Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በአዲሱ ዓመት ለሰላምና ለአብሮነት ቁርጠኝነት ይታይ!

ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን፣ እንዲሁም ሁሉም ዜጎች በየተሰማሩበት መስክ ፍሬያማ ውጤት እንዲያገኙ ከወዲሁ መልካም ምኞታችንን እንገልጻለን፡፡ አሮጌው ዓመት አልፎ ለአዲሱ ዓመት አቀባበል ሲደረግለት ብሩህ ተስፋ መሰነቅም ሆነ በመነቃቃት ስሜት መነሳት፣ ከወዳጅ ዘመድ ጋር በዓልን በደስታ ማሳለፍ፣ የተቸገሩ ወገኖችን ባለ አቅም ማገዝ፣ ለአገር መልካም የሆኑ ነገሮችን መመኘት፣ መተሳሰብና አንድነትን ማሳየት የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ የአብሮነት መገለጫ እሴት ነው፡፡ አዲስ ዓመት ሲጀመር የአገር አንድነት ተጠብቆ ሕዝብ በሰላምና በፍቅር የሚኖርበት መልካም ጊዜ እንዲመጣ የብዙዎች ምኞት ነው፡፡ ሰላም ሲኖር በጠንካራ ሥራ ድህነት ተወግዶ ልማትና ዕድገት ይኖራል፡፡ ሰላም ለሁሉም ዜጎች እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማስገኘት የሚረዳ ሲሆን፣ ዜጎችም ለአገራቸው የሚፈለግባቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ሙሉ ፈቃደኛ ይሆናሉ፡፡ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው የእኩልነት ሥርዓት ለመገንባት፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ተሳትፎ ስለሚያግዝ በአዲሱ ዓመት ይህ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ይሰጠው፡፡ የአዲስ ዓመት ስጦታም ሰላምና አብሮነት ይሁን፡፡

በአዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ በመንግሥት ሊታሰብባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ የመተማመን ዕጦት ነው፡፡ ሕዝብ የሚመራውን መንግሥት እንዲያምን ለአገር የሚጠቅሙ ዕቅዶች ያስፈልጋሉ፡፡ መንግሥትም ከሚመራው ሕዝብ አመኔታ ለማግኘት ሥራውን በግልጽነትና በኃላፊነት መርህ እንደሚያከናውን በተግባር ማሳየት አለበት፡፡ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ለዓመታት የዘለቁት አለመተማመን፣ ጥላቻ፣ ቁርሾና ክፋት እንዲወገዱ ብርቱ ጥረት መደረግ ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያን ከመራር ድህነትና ከከፋ ግጭት ውስጥ ማውጣት የሚቻለው፣ በአዲሱ ዓመት እነዚህ አላስፈላጊ ችግሮች እንዲወገዱ በቅንነት በመነጋገር ነው፡፡ የእልህና የጉልበት መንገድ ሕዝብ ከማስለቀስና አገር ከማመሰቃቀል ውጪ ምንም የፈየደው ነገር የለም፡፡ በአዲሱ ዓመት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለአገራቸው ሰላምና ደኅንነት ሲሉ፣ ለዓመታት ከተዘፈቁበት የመጠራጠርና የመጠላላት አባዜ የሚያስወጣቸውን መላ ይፈልጉ፡፡

ሰላማዊ ማኅበረሰቦች የሚኖሩባት አገር በጥንካሬ ማስቀጠል የሚቻለው፣ ችግሮችን በመተማመንና በንግግር ለመፍታት ቁርጠኝነት ሲኖር ነው፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙ መሣሪያ አንግቦ ይዋጣልን ማለት ማንንም አሸናፊ እንደማያደርግ ታሪካችን በሚገባ ያስተምረናል፡፡ ‹‹በጦርነት አሸናፊ መሆን የሚቻለው ጦርነቱ እንዳይነሳ በማድረግ ነው›› የሚለው ዕድሜ ጠገብ የጦር ስትራቴጂ አስተምህሮ የሚያሳስበው፣ ጦርነት ከተነሳ በኋላ ሊገኝ ይችላል ተብሎ የሚታሰበው ድል አስተማማኝ አለመሆኑን ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን አማካይነት በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ከሚደረጉ የመነጋገሪያ መድረኮች በተጨማሪ፣ መንግሥት በበኩሉ የራሱን መድረኮች በማዘጋጀት ትጥቅ አንግበው ከሚዋጉት ኃይሎች ጋር መነጋገርና መደራደር ይጠበቅበታል፡፡ በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ደግሞ፣ ሁሉም አኩራፊ ኃይሎች ወደ መደራደሪያው መድረክ ለመቅረብ ፈቃደኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉት በሰላማዊ የንግግርና የድርድር መድረክ ስለሆነ፣ ሁሉም ወገኖች ከጠመንጃ ንቅነቃ በመውጣት ለአገር ሰላም ቁርጠኝነት ማሳየት አለባቸው፡፡

በአዲሱ ዓመት የጠመንጃ ላንቃዎች ተዘግተው ፊትን ወደ ልማት ማዞር የግድ መሆን አለበት፡፡ አሸናፊው በማይታወቅበት ውጊያ አገርን ማድቀቅና ሕዝብን ማሰቃየት ይብቃ፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አድጎ ሕዝብ ከአስመራሪው ድህነትና ከተመሰቃቀለ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ ወጣቶች ከሥራ አጥነት ተላቀው ትርፍ አምራች በመሆን ለአገር አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ የሥራ ፈጠራ አማራጮችን በብዛትና በጥራት የሚያስገኙ ስትራቴጂዎች ይዘርጉ፡፡ በዘፈቀደ ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ በሚል ሰበብ የሚደረጉ የይስሙላ እንቅስቃሴዎች ይገቱ፡፡ ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ የውኃ ሀብት፣ በአፍሪካ አንደኛ የእንስሳት ሀብት፣ ተስማሚ የአየር ፀባዮች፣ ለቁጥር የሚያዳግቱ የማዕድናት ፀጋ፣ በርካታ የቱሪዝም መስህቦችና ሌሎች የተፈጥሮ ዕድሎች ከፍተኛ ቁጥር ካለው የወጣት ኃይል ጋር በኢትዮጵያ ተዓምር መሥራት የሚያስችል ዕምቅ አቅም እንዳለ ያሳያሉ፡፡ ይህንን የመሰለ ዕድል ይዞ መራብም ሆነ ግጭት ውስጥ መኖር በአዲሱ ዓመት እንዳይቀጥል የጋራ ርብርብ ይደረግ፡፡ በተለይ መንግሥት ለዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ይስጥ፡፡

በአዲሱ ዓመት የሞራልና የሥነ ምግባር ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በዓለማዊውም ሆነ በመንፈሳዊው አስተምህሮ ተቀባይነት የሌላቸው ኢሞራላዊ ድርጊቶች እንዲከስሙ የጋራ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብን ለማገልገል በአደራ የተሰጠ ሥልጣን እየተባለገበት አገር መዘረፍ የለባትም፡፡ የሕዝብ አገልጋይነት ኃላፊነት ያለባቸው ሹማምንት ሥልጣናቸውን ለጉቦ፣ ለዝርፊያና ለመጠቃቀሚያነት ሲያውሉ በሕግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ ከሕገወጦች ጋር በመተባበር የግብይት ሥርዓቱን ጤና የሚነሱ፣ የመንግሥት በጀት የሚዘርፉ፣ ያለ ጨረታ ኮንትራቶችና ግዥዎችን የሚያከናውኑ፣ የሕዝብና የመንግሥት የሚባለውን መሬት የሚወሩና የሚያስወርሩ፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያፍኑና ከሕግ በተቃራኒ በሥልጣናቸው የሚባልጉ ተጠያቂነት እንዳለባቸው በተግባር ይረጋገጥ፡፡ በአዲሱ ዓመት ሊዘመትባቸው ከሚገቡ መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት ከኢሞራላዊ ባለሥልጣናት ጋር አገር የሚያጠፉ ባለሀብት ተብዬዎች ናቸው፡፡ ግብር በማጭበርበርና በመሰወር፣ ኮንትሮባንድ በመነገድ፣ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት በመፍጠርና በጥቁር ገበያ አገር የሚበድሉ በሙሉ በሕግ ይጠየቁ፡፡ እነዚህ ጥገኞች በዚህ ከቀጠሉ አገር ከማፍረስ ወደኋላ አይሉም፡፡

ኢትዮጵያን ዓለም የሚያውቃት ሉዓላዊ ግዛት ያላትና በታሪክ በርካታ ሁነቶች የተከናወኑባት መሆኗን ነው፡፡ የአገረ መንግሥት ምሥረታ ሒደቷም ቢሆን ከሌሎች አገሮች የተለየ አይደለም፡፡ በሌሎች አገሮች ከዚህ ቀደም እንደተስተዋለው፣ በአገረ መንግሥት ምሥረታ ሒደቱ ውስጥ አለመስማማቶች መኖራቸው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን ትውልዶች በተቀያየሩ ዘመን አንዱ የሌላውን እያስቀጠለ አገራቸውን ሲጠብቁ መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ግን አለመስማማትና መገፋፋት፣ የሥልጣን ሽኩቻ፣ መከፋትና ማመፅም ነበሩ፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለምን ተከትሎ የመጣው ፅንፈኛ ብሔርተኝነት ከባዱ ተግዳሮት ነው፡፡ ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በስፋት የናኘው የብሔርተኝነት ፖለቲካ፣ በኢትዮጵያ ላይ ይዞት የመጣው አሉታዊ ነገር መከፋፈልና የሰላም ዕጦት ነው፡፡ በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጥ በእኩልነት እየኖሩ በአንድ ሕዝብነት ለመቀጠል፣ የግድ ብሔረሰባዊ ማንነትን አውልቆ እንደማይጣል ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያም በበርካታ ብሔር ብሔረሰቦቿ ስብጥር ጠንካራ አገር መሆን እንደምትችልም ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ኅብረ ብሔራዊነት የግጭት መነሻ ማድረግ የከፋ ጥፋት ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ለሰላምና ለአብሮነት ቁርጠኝነት ይታይ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...