Saturday, July 20, 2024

በዓባይ ውኃ ላይ የሚነሳው የግብፅ ታሪካዊ መብትና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ኃላፊነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከተጀመረ 11ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ፣ በኢትዮጵያውያን የፋይናንስና የሞራል ድጋፍ ከተገነቡ ግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክቶች የመጀመሪያው ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡

 ይሁን እንጂ ይህንን ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ መገንባት ከተጀመረ ወዲህ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች በተለይም ከግብፅና ከሱዳን የሚነሳው በውኃው ላይ የበላይነት የመያዝ ጥያቄ የቀጠለ ሲሆን በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል ለተከታታይ ዓመታት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ሰባተኛ ዙሩን ይዟል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ እየተካሄደ ያለው ድርድር የአንድ ግድብን ጉዳይ የሚመለከት ቢሆንም፣ ከግብፅ በኩል የሚታየው ከፍተኛ ግፊትና ፍላጎት ግን በአመዛኙ አጠቃላይ የዓባይን ውኃ የመቆጣጠር ፍላጎት ስለመሆኑ በስፋት ከኢትዮጵያ በኩል ይነሳል፡፡

በግድቡ ዙሪያ አገሮቹ የደረሱበት አሁናዊ ቁመና መደበኛ የሆነ የውኃ ስምምነት ሳይሆን የመጀመርያ ውኃ ሙሌትና ዓመታዊ የውኃ አለቃቀቅ መመርያና ደንብ ለማዘጋጀት እንደሆነ፣ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ዲፕሎማት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ይህ ማለት እየተደረገ ያለው ድርድር ስለአንድ ግድብ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡

አሁን የቀጠለው ድርድር መጋቢት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በተካሄደው የመሪዎች ስምምነት መግለጫ ላይ ተመርኩዞ ሲሆን ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መሠረታዊ በሆኑ የውኃ አጠቃቀም መርሆች፣ በተለይም ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም፣ እንዲሁም ጉልህ ጉዳት ያለ ማድረስ የሚሉትን መርሆች የተቀበለበት  ነበር፡፡

 ይሁን እንጂ የግድቡን የውኃ ሙሌትና ዓመታዊ የውኃ አለቃቀቅ በተመለከተ ወደ ስምምነት ቢመጣም ግድቡ እየተገነባ ያለው የሱዳን ድንበር ላይ በመሆኑና ይህም ለግብፆች አስደሳች ባለመሆኑ፣ የሚያሳዩት ፍላጎት አጠቃላይ የዓባይን ገባሮች በሙሉ፣ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ገባር የሚወጣውን ውኃ ጠብታ መቆጣጠር ስለመሆኑ የሪፖርተር ምንጭ ያብራራሉ፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ በተመለከተ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባት የምትገልጽ ሲሆን፣ በግብፅ በኩል የሚነሳው ድግሞ ውኃው ላይ ታሪካዊ መብት ያላት መሆኑን በተደጋጋሚ ማሳየት ነው፡፡

የዓባይ ወንዝ የግብፅን አጠቃላይ የውኃ ፍላጎት 95 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 86 በመቶ የሚሆነው ከኢትዮጵያ ይፈሳል፡፡

የሦስትዮሽ ድርድሩን አጀንዳ አንዴ ወደ ዓረብ ሊግ፣ ሌላ ጊዜ ወደ አሜሪካና የፀጥታው ምክር ቤት በመውሰድ አጀንዳ በማድረግ የሚታወቁት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ አንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ በናይል ውኃ ላይ ጠብታ ያክል ቢሆንም እንዲነኩብን አንፈልግም ሲሉ ኢትዮጵያ ላይ የዛቻ መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡ ካልሆነ ግን ሁሉንም አማራጭ መጠቀም እንደሚችሉም ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ሲሞላ የግድቡን ውኃ የሚይዘው አካል 246 ኪሎ ሜትር በመዘርጋት፣ 74 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ይይዛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የግድቡ የውኃ ሙሌት ከተጀመረ ጀምሮ የግድቡ የመጀመርያ የውኃ ሙሌት ተብሎ የሚጠራው፣ ከአንደኛው ዓመት እስከ አራተኛው ዓመት በተከታታይ ለአራት ጊዜያት የሚደረገው ሙሌት ነው፡፡

ሦስቱ አገሮች የሚያደርጉት ስምምነት ውኃውን እንዴት እንሙላው ቢሆንም፣ ግድቡ መቼና እንዴት ይሞላ የሚለውን ስምምነት በ2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ  በገለልተኛ ቡድን አማካይነት መጀመርያ በግንባታው ፍጥነት መሠረት ሙሌቱ እንዴት ይካሄዳል በማለት ስምምነት ስለማድረጋቸው ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑት ባለሙያ ለሪፖርተር ይናገራሉ፡፡ ይህ ማለት አሁን ሙሌቱን ከዚህ በፊት በነበረው ስምምነት መሠረት ሲሆን፣ የሚደረገው ሙሌት በተመለከተ ለሱዳንና ለግብፅ መረጃ ስለመሰጠቱ የሪፖርተር ምንጭ አክለው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት አስገዳጅ የሞራልና ታሪካዊ ኃላፊነት ባይኖርበትም፣ ከአብሮ ከመጠቀምና በጋራ ከመልማት በመነሳት እስካሁን በነበሩት ጊዜያት ለግብፅና ለሱዳን የውኃ አጠቃቀሙን የተመለከቱ 159 የጥናት ሰነዶች መስጠታቸውን ይናገራሉ፡፡  ግብፅና ሱዳን ግድቡን የኢትዮጵያ ብቻ አድርገው ቢቆጥሩትም ሁኔታው ግን እንደዚያ አለመሆኑን የሚናገሩት ባለሙያው፣ ኢትዮጵያ ውኃውን በምክንያታዊነትና በፍትሐዊነት መጠቀም እንደ ባህል አድርጋ የወሰደችው ስለመሆኑ ያብራራሉ፡፡

ሦስቱ አገሮች ለሰባት ጊዜ ያህል ለድርድር የተቀመጡ ሲሆን፣ በእነዚህ መድረኮች በአብዛኛው ጊዜ የሚጠበቁት ውኃን የተመለከቱ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ በግብፅ በኩል አጀንዳውን በዋነኝነት የሚመራውና የሚፈተፍተው የአገሪቱ ጄኔራል ኢንተሌጀንስ የተሰኘው የደኅንነት ተቋም መሆኑን፣ በተቃራኒው ደግሞ በኢትዮጵያ ጉዳዩን በባለቤትነት የያዘው በአዋጅ ሥልጣን የተሰጠው የውኃና የኢነርጂ ሚኒስቴር ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ ዕገዛ የሚያደርግ ተቋም ነው፡፡

በመሆኑም አሁን ላይ እየተካሄደ ያለው ስለውኃ ጉዳይ ለመደራደር ከሁለቱም ወገን የውኃ ባለሙያዎች መኖር ሲገባቸው፣ በአንድ በኩል የውኃ ባለሙያዎች በሌላ በኩል የደኅንነትና የፖለቲካ ሰዎች ተቀምጠው የሚደራደሩበት ነው፡፡

እንደ ባሙያው ገለጻ በግብፅ በኩል ጉዳዩ በደኅንነት ተቋም እንዲያዝ መደረጉ የውኃውን ጉዳይ የፖለቲካና የደኅንነት አጀንዳ ያደረገው ሲሆን፣ እስካሁን ከተከናወኑት ሰባት ድርድሮች ለስድስተኛ ጊዜ የተካሄደው አሜሪካ በአደራዳሪነት ገብታ ነው፡፡

 የአሜሪካ አደራዳሪነት የመጣው የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ  እ.ኤ.አ. በ2019 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ዕርዳታ ጠይቀው የተካሄደ ድርድር እንደሆነ በኢትዮጵያ በኩል ይታመናል፡፡

በዚህ ስብሰባ ኢትዮጵያ እንነጋገርና ጉዳያችንን እናስረዳ በሚል ለቀረበው ግብዣ በአዎንታ ወደ አሜሪካ በመሄድ ለማስረዳት ቢሞከርም፣ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ በመውጣታቸው እ.ኤ.አ. በ2020 ኢትዮጵያ ድርድሩን ማቋረጧን ባለሙያው ያስታውሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ድርድሩን አቋርጣ ስትመለስ የፖለቲካና የደኅንነት ጉዳይ በማድረግ ግብፅ ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰዷ ይታወሳል፡፡

የግብፅ የውኃውን ጉዳይ በፀጥታው ምክር ቤት እንዲታይ መውሰዷ በምክር ቤቱ ታሪክ ከታዩ አጀንዳዎች መካከል ከውኃ ጉዳይ ጋር የተገናኘ አጨቃጫቂ ጉዳይ የፀጥታና የደኅንነት አጀንዳ ሆኖ፣ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ቀርቦ እንደማያውቅ ከኢትዮጵያ በኩል ሲነሳ ይደመጣል፡፡

የዓባይ ጉዳይ የፀጥታና የፖለቲካ መልክ እንዲይዝ የተደረገበት ዓላማም የቅኝ ግዛትን ውል ማደስ ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያየ ጊዜ በሚያወጣቸው መግለጫዎች አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ እንደሚጠቅማትና ጉልህ ጉዳት (No Significant Harm) እንደማያደርስ ብታሳውቅም፣ ግብፅ በአዎንታዊ መንገድ ልታየውና ልትቀበለው አልቻለችም፡፡ ይሁንና ግብፅ በተደጋጋሚ የምታነሳቸውና የድርድር አካል እንዲሆኑ የምትጠቅሳቸው እ.ኤ.አ. የ1929 እና የ1959 ሁለት ስምምነቶች ሲሆኑ እነዚህን የቅኝ ግዥ ውሎችን በመጥቀስ ውኃውን የመጠቀም ዓለም አቀፍ መብት እንዳለት በተደጋጋሚ ትገልጻለች፡፡

በአሜሪካ የተካሄደውን የስድስተኛው የድርድር ሒደት ኢትዮጵያ ያቀረበቸው ጉዳዩን በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ እንዲታይ የሚለው በአብለጫ ተወስኖ፣ በፀጥታው ምክር ቤት በተወሰነው መሠረት አሁን እየተካሄደ ያለው ሰባተኛው ደረጃ ድርድር በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡

በሐምሌ ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከግብፅ ፕሬዚዳንት ጋር ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ ድርድሩን እናፋጥን የሚል የጋራ መግለጫ አውጥተው ነበር፡፡

ይህንንም ተከትሎ ድርድሩ ወደ አፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ከመጣ ወዲህ፣ በሌላ ሦስተኛ አገር አንድ ኢመደበኛ ውይይት ስለመካሄዳቸው የሪፖርተር ምንጭ ይናገራሉ፡፡

 በቅርቡ ሁለቱ መሪዎች ከተገናኙ በኋላ በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ሥር ሦስቱ አገሮች እ.ኤ.አ. ነሐሴ 27 እና 28 ቀን ተገናኝተው የተነጋገሩ ሲሆን፣ በዚህ ሁሉ ሒደት ግን ግብፆች መስማማት ይፈልጋሉ ወይ የሚለው ጥያቄ አሁንም ከኢትዮጵያ በኩል ጥርጣሬን የሚያጭር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ባለሙያው እንደሚሉት ድርድር ሲባል ዙሪያ ጥምጥም መሆን የለበትም፡፡ ተደራዳሪ አካላት የቱን ሰጥተው የቱ ጋ መደራደር ላይ እንዳለባቸው ቢታወቅም፣ ኢትዮጵያ ግን በራሷ ጉዳይ ላይ የምትደራደር አገር ናት ይላሉ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ  ድርድር ውስጥ ገብታ ሳለ ከግብፅ በኩል እየመጣ ያለው የቅኝ ግዛት ስምምነት  በየመሀል እየገባ፣ የድርድሩ እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሀል ደግሞ የግብፅ ባለሥልጣናት የዓረብ ሚዲያዎችን በመጠቀም እየወጡ የሚያደርጉ ንግግር፣ ኢትዮጵያ አቋማን ለመቀየር ፈቃደኛ አለመሆኗን የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ችግሩን በተረጋጋ መንገድ ለመፍታት ነው፡፡ ሐሳብን ሚዲያ ላይ አውጥቶ ማስተጋባትና ድርድር ማድረግ አደጋ ያለው በመሆኑ፣ ማስተጋባት አስፈላጊ ነው የሚል አቋም እንዳለው ይገልጻል፡፡

የግብፅ መንግሥት ባለሥልጣናት ሕዝቡ ይቆጣል አግዙን በሚል የኢትዮጵያን ባለሥልጣናት እንደሚጠይቁ፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት እሺ እንተጋገዝ በሚል ለመቅረብ ሲሞኮር ራሳቸው እሳቱን ለኩሰው ጉዳዩን ወደ ማጋጋል እንደሚሄዱ ባለሙያው ያብራራሉ፡፡

የዓባይን ውኃ በተመለከተ በግብፅ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 44 መሠረት ማንኛውም የግብፅ መንግሥት በናይል ጉዳይ ጥቅምን አሳልፎ እንዳይሰጥ እስረኛ ስለማደረጉ የሚናገሩት የሪፖርተር ምንጭ፣ ፕሬዚዳንቱን በዓባይ ጉዳይ መደራደር እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ሦስቱ አገሮች የጀመሩት ድርድር መጨረሻ እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡

 ኢትዮጵያ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት አቋሟን ግልጽ ስታደርግ መቆየቷን ታስታውሳለች፡፡ አገሪቱ ምንም እንኳ 86 በመቶ የሚሆነውን የዓባይ ውኃ ምንጭ ብትሆንም ግብፅ ካለችበት በረሃማነት የተነሳ ሊከሰት ለሚችል የድርቅ ምላሽ አሰጣጥ፣ ወይም የድርቅ አስተዳዳር በሚል አዲስ ጉዳይ በማንሳት ያለ መግባባት መነሻ እያደረገችው ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ ውኃውን ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀም እንችላለን ትላለች፡፡

በዚህም የተነሳ ድርቅ የጋራ ጉዳይ ቢሆንም ግብፅ ድርቅን እንደ ምክንያትና ሽፋን በመጠቀም በድጋሚ እ.ኤ.አ. የ1959 የቅኝ ግዛት ስምምነትን፣ ወይም 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ማግኘትን እንደ መብት በመውሰድ ትከራከራለች፡፡

 እንደገና ከጀርባ በመሄድ የድርቅ አስተዳደር እንደ ሽፋን ይቀርባል፡፡ ኢትዮጵያ ላለመስማማት የሚያስችል ምክንያት ባይኖራትም በግብፅ በኩል ግን ዝግጁነቱ አለመኖሩን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

ግብፅ የድርቅ አስተዳደሩን ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በማያያዝ ትልቅ ግዴታ ለመጣል መሞከር፣ ለኢትዮጵያ ቀይ መስመር መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ይገልጻል፡፡

የዓባይ ተፋሰሰስ አገሮች ወደፊት ሊካሄዱ በሚችሉ ልማቶች የፈረሙትን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት አራት አገሮች አፅድቀውት ስድስት አገሮች የፈረሙ ሲሆን፣ ይህ ስምምነት ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲኖር የሚያደርግ ቢሆንም በዚህ ማዕቀፍ መሠረት በሚኖር የውኃ ክፍፍል በግብፆች በኩል ፍላጎት አለመኖሩን የኢትዮጵያ መንግሥት ያስታውቃል፡፡

በግብፅ በኩል ከሚባሉት መካከል ‹‹ኢትዮጵያ የግድቡ ኮንክሪት ባለቤት ልትሆን ትችላለች፣ ነገር ግን የውኃው ባለቤት አትሆንም፤›› የሚለው አንዱ ነው፡፡

የግድብ ውኃ ከሞላ ጎደል እያለቀ ሲሆን፣ የግብፅም ሆኑ የሱዳን ባለሥልጣናት በዚህ ጉዳይ አጨቃጫቂ ባህሪ የሌላቸው በመሆኑ የውኃው ፍሰትም በሚፈልጉት መጠን እየተለቀቀ ነው፡፡ አሁን ዋነኛ የስምምነቱ አጀንዳ ዓመታዊ የውኃ አለቃቀቅ መሆኑን የሪፖርተር ምንጭ ተናግረዋል፡፡

ባለሙያው አክለውም የድግቡ የኃይል የማመንጨትና የውኃ አለቃቅን በተመለከተ ግብፆች የሚያሳዩት ፍላጎት ግድቡ በራሱ ከዋናው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ግሪድ እንዲነጠል ነው፡፡ እነሱ እንደፈለጉ ውኃ የሚለቅና ካልፈለጉ ባለው እንዲንቀሳቀስ እንጂ፣ ኢትዮጵያ ይህን ግድብ ከሌሎች ግድቦች ጋር በማገናኘት የኤሌክትሪክ ኃይል  ማመንጨት የምትችልበት መብት እንዲኖራት አይፈልጉም ይላሉ፡፡

በተመሳሳይ በግብፅ በኩል የሚታየው ፍላጎት የአስዋን ግድብ ካልሞላ የህዳሴ ግድብ አይሞላም የሚል መሆኑን በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሲነገር ይደመጣል፡፡

ዋነኛ የውኃ ምንጩ የዓባይ ወንዝ እንደሆነ የሚነገርለት የግብፁ አስዋን ግድብ እንዴት እንደሚንቀሳቀስ፣ እንዴት ውኃ እንደሚለቅና እንዴት አገልግሎት እንደሚሰጥ  ኢትዮጵያ አታውቅም፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ በህዳሴ ግድብ ላይ ከግብፅ በኩል የሚሰማው ጩኸት፣ በሉዓላዊ መሬት የገነባሁትን ግድብ እኔ ላንቀሳቅሰው የሚል ዓይነት ፍላጎት ያዘለ ስለመሆኑ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ይወሳል፡፡

ግብፅ ከአስዋን ግድብ በሚሄድ ውኃ ሌሎች የውኃ ፕሮጀክቶችንና ግድቦችን እየገነባች ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ በቅርቡ በካይሮ በነበረው ስብሰባ መሪዎች በደረሱት ስምምነት መሠረት በመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት ማለትም በመስከረም መጨረሻ ሳምንት በአዲስ አበባ በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ መሠረት ቀጣዩ ድርድር የሚካሄድ ሲሆን፣ አገሮቹ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚለው አሁንም ጥያቄ ውስጥ ያለ ይመስላል፡፡

ይህም በግብፅ ሕገ መንግሥት መሠረት የአገሪቱ መሪ የዓባይን ውኃ የመጠበቅና  ታሪካዊ መብቷን የማስጠበቅ ግዴታ አለበት የሚል አንቀጽ በመሥፈሩ ሲሆን፣ ጉዳዩ ፕሬዚዳንቱን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከተው ነው ይባላል፡፡

በግብፅ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 44 መሠረት የግብፅ መንግሥት የዓባይን ውኃ የመጠበቅ ግዴታ ጥሎበታል፡፡

የናይል ተፋሰስ አገሮች በፍትሐዊና በምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ የፈረሙትን ስምምነት ግብፃውያን ከሕገ መንግሥታቸው ጋር ስለሚጋጭ፣ ይህንን ስምምነት እንደማይቀበሉትና ፕሬዚዳንቱ በፍርድ ቤት ክስ ቀርቦባቸው እንደበር ይጠቀሳል፡፡

በአጠቃላይ ግን ግብፃውያን የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚያደርጉት ድርድር  እንዲቀጥል ካልሆነ በስተቀር፣ ወደፊት ስምምነት ላይ ለመድረስ ፍላጎት አላቸው ተብሎ እንደማይጠበቅ ከኢትዮጵያ በኩል ይደመጣል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -