ከ900 በላይ አባላት ያሉት አራራይ የታክሲ ማኅበርን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ከቀረጥ ነፃ ተሽከርካሪዎች እንዳያስገባ መከልከሉን፣ ‹‹አስተዳደራዊ በደል ሆኖ አግኝተነዋል›› ሲል የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ገለጸ፡፡
ዕንባ ጠባቂ ተቋም ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የምርመራ ውጤቱንና የመፍትሔ ሐሳቡን የሰጠበትና ሪፖርተር የተመለከተው ደብዳቤ እንደሚገልጸው፣ ማኅበሩ ከቀረጥ ነፃ ተሽከርካሪ እንዲያስገባ ደብዳቤ ተጽፎለት ከተፈቀደ በኋላ ትራንስፖርት ቢሮው ማገዱ ‹‹በደል›› ነው፡፡
ማኅበሩ ለታክሲ ማኅበራት ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ የሚያደርገውን የገንዘብ ሚኒስቴር መመርያን ተመርኩዞና መሥፈርቱን አሟልቶ፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄ በማቅረብና ፈቃዱንም በማግኘት የዝግጅት ሥራ ሲያከናውን እንደነበር ለዕንባ ጠባቂ ተቋም ባቀረበው አቤቱታ አመልክቷል፡፡
ሆኖም የከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ ‹‹አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት›› ቀደም ሲል የድጋፍ ደብዳቤ ለሰጠው ማኅበር፣ ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ፣ የቀረጥ ነፃ መብት ተጠቃሚ እንዳይሆን እንዳገደው ነው ለዕንባ ጠባቂ አቤቱታውን አቅርቦ የነበረው፡፡
ተሽከርካሪዎችን ከሚያቀርብና ከሚገጣጥም ኤል አውቶ ኢንጂነሪንግና ትሬዲንግ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር ማኅበሩ ወደ ሥራ እንዲገባ በመስማማት ቅድሚያ ክፍያ 30 በመቶ መክፈሉን፣ በስድስት ወራት የማኅበሩ አባላት ተሽከርካሪዎችን ተረክበው ቀሪውን 70 በመቶ በባንክ ብድር ለመክፈል እየተጠባበቁ እንደነበር ማኅበሩ አሳውቋል፡፡
የከተማው ትራንስፖርት ቢሮ ለዕንባ ጠባቂ ተቋም በሰጠው መልስ፣ ቢሮው የብዙኃን ትራንስፖርት አቅርቦትን የማሳደግና የመንገድ መጨናነቅን የሚፈጥሩ ተሽከርካሪዎችን የማያበረታቱ ስለሆነ ተሽከርካሪዎቹ ከቀረጥ ነፃ እንዳይገቡ ማገዱን አስታውቋል፡፡
ቢሮው በተጨማሪም በሰጠው ምላሽ የገንዘብ ሚኒስቴር አውጥቶት የነበረው የቀረጥ ነፃ ፈቃድ መመርያ ግልጽነት ያልነበረውና የከተማዋን ‹‹ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ›› በመሆኑ፣ ሚኒስቴሩ ማብራሪያ እንዲሰጠው በደብዳቤው ጠይቆ ምላሽ አላገኘሁም ብሏል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር አውጥቶት የነበረውን የሜትር ታክሲዎች ከቀረጥ ነፃ መመርያ፣ ከመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሰርዞት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ዕንባ ጠባቂ አደረግኩት ባለው ምርመራና በያዘው ጭብጥ መሠረት እንደገለጸው፣ ቢሮው ዕግዱን ከማውጣቱ በፊት ለማኅበሩ አባላት የትብብር ደብዳቤ ጽፎላቸው ነበር፡፡ ቢሮው ቅድሚያ የሚሰጠው ለብዙኃን ትራንስፖርት እንደሆነ ቢገልጽም፣ ይህንን ማለት የነበረበት የድጋፍ ደብዳቤውን ከመስጠቱ በፊት እንደነበር አስታውቋል፡፡
ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ መፍትሔ ብሎ ያቀረበው፣ ለማኅበሩ ከዚህ በፊት የተጻፉ የድጋፍ ደብዳቤዎችና ሌሎች አስፈላጊ ማስረጃዎችን በማካተት ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በመላክ ውጤቱን በ15 ቀናት ውስጥ ለዕንባ ጠባቂ ተቋም እንዲያሳውቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡