Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች መንግሥት የዘፈቀደ እስር መቀጠሉን አስታወቁ

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች መንግሥት የዘፈቀደ እስር መቀጠሉን አስታወቁ

ቀን:

መንግሥት በተለመደና በተሳሳቱ መንገዶች ጋዜጠኞችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን በጅምላና በዘፈቀደ ማሰር መቀጠሉን፣ አገር በቀል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አስታወቁ፡፡

በተደጋጋሚ የምርመራ ጊዜ በመጠየቅ ለተራዘመ የቅድመ ክስ ጊዜ ለእስር መዳረግ፣ ፍርድ ቤት የዋስትና መብት ሲፈቅድ ፖሊስ አለቅም ብሎ ማቆየትና ጋዜጠኞችን ያለ ምንም ክስ አስሮ ማቆየት የተለመዱ የመንግሥት ድርጊቶች ሆነው መቀጠላቸውን፣ 35 የሰብዓዊ መብት ድርጀቶቹ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም. ከአምስት ወራት በላይ የቆየና አሁንም በከፊል በተለያዩ አካባቢዎች ኢንተርኔት የተቋረጠ መሆኑን፣ ግጭቶች በተነሱ ቁጥር ለተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች አግባብነት የሌላቸው ፍረጃና ስያሜ መስጠት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገጉ የዜጎች ነፃነትና መብት ላይ የተራዘሙና ጊዜያዊ ጉዳቶች ማድረስ፣ እንዲሁም ያልተመጣጠኑ የኃይል ዕርምጃዎች በመንግሥት በኩል በስፋት የታዩና የተወሰኑትም የቀጠሉና ሥጋት የሆኑ ችግሮች መሆናቸውን ድርጅቶቹ ገልጸዋል፡፡

መግለጫውን ከሰጡት 35 የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጀቶች መካከል  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት (CEHRO)፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (EHRCO)፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC)፣ የመብቶችና የዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD)፣ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (AHRE)፣ የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (EWLA) የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች (LHR) እና ሴታዊት ንቅናቄ ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ (IAG)፣ የኢትዮጵያ ሴቶች መብቶች ተሟጋች (EWRA) የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (NEWA)፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች መብት ተሟጋች (ELRW)፣ የሴቶች ኅብረት ለሰላምና ለማኅበረሰብ ፍትሕ (WAPSJ)፣ ሲቄ ውሜንስ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን (SWDA)፣ ሴቶች ይችላሉ ማኅበር (WCDI)፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ተሳትፈውበታል፡፡

ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ የተሰኘው ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መሠረት ዓሊ እንደገለጹት፣ በዓመቱ በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ መረጃ ለመሰብሰብና የሰብዓዊ መብቶች ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም በፀጥታ ችግር ምክንያት ዕድሉን ማግኘት አልተቻለም፡፡

አገር አቀፍ የሰላም መድረክ እንዲዘጋጅ ጥሪ ያደረገው የድርጀቶቹ መግለጫ ሁሉንም ባለጉዳዮች ያካተተ የምክክር መድረክ ያስፈልጋል ብሏል፡፡ በዚህ እንዲካሄድ በሚታሰበው ውይይት ማንኛውም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑም ሆኑ ያልሆኑ አካላት የሚሳተፉበት አገር አቀፍ መድረክ እንዲዘጋጅ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ዋና ዳይሬክተር ዳን ይርጋ በበኩላቸው፣ እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ዕርምት ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ተመርጠው ለመንግሥት ቢላኩም ከመንግሥት በኩል በሚጠበቀው ልክ መልስ እየተሰጠ አይደለም ብለዋል፡፡

የመንግሥት አካላት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር በሚሠሩ ድርጅቶች ላይ በሚያደርጉት ዛቻና ማስፈራሪያ ምክንያት፣ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ለመንግሥት እንዲህ ቢደረግ ብሎ መናገር ከባድ እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት የሴታዊ ንቅናቄ መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ስሂን ተፈራ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ድርጅቶቹ ባለው ጠባብ መንገድ ብቻ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡  

ድርጅቶቹ በመግለጫቸው ባለድርሻ አካላት ለሰላም ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ፣ የሲቪክ ምኅዳሩ ጥበቃ እንዲደረግለት፣ የጥላቻ ንግግርና የተዛቡ መረጃዎች ሥርጭት እንዲቆም፣ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ሳይስተጓጎል እንዲቀጥልና የቅድመ ግጭት መጠቆሚያና መከላከያ ሥርዓት (Early Warning System) እንዲዘረጋ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እንዲረጋገጥ፣ የተጋላጭና የግፉአን ጥበቃ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ፣ ፆታዊ ጥቃቶች ተገቢው ትኩረት እንዲሰጣቸው፣ ገለልተኛ ምርመራና ተጠያቂነት እንዲሰፍንና  አገር አቀፍ የሰላም መድረክ እንዲመቻች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሚታየውን አገራዊ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉንም የማኅበረሰብ አካላት የሚያሳትፍ አገር አቀፍ የሰላም መድረክ ተመቻችቶ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ግጭትን የመከላከል፣ የመፍታትና የሰላም ግንባታ ሥራዎች የሚጠናከሩበት አገራዊ ፍኖተ ካርታ እንዲዘጋጅ ጠይቀዋል፡፡

የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በሀቀኝነትና ሕዝባዊ ተቀባይነት ባለው መንገድ ወደ ተግባር እንዲገባ፣ በሒደቱም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ዓለም አቀፍ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የታመቁ ቅራኔዎች ወደ ነውጥ እንዳይሸጋገሩ፣ ነውጥ አዘል ግጭቶች በሰላማዊ ንግግሮች እንዲፈቱ፣ እንዲሁም የሰላም ጅምሮች ሁሉን አካታችና ዘላቂ እንዲሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...