Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ ዓመት ዋዜማ በተለያዩ አካባቢዎች

የአዲስ ዓመት ዋዜማ በተለያዩ አካባቢዎች

ቀን:

የሰማዩ ደመና ተገፎ መስከረም ሲጠባ ከሚፈነድቁ አደይ አበባዎች ጋር አዳዲስ ሐሳቦች ይፈልቃሉ። ብዙዎች ይቅርታና ምሕረትን ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል ይዘጋጃሉ።

መጪውን ዓመት በንፁህ ልቦናና በአዲስ መንፈስ ለመቀበል ከወዲሁ ይሰናዳሉ። ዓመቱ የሰላም፣ የፍቅርና የደስታ ይሆን ዘንድ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው የመልካም ምኞት ስጦታን ይሰጣጣሉ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ!›› በማለት ሰላምታን ይለዋወጣሉ።

ዓመቱ ሰላም፣ ፍቅር፣ መረዳዳትና መተጋገዝ የሠፈነበት ይሆን ዘንድ ሁሉም ወደ አምላኩ እጁን የሚዘረጋበትና የሚማፀንበት ወቅት ነው።

አገር በአረንጓዴና በለመለሙ ዛፎች ትሸፍናለች፣ ጋራ ሸንተረሮች በአደይ አበባ ይዋባሉ፣ የደፈረሱ ወንዞች ይጠራሉ፣ ፏፏቴዎች ኩልል ብለው ይወርዳሉ።

የዱር አራዊቶች ሳይቀሩ የደመናውን መነሳት አውቀው ከየጉራንጉሩ ይወጣሉ ወፎችም ቢሆኑ የሚፈነጥቁ ሰብሎችን ቀድመው ለመብላት ያንዣብባሉ።

ልጃገረዶችም አደይ አበባን ፀጉራቸው ላይ በመሰካት ያጌጣሉ ‹‹አበባ አየሽ ወይ!›› በማለት ከበው በመጨፈር ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት በመዞር ስጦታን ይቀበላሉ።

እነዚህ ሁሉ ከግዑዛን እስከ ህያዋን ያሉ ነገሮች የሚያሳዩት ክረምቱ መጠናቀቁንና አዲስ ዓመት መምጣቱን የሚያበስሩ ሁነቶችን ነው።

ከእነዚህ ባሻገር የአዲስ ዓመት መምጣትን የሚያመላክቱ በርካታ ማኅበራዊና ባህላዊ ክንውኖች በሰፊው ይስተዋላሉ።

አሮጌውን ዓመት ሸኝቶ ዓውደ ዓመቱን በአዲስ መንፈስና ስሜት ለመቀበል የሚደረገው የቤት ፅዳትና ዕድሳቱ፣ ልብስ አጠባውና አሮጌውን በአዲስ ለመቀየር የሚከናወነው ግብይት፣ የሳር (ቄጤማ)፣ የአደይ አበባ ጉዝጓዞ፣ የጠላው፣ የጠጁ፣ የበግና የፍየሉ፣ የዶሮው፣ የዳቦው ዝግጅትና አጠቃላይ ሽር ጉዱ፣ ዕለቱን በይበልጥ እንድንናፍቅ ከሚያደርጉት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።

አሮጌው የ2015 ዓመት የተለያዩ መልካምና አስከፊ ኩነቶችን አስተናግዶ በማለፍ ተራውን ለመጪው አዲስ ዓመት ሊያስረክብ አንድ ቀን (ነገ) ቀርቶታል።

የ2016 ዓ.ም. ዘመን መለወጫ በዓልን ለመቀበል ከወዲሁ ዝግጅት ማድረጋቸውን ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው።

በሌላ በኩል እየታየ ያለው ግጭት፣ ሞትና መፈናቀል፣ እንዲሁም የኑሮ ውድነት በዓሉን እንደ ወትሮው ሁሉ በደስታና በፌሽታ ለማክበር የሚያበቃ ፈንጠዝያ እንደሌለ ብዙዎች ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በአንዳንድ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ፣ በዓሉን በደስታ ተቀብሎ ለማክበር የሚያስችል ነገር እንደሌለና ለወትሮው ይደረጉ የነበሩ የበዓል ወቅት እንቅስቃሴዎች አይታዩም ሲሉ ተናግረዋል።

 ባህር ዳር

የክልሉ ርዕሰ ከተማ በሆነችው ባህር ዳር ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች፣ ‹‹በዚህ ወቅት በዓልን ማክበር እንደ ቅንጦት ይቆጠራል፤›› ነው ያሉት።

በግና ዶሮ፣ ሽንኩርትና ዘይት፣ እንዲሁም ሌሎች የበዓል ግብዓቶችን ለመግዛት በየቦታው የነበረው ድባብ አይታይም ብለዋል።

የአዲስ ዓመት ዋዜማ በተለያዩ አካባቢዎች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ኅብረተሰቡ ከዚህ በፊት ከበዓሉ ዋዜማ ቀደም ብሎ ወደ ገበያ ይወጣ እንደነበር፣ ነገር ግን በዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል ላይ ምንም ዓይነት የጎላ እንቅስቃሴ እንዳልተመለከቱ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ትበይን አትንኩት ይገልጻሉ።

 ነዋሪዎቹ እንደ ወትሮው ቀደም ብለው ለበዓሉ ዝግጅት ከመሰናዳትና ወደ ገበያ ከመውጣት ይልቅ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያዘወትሩ ነው የተናገሩት።

‹‹ከተማው ጭር ያለ ነው፤›› የሚሉት ወይዘሮዋ በበኩላቸው፣ ቀደም ባለው ጊዜ ቤት ያፈራውን ለማቅረብ፣ በግም ሆነ ዶሮ ለመግዛት በዓሉ አንድ ሳምንት ሲቀረው ወደ ገበያ ይወጡ እንደነበር አስታውሰው፣ ነገር ግን ለዘንድሮው በዓል ብዙም ዝግጅት እንደማያደርጉ ገልጸዋል።

ለልጆቻቸው ሲሉ ብቻ ከዶሮ ላይ የተወሰነ ሥጋን በመግዛት፣ እንዲሁም ዳቦና ጠላም እንደ ነገሩ በማድረግ ሊያሳልፉ እንደሆነ የተናገሩት ወ/ሮ ትበይን፣ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ በክልሉ ላይ እየተደረገ ባለው ጦርነት ብዙዎች ሕይወታቸውን እያጡ ባሉበት ወቅት፣ በዓል ለማክበር ማሰብ ቅንጦት እንደሚመስላቸው ነው የገለጹት።

ከዚህ ባሻገር የኑሮ ውድነቱም ቢሆን እንደቀጠለ መሆኑን ጠቁመው፣ በክልሉ ሚዲያ በኩል በዓሉን በማስመልከት ዘይትን ጨምሮ የተለያዩ ሸቀጦች ገብተዋል የሚባለው ከወሬ ያለፈ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት፡፡

 በባህር ዳር ከተማ ያለውን አንዳንድ የሸቀጦች ወቅታዊ ዋጋ ካዩት በመነሳት ሲናገሩ፣ ዑመር የተባለው ዘይት ከ1,100 እስከ 1,200 መቶ ብር እንደሚሸጥ ጠቅሰው፣ ከ60 እስከ 70 ብር ደግሞ የሽንኩርት መሸጫ ዋጋ እንደሆነ አክለዋል።

አሁንም ቢሆን ከከተማው ውጪ ባሉ አካባቢዎች በፋኖና በመከላከያ መካከል ግጭቶች እንዳሉ በወሬ ደረጃ እንደሚሰሙና ወደ ባህር ዳር የሚያመጡ መንገዶች በብዛት ዝግ መሆናቸውን እንደሰሙ ነው የተናገሩት፡፡

በዚህም ወደ ከተማዋ የሚገቡ የበዓል ሸቀጦች በወቅቱ መድረስ ባለመቻላቸው ገበያውን እንዳናረው መገመት አያቅትም ሲሉ ወ/ሮ ትበይን አውርተዋል።

በሌላ በኩል እየታየ ያለው ግጭት ሞትና መፈናቀል፣ እንዲሁም የኑሮ ውድነት በዓሉን እንደ ወትሮው ሁሉ በደስታና በፌሽታ ለማክበር የሚያበቃ ፈንጠዝያ እንደሌለ ብዙዎች ተናግረዋል።

አቶ ይልማ ሙሉጌታም በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 16 ነዋሪ ናቸው፡፡ ባህር ዳሴ ከተማ ከአማራ ክልል ሌሎች ከተሞች በአንፃራዊ ሰላምና የበዓል ዋዜማ ድምቀት እንዳለው የገለጹት አቶ ይልማ፣ ይሁን እንጂ በክልሉ ያለው ሰላም ሁኔታ እንደ ቀድሞ በመሆኑ ነዋሪው በሥጋት እንደሚንቀሳቀስ ይገልጻሉ፡፡ ነዋሪዎች በዚህ ወቅት የሚፈልጉት ሰላምና ፀጥታ ያለበት ከተማ ሆኖ እንደ ልብ ወጥቶ መግባትና መሥራት መሆኑን አቶ ይልማ ይናገራሉ፡፡ በባህር ዳር፣ ደሴ ወደ ዱር ቤቴና አዲስ አበባ መሄጃ መንገዶች በመዘጋጀታቸው፣ የሽንኩር፣ የጤፍ፣ የዶሮና ሌሎችም በዓልን የሚያደምቁ ነገሮች ዋጋቸው ጣሪያ መንካቱን ገልጸዋል፡፡ ዶሮ ከ1,000 ብር ጀምሮ፣ ሽንኩር በኪሎ 70 እና 80 ብር፣ ጤፍ ከ11 ሺሕ ብር ጀምሮ እየተሸጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የፀጥታ ችግር ላይ የኑሮ ውድነት በጨመረበት ለነዋሪዎች ትልቅ ሥጋት መሆኑን፣ ነጋዴዎች ያላቸውን ሸቀጦች በመደበቅ መንገድ ዝግ ነው በሚል ምክንያት ሸቀጦች ላይ ዋጋ መጨመራቸውን ገልጸዋል፡፡

በፀጥታው መደፍረስ ምክንያት በቀን ሥራ የሚተዳደሩ እንደ ጫኝና አውራጆች በችግር ውስጥ እንደሚገኙ አቶ ይልማ ተናግረዋል፡፡ የንግድ እንቅስቃሴ በመቀዝቀዙና የትራንስፖርት አገልግሎት ባለመኖር በእነዚህ የሥራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ዜጎች በችግር ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ ምክንያት የባህር ዳር ከተማና አካባቢዋ የበዓል ዋዜማ ድባብ በእጅጉ መቀዝቀዙን ተናግረዋል፡፡

ጎንደር

ቀደም ሲል በአካባቢያቸው ተከስቶ የነበረ ግርግር የሚወዱትንና በጉጉት የሚጠብቁትን የአዲስ ዓመት በዓል በሰላም እናሳልፋለን የሚል ግምት እንዳልነበራት የተናገረችው ደግሞ በጎንደር ከተማ የአዘዞ አካባቢ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ሎዛ ንጉሤ ናት፡፡

የአዲስ ዓመት ዋዜማ በተለያዩ አካባቢዎች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በጎንደር ከተማ ያለው የሸቀጦች ዋጋም ከባህር ዳር ከተማ ካለው የገበያ ሁኔታ ጋር ተቃራራቢነት ያለው መሆኑን ለመገንዘብ ችለናል፡፡

ምንም እንኳን አንፃራዊ የሆነ ሰላም ያለ ቢመስልም ትንሽ ከሚባለው ከሽንኩርት ገበያ ጀምሮ የሚገዛበት ዋጋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከነበረው ዋጋ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን የተናገረችው ሎዛ፣ ቢሆንም ግን በዓሉን ያላቸው ለሌላቸው ሰዎች በማካፈል እንደሚያሳልፉ ገልጻለች፡፡

አዲስ ዓመትን በግና ዶሮ በማረድ፣ እንዲሁም ከጠላው ድግስ ባሻገር ቤተሰብና ዘመድ ጎረቤቱ ተጠራርቶ በጋራ ማሳለፉ ከሁሉም የበለጠ ደስታን እንደሚፈጥርባት ነው የተናገረችው፡፡

ያለው ለሌለው ማካፈል የበዓሉ አንዱ አካል ነው የምትለው ሎዛ ከውጭ አገርም ሆነ ከአገር ውስጥ ለበዓል ተብሎ ገንዘብ የተላከለት ሰው በገንዘብ እጥረት ለበዓል ቢያንስ ዶሮ መግዛት ለማይችል ሰው ማካፈል ወይም ገዝቶ መስጠት ይኖርበታል ነው የምትለው፡፡ ይህንን ተግባርም አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ማድረግ ጀምረዋል ብላለች፡፡

ደሴ  

አዲሱን የዘመን መለወጫ (ዕንቁጣጣሽ) በዓል በኑሮ ውድነት አጣብቂኝ ውስጥ ሆነው እንደሚያሳልፉ የተናገሩት ደግሞ የደሴ ከተማ ሮቢት አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ነፃነት ካሴ ናቸው፡፡ በተለይ በደሴና አካባቢ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የበዓል ድባቡ፣ በዓል ያለ እንደማይመስል አድርጎታል ይላሉ፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ነዋሪዎች ባላቸው አቅም እንደ ልብ እንዳይሸምቱ በኑሮ ውድነቱ የፊጥኝ ታስረዋል በማለት ወ/ሮ ነፃነት ያስረዳሉ፡፡

የአዲስ ዓመት ዋዜማ በተለያዩ አካባቢዎች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

 

ነዋሪዎች በዓል ከማክበር ይልቅ በእጅጉ የሰላም የፀጥታ ጉዳይ እንዳሳሰባቸው የሚገልጹት ወ/ሮ ነፃነት፣ ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሶ ለመሸመትም ሆነ ለመሸጥ አዳጋች መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

በደሴ ከተማ ሠርገኛ ጤፍ ወይም ነጭ ጤፍ እስከ 14,000 ብር እንደሚሸጥ አክለዋል፡፡  ለዚህ ደግሞ ነዋሪዎች እንደ ልብ ለመነገድም ሆነ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ አማርጦ ለመሸመት አስቸጋሪ ሁኔታ በመሆኑ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ጤፍን የዋጋ መናር ከዓምና ጋር ያነፃፀሩት ወ/ሮ ነፃነት፣ 4,000 እስከ 5,000 ብር መሸጡን ያስታውሳሉ፡፡ የዘንድሮ የዋጋ መናር በእጥፍ መጨመሩና የፀጥታ ሁኔታ መደፍረሱ በዓሉ በዓል እንዳይመስል አድርጎታል ብለዋል፡፡ ሽንኩርት ከ80 ብር ጀምሮ እንደሚሸጥ፣ ቲማቲም በኪሎ 100 ብር እንደሆነ ገልጸው፣ ከዓምና ጋር ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር በሦስት እጥፍ እንደጨመረ ተናግረዋል፡፡ በደሴ አሁን ላይ ያልጨመረው ዘይት ብቻ መሆኑ የተናገሩ ሲሆን፣ ስኳር በኪሎ 120 ብርና ከዚያ በላይ እንደሚሸጥ ጠቁመዋል፡፡ ዕንቁላል 15 ብር፣ ዶሮ ከ1,000 ብር በላይ፣ የበግ ዋጋም ቢሆን ከ10,000 ብር በላይ መሆኑን ነው ወ/ሮ ነፃነት የገለጹት፡፡

የ2015 ዓ.ም. ዘመን መለወጫ በዓልን ወ/ሮ ነፃነት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲያከብሩ፣ ለቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልገውን ሁሉ ሸምተውና ዘመድ አዝማድ ተሰባስቦ እንዳከበሩ ያስታውሳሉ፡፡ የ2016 ዓ.ም. በፀጥታ ችግርና በኑሮ ውድነት ምክንያት የዘመን መለወጫን ‹‹ከአንገት›› በላይ በሆነ ደስታ ለማክበር መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡

መቀሌ

በመቀሌ ከተማ የአዲስ አመት ዋዜማ ወጣት መዓዛ ፀጋዬ በመቀሌ ወጣ ባለች የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ አስተባባሪ ናት፡፡ በመጠለያ ጣቢያው 10,000 የሚሆኑ ዜጎች እንደሚኖሩ ገልጻ፣ የአዲስ ዘመን መለወጫ ለማክበር ማሰብ ይቅርና መሠረታዊ ምግብ ካገኙ ስድስት ወራት እንዳለፋቸው አስተባባሪዋ አስረድታለች፡፡ በስደተኛ መጠለያ የሚገኙ ዜጎች የበዓል ዝግጅት ማሰብ የማይታሰብ መሆኑን፣ የዕለት ጉርስ ለማግኘት እንኳን ያልታደሉ ናቸው በማለት አስረድታለች፡፡

የአዲስ ዓመት ዋዜማ በተለያዩ አካባቢዎች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

‹‹ለአንድ ቤተሰብ አምስት ኪሎ ዱቄት ተሰጥቶት እስከ መቼ እንደሚቆይ ፈጣሪ ይፍረድ፤›› የምትለው ወጣት መዓዛ፣ በቅርቡ ዕርዳታ ካላገኙ ብዙዎች ችግር ውስጥ ይወድቃሉ ብላለች፡፡ ከመጠለያ ጣቢያው ውጪ የሚገኙ ነዋሪዎች የተሻለ የበዓል ዋዜማ ድባብ መኖሩን ገልጻ፣ ይሁን እንጂ የሸቀጦችና የምግብ ፍጆዎች ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት የሰው የመግዛት አቅም መዳከሙን ትገልጻለች፡፡ እንደ ወጣት መዓዛ ገለጻ፣ የጥይትና የከባድ መሣሪያ ድምፅ አለመስማት የተሻለ መሆኑን፣ ይሁን እንጂ ሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ አለማግኝቱና የዋጋ መናገር የበዓሉን ድባብ ቀዝቀዝ አድርጎታል፡፡ ዕንቁላል ከ17 እስከ 18 ብር፣ ዶሮ ከ1,200 ብር ጀምሮ፣ ጤፍ ሠርገኛ የሚባለው እስከ 10,000 ብር እየተሸጡ መሆኑን ወጣት መዓዛ ነግራናለች፡፡

ድሬዳዋ      

አዲስ ዓመት በድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ ክብሩ ይስፋ ሥራ እየሄዱ ወደ ቤት ቢገቡም፣ የበዓል ሁኔታ ምንም አልታየኝም ይላሉ፡፡ ‹‹አቦ እኔ በገበያና በከተማ ሁሉ ለመሸመት ዞሬያለሁ፣ ይሁን እንጂ እንደ ቀድሞው የበዓል ድባቡ ምንም አልታየኝም፤›› በማለት ስሜታቸውን አጋርተውናል፡፡ በድሬዳዋ ከተማ ቲማቲም በኪሎ 100 ብር፣ ሽንኩርት 70 እና 80 ብር፣ ዶሮ አነስተኛ መጠን ያለው 700 እና ፍየል ደግሞ ከ4,000 ብር ጀምሮ እየተሸጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ ዓመት ዋዜማ በተለያዩ አካባቢዎች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የነዋሪዎች የሚያገኙት ገቢና ወጪ ባለመመጣጠኑ ለበዓል ወቅት የሚደረገው ሸመታና ሽር ጉድ የመቀነሱ ምክንያት የኑሮ ውድነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በሐዋሳ ከተማ ዓረብ ሠፈር ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ማኅሌት አዳነ የበዓል ሁኔታ መቀዛቀዙን ይናገራሉ፡፡ በምክንያትነት ያነሱትም የኢንዱስትሪ፣ የግብርና ምርቶች ዋጋ መናር የዜጎችን የመግዛት አቅም በመፈታተኑ፣ የነዋሪዎች እንቅስቃሴ መገደቡን አስረድተዋል፡፡ ሁሉም እንደ ነገሩ አዲስ ዓመትን ለማክበር ታች ላይ ቢልም ገና ከዋዜማው ያለው ድባብ ቀዝቀዝ ማለቱን አልሸሸጉም፡፡

በአበበ ፍቅርና በሔለን ተስፋዬ

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...