መንግሥት በቀጣይ ሦስት ዓመታት ተግባራዊ በሚያደርገው በሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ፣ ሲቪል ሰርቪሱ ላይ ሙሉ ለሙሉ ማሻሻያ እንደሚያደርግበት አስታወቀ፡፡
የመጀመርያው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ መጠናቀቁን ተከትሎ ተግባራዊ ለመደረግ እየታቀደ ያለው ሁለተኛ አጀንዳ አራት ምሰሶዎችን የያዘ ሲሆን፣ አራተኛው ምሰሶ የመንግሥትን ሥራ የመፈጸም አቅም በማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው የሚሆነው፡፡
ዕቅዱን አዘጋጅቶ በበላይነት የሚመራው የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዳሳወቁት፣ መንግሥት የሚያስበውን ለውጥ ለመሸከም የሚችል ሲቪል ሰርቪስ እንዲኖር እንደሚያደርግና ማሻሻያዎችን ማሳካት እንዲችል እንደሚያደርጉ ነው፡፡
‹‹ሲቪል ሰርቪሱን ላይ ሙሉ ለሙሉ ማሻሻል የሚያደርግና ዕሳቤውን የሚቀይር፣ ዘመኑ የሚፈልገውን የመፍጠን ዕሳቤ የያዘ ሲቪል ሰርቪስ እንዲፈጠር ይደረጋል፤›› ሲሉ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ለውጡን ዋነኛ ምሰሶ ይዘት አስረድተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ይህን የገለጹት የኢትዮጵያ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ማኅበር ከሚኒቴር መሥሪያ ቤታቸው ጋር በጋራ ባዘጋጀው የሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ በሥራ ፈጠራ ላይ የሚኖረውን አስተዋጽኦ በተመለከተ በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ ነበር፡፡
ባለፈው ረቡዕ ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በሳይንስ ሙዝየም በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታው ባቀረቡት የመድረክ መክፈቻ ንግግር ላይ ሲሆን፣ ስለ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ይዘቶች የተናገሩት፣ ከሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ጋር በመሆንም በፓናል ውይይት ላይም ተሳትፈው ነበር፡፡
እንደ ከዚህ በፊቱ በተለያዩ የቴክኒክ ቃሎች ቤተ ሙከራ ማድረግ ሳይሆን ማሻሻያው ሲቪል ሰርቪሱ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚሸጋገር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሲቪል ሰርቪሱ ቢፒአር እየተባለ የተለያዩ ሞዴሎች መምከሪያ ሆኖ ቆይቷል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከተጠናቀቀው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የበለጠ አሁን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ያለው ሁለተኛው ዕቅድ ከባድ እንደሚሆን፣ ነገር ግን ከተሳካ ‹‹ለውጦች መሸከም የሚያስችልን ሲቪል ሰርቪስ እንዲፈጥር ነው የሚደረገው፤›› ብለዋል፡፡
ደንበኛ ተኮር የሆነ ሲቪል ሰርቪስ መፍጠር እንደሚቻልና ሲቪል ሰርቪሱን እየሸሸ ያለውን የተማረ አቅም ማስቀረት እንደሚቻል አሳውቀዋል፡፡ ዘርፉን ለሥራ የሚያበረታታ እንደሚሆን እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡
‹‹ቢፒአርና ሌሎች የቴክኒክ ቃሎችን ትተን ሰው በሠራው መጠን እንዲከፈለው ማድረግ፣ ውጤታማ የሆኑ ሰዎችን በተሻለ ተጠቃሚ ማድረግና የስንፍና መደበቂያ ዋሻ አለማድረግ ነው፤›› ሲሉም ኢዮብ (ዶ/ር) በተጨማሪ አስረድተዋል፡፡
የኢኮኖሚ ማሻሻያው ካሉት ተጨማሪ ዋና ምሰሶዎች ውስጥ በመጀመርያው የማክሮ ኢኮኖሚውን መረጋጋት ማረጋገጥ ላይ የቀሩ ሥራዎችን ማስቀጠል፣ በሁለተኛው ደግሞ የንግድና ኢንቨስትመንት ምኅዳርን ማሻሻል ሲሆን፣ በሦስተኛው ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ነው፡፡
ከማክሮ ኢኮኖሚ ቀጣይነት አንፃርና ከሥራ ፈጣሪነት አንፃር የታሰቡ ሥራዎች በተፈለጉት ርቀት ስላልተኬደባቸው በሁለተኛው አጀንዳ እንደሚጨረሱ ሚኒስትር ዴኤታው አሳውቀዋል፡፡
‹‹በመጀመርያው ማሻሻያ ዕቅድ መልካም የሚባሉ ስኬቶች ቢገጥሙንም ያቀድናቸውና ያልጨረስናቸው ነገሮች እንዳሉ ዓይተናል፤›› ብለዋል፡፡
ኢዮብ (ዶ/ር) ቀጣዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ስለሚያመጣቸው ለውጦች ሲያስረዱ፣ የዋጋ ግሽበትን ዝቅ እንደሚያደርግ፣ የውጭ ምንዛሪ ላይ ያለውን ችግር እንደሚፈታና በውስጡ ያለውን መዛባት እንደሚያጠፋ ነው፡፡
የተለያዩ እንደ ቴሌኮም ዘርፍ ዓይነት ቢዝነሶችን ለውድድር ክፍት የተደረጉበት፣ አዳዲስ የኢኮኖሚ አቅም የዕድገት ምንጮች ለመፍጠር ተወጥነው በተሳካ የተተገበሩበት እንደነበር የመጀመርያው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ አስረድተው ነበር፡፡
‹‹ምንም ጠንካራ ቡድን ቢኖረውም ኢትዮ ቴሌኮም የውድድር መንፈስ ባይመጣ ኖሮ በዚህ ደረጃ ይለወጣል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፤›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ‹‹ማን ያርዳ የነበረ እንደሚባለው በቅርብ ስለነበርኩ የውድድር መንፈስ ያመጣውን ለውጥ አውቀዋለሁ፤›› ብለዋል፡፡