Sunday, July 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበዋግ ኽምራ ዞን በሰሀላ ሰየምት ወረዳ በተከሰተ ድርቅ የሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰማ

በዋግ ኽምራ ዞን በሰሀላ ሰየምት ወረዳ በተከሰተ ድርቅ የሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰማ

ቀን:

በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ዞን በሰሀላ ሰየምት ወረዳ በተከሰተ ድርቅ ሁለት ሰዎችን ጨምሮ፣ በርካታ እንስሳት መሞታቸውን የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን መምርያ አስታወቀ፡፡

በ2015 ዓ.ም. ዝናብ በበቂ መጠን ስላልነበር አደጋው ማጋጠሙን፣ የዞኑ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምርያ ኃላፊ አቶ ከፍያለው ደባሽ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በሰሀላ ሰየምት ወረዳት ድርቁ ባስከተለው ጉዳት ሁለት የወረዳው ነዋሪዎች መሞታቸውን ተናግረው፣ ከ1,200 በላይ እንስሳት መሞታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ከሞቱት እንስሳት 263 የቀንድ ከብቶች 37 በቅሎና አህዮች፣ እንዲሁም 936 ፍየሎችና በጎች መሞታቸውን አብራርተዋል፡፡

ከሐምሌ 28 ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በጣለው ዝናብ 800 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኖ ነበር ያሉት የመምርያ ኃላፊው፣ ከሰባት መቶ ሺሕ ሔክታር በላይ የሚሆነው ቡቃያ ደርቋል ብለዋል፡፡

አካባቢው ዝናብ አጠር ነው ያሉት አቶ ከፍያለው ከዚህ በፊትም በድርቅ ይጠቃ እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ግን ለየት ባለ ሁኔታ ወረዳው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በድርቁ መጎዳቱን አስታውቀዋል፡፡ ከሰሀላ ሰየምት ወረዳ በተጨማሪ በዝቋላ ሦስት ቀበሌዎች በድርቁ መጠቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ጦርነት ውስጥ የነበረ አካባቢ እንደነበር ጠቅሰው፣ ከጦርነቱ ሳያገግም የተከሰተው ድርቅ በሰዎች፣ በእንስሳትና በሰብል ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ ነው ሲሉ አቶ ከፍያለው አስረድተዋል፡፡

ችግሩ እንደ ቀላል መታየት እንደሌለበት፣ ከክልሉ መንግሥት በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

በሁሉም አቅጣጫዎች የፀጥታ ሥጋት ያለበት አካባቢ በመሆኑ ሰዎች እንደፈለጉ ወደ ሌላ አካባቢ ተንቀሳቅሰው ራሳቸውን የሚያተርፉበት ሁኔታ ባለመኖሩ፣ ከ80 ሺሕ በላይ የወረዳው ነዋሪዎች ችግር ላይ መውደቃቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከ95 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች የነበሩበት አካባቢ እንደነበር የተናገሩት የመምርያ ኃላፊው ተፈናቃዮች እርስ በርስ ይረዳዱ እንደነበር አሁን ግን ድርቁ በመከሰቱ ለተጨማሪ ጉዳት መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡

እየደረሰ ያለውን ጉዳት አገር በቀልና አገር በቀል ያልሆኑ የረድኤት ድርጅቶች ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ አቶ ከፍያለው አሳስበዋል፡፡

ድርቁ በተከሰተበት አካባቢ በመንግሥትም ሆነ በማንኛውም አካል ነዋሪዎችን ለመርዳት የተደረገ እንቅስቃሴ አለመኖሩን የተናገሩት የመምርያ ኃላፊው፣ አንዳንድ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የዞኑ የምግብ ዋስትና መምሪያ ለክልሉ መንግሥት ችግሩን በተመለከተ ሪፖርት ማድረጉን ተናግረው፣ ምናልባት ክልሉ ለፌዴራል አሳውቆ መፍትሔ ሊኖር ይችላል በማለት በተስፋ እየተጠባበቀ መሆኑን አክለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በፃግብጂና በአበርገሌ ወረዳዎች እስካሁን ከሕወሓት ነፃ ያልወጡ ቀበሌዎች መኖራቸውን የተናገሩት አቶ ከፍያለው፣ በቀበሌዎቹ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ወደ ቀዬአቸው አልተመለሱም ነው ያሉት፡፡

የክልሉ መንግሥት መደበኛ ተፈናቃዮች ናቸው ብሎ ዕውቅና ያልሰጣቸው፣ ነገር ግን ከአካባቢያቸው ርቀው የሚኖሩ ከሰባት ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን አቶ ከፍያለው ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በአሁኑ ወቅት በፀጥታ ችግር የተወጠረ በመሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥት በቀጥታ ገብቶ አካባቢውን መታደግ መቻል አለበት ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ከድርቁ በተጨማሪ 70 ሺሕ ያህል ተፈናቃዮች ያሉበት አካባቢ በመሆኑ፣ በተለይ ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ወደ አካባቢው ሄደው የበኩላቸውን አስተዋጽኣ እንዲያበረክቱ ሲሉ አቶ ከፍያለው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...