን ዘና አድርገው ለማሳለፍ ጥረት ያደርጋሉ። እንደየ ብሔራቸው ባህል ተውበውና በአገር ጥበብ አልባሳት ደምቀው ከቤተሰቦቻቸው፣ ከዘመድ አዝማድና ከጎረቤቶቻቸው ተቀላቅለው በጋራ ያሳልፉታል። 2016 .. ዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ልንዘክራቸው የመረጥናቸው ባለታሪኮች ግን ቱታና ገዋን ለብሰው የበዓል ቀናትን በሥራ የሚያሳልፉ ትጉኃን ናቸው። ብዙ ሰዎች በበዓላት ከቤተሰብና ከዘመድ አዝማድ ጋር ተሰባስበው ይውላሉ እነዚህ ባለታሪኮች ግን ግዳጃቸውን ለመወጣት በተጠንቀቅ ሆነው ያሳልፋሉ፣ የቤተሰብም ሆነ ወዳጅ ዘመድ ናፍቆትን ወደ ጎን ብለው ጊዜያቸውን ማኅበረሰቦቻቸውን ለማገልገል ያውላሉ፡፡  በበዓላት ቀናት ማኅበረሰብን በማገልገል ሥራዎች ወይም ግዳጅ በመወጣት የሚያሳልፉት እነዚህ ሰዎች የተሸከሙት ኃላፊነትና ጫና ከባድ ቢሆንም ሥራቸው በስተመጨረሻ በሚያጎናጽፋቸው ደስታና ዕርካታ እንደሚካሱ ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ሕዝብ አገልጋዮች በሆስፒታሎችና ጤና ተቋማት አሉ፣ በመከላከያና በፖሊስ ሠራዊት ውስጥ ይገኛሉ፣ በእሳት አደጋ፣ በአምቡላንስ አገልግሎት፣ በፋርማሲ፣ በትራንስፖርት፣ በቴሌኮም፣ በአየር መንገድ፣ በምግብና መጠጥ ቤቶች ልክ እንደ አዘቦቱ በበዓላት ቀናትም ሕዝብ በማገልገል የሚያሳልፉ ጀግኖች ናቸው፡፡    

ኅብረተሰቡ ብዙም ላይረዳቸው ይችላል፡፡ በየቤቱ ከቤተሰቡ ጋር ተሰባስቦ እየበላና እየጠጣ በዓልን ከሚያከብረው መካከል የወሬ ማጣፈጫ አድርጎ ስማቸውን በመጥፎ የሚያነሳም አይጠፋም፡፡ ‹‹እነሱማ እንኳን እንደ ዛሬው ያለ የበዓል ቀን ይቅርና፣ በመደበኛ የሥራ ቀንም መቼ በአግባቡ ሥራቸውን ይሠሩና፤›› እየተባለ መታማታቸው የተለመደ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ባለታሪኮች በሚችሉት አቅም አገልግሎት ባይሰጡ ኖሮ በዓላትን ማክበርም ሆነ መደበኛ ሕይወትን መምራት ከዚህ በላይ መክበዱ እንደማይቀር በቀላሉ መገመት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ አድጋና በልፅጋ በአደጋም ሆነ በድንገተኛ አጋጣሚዎች የሚጠፋውን ሕይወትና የሚወድመውን ንብረት አሁን ካለው በላይ መቀነስ ቢቻል የሁሉም ደስታና ምኞት ነበር፡፡ በአቅማቸው እስከዚያው ግን በየተሰማሩበት ሕዝብ አገልግሎት ሰጪነት ዘርፍ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ለሕዝቡ አገልግሎት የሚሰጡ ጀግኖችን እንዲህ ባለው የበዓል ቀናት ጀግና ብሎ ማመሥገኑ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ዓውድ ዓመት ሲመጣና ኅብረተሰቡ በያለበት በዓሉን ለማሳለፍ ሲጣጣር እነሱ ሕዝብን ለማገልገል የሚሸከሙት ኃላፊነት ከሌላው ጊዜ ከፍ ያለ ነው፡፡ እነዚህን ሕዝብ አገልጋይ ‹‹የበዓል ቀናት ጀግኖች›› ብለን በዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ በሪፖርተር ጋዜጣ ዕትማችን ከፍ ያለ ቦታ ሰጥተን በዓላትን የሚያሳልፉበትን መንገድ፣ አገር ከአደጋ እንድትጠበቅ ያላቸውን በጎ ምኞት፣ ኅብረተሰቡ ‹‹ቢረዳልን›› የሚሉትን ቁም ነገር፣ በበዓላት ወቅቶች ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎችና የበዓል ቀናት ልዩ ገጠመኞቻቸውን እያወጋን እንዘክራቸዋለን።

‹‹ኅብረተሰቡ በዓልን በሰላም ካከበረ ነው የእኛ በዓል በዓል የሚሆነው››

ትዕግሥት ተክለአብ ትባላለች በእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ሥራ አመራር ኮሚሽን በቡድን መሪነት በማገልገል ላይ ትገኛለች። ትዕግሥት የሦስት ልጆች እናት ሰትሆን፣ አንደኛዋን ልጇን እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ አስተምራና አስመርቃ ለሥራ አብቃታለች። ትዕግሥት ስለ ተሰማራችበት ከአደጋ የሚያጋፍጥ የሕዝብ አገልግሎት ሥራዋና በዓላት በእሷ ሕይወት ውስጥ ያላቸው ትርጉምና እነዚህን ቀናት እንዴት እንደምታሳልፋቸው አውግታናለች። 

የበዓል ቀን ትጉኃን | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በእሳት አደጋ ውስጥ ስሠራ 16 ዓመታት አሳልፌያለሁ፡፡ ሙያውን ወድጄው ነው የምሠራው፡፡ አንቺን ትተን እንዴት በዓል እንውላለን፣ ተሰብስበን የምናከብረው መቼ ነው፣ ሴት ውጪ ሆና ወንድ ቤት ውስጥ የሚሉ ጫናዎች ከቤተሰብ ይመጣሉ፡፡ በዚህ ሥራ ለመዝለቅ አሉታዊ ነገሮችን ማለፍ ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን ደግሞ ሥራው ብዙ አዎንታዊ ጎኖችም አሉት፡፡ እንዲህ ዓይነት አደጋ ተፈጥሮ በዚህ መንገድ ደርሰን የሰው ሕይወት አተረፍን ስትል ሰው ይረዳል፡፡ 

በልምድና በሒደት ቤተሰቤ እየተረዳኝ መጥቷል፡፡ መጀመሪያ ላይ ግን ዛሬ እናታችን የለችምና ዓመት በዓል ቤታችን የለም የሚል ሐዘንና ለቅሶ ጭምር ልጆቹ ላይ ይታይ ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን እየተረዱኝ መጥተዋል፡፡ ከጎንህ ያለው የትዳር አጋር ደግሞ የሚረዳህ ከሆነ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ባለቤቴም ፖሊስ ስለሆነ ሁኔታውን ይረዳል፡፡ ተጋግዘን ነው ሥራዎችን የምንሠራው፡፡ በበዓል ቀናት ለ24 ሰዓታት ሥራ የምውል ከሆነ ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ አስፈላጊውን የዝግጅት ሥራ ሠርቼ እገባለሁ፡፡ በዕለቱ የቤት ሥራው ባይኖርም ቤተሰቤ በዓሉን ያከብረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ሁኔታ እስክትቀበለው ይከብዳል፡፡

አደጋው እኛ ቤት ቢሆንስ የደረሰው ብለህ ስታስበው በበዓል ቀናት በሥራ ማሳለፉን ትቀበለዋለህ፡፡ በዓል ውጪ ማሳለፍ ይከብዳል፡፡ ነገር ግን ስትለምደው ደግሞ ቤት መዋሉ ነው የሚከብደው፡፡ እኔ ለምሳሌ በዓል ሥራ ሳልገባ ቤቴ በማሳልፍባቸው ቀናት ልቤ አያርፍም፡፡ ምን ይፈጠር ይሆን ብለህ ሥራህን ታስባለህ፡፡ አንዴ የሥራ ባህሪውን ከለመድከውና አምነህበት ከተቀበልከው ነገሮች ቀላል ይሆናሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ምነው ቢቀርብኝ ብለው ሥራውን እስከመተው ሊደርሱ ይችላሉ፣ አዳር ሥራ ይቅርብኝ የሚሉም ይኖራሉ፡፡ ዋናው ሥራው የሚጠይቀውን ከባድ ኃላፊነት አምኖ የመቀበል ጉዳይ ነው፡፡

ሰው ተሰብስቦ በዓልን ሲያከብር እኛ ደግሞ በዓል አክባሪውን ሕዝብ እየጠበቅን ነው በዓል የምናከብረው፡፡ በዓላትን ሁሌም ሕዝብን  እያሰብን ነው የምናከብረው፡፡ በዓሉ ሲቃረብ ስታንድ ባይ ይባልና ዕቃዎቻችን በሙሉ ተፈትሸው ከሌላው ጊዜ በተለየ ዝግጁ ይደረጋሉ፡፡ የጎደለው ይሟላል የተበላሸውም ይጠገናል፡፡ የሰው ኃይል የሚጎድል መሆኑ ከታመነ የዓመት እረፍት ላይ የሚገኙ ሠራተኞች እረፍታቸው ለሌላ ጊዜ እንዲዘዋወር ተደርጎ ለበዓል ሥራ ዝግጁ ይሆናሉ፡፡ በዚህ መንገድ ራሳችንን በቁሳቁስም ሆነ በሰው ኃይል አዘጋጅተን ነው ለበዓላት የአደጋ መከላከል ሥራችን የምንጠባበቀው፡፡ 

ከዚሁ ጎን ለጎን ግን ከበዓላት ቀደም ብሎ በበዓላት ወቅት በምን ምክንያቶች አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ለኅብረተሰቡ የተለየ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ይሠራል፡፡ የበዓላት ዝግጅት ሥራዎችን ሰዎች ሲሠሩ ከጥንቃቄ ጉድለት ወይም ባለማወቅና በድንገት ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በተመለከተ ትምህርት ይሰጣል፡፡ በሙቀትም ሆነ በፍጭት የሚከሰቱ አደጋዎች ይኖራሉ፡፡ 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሳኒታይዘር ከሰል የማቀጣጠል ልማድ መጥቷል፡፡ እጅግ ተቀጣጣይ በሆኑ አልኮልና ሳኒታይዘሮች እሳት ማያያዝ አደገኛ መሆኑን ቅስቀሳ እናደርጋለን፡፡ በየመኖሪያው መንደር ታች ድረስ ባሉ አደረጃጀቶችም ሆነ የጥንቃቄ መልዕክት የያዙ በራሪ ወረቀቶችን መበተን ግንዛቤ እናስጨብጣለን፡፡ ከግንዛቤው በተጨማሪም አደጋ ቢደርስ ለማን መደወል እንዳለበት በቅርበት ያሉ አደጋ መከላከል ቅርንጫፎች ስልክ ቁጥርም ይበተናል፡፡ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅትና ጥንቃቄ ካደረግን በኋላ የበዓሉን ዕለት ለግዳጅ ራሳችንን ዝግጁ በማድረግ በየመሥሪያ ቤታችን የበዓል ድባብ በመፍጠር ነው የምናሳልፈው፡፡ በግ ሊታረድ ይችላል፣ ወይም ሥጋ ሊገዛ ይችላል፣ ቡና ተፈልቶ የቤቱ የበዓል ድባብ ሳይቀርብን ነው በሥራ የምናሳልፈው፡፡ 

የእኛ በዓል ኅብረተሰቡ ካከበረ በኋላ ነው የሚመጣው፡፡ በዓላት በሰላም ያለአደጋ ተከብረው ከሥራ ወጥተን ወደ ቤተሰቦቻችን ተቀላቅለን የቀረውን የበዓል ጊዜ ማሳለፉ ትልቅ ዕርካታ አለው፡፡ ኅብረተሰቡ በዓልን በሰላም ካከበረ ነው የእኛ በዓል በዓል የሚሆነው፡፡ 

በበዓላት ቀኖች የእሳት አደጋ፣ የመቃጠል አደጋ ወይም የሕይወት አደጋዎችን እምብዛም ላንሠራ እንችላለን፡፡ በበዓላት ቀናት ከሁሉ በላይ ከትራፊክ አደጋ ጋር የተያያዙ የአደጋ ሥራዎች ናቸው የሚበዙት፡፡ ጠጥቶ በማሽከርከር፣ መኪና ለሌላ ወገን አሳልፎ በመስጠት፣ ብዙ ሆኖ በመጓዝ፣ ከልክ በላይ በሆነ ፍጥነት መንዳት የሚከሰቱ አደጋዎች በርካታ ናቸው፡፡ አንዳንዴ የማይጠበቁ ዓይነት የተሽከርካሪ አደጋዎች ናቸው የሚገጥሙን፡፡ መንገድ ስቶ ደረጃ ወርዶ ሁሉ አደጋ የማድረስ ሁኔታ ያጋጥሙናል፡፡ እንደዚህ ዓይነት አደጋ በበዓላት ማየቱ ሰው ነህና ይረብሻካል፡፡ ከአደጋው ቦታ የምናነሳቸው ሰዎች መጠንቀቅ ሲችሉ ለዚያ መሰል አደጋ መዳረጋቸው ያሳስባል፡፡ 

ኅብረተሰቡ ጋር ሥራችን የሚጠይቀውን ውጣ ውረድ ያለመረዳት ችግር እንዳለ ይሰማኛል፡፡ እናንተማ እዚያ ተቀምጣችሁ እየበላችሁና እየጠጣችሁ ታሳልፋላችሁ እንጂ በበዓላት ቀናት መቼ መልስ ትሰጣላችሁ የሚል ስሞታ ይቀርብብናል፡፡ በአንድ አጋጣሚ ለአደጋ መከላከል በሄድንበት ቦታ ምን ትሠሩልናላችሁ ሂዱ ከዚህ ተብሎ በእልህና በዱላ ሰዎች ሊያባርሩን የሞከሩበትን አጋጣሚ አልረሳውም፡፡ ዱላውንም ነቀፌታውንም ችለን መሥራት ነበረብን፡፡ ብዙ ጊዜ ሱቆች ሲቃጠሉ፣ ሥጋ ቤትና ንግድ ቤቶች አደጋ ሲደርስባቸው ግርግርና ሁከት ይገጥመናል፡፡ አሁን ነው ወይ የምትመጡት የሚል ቁጣና እልህ የተቀላቀለበት ስሜት እናስተናግዳለን፡፡ ዕቃ ካላወጣን በሚልም ለአደጋ የሚያጋልጥ ግብግብ ያጋጥመናል፡፡ በሒደት ግን በጎ ፈቃደኞችን አሠልጥነን በማሰማራት ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቀየር ጥረት አድርገናል፡፡     

አደጋ ተብሎ ንግግር የለም፡፡ እኛ በማንኛውም ቀን ይሁን አደጋ ተብሎ ደውል ከተደወለ የያዝነውን ነገር ጥለን ነው የምንሰማራው፡፡ አንድ የበዓል ዕለት በግ ታርዶ ውጪ እየተጠበሰ ሳለ የአደጋ ጥሪ መጣ፡፡ ሁሉም ሠራተኛ ጥሎት ነበር ወደ ግዳጁ የተሰማራው፡፡ አደጋውን የመከላከል ሥራ ሠርተን ከሰዓታት በኋላ ስንመለስ የበጉን ጥብስ አላገኘነውም ነበር፡፡ በውሾችና ድመቶች ተበልቶ ነበር የጠበቀን፡፡ ሌላው ቀርቶ ጥብሱ የሚጠበስበትን እሳት እንኳን የተቋማችን ጥበቃዎች ነበር ያጠፉት፡፡ አንዳንድ ሰዎች እናንተማ ለበዓል ስትጠጡና ስትበሉ ነው የምታሳልፉት ቢሉም እኛ ግን የአደጋ ጥሪ ከመጣ ምንም ነገር ቢሆን ጥለን ነው ወደ አደጋው ቦታ የምንበረው፡፡  የምንሠራው ሥራ ስለሚያረካ የሚበላው ጥብስ ከነመኖሩም ይረሳል፡፡ የሰው ሕይወት ካልጠፋ የንብረት ጉዳቱ መልሶ ስለሚተካ የሰው ሕይወትን ማትረፍ ላይ ነው ቅድሚያ ሰጥተን የምንሠራው፡፡ 

አሁን አሁን ከኅብረተሰቡ ጋር በደንብ የመማማር ዕድል እየፈጠርን እንገኛለን፡፡ በበዓላት ቀናት መዋያ ብሎ ራሱ አስቦ በግ ገዝቶ የሚያመጣው በየአካባቢው ያለው ኅብረተሰብ ነው፡፡ እነሱስ ማን አላቸው ብሎ ላግዛቸው የሚለው ሰው እየበረከተ ነው፡፡ አደጋ ቦታዎች ላይ ስንደርስ ጭምር ሸራውን መዘርጋትና ሌላም እገዛ የሚያደርግልን ኅብረተሰቡ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጎ ፈቃደኝነትና ቀና ድጋፍ እየጨመረ መጥቷል፡፡ 

የበለጠ ባደረግነው ብዬ የሚቆጨኝ ነገር የትራፊክ አደጋ መቀነስን ነው፡፡ እሳት አደጋ እየቀነሰ የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች ግን እየጨመሩ ነው፡፡ በአገራችን ባለው የኢኮኖሚ ድህነትና የኑሮ አስቸጋሪነት እጅግ ከባድ የሕይወትና ንብረት አደጋ መብዛቱ በጣም ያሳስባል፡፡ ለምን ሰዎች ያለመንጃ ፈቃድ መኪና ያሽከረክራሉ፡፡ ተቆጣጣሪ ሳይሆን ራሳችንን መግዛት አለብን፡፡ የመኪና አደጋ ደርሶ ቦታው ስንደርስ ሹፌሩ ሳይሆን ረዳቱ ሲያሽከረክር አደጋው መፈጠሩን እናያለን፡፡ ሁሉም ኃላፊነት ቢወስድ ይህ አደጋ ይቀንሳል፡፡

ሌላው ለመሠረተ ልማት ተብለው የምንቆፍራቸው ጉድጓዶች እያደረሱት ያለው አደጋን ማስቀረት አለመቻላችን ይቆጨኛል፡፡ አንዱ ሲገነባ ሌላው የተቆፈረውን ነገር የሚመልስበት ሁኔታ ካልተፈጠረ ወይም ለጊዜውም ቢሆን የአደጋ ምልክት በቦታው የሚያደርግ ከሌለ ችግሩ አይቀረፍም፡፡ ከጉድጓድ አደጋ ራሱ እንዲጠበቅ የሚያደርግ አሠራር የለም፡፡ በዚህ ዓመት በብዛት የተሠራው የጉድጓድ አደጋ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡በተለይ ልጆች ኳስ ሲጫወቱ ኳስ ተንከባሎ ጉድጓድ ውስጥ በመግባቱ እሱን አመጣለሁ በሚል ሰጥመው አደጋ የደረሰባቸው ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ እየተነጋገርን ተናበን ብንሠራ እላለሁ፡፡ ቴሌ ወይ መብራት ኃይል የቆፈረውን መልሶ ቢጠግን፡፡ መንገዶች የቆፈረውን መልሶ ቢሞላው፡፡ እኛም ቢሆን በተቆፈሩት ቦታዎች አደጋ እንዳይደርስ የሚያስጠነቅቅ ሥራ ብንሠራ፡፡ በአጠቃላይ የቅንጅት ሥራ ብንሠራ ነው የምለው፡፡ 

እንደ ኅብረተሰብ ደግሞ ለአደጋ ሥራዎች የበለጠ ትብብር ቢደረግ እላለሁ፡፡ ለአደጋ መከላከል እየሄድን አንዳንድ መኪናዎች መንገድ ይዘጉብናል፡፡ የአደጋ ጊዜ መፍጠኛ መስመር የለንም፡፡ አንድ መንገድ ነው የምንጠቀመው፡፡ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ሳይረን ድምፅ እየሰማ መንገድ የማይለቅና መንገድ የሚዘጋ አለ፡፡ ያን ሰው ገጭተን ማለፍ አንችልምና ቀና ትብብር ከሁሉም ብናገኝ፡፡ ቀድመን አደጋው ቦታ ለመድረስ ጥረት የምናደርገው የአደጋውን ጉዳት ለመቀነስ ነው፡፡ ቀድመን ለማለፍ እንጂ አደጋውን ለማሳለፍ ብዙ ጊዜ አንሮጥም፡፡ ይህ በኅብረተሰባችን ዘንድ ቢስተካከልና በጎ ትብብር ቢደረግ እላለሁ፡፡     

‹‹ልንከላከለው የምንችለው አደጋ ሆኖ ሰዎች ከተጎዱ በኋላ መድረስ ፍፁም ስሜት የሚጎዳ ነገር ነው››

በእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአራዳ ቅርንጫፍ የአደጋ ምላሽ ሥራ ክፍል ኃላፊ

አዲስ አበባ ከተማ ሰፍታለች፡፡ ለሰፊዋ አዲስ አበባ ከጊዜው ጋር አብሮ የሚሄድ እሳትና ድንገተኛ አደጋ ተከላካይ ተቋም ያስፈልጋል በሚል በከተማ ደረጃ የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ተዋቅሯል፡፡ ተቋሙ አሁን ላይ በዘጠኝ ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም ለከተማዋ 36 ቅርንጫፍ ማዕከላት እንደሚያስፈልግ ነው የቅርብ ጊዜ ጥናት ያረጋገጠው፡፡ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ረዣዥም ፎቆች እየገነባች ያለች ከተማ ብትሆንም የዚህ ተቋም አደጋ የመከላከል ከፍታ 74 ሜትር የሚረዝም ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ተቋሙ ከከተማዋ ዕድገት ጋር የሚሄድ አገልግሎት ለማቅረብ ድሮንና ሄሊኮፕተር የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች እንዲሟሉለት ጥያቄውን ለመንግሥት አቅርቧል፡፡ 24 ሰዓታት ወደ 3,000 የሚሆን ሐሰተኛ አደጋ ጥቆማ ጥሪ ይደርሰኛል የሚለው ተቋሙ ይህን የሚያጣራ አዲስ ቴክኖሎጂ ስለማስገጠሙ ይገልጻል፡፡ 

የበዓል ቀን ትጉኃን | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአራዳ ቅርንጫፍ የአደጋ ምላሽ ሥራ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ከበደ በእሳቸው የሙያ ዘርፍ ሁሉም ዕለት የሥራ ቀን እንደሆነና የበዓል ቀን ሆነ አልሆነ ለውጥ እንደሌለው ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ደግሞ ልጆች ጥሎ፣ የትዳር አጋር ጥሎ፣ ቤተሰብ ጥሎ ከቤት ውጪ በሥራ ማሳለፍ ከባድ መሆኑንና እንዲህ ዓይነት የሥራ ሕይወት ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ ያምናሉ። እሳቸው የተሰማሩበት አገልግሎት ከሌላው የተለየ ባህሪ እንዳለው፣ ጊዜ እንደማይሰጥ በመጠቆም ከሚያገለግሉት ማኅበረሰቡ በኩል አለ ያሉትን የግንዛቤ ክፍተትም ያነሳሉ።

የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አገልግሎት የሚሰጠው ዓመቱን ሙሉ ለ365 ቀናትና በየቀኑ ለ24 ሰዓታት ነው፡፡ በተቋሙ ባህሪ፣ በሚሰጠው አገልግሎት፣ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት በማንኛውም ቀን በማንኛውም ሰዓት ማንኛውም አደጋ ቢከሰት አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ባወጣው አዋጅ ቁጥር 74/2014 የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ አገልግሎት የምሰጥበት ሁኔታ ደግሞ ሁሌም ክፍት ነው፡፡ ተቋሙ ግዳጅ በመጣ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በመደበኛ ወቅትም አደጋ ሲከሰት የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ይሠራል፡፡ በሰው ሕይወትም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥረት ያደርጋል፡፡ በአደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን በጊዜያዊነት የማቋቋም ሥራም ይሠራል፡፡ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕርዳታዎችን በማቅረብ በአደጋ የተፈናቀሉ ሰዎችን በጊዜያዊነት የመደገፍ ሥራ ይሠራል፡፡ 

በመጀመሪያ እኛ ኅብረተሰቡ ጋር መድረስ አለብን፡፡ የምንሠራቸውን ሥራዎች ማሳወቅ አለብን፡፡ ኅብረተሰቡ ደግሞ እኛ ምንነግረውን ነገር መቀበል መቻል አለበት፡፡ ሕዝቡ እኛ የምንሰጠውን አገልግሎት በደንብ ሲያውቅ ነው በእኛ ላይ አዎንታዊ አመለካከት ሊያሳድር የሚችለው፡፡ እኛም ኅብረተሰቡ ውስጥ ነው ያለነው ብዙ ጊዜ ባለማወቅ በቅጡ ተገቢ የሆነ አገልግሎት አይሰጡም የሚል አመለካከት አለ፡፡ 

የእኛ አገልግሎት ከሌላው የተለየ ባህሪ ያለው ነው፡፡ አገልግሎታችን ጊዜ አይሰጥም፡፡ ሌላው ዘርፍ ላይ መከላከያም ሆነ ፖሊስና ሌላ ጊዜ የሚሰጡ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ የምታደራጅበትና የምታሰማራበት ጊዜ ልታገኝ ትችላለህ፡፡ እኛ ተቋም ጋር ግን ሁልጊዜ ስታንድ ባይ ሆነህ መገኘት ነው ያለብህ፡፡ በስታንዳርድ ነው የምንንቀሳቀሰው፡፡ በዓል ሆነ አልሆነ ለእኛ ለውጥ የለውም፡፡ ሁልጊዜ የሥራ ቀን ነው፡፡ ኅብረተሰቡ እንዲገነዘብ የምንፈልገው በማንኛውም ሰዓትና ሁኔታ እኛ ከጎናቸው እንዳለን ነው፡፡ ከአደጋ ልንጠብቃቸው ዝግጁ መሆናችንን መረዳት አለባቸው፡፡

በኅብረተሰቡና በእኛ መካከል አንድ ክፍተት አለ ብዬ የማስበው ነገር የአደጋ ጥቆማ መስጫ ነፃ የስልክ መስመራችንን ብዙው ሰው አለማወቁን ነው፡፡ ብዙዎች አደጋ ከደረሰባቸውና ችግሩ ከተባባሰ በኋላ ዘግይተው ነው ለእኛ ጥቆማ የሚሰጡት፡፡ አደጋው ገና እንደ ጀመረ ቢደወልልን ብዙ ሕይወት፣ አካልና ንብረት ለማትረፍ ዕድል ይኖረናል፡፡ እኛ ጋ ደውለው አደጋው ቦታ ጋር የምንደርስበትን ሰዓት መመዝገብና አገልግሎታችንን መመዘን ይችላሉ፡፡ አደጋው ከተከሰተ ሰዓት ጀምሮ ያለውን ሰዓት ሳይሆን እኛ ጋር ከደወሉበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ምላሽ አሰጣጣችንን ነው መለካት ያለባቸው፡፡ በዋናው 939 ነፃ ጥሪ መቀበያ መሥመራችን ብቻ ሳይሆን ወደ 24 የቅርንጫፎች አደጋ ሪፖርት መቀበያ መስመሮች አሉን፡፡ እኛን ካገኙበት ሰዓት ጀምሮ ምላሽ ፈጥነን ካልሰጠን ችግሩ እኛ ጋ ነው ያለው ብለን ራሳችንን እንፈትሻለን፡፡ 

ይሁን እንጂ በአብዛኛው በአካባቢው ያሉ ቅርንጫፍ አገልግሎት መስጫዎቻችንን ኅብረተሰቡ አያውቅም፡፡ አደጋ ሲከሰት ወዴየት መደወል እንዳለበት ብዙ ሰው አያውቅም፡፡ ሕዝቡ እኛ ጋ ቅድሚያ ደውሎ በራሱ መንገድ አደጋ የመከላከል ሥራ ቢሠራ ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን እኛ ጋር ሳይደውል በራሱ አደጋውን ለመከላከል ጥረት አድርጎ አልሳካ ሲልና አደጋው ከቁጥጥር ውጪ ከሆነ በኋላ የሚደውል ከሆነ ምላሽ አሰጣጣችን ላይ እንቅፋት ነው የሚሆነው፡፡ ምንም ዓይነት አደጋ ቢደርስ ቅድሚያ መደወል ያለበት እኛ ጋር ነው፡፡ ቦታው ደርሰን አደጋው ሥጋት ካልሆነ ይህንኑ አረጋግጠን መመለስ እንችላለን፡፡ ቀላል ነው በራሳችን እንሞክረው ተብሎ አደጋው እስኪባባስ መጠበቁ ከፍተኛ ጉዳት ሊያመጣ እንደሚችል ኅብረተሰቡ እንዲገነዘብልን እንፈልጋለን፡፡ 

ሦስት የሥራ ፈረቃዎች አሉ፡፡ በዓል በሚሆን ጊዜ አንደኛው ጠዋት ገብቶ ለከሰዓቱ ተረኛ አስረክቦ በዓል ወደ ማክበሩ ይሄዳል፡፡ ቀን የዋለው ደግሞ ለምሽት ተረኛ አስተላልፎ ይወጣል፡፡ ፈረቃው ባልሆነ ሰዓት ሁሉም ሠራተኛ ከቤተሰቡ ጋር በዓልን ማክበር ይችላል፡፡ ነገር ግን በዓልም ሆነ በመደበኛ ቀን ቤተሰባዊነት ያለው ነው የእኛ ሥራ፡፡ የሥራው ባህሪ ስለሆነ ቤተሰብም ሆነ ዘመድ አዝማድ ሁኔታውን ለምዶታል፡፡ በዓል ሲመጣ በተመደብንበት ሰዓት በሥራ ቦታችን ሰብሰብ ብሎ ለሥራ ዝግጁ ሆኖ በዓል በዓል በሚሸት መንገድ ማሳለፉ የተለመደ ነው፡፡ 

የፈለገ ቢሆን ግን ልጆች ጥሎ፣ የትዳር አጋር ጥሎ፣ ቤተሰብ ጥሎ ከቤት ውጪ በሥራ ማሳለፉ ይከብዳል፡፡ እንደዚህ ዓይነት የሥራ ሕይወት ለማሳለፍ ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ የምትሠራውን ሥራ መውደድ ያስፈልጋል፡፡ ስለ ሕዝብ አገልጋይነት ጽንሰ ሐሳብ በደንብ መረዳት ይጠይቃል፡፡ አገልግሎቱን ለማን ነው የምሰጠው ብለህ ማሰብ አለብህ፡፡ እኔ ቤት አደጋ ቢነሳስ ብለህ ማስተዋል ይጠይቃል፡፡ ወጣም ወረደ በግለሰቡ ውስጥ ከፍ ያለ የአገልጋይነት ስሜት መኖር አለበት እንዲህ ባለው ሥራ ለረዥም ጊዜ ፀንቶ ለመዝለቅ፡፡ 

ብዙ ገጠመኞች አሉ፡፡ በበዓል ጊዜ ሰው ብዙም ጥንቃቄ አያደርግም፡፡ ከእሳት ጋር በተያያዘ ከሌላው ቀን በተለየ ማብሰያ ወይም ኃይል የመጠቀም በበዓል ስለሚበዛ የእሳት አደጋ በብዛት ይገጥመናል፡፡ በበዓላት ጊዜ ዝናብ ሊጥል ይችላል፡፡ የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ ነገሮች ይፈጠራሉ፡፡ ከመጠጥ ጋር ተያይዞ ሰዎች መኪና ይገጫቸዋል፡፡ ገደልና ድልድዮች ውስጥ ገብተው ለአደጋ ሊዳረጉም ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ በዓላት በሚፈጥሩት አለቅጥ የመደሰት ስሜትን ተከትሎ ብዙ ዓይነት አደጋዎች ያጋጥሙናል፡፡ ከሚዲያ ጀምሮ ቤት ለቤት እየሄድን ቅድመ ጥንቃቄዎችን በዓላት ሲደርሱ የምንሠራው እነዚህን አደጋዎች በተቻለ መጠን ለመቀነስ ነው፡፡ በበጎ ፈቃደኞችና በማኅበራት ታች ድረስ እየወረድን ግንዛቤ ማስጨበጥ እንሠራለን፡፡

ብናደርግና ቢሆን የምለው ኅብረተሰቡ የእኛን ሥራ በቅጡ ቢያቅና የራሴነት ስሜት ተሰምቶት አደጋ መጠቆሚያ ስልኮቻችንን እንዲሁም አገልግሎታችንን በቅጡ ቢያውቅ ነው፡፡ ይህ ነገር ከተፈጠረ ብዙ ነገሮች ይቀላሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ በእኛ ቢተማመን ትልቁ ነገር ነው፡፡ አደጋ ተከሰተ ተብሎ ቦታው ላይ ስትደርስ እኛን በጊዜ ባለማግኘታቸው ሰዎች ተጎድተው፣ ሞተው፣ ንብረት ወድሞ ትደርሳለህ፡፡ ቀድሞ ባለመደወሉ የተነሳ ይህ ነገር በመድረሱ በጣም ስሜት ይጎዳል፡፡ ሰው ከአደጋው ቦታ ሲወጣ ነው እኛ ወደ አደጋው የምንገባው፡፡ አደጋ መድረሱ ጥቆማ ደረሰን ማለት ለእኛ ከመቼው ቦታው ላይ ደርሰን ምንችለውን ሁሉ አድርገን የሰውን ሕይወትና ንብረት በታደግን የሚል ስሜት ነው እኛ ጋር ያለው፡፡ ልንከላከለው በምንችለው አደጋ ሰዎች ከተጎዱ በኋላ ከደረስን ግን ፍፁም ስሜት የሚጎዳ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ አደጋ በደረሰ ጊዜ በቶሎ ኅብረተሰቡ እንዲጠቁመንና በተቻለ መጠን ብዙ ሕይወትና ንብረት መታደግ በቻልን ነው የምለው፡፡  

‹‹በእኛ ሙያ በሕመምተኛ ሁኔታ ላይ መሳቅ ክልክል ቢሆንም የዛን ቀን ግን አልቻልንም››

ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት የሆነው አንለይ ደረሰ የሕክምና አምቡላንስ አሽከርካሪ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ኮሪያ ሰፈር የሚኖረውና በፓዮኔር ዲያግኖስቲክ ሴንተር የአምቡላንስ አሽከርካሪ የሆነው አንለይ፣ በተሰማራበት ሙያ ማኅበረሰብን ማገለገል ስለሚሰጠው ዕርካታ፣ የበዓል ቀናትን እንዴት እንደሚያሳልፍ እንዲሁም አዝናኝና አሳዛኝ የበዓል ቀን የሥራ ገጠመኞቹ እንደሚከተለው አውግቶናል።

የበዓል ቀን ትጉኃን | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር በዓልን በሥራ የምናሳልፍበት ጊዜ ይበልጣል፡፡ እኔ ይህን እንደ ዕድልም አየዋለሁ፡፡ የእሳት፣ የመኪናም ሆነ የስትሮክ አደጋ በእዲህ ዓይነቱ ቀን የገጠማቸው ሰዎች ምን ያህል ስሜታቸው እንደሚጎዳ ስታይ በጣም ነው የሚያሳዝነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ተሽሏቸውና ደስተኛ ሆነው ቢያንስ ቀጣዩን በዓል ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተሰብስበው ለማክበር እንዲችሉ አስተዋጽኦ ማድረግ ትልቅ ዕድለኝነት ነው፡፡ 

እኔ የአንድ ልጅ አባት ነኝ፣ ትዳር መሥርቻለሁ፡፡ ድሮ ድሮ ከቤተሰብ ጋር በዓልን ማክበር በእኛ ቤት የሚናፈቅ ነው፡፡ የእኛ ቤተሰብ ትንሿ ኢትዮጵያ ነች ማለት እችላለሁ፡፡ በአካባቢያችን የእናቴ እህቶችና ወንድሞች አሉ፡፡ ጠዋት ቁርስ እኛ ጋር ከሆነ የተበላው ከሰዓት ደግሞ ቡና ተፈልቶ ምሳ አጎቴ ጋር፣ ከዘያም አክስቴ ጋር እያልን ደስ በሚል የመሰባሰብ ሁኔታ ነው የምናሳልፈው፡፡ በዚህ ሁኔታ ላደገ ሰው በዓልን በሥራ የማሳለፍ ግዴታ ሲገጥመው ትንሽ ቅር ሊያሰኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ስታስበው ሰዎች ከአንድ በዓል በተጨማሪ ብዙ በዓላት በሰላም እንዲያሳልፉ አስተዋጽኦ እንዳደረክ ይሰማሃል፡፡ እንቁጣጣሽን በሰላም አክብረው መስቀልን እንዲደግሙ ያንተ አስተዋጽኦ አለበት ማለት ነው፡፡ እዚያ ጋር በሥራ ዕድገትም ሆነ በተለያየ ምክንያት ለዘልዓለም ላትቆይ ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ለአንድም ቀን ቢሆን አገልግለህ የሰዎችን ሕይወት ከአደጋ መጠበቅ መቻል ትልቅ ዕድለኝነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ በምንም ተመን የሌለው ደስታ ይሰጣል፡፡ አንዳንዴ በቶሎ ደርሰን ከአደጋ የታደግናቸውን ሰዎች በሌላ ጊዜ ደውዬ እንዴት ናችሁ ስላቸውና ደህና መሆናቸውን ስሰማ ደስታ ነው የሚሰማኝ፡፡ 

ሥራው ጫና አለው፡፡ ሁሉም ሰው፣ ቤተሰብ፣ ጎረቤት፣ ወዳጅ፣ ጓደኛ፣ ዘመድ ጫና አያሳድርብኝም ማለት አትችልም፡፡ ከአስተሳሰብህ ይጀምራል ጫናው፡፡ ፍቃድ ሞልቼ ይህቺን በዓል አብሬያቸው ለምን አልሆንም ማለት ትጀምራለህ፡፡ ቤተሰብም ገና በበዓሉ መዳረሻ እኛ ጋር ትመጣላችሁ አይደል ብሎ መደወል ይጀምራል፡፡ እናቴም አባቴም ትመጣላችሁ አይደል ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ጓደኞቼም ኧረ ዛሬ እንኳን ተሰብስበን ዘና እንበል፣ ምንድነው ሁሌ ሥራ ይሉሃል፡፡ ልጄ ገና የሦስት ዓመት በመሆኑ የበዓልን ጣዕም አያውቀውም፡፡ ነገር ግን ከባለቤቴ ሁሌም ቅሬታ ሊገጥመኝ ይችላል፡፡ ዛሬም ሥራ ነህ ብላ ገና ስጠይቀኝ ነው ስሜቷን የምረዳው፡፡ በተቻለ መጠን እነግራታለሁ፡፡ በዓሉን ከሥራ ውጪም ቢሆን ሰዓት አብረን እንደምናሳልፍ አስረዳለሁ 

እኛ በእንዲህ ዓይነቱ ቀን የምናገለግላቸው ሰዎች በሌላ ቀን ተሽሏቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለው ያሳልፋሉ፡፡ ድነው በተራቸው ሕዝብ ያገለግላሉ፡፡ በእንጀራ ምክንያት ክፍለ አገር የሚሄዱ ወይም ከአገር የሚወጡ ጭምር አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ነገሮች በመገንዘብ ነገሮች እስኪስተካከሉ ድረስ ጫናቸውን እንዲቀንሱ ለባለቤቴም ሆነ ለቤተሰቦቼ ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡ በቀጣዩ ቀን ደግሞ ያው እረፍት ስሆን ከእነሱ ጋር በዓሉን ለማክበር እሞክራለሁ፡፡

ከዚህ ሥራ ጋር ተያይዞ የሚያስቅ ወይም የሚያዝናና ገጠመኝ ይገጥመኛል ብለህ ብዙም አትገምትም፡፡ አብዛኛውን እጅግ የሚያስደነግጥ፣ የሚያሳዝንና መፈጠርህን ጭምር የሚያስጠላ አጋጣሚዎች ነው የሚገጥምህ፡፡ ከበዓል ጋር ተያይዞም ባይሆን በአንድ አጋጣሚ የተከሰተው ነገር ግን እስካሁንም ሳስበው እያስደነገጠ የሚያስቅ አጋጣሚ ሲከሰት ተመልክቼያለሁ፡፡ እኔን ብቻ አይደለም በአካባቢው የነበሩትን ጭምር ነበር አጋጣሚው ያስገረመው፡፡ 

በየሆስፒታሉ ኦክሲጅኖች አሉ፡፡ ዘውዲቱ ሆስፒታል ኢመርጀንሲ ክፍል ገብተን ነበር፡፡ በቦታው በዊልቼር ያለ ታካሚ ነበር፡፡ በቦታው የነበረ ትልቅ ኦክሲጅን ግን በድንገት ወደቀ፡፡ የኦክሲጅን ሲሊንደሩ ሲወድቅ ከፍተኛ ድምፅ አሰማ፡፡ አጋጣሚው በጣም የሚያስደነግጥ ነበር፡፡ በዊልቼር የነበረው ታካሚ በድንጋጤ ብድግ ብሎ ሮጠ፡፡

በእኛ ሥራ በሕመምተኛ አይሳቅም የሚባል ጥብቅ ሥነ ሥርዓት አለ፡፡ ነገር ግን ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ በሥፍራው የነበረውን ሰው ሁሉ ነበር ያሳቀው፡፡ ታካሚውን ጭኜ መውጣት ነበረብኝና በሥፍራው ብንፈልገው ሁሉ አጣነው፡፡ ሁኔታው ከማሳቅ አልፎ ያስገርምም ነበር፡፡ 

ከዚህ አጋጣሚ ውጪ ግን ብዙ ጊዜ የሚያሳዝን ሁኔታ ነው የሚገጥመኝ፡፡ በበዓላት ልጆች ሥጋ አንቋቸው፣ ወድቀው፣ እሳት አደጋ ደርሶባቸው፣ በተለይ ወጣቶች ጠጥተው መኪና ሲያሽከረክሩ መኪና አደጋ ደርሶባቸው መመለስ በማይችሉበት ሁኔታ ከባድ ፀፀት ውስጥ ገብተው ያየሁበት ሁኔታ ይበዛል፡፡ በአንድ አጋጣሚ ለበዓል ዋዜማ ሊዝናኑ የወጡ ሁለት ጓደኛሞች በመዝናናት ሁኔታ ውስጥ ስለነበሩና በጠራ ሁኔታ ማየት በሚያስችል መንገድ ሲያሽከረክሩ ስለነበር ከፊት ካለ መኪና ጋር ይጋጫሉ፡፡ ሆስፒታል ኢመርጀንሲ ክፍል በተለያየ ቦታ የተኙትን ወጣቶች ሲቲ ስካን ለማስነሳት መውሰድ ነበረብኝ፡፡ የመጀመሪያው ልጅ ከላይ ባይጎዳም ውስጡ እያመመው እንደሆነ ይጮህ ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ጓደኛዬ ደህና ነው ወይ ይለኝ ነበር፡፡ ምነው በቀረብኝ እያለ ለእሱም ለጓደኛውም ለቤተሰቡም በፀፀት ያለቅስ ሁሉ ነበር፡፡ ሌላ ክፍል ያለው ጓደኛውም እግሩ ተሰብሮ እንዳይንቀሳቀስ ታስሮ የተኛ ቢሆንም ስለጓደኛው በሕመም ውስጥ ሆኖ ይጠይቀኝ ነበር፡፡ እንደዚያ እየተዛዘኑ ለዚህ መሰል ጉዳት መዳረጋቸውና ለከባድ ፀፀት መዳረጋቸው ያሳዝን ነበር፡፡ 

ሰዎች አይዝናኑ አይደለም ግን ሲዝናኑ ጥንቃቄ ሊለያቸው አይገባም፡፡ እነዚያ ወጣቶች ንብረትም የአካልም ጉዳት አጋጥሟቸው በዓልን ከነቤተሰቦቻቸው በሐዘን አሳልፈዋል፡፡ ከረዥም ጊዜ በኋላ ደውዬላቸው ጤናቸውን ስጠይቅ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ነግረውኛል፡፡ ነገር ግን ጠጥቶ ከማሽከርከር ጋር በተያያዘ የምን ጊዜም ፀፀታቸው መሆኑን ነግረውኛል፡፡ ስለዚህ ሰዎች ከጠጡ ባያሽከረክሩ፡፡ ቢቻል በራይድ ወይ በሹፌር ቢጓዙ ነው የሚመከረው፡፡ 

በተለይ የመንግሥት ሆስፒታል ላይ ሁሌም በሄድኩ ቁጥር ልቤን የሚያሳምም ነገር ይገጥመኛል፡፡ ድንገተኛ ክፍል ስንገባ ከወለጋ፣ ከጎጃም፣ ከድሬዳዋ፣ ከሌላም ሊሆን ይችላል ከብዙ ቦታዎች መጥቶ ሕክምና ማግኘት ሲገባቸው አይደለም ሕክምና ማረፊያ ቦታ አጥተው የተቀመጡ ሰዎችን ታገኛለህ፡፡ በረንዳ ላይ ካርቶን አንጥፈው ወንበር ላይ ወይም በቃሬዛ ላይ ተኝተው ታያለህ፡፡ ኢኮኖሚያችን ደካማ ነው እንደ አገር ብዙ ችግር አለብን ሕክምናችንም ብዙ ይቀረዋል፡፡ ነገር ግን እዚያ ቦታ በእግር ኳስ ምክንያት ተደባድቦ ለሕክምና የሚመጣና ቦታ የሚያጣብብ ስታይ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ጠግቦ ያውም በእግር ኳስ ምክንያት የሚደባደብ፣ የሚፈናከትና በጩቤ የሚወጋጋ ማየት ያሳዝናል፡፡ ሰሞኑን በሶሻል ሚዲያ ሲለቀቁ ያየናቸው ነገሮች አሉ፡፡ እባብ ቢነድፈው የሰውን ልጅ ከቁጥጥር ውጪ የሚከሰት ተፈጥሯዊ አደጋ ስለሆነ ይህን አደጋ የማከም የሆስፒታሎች ግዴታ ነው፡፡ አንድ ሰው ግን ጠግቦ ያውም ከእኛ ሕይወት ጋር ብዙ በማይገናኝ እንደ መዝናኛ ሊታይ የሚገባውን ጉዳይ መደባደቢያና መፈናከቻ አድርጎት ሆስፒታል ሲያጣብብ ማየት ያሳዝናል፡፡ በእነዚህ ዓይነት ሰዎች ምክንያት በአግባቡ ሊታከም የመጣው ሰው የሐኪም እጥረት፣ የመድኃኒትና የኦክሲጅን እጥረት ሲከሰት ማየት በጣም ያሳዝናል፡፡ ተጣልተን ብንመታ እስር ቤት፣ ብንመታ ደግሞ ሐኪም ቤት ነን፡፡ በመጣላት የሚገኝ ነገር የለም፡፡ 

ድንገተኛ ክፍል ውስጥ ወትሮም የተሟላ ሁኔታ በመንግሥት ሆስፒታሎቻችን የለም፡፡ በጣም በጥሩ ሁኔታ የሚሠሩ የመንግሥት ሆስፒታሎች እንዳሉ መዘንጋት አይኖርብንም፡፡ ሆኖም አብዛኛው አገልግሎት ደካማ እንደመሆኑ ይህ ቢስተካከል ለታካሚዎች ብቻ ሳይሆን ለሕክምና ባለሙያዎችም ትልቅ ሰላም አለው፡፡ 

ከአምቡላንስ ጋር በተያያዘ ሰው ጋር የሰረፀ ክፉ ስም አለ፡፡ አምቡላንስ ሲባል ብዙ ጊዜ አደጋ ምልክት መስጫ ሳይረን እያስጮኸ ሲሄድ ይሄኔ ከሰል ጭኖ ነው፣ እንጀራ ጭኖ ነው ወይም እንትን ብሎ ነው የሚል አመለካከት ይንፀባረቃል፡፡ ይህ ደግሞ ብዙዎች ጋር ሰርጿል፡፡ ነገር ግን በየትኛውም ዘርፍ ቢኬድ ሁሌም ፍፁምነት የለም፡፡ በየትኛውም ሙያ ፍፁምነት ይጎድለናል፡፡ አንዳንዴ ልጁ ወይም እናቱ ታመውበት አምቡላንስ የሚጠብቅ ሰው ካልሆነ በስተቀር የእኛን አገልግሎት በቅጡ መረዳት ሊከብድ ይችላል፡፡ አንድ ታማሚ ወይም ተጎጂ ዕርዳታ ፈልጎ አምቡላንስ ወደ እሱ እየመጣ መሆኑን ሲያውቅ አንዳች መፍትሔ ይዞ እንደሚመጣ ስለሚያምን ለመዳን ተስፋ ያደርጋል፡፡ በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አስሬ የት ደረስክ እያለ ለሚደውልልኝ ታካሚ አይደለም ሳይረን ሌላም ነገር እያስጮኩ ብሄድ ደስ ባለኝ፡፡  ፍፁምነት ሊጎድለን ይችላል፡፡ ነገር ግን ለደወለልን ሰው ለመድረስ መፍጠን ግዴታችን ነው፡፡ ታካሚውን ከያዝን በኋላ ደግሞ ከመጀመሪያውም በላይ አፍጥነን ሆስፒታል ማድረስ አለብን፡፡ እባክህ እናቴ ልትሞት ነው፣ ልጄ ትንፋሹ ሊቆረጥ ነው ለሚለኝ ሰው ፈጥኜ ሆስፒታል የማድረስ ግዴታ አለብኝ፡፡ እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት ቢቻል የአምቡላንስ መንገድ እንዳደጉት አገሮች ቢኖረን፡፡ ካልሆነ ግን ማኅበረሰቡ መንገድ በመልቀቅና ባለመስደብ ቢተባበር፡፡ ነገ በራሳችን ሕይወት እስኪደርስ አንጠብቅ፡፡ ዛሬ የዳነው ሰው ነገ የአገር መሪ፣ ነገ የእኛ ቤተሰብ፣ ነገ ራሳችን ልንሆን እንችላለን፡፡ 

በሌላ በኩል በዚህ አንቡላንስ ማሽከርከር ላይ የተሰማራን ወገኖች ሙያውን በሥነ ምግባር መወጣት አለብን፡፡ ምሳ ልንበላ ስንሄድ ሳይረን የምናስጮህ ከሆነና ሙያውን የማንወድ ወይም የማናከብር ከሆነ ሌላውን ለማገልገል ይከብደናል፡፡ እኛ ሙያውን ስናከብረው ነው ሌሎችም የሚያከብሩት፡፡ ሌሎችም ሰዎች እኛ ላይ ነገ ሊደርስ ይችላል በሚል ዘርፉን ቢያከብሩት በሙያው ላይ አሉታዊ አመለካከት ባያንፀባርቁና ለሥራችን ቢተባበሩ እላለሁ፡፡         

የሕክምና ባለሙያዋ በበዓል ቀናት

የበዓል ቀናትን ለሌሎች ደኅንነት ተጨንቀው ማኅበረሰባቸውን ሲያገለግሉ ከሚያሳልፉ የሙያ ዘርፎች አንዱ የሕክምና ሙያ ነው። የበዓል ቀናት ባለውለታ የሆኑትን የሕክምና ባለሙያዎች ለመዘከር ያነጋገርናት የሕክምና ባለሙያዋ ሲስተር ዊንታና ብርሃኑ የሕክምና ባለሙያዎች ሕይወት በበዓል ቀናት ምን እንደሚመስል ከበዓል ቀን ገጠመኞቿ አንዱን በመምዘዝ እንዲህ አጫውታናለች። 

‹‹ከሁለት ወይም ከሦስት ዓመታት በፊት ይሆናል፡፡ የፋሲካ በዓል ነበር፡፡ አንድ ወጣት ከከፍታ ቦታ በሬ ገፍትሮ ጥሎት በፖሊስ ታጅቦ ወደ ጤና ጣቢያው መጣ፡፡ ሆኖም እኛ ጋር ሲመጣ ሕይወቱ አልፎ ነበር፡፡ ከኪሱ ውስጥ ምንም መረጃ ባለመገኘቱ ቤተሰቦቹን እንኳን ለማግኘት አልተቻለም ነበር፡፡ ከብዙ ሰዓታት በኋላ እናውቀዋለን የሚሉ መጥተው አስከሬኑን ከፖሊስ ጋር በመሆን ወደ ሆስፒታል ወሰዱት፡፡›› 

ይህ ባለፉት አሥር ዓመታት የሕክምና ሥራዋ ካጋጠሟትና ከማትረሳቸው መጥፎ ገጠመኞች አንዱ እንደሆነ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የመንግሥት ጤና ጣቢያዎች በአንዱ የምትሠራው ሲስተር ዊንታና ብርሃኑ ትግልጻለች፡፡ 

በመንግሥት ጤና ተቋማት ሁሌም ክፍት ሆነው የሚያገለግሉት ማዋለጃ፣ አስተኝቶ ማከም፣ ገንዘብ ቤት፣ ካርድ ክፍል፣ ድንገተኛ ክፍል የሚጠቀሱ ሲሆን፣ የሷ ሥራ ደግሞ በድንገተኛ ክፍል ነው፡፡ 

የሥራዋ ባህሪ አንድ ቀን ዘሎ አንድ ቀን ለ24 ሰዓት በሥራ ገበታዋ ላይ እንድትገኝ የሚያስገድድ በመሆኑ፣ በዓላትን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በሕክምና ተቋማት ውስጥ እንደምታሳልፍ ትናገራለች፡፡ 

ሲስተር ዊንታና እንደምትለው፣ በዓልን ከቤተሰብ ጋር ማሳለፍ ይናፍቃል፡፡ ሆኖም በጤና ተቋማቸው ውስጥ ሥራ ካልበዛ በዓል ለማስመሰል ይጥራሉ፡፡ 

‹‹በዓል ለማስመሰል የምንሞክረው ከእኛ ይልቅ ታካሚዎችን ለማስደሰት ነው፡፡ በበዓላት ቀን ተኝቶ መታከም ክፍል ያሉ ሕሙማን በጣም ይሰማቸዋል፡፡ እነሱን ለማስደሰት ስንል በዓል ለማስመሰል እንሞክራለን፤›› ትላለች፡፡ 

ሆኖም በአብዛኛው በሥራ ተወጥረው የሚያሳልፉበት ጊዜ ይበልጣል፡፡ የበዓላት ቀን ከወትሮው ለየት ያሉ ክስተቶች የሚስተናገዱበትም ነው፡፡ ምጥ የያዛቸው እናቶች ወትሮም እንደሚመጡት ሁሉ በበዓላትም ይመጣሉ፡፡ ነገር ግን በአዘቦት ቀናት ብዙም ያልተለመዱት በበሬ የመወጋት፣ ዕርድ ሲያከናወኑ የመጎዳት፣ የትራፊክ አደጋ፣ እርስ በርስ በሚፈጠር ግጭት ጉዳት የደረሰባቸው በብዛት የሚመጡበት ነው፡፡ 

ከቤተሰቦቿ ጋር እንደምትኖር የነገረችን ሲስተር ዊንታና፣ የራሷን ሕይወት ለመመሥረት የሥራዋ ሁኔታ እንደማያስችላት ትገልጻለች፡፡ 

‹‹በትዳር ዓለም ያሉ ጓደኞቼ ሲቸገሩ አያለሁ፡፡ በተለይ በበዓላት ቀን ቤት ውስጥ መሥራት፣ ከልጆችና ከቤተሰቦች ጋር ማሳለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሆኖም ይህንን ለማሳካት ይቸገራሉ፡፡ የሥራው ባህሪ ቤተሰብን ለማስደሰት ብዙም አይመችም፤›› ብላለች፡፡ 

‹‹በዓላትን አጣጥሜያለሁ ብዬ አላስብም›› የቤት ሠራተኛዋ ፀደይ

በበዓላት ቀን በሥራ ተጠምደው ከሚውሉ ባለሙያዎች መካከል የቤት ሠራተኞች ይጠቀሳሉ፡፡ ከቤት ውስጥ ሠራተኞች በዓላት ሲደርሱ ቤተሰብ ለመጠየቅ ፈቃድ የሚወጡ ቢኖሩም፣ እዚያው ካሉት ቤተሰብ ረግተው አብረው የሚያሳልፉም አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ቀናት ለቤት ሠራተኞች በእጅጉ አድካሚ መሆኑ ይታወቃል። የበዓል ቀናትን ለሌሎች ሰዎች ደስታና ምቾት የሚለፉትን የቤት ሠራተኞች የምትወክልልን የቤት ሠራተኛዋ ፀደይ በዓላትን አጣጥማ አሳልፋ እንደማታውቅ አውግታናለች።

የበዓላትን ሥራ በተለይ ከወትሮው ለየት የሚያደርገው ሥራው ቀደም ብሎ የሚጀምር በመሆኑ ነው የምትለው የቤት ሠራተኞችን የምትወክለው ባለታሪካችን ፀደይ፣ ጠላ ከማዘጋጀት ጀምሮ አብዛኛውን የበዓል ሰሞን ሥራዎች እሷ እንደምታከናውን፣ ነገር ግን የምታገለግልበት ቤተሰብ ሥነ ሥርዓት ያለው ከመሆኑ አኳያ የቤተሰቡ ወንድ ልጆች የበዓል ቀናት የሥራ ጫናዎችን ተካፍለው እንደሚያግዙ ትናገራለች። 

የምታገለግልበት ቤተሰብ ውስጥ በሁሉም በዓላት ሦስት ዶሮና በግ እንደሚታረድ፣ ዶሮ ሲታረድ ወንዶቹ ልጆች በመገንጠል እንደሚያግዟት ገልጻለች፡፡ እሷ እንደምትለው፣ መተጋገዙ ቢኖርም፣ በተለይ ገና ፋሲካ ሲሆን፣ ዘመድ ስለሚሰበሰብ ሥራው ይበዛል፡፡ ዕቃ ማጠብ፣ ቡና ማፍላትና ምግብ ማቀራረቡ አድካሚ ይሆናል፡፡

‹‹በዓሉን በሥራ አሳልፌ ዕረፍት የማገኘው ከአሥር ሰዓት በኋላ ነው፡፡ በዓላትን አጣጥሜያለሁ ብዬ አላስብም፤›› ትላለች፡፡

ከስምንት ዓመታት በላይ በቆየችበትና ለመጀመርያ ጊዜ ለሥራ በገባችበት ቤት ሆና ትምህርቷን 11ኛ ክፍል መድረሷን፣ ቤተሰቡም ትምህርቷን እንድትማርና እንድታጠና እንደሚደግፏት ገልጻለች፡፡

በበዓልም ሆነ በአዘቦት ምግብን በተመለከተ ምንም ችግር እንደሌለባት፣ በበዓላትም አንድ ላይ ተሰባስበው እንደሚመገቡ፣ ‹‹ምግቡ ሁሉ በእኔ ቁጥጥር ሥር ነው፤›› ስትል ተናግራለች፡፡

በበዓላት ቀን ለወላጅ ቤተሰቦቿ ደውላ እንደማታውቅ፣ በዋዜማው ወይም በማግሥቱ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› እንደምትልም አክላለች፡፡

‹‹በዓላት ሲመጡ ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ የሥራ ጫናው በጣም ይበዛል የምትለው ደግሞ ወጣት መሠረት ቢሆነኝ ናት፡፡

በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ መሥራት ከጀመረች ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆናት የተናገረችው ወጣቷ፣ በዓላት ሲመጡ በእሷና በመሰሎቿ ላይ ከፍተኛ የሥራ ጫና እንደሚኖር ተናግራለች፡፡

አዲስ ዓመትን ለመቀበል የሚደረገው ዝግጅት ከበዓሉ ሦስትና አራት ቀን ቀደም ብሎ መሆኑን በቤት ውስጥ ያሉ ልብሶች ቆሸሹም አልቆሸሹም መታጠብ አለባቸው ስለሚባል ሁሉም ልብሶች እንደሚታጠቡና አድካሚ ዝግጅቶች እንዳሉ ‹‹የሚታጠበው ልብስ በአንድ ቀን ብቻ ላያልቅ ይችላል፡፡ ከልብሶቹ በተጨማሪ የቤት ዕቃዎችም ወጥተው ይታጠባሉ፡፡ ምናልባት ልብስ ማጠብ ቀላል የሚመስላቸው ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ማጠቡና ቀድሞ ወደነበረበት ቦታ መመለሱ የልጆችንና የአዋቂዎችን ለይቶ ማስቀመጥ በጣም አድካሚ ሥራዎች ናቸው፤›› ትላለች፡፡

ከዚህ ባሻገር ቤቱን ለአዲስ ዓመት ማፅዳት፣ ማስዋብና ማስጌጥ ላይ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ቀላል የማይባሉ ሥራዎችን እንደምትሠራ አክላለች፡፡ 

‹‹የምትሠራባቸው ሰዎች ከሌላው እንደማየውና እንደምሰማው ለሠራተኛ የተለየና ክፉ የሚባል ፀባይ አላየሁባቸውም እኔም ቢሆን መሥራት ያለብኝን ስታዘዝም በራሴ የምችለውን ደግሞ አስቤ ነው የምሠራው፤›› ያለችው ወጣቷ፣ በዓል ሲመጣ በቤት ውስጥ ያለው ሥራ አሰልቺ መሆኑን ገልጻለች፡፡ 

እንደ መሠረት፣ በበዓል ወቅት የሚሠሩ የምግብ ዓይነቶች ብዙ ሲሆኑ፣ እነዚህን ምግቦች ለመሥራት የሚያስፈልጉ ማብሰያዎችን ማዘጋጀት፣ የሚታጠቡ ማጠብ፣ የሚበስለውም እንዲሁ ማብሰል አድካሚ ነው፡፡ የተለያየ አሠራርና ዕቃዎች የሚፈልግ መሆኑም የተቀመጡ ዕቃዎችን ማውጣት ያደክማል ብለዋል፡፡

‹‹ምግቦቹ ሁሉ ተሠርተው ሁሉ ነገር ተዘጋጅቶ ለመመገብ ሲበቁ ከድካሜ የተነሳ የመብላት ፍላጎቴ በጣም ይቀንሳል፤›› የምትለው ወጣቷ፣ ከዚህ ባሻገር ቤተሰቡ ሁሉ ተሰብስበው ከተመገቡ በኋላ ዕቃዎች ሁሉ እኔን የሚጠብቁ በመሆኑ ገና ሳልሠራው ይደክመኛል ትላለች፡፡ 

እነሱ አስበው ማታ ማታ ስለሚያስተምሯት ያላትን ሙሉ አቅም ተጠቅማ እንደምትሠራ፣ ሆኖም ምንም ቢሆን በዓልን ከቤተሰብ ጋር እንደ ማሳለፍ ያለ ደስታ እንደማይገኝ አክላለች፡፡

በበዓል ዋዜማ ከአምስት ሺሕ በላይ የቀንድ ከብቶችን እርድ የሚያከናውኑት የቄራ ሠራተኞች

በበዓልም ሆነ በመደበኛ ቀን ማኅበረሰብን ከሚያገለግሉ ተቋማት መካከል አንዱ የእርድ አገልግሎት የሚሰጠው የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ተጠቃሽ ነው። በተለይ በበዓል ወቅት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለሚገመተው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የእርድ አገልግሎት መስጠት አድካሚ በመሆኑ በእረፍት ላይ የነበሩ ሠራተኞች እንዲገቡ ተደርጎም በቂ ባለመሆኑ ጊዜያዊ ሠራተኞችን ለመቅጠር ጭምር ይገደዳል። በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የቀንድ ከብት ቆዳ መግፈፍ አገልግሎት የሚሰጠው አቶ ዓለማየሁ ሰሎሞን ስለ በዓል ቀን ውሎውና ገጠመኞቹ እንደሚከተለው አጫውቶናል።

ሰው ከቤተሰቡም ሆነ ከጓደኛው ጋር ተሰብስቦ በዓልን ሲያከብር እኛ የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ቀንና ለሊት ሳይገድበን እየሠራን ነው በዓልን የምናከብረው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሁሉም ሠራተኛ በዓል ሲመጣ ማኅበረሰቡን ለማገልገል ደፋ ቀና ሲለሚል በዓልን ከቤተሰብ ጋር ያሳለፍንበት ወቅት ትዝ አይለኝም፡፡ በበዓል ዋዜማ ከመደበኛው የሥራ ጊዜ የተለየ ስለሚሆንና በርካታ የቀንድ ከብቶችም ለእርድ ዝግጁ እንዲሆኑ ስለሚደረግ የክርስቲያንም ሆነ የሙስሊም እምነት ተከታይ የሆኑ ሠራተኞች በጋራ ለመሥራት ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ በተለይ የዘመን መለወጫ፣ የትንሳዔ፣ የመስቀልና የገና በዓል ወቅት ለእርድነት የሚገቡ የቀንድ ከብቶች ቁጥር ከፍ ስለሚል ድርጅቱም የሰው ኃይል ጨምሮ ወደ ሥራ ይገባል፡፡ 

በእነዚህ በዓላቶች ወቅት ሠራተኛውን ለማገዝ የሚገቡ የድርጅቱ የሙስሊም እምነት ተከታይ ሠራተኞች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ተገቢ የሆነ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንዲሁም ለክርስቲያን እምነት ተከታዮች የሚታረዱ ከብቶችን መባረክ እንደማይችሉም ቅድመ ግንዛቤ በመስጠት ለበዓል የሚሆኑ ከብቶች እንዲዘጋጁ ይደረጋል፡የቀንድ ከብት እርድ የሚያከናውኑ ሠራተኞችም በየፊናቸው የተለያየ ሥራ እንዳላቸው አንድ ፈጣን የሆነ ብልት የሚበልት ሠራተኛም በቀን ከ30 በለይ ከብቶችን በልቶ ለበዓል ያደርሳል፡፡ ድርጅቱም በዓል ሲመጣ ቀደም ብሎ ለሠራተኞች የሚሆኑ ግብዓቶችን በማዘጋጀት በፍጥነትና በቅልፍጥና ለዕርድ የተዘጋጁ ከብቶችን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፡፡ በበዓል ዋዜማ በድርጅቱ ውስጥ ከአምስት ሺሕ በላይ የቀንድ ከብቶች ለእርድ ዝግጁ ስለሚሆኑ ሁሉም ሠራተኞች በሚባል ደረጃ በሥራ እንደሚጠመዱና በዓልንም እዚያ በመሰባሰብ እናከብራለን፡፡ 

የ2016 ዓ.ም. የዘመን መለወጫ በዓልን ሁሉንም ማኅበረሰብ ሆነ መደበኛ የሆኑ ደንበኞችን ለማስደሰት ድርጅቱ ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ የበዓል ሰሞን አብዛኛውን ሠራተኛ ውጥረት ውስጥ ስለሚገባ ግቢው ጭንቅንቅ እንደሚል ከዚህ በፊትም በተለያዩ በዓሎች ላይ ከአፋር ከቦረና ለእርድ የመጡ ፊጋ ከብቶች ጓደኞቹ ላይ ጉዳት አድርሰው እንደነበር ይኼንንም አጋጣሚ በዓል በመጣ ቁጥር እንደማይረሳው ያስታውሳል፡፡

ከእነዚህም አካባቢ የሚመጡ የቀንድ ከብቶች አስቸጋሪና ለሠራተኛ ጠንቅ እንደሆኑ ነገር ግን ሠራተኛው ተባብሮ ከብቶቹን በመጣልና በመበለት ለማኅበረሰቡ እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡

በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ውስጥ በዚህ ሥራ ከተሰማራ አሥራ ሁለት ዓመት ማስቆጠሩን ወደ ድርጅቱ መጀመሪያ ሲገባ ፅዳት ላይ መቆየቱንና ቀስ በቀስም ልምድ ከጓደኞቹ አካብቶ እዚህ ሥራ ላይ መግባቱን ይናገራል፡፡

ከዚህ በፊት በቀን 50 የቀንድ ከብቶችን ይገፍ እንደነበር ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ድርጅቱ ሠራተኞቹን በፈረቃ እንዲሠሩ ሲያደርግ ሥራ እንደቀለለት ያስረዳል፡፡ የትኛውም የበዓል ወቅት ብልት አውጪ የሆኑ ሠራተኞች እረፍት እንደሌላቸው በዓልንም ከቤተሰብ ጋር አክብረው እንደማያውቁ ይናገራል፡፡  

ፖሊስና የበዓል ቀን

በማንኛውም የበዓላት ወቅት በሥራ ላይ ከሚያሳልፍ የሥራ ዘርፎች አንዱ ፖሊስ ነው፡፡ በበዓል ወቅት ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ ከዋዜማ ጀምሮ ዝርፊያና መሰል ወንጀሎችን ለመከላከልና ሕግን ለማስከበር በየአካባቢው የሚዘዋወሩ ፖሊሶችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ ለረዥም ዓመታት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ የሥራ ክፍል አገልግለዋል፡፡ አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ናቸው፡፡ በበዓል ቀናት የፖሊስ አባት እንዴት እንደሚያሳልፉና አዝናኝና አሳዛኝ የበዓል ቀን ገጠመኛቸውን እንደሚከተለው አውግተውናል፡፡

የበዓል ቀን ትጉኃን | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በበዓላትም ሆነ በአዘቦት ቀናት የወንጀልና የትራፊክ አደጋን መከላከል የፖሊስ ግንባር ቀደም ሥራ መሆኑን ኮማንደር ማርቆስ ያስረዳሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ከከተማዋ መስፋፋት፣ የሕዝብ ቁጥር ሁኔታ ዕለት ዕለት መጨመር ምክንያት የፖሊስ ሥራን ከባድ አድርጎታል ብለዋል፡፡

በተለይም በዓላት ሲቃረቡ ደግሞ የተለያዩ ወንጀሎች ሊፈጸሙ ስለሚችሉ ከነበረው የፖሊስ አባላት ቁጥር ከፍ ተደርጎ በየአካባቢው እንደሚሰማሩ ኮማንደር ማርቆስ ያስረዳሉ፡፡

በዓላት በመጣ ቁጥር ወንጀል ፈጻሚዎች ለመዝረፍ ምቹ ሁኔታዎች እንደሚሆንላቸው የፖሊስ አባላትም ደግሞ በተጠንቀቅ የሕዝቡን ኪስ ከዘረፋ ለማዳን ይታትራሉ፡፡

ከዚህም ባሻገር የነጋዴዎች ስም የሚያጠለሹ ጥቂት ግለሰቦች ደግሞ በሚበሉና በሚጠጡ ነገሮች ላይ ባዕድ ነገሮች በመቀላቀል ወደ ገበያ የሚያስገቡ በመኖራቸው፣ ችግሩን ለመከላከል፣ የፖሊስ አባላት ወንጀሉ ከደረሰም ለሕግ ለማቅረብ በየገበያው ይሰማራሉ በማለት ይገልጻሉ፡፡

ስለዚህ የዚህ ዓይነት ወንጀሎች በበዓላት ወቅት እንዳይፈጸሙ፣ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት መላው የፖሊስ ኃይል በተጠንቀቅ እንደሚቆሙ ገልጸዋል፡፡

ይህ የሚሆነው የወንጀል መከላከልና የትሪፊክ ተቆጣጣሪ ብቻ ሳይሆን በየቢሮ ያሉ ባለሙያዎች ሁሉ በበዓል ወቅት በሥራ ላይ ይሆናሉ ሲሉ ምክትል ኮማንደሩ ያስረዳሉ፡፡

ይሁን እንጂ በበዓላት ወቅት የትኛውም የፖሊስ አባል በቤቱ ከቤተሰቡ ጋር የሚያሳልፍበት ሁኔታ ብዙም አይታይም ብለዋል፡፡

ሁሉም የፖሊስ አባልና አመራር በዓልን የሚያከብሩት በሥራ ላይ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹አንድ የፖሊስ አባል አስቀድሞ ወደ ሥራ ሲገባ በዓልን በሥራ ላይ እንደሚያሳልፍ ያውቀዋል፤›› አንዳንዴ ሆድ የሚያስብሱ ነገሮች ሲያዩ የሚከፉም አባላት አይጠፉም ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ለምሳሌነት ያነሱትም ሁሉም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በባህል ልብስ አጊጠውና አሸብርቀው ሲያዩ የሚሰማቸውና እኔም እንዲህ በሆንኩ ብለው ቅር የሚላቸው የፖሊስ አባላት እንዳሉ፣ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥራውን እየለመዱት ስሄዱ የአባሉ ቤተሰቡም ሆነ ፖሊሲ አባሉም ይለምዱታል በማለት ያብራራሉ፡፡

የዚህ ዓይነት ስሜት የሚታየው በአዲስ የፖሊስ አባላት ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ በጊዜ ሒደት ለምደውት እንደ ማንኛውም አባል በዓሉን በሥራ ያከብራሉ በማለት አስረድተዋል፡፡ በበዓል ወቅት አስቂኝና አሳዛኝ ገጠመኞችን ከአባላቱ እንሰማለን ያሉት ኮማንደር ማርቆስ፣ በተለይም ገዥዎች ተሸውደው ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሚመጡ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥም ‹‹ሁለት ግራ እግር ጫማ›› ሸምተው ቅሬታቸውን ያሰማሉ ይህም ሁኔታ ለአባላቱ አስቂኝ ለሸማቹ ደግሞ ሆድ የሚያስብስ እውነታ ነው ሲሉ ያስታውሱታል አንዳንድ ደግሞ ልብስ ገዛሁ ብለው ኮባ ቅጠል ከሸመቱ በኋላ መሸወዱን አውቆ ፖሊስ ጣቢያ የሚመጡ መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም የዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ወይም ገጠመኞች በበዓላት ወቅት የሚታዩ መሆኑን፣ ይህም ለገዥዎች የሚያባሳጭና የሚያናድድ ገጠመኝ ቢሆንም አንዳንዶች አስቂኝ የበዓል ትውስታ እንደሆናቸው ይገልጻሉ፡፡ ዶሮ ሲሰርቁ የሚያዙ መኖራቸውን፣ ይህ በጣም ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን ለገዥ ከባድ የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ከዓመታት በፊት በፖሊስ አባል ላይ በገበያ አካባቢ እያለ የደነበረ በሬ መወጋቱን ያስታወሱት ኮማንደር ማርቆስ በወቅቱ ለተመልካች አስቂኝ ቢሆንም ለአባሉ ግን ከባድ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በአጠቃላይ ለፖሊስ አባል በዓልን የሚያሳልፈው በሥራና ሥራ ላይ እንደሆነ፣ ‹‹የፖሊስ አባል የበዓል ሥራው ነው በዓሉ›› በማለት ይገልጹታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...