Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት እየፈጸማቸው ባሉ የንግድና ኢንቨስትመንት ስምምነቶች የግል ዘርፉ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ ማድረግ አለበት

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ በመሥራችነትና በአባልነት ተሳታፊ በመሆን በአፍሪካ ተጠቃሽ አገሮች በቀዳሚነት የምትጠቀስ ነች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች ነች፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ቀዳሚ መሥራችና ለድርጅቱ ዕውን መሆን የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድም ትታወቃለች፡፡

እንዲህ ካሉት ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ ድርጅቶች ውስጥ በአባልነት ከመሳተፍ ባሻገር፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ተግባራትን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ በአባልነት ዘልቃለች፡፡ ከንግድና ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ እንደ ኮሜሳ ያሉ በአባልነት የታቀፈችበትን ቡድን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በመወሰን ለዓመታት በዝግጅት ሒደት ላይ ይታወቃል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጠሩ ያሉ እንደ አፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ያሉ ስምምነቶችን ለመተግበር ፊርማቸውን በቀዳሚነት ያኖረች አገርም ነች፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የዓለምን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በተለየ እንዲጓዝ ያደርጋል ተብሎ የሚጠቀሰውን ‹‹ብሪክስ›› ተቀላቅላለች፡፡ የንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ መጪውን ጊዜ ያራምዳሉ የተባሉ እንዲህ ያሉ ስምምነቶችን መፈረምና በአባልነት መቀላቀል ያስገኛሉ ተብለው የሚጠበቁ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ብዙ ናቸው፡፡

በተለይ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት የአፍሪካ አገሮችን ድንበር በመስበር እስከ ዜሮ በሚደርስ ታሪፍ እርስ በርሳቸው እንዲስተናገዱ ያስችላል በሚል ወደ ስምምነቱ ወደ ትግበራ እየተገባበት ነው፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ድንበሮቿን ለሌሎች አገሮች ንግድ የምትከፍትበት፣ እሷም ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ ምርቶቿን እንድትልክ የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህንን ስምምነት ለመተግበርም መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡

ሰሞኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ደኤታው አቶ ካሳሁን ጎፌ እንደገለጹት፣ ለነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ ኢትዮጵያ የምታቃርባቸው የንግድና አገልግሎት ዓይነቶች ተለይተው በመንግሥት ይሁንታ አግኝቷል፡፡ ይህንን ስምምነት ወደ ተግባር ለመቀየርም ሌሎች በርካታ ሥራዎች የተጠናቀቁ በመሆኑ፣ ስምምነቱ በቅርቡ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምርም ማረጋገጫ እስከ መስጠት ተደርሷል፡፡ የብሪክስ አባልነቷም ቢሆን በጥቅል ሲታይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚውን ለማሳደግና ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችላትን ዕድል እንደሚሰጣት እየተነገረ ሲሆን፣ ከጥቂት ወራት በኋላ በተግባር የሚታዩ ነገሮች እንደሚጠበቁ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጠቁመዋል፡፡ ቀጣናዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ የንግድ ስምምነቶች፣ እንዲሁም የብሪክስ አባል ሆና አገሪቱ ታገኛለች ተብሎ የሚጠበቀውን ጠቀሜታ በተጨባጭ ለማግኘት ግን ቀላል እንደማይሆንም ካነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ለመገንዘብ ይቻላል፡፡

የኢንቨስትመንት አማካሪ አቶ ያሬድ ኃይለ መስቀል አኅጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ የንግድ ስምምነትን በትክክል በነፃ ገበያ መርህ መሠረት ለማውረድና አገር ተጠቃሚ እንድትሆን ከተፈለገ የግል ዘርፉ ግንባር ቀደም ሚና እንደሚኖረውም ያምናሉ፡፡    

እንደ አቶ ያሬድ ገለጻ የግል ዘርፉን በተመለከተ በብዙ አገሮች የመንግሥት ሚና እንደ ዳኛ የሚታይ ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች የግል ዘርፍ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ የሚደረግ ሲሆን፣ ውድድር ውስጥ የማይገባባቸው ብቻ ሳይሆን፣ የመንግሥት የሚባል ኩባንያ የለም ማለት እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡ በእኛ አገር ይህ ዓይታይምና እንዲያውም የግል ዘርፉን የሚያዳክሙ ሁኔታዎች የሚታዩ መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡ የእኛና የእነሱ የመንግሥትና የግል ከሚለው ነገር ያልተላቀቅን በመሆኑ እንጂ ቀዳሚው ተጠቃሚ የሚሆነው የግል ዘርፉ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡

የግሉ ዘርፍ ሚና ጎልቶ በሚታይባቸው አገሮች መንግሥት ኩባንያዎቻቸውን ፕሮሞት በማድረግ ገበያቸው የሚያሳድጉበት ሥራዎች ሁሉ የሚሠሩ በመሆኑ ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ስምነነቶችን በአግባቡ ለመጠቀም መንግሥት እንደ አንደኛ ሆኖ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ የመንግሥት ተግባር በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ሲሆን፣ ለምሳሌ አገር በቀል ኩባንያዎች ገበያ እንዲያገኙ ከኢትዮጵያ ውጪ ይዟቸው በመሄድ ጭምር አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ማድረግ አንድ ቀላል ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል አመላክቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል ብለው የጠቀሱት በቅርቡ የኬንያው ፕሬዚዳንት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የአገራቸው የግል ኩባንያ የሆነው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ውስጥ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ እንዲሳተፍ ኢትዮጵያን ያግባቡትና ያገኙትን ውጤት ነው፡፡

ሳፋሪኮም በዘርፉ እንዲሠራ መፈቀዱ ደግሞ ከዚህ ቢዝነስ የሚገኘው ትርፍና ሀብት፣ የአገር ሀብት መሆኑን ስለሚያውቁ የግል ዘርፋቸውን ያበረታታሉ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ ከየትኛውም ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ስምምነት ተጠቃሚ ለመሆን የግል ዘርፉን ሀብት እንደ አገርና የመንግሥት ሀብት ማየት የግድ ይላል፡፡ እኛ ጋ ያለው  ችግር የግል ዘርፉን እንደ አገር ሀብት ያለማየት በመሆኑ መንግሥት የእኔ ነው ብሎ ያለመቀበል ችግር ያላት ስለመሆኑ አቶ ያሬድ ይጠቅሳሉ፡፡ እንዲህ ያለው አመለካከት መቀየር አለበት፡፡ በዚህ አገር ለዲጂፒው አስተዋጽኦ የሚያደርገው ነገር ሁሉ የኢትዮጵያ ሀብት ነው ተብሎ መወሰዱ ካልቻለ ተጠቃሚ መሆን ይችላል ብለው አያምኑም፡፡

ይህ ችግር ሊፈጠር የቻልበት አንዱ ምክንያት ኢትዮጵያ ከሲቪሊዝም ሥርዓት በመቆየትና ይህንንም ቻሌንጅ የሚያደርግ አይዶሎጂ ስላልመጣ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ አሁን የመንግሥት ብቻ፣ የግል ደግሞ እንደ በዝባዥና እንደ ችግር እየታየ መቆየቱ እንጂ ኢኮኖሚው መመራትና መፎካከር ያለበት እንዲሁም አገልግሎቱን መስጠት ያለበት የግሉ ዘርፍ መሆኑን የሚስማሙበት አቶ ያሬድ፣ ውጤታማ የሚሆነውም ስለግል ዘርፉ ያለው አመለካከት ሲቀየር ጭምር ነው፡፡

እንደ አፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ገበያ ውስጥ ሲገባም የተዳከመ የግል ዘርፍ ይዞ መሆን እንደሌለበት የሚገልጹት አቶ ያሬድ፣ ‹‹የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ነገር ግን ተጠቃሚዎች አይደለንም፤›› ብለዋል፡፡ እንዲያውም የግል ዘርፎችን በደንብ ስላልጠነከረ ነፃ ንግድ ከሆነ የሌሎች አገሮች ኩባንያዎች ኢትዮጵያን እንደ ጥሩ ዕድል ተጠቅመውባት ምርታቸውን እንደ ልብ ለመሸጥ በር ይከፍትላቸዋል፡፡ ምክንያቱም ትልቅ አገርና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ያለባት በመሆኗ ትልቅ ገበያ ያለባት በመሆኑ አገሮች ይህንን ዕድልና የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ደካማ መሆንን ተንተርሰው ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው፡፡ የኬንያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ አፍሪካም ሆነ የሌሎች አገሮች ኩባንያዎች ብርቱ ተፎካካሪዎች ሆነው ሊመጡ መቻላቸው ሊታሰብበት የሚገባ መሆኑን ጠቅሰው፣ እንዲህ ካሉ ስምምነቶች ተጠቃሚ ለመሆን የግል ዘርፉን የሚወድ መንግሥት ሊኖር ይገባልም ብለዋል፡፡

የአገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበባየሁ ግርማ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የምትፈራረማቸው የንግድና ኢንቨስትመንት ስምምነቶችም ሆኑ አባል የሞትሆንባቸው ድርጅቶች ውጤታማ የሚሆኑት የግል ዘርፉ ሲጠነክርና ሲበረታታ ብቻ መሆኑን ይስማሙበታል፡፡ ነገር ግን ባልጠነከረ የግል ዘርፍ የአፍሪከ ነፃ የንግድ ቀጣናን መተግበር የቱንም ያህል ቢፈተን ባለን አቅም ገንብተን መወዳደር የግድ ነው ይላሉ፡፡ ካልሆነ አሁን ያልጀመርነው ወደፊት አያስኬድም ይላሉ፡፡

ስለዚህ አሁን እየተሠራ ያለው ሁኔታ በአንፃራዊነት ክፍተት ቢሆንም፣ መንግሥት የግል ዘርፉን ሊያጠናክሩ በሚችሉ አሠራሮች ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሠራ ይገባል፡፡ መንግሥት አድምቶ መሥራት ያለበት ኤክስፖርተሮች ላይ መሥራት የተለያዩ የንግድ ስምምነቶችን ያለ ችግር ለመሥራት የሚያግዝ ይሆናል፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያ፣ አፍሪካ የንግድ ቀጣና ስምምነትን መፈረሟ ተግዳሮት ሊኖረው ቢችልም፣ እነዚህን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ ጥሩ ተወዳዳሪ ለመሆን መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡

የማምረት አቅማችን ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አንፃር ሲታይ ምናልባት አንሶ ሊታይ ይችል ይሆናል የሚሉት አቶ አበባየሁ ግን፣ ‹‹ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም›› እንደሚባለው ሁሉ፣ ቢያንስም እንጀምርና እየተመካከርን እየሰፋን መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡   

 እንዲህ ዓይነት ስምምነቶች መተግበር የሚቻለው በግል ዘርፍ ስለመሆኑ የገለጹት የኢኮኖሚ ባለሙያው ቆስጠንጦኒዮስ በረሃ (ዶ/ር) ዋና ተጠቃሚም የግል ዘርፉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ምክንያቱም ሌላው ቀርቶ በአጎዋ የተከለከልነውን በአማራጭ ገበያ መሸጥ ይችላሉ፡፡ በተለይ አፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ከታሪፍ ነፃ በመሆኑ የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ ምርቱን በቀላሉ ለመሸጥ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የኢንዱስትሪ ውጤቶች ሊኖሩን ይገባል ብለዋል፡፡ እስካሁን ኢትዮጵያ ኤክስፖርት የምታደርገው ቡና፣ ሰሊጥና ጫት መሆኑን ያስታወሱ ቆስጠንጢኖስ፣ ይህንን መቀየር ግን ወሳኝ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር መሆኗም ቢሆን በዋናነት ተጠቃሚው የግሉ ዘርፉ መሆኑን የገለጹት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ የብሪክስ አባል አገሮችም የታሪፍ ነፃ የንግድ ቀጣና የመፍጠር ዕቅድ አላቸው የሚል ግምት ስላለ እንዲህ ያለው ሁኔታ ከተፈጠረ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመምከር የብሪክስ ኤክስፖርተሮች ለምክር የተቀመጡ በመሆኑ አባልነቱ ሊያስገኝ የሚችለው ጠቀሜታ በቀጥታ ከግሉ ዘርፍ ጋር ስለመያያዙ አመልክተዋል፡፡ ከብሪክስ አባል አገሮች ከባድ ኢንቨስትመንት ሊመጣ ይችላል ያሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ ስለዚህ ኢትዮጵያ የግል ዘርፍ ለዚህ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ሊሠሩበት የሚችሉት የኢንቨስትመንት ዓይነት ደግም ማዕድን፣ እርሻና የመሳሰሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ መሳተፍ የውዴታ ግዴታቸው ስለሚሆን የኢትዮጵያ የግል ዘርፉም እንዲህ ያለውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት መሥራት ይጠበቅበታል፡፡  

ኢትዮጵያ የብሪክስ አገልግሎት በአባል አገሮች መካከል ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እንቅስቃሴ ይኖራል፡፡ ኢንቨስትመንት ይኖራል፡፡ ይህ ሲባል እንደ ቻይና ያሉ አገሮች በቀጥታ መጥተው ይሠራሉ ሳይሆን ኢትዮጵያውያኖች በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ ኢንቨስ አድርገው ሊጠብቁ ይገባል፡፡ የቻይና ኩባንያዎችም በእነዚህ ኢንቨስትመንቶች ላይ ካፒታል በማፍረስ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ዝግጅት ያስፈልጋል እንጂ አባል መሆኗ አገርንም የግል ዘርፉንም እንደሚጠቅም ቆስጠንጢኖስ ገልጸዋል፡፡   

አቶ ያሬድ ግን የተለየ አመለካከት አላቸው፡፡ ብሪክስ ከኢኮኖሚው ጉዳይ የበለጠ የፖለቲካ ጉዳይ አጀንዳው ያደረገ ይመስለኛል ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ከቻይና ጋር እየተገበያየች ነው እነሱ ወደ እኛ ገበያ ይመጡ ይሆናል እንጂ እንደ አጎዋ እንኳን ከቀረጥ ነፃ ዕድል ይዘው መምጣታቸውን ይጠራጠራሉ፡፡ ስለዚህ ከቻይና ጋር ተፎካካሪ ሆነን መውጣት ይከብደናል፡፡ ከሩሲያ ጋር እንኳን ገበያ ሊኖረን ይችላል፡፡ እንደ ቡናና አበባ ያሉ ምርቶችን መላክ ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ብሪክስ የሚታየው እንደ ፖለቲካ ቡድን የሚለውን እምነታቸውን ያጠነክራሉ፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያ እንደ ብሪክስ ያሉ ድርጅቶች ውስጥ አባል ከመሆን ይልቅ አፍሪካ ላይ ብታተኩር ተጠቃሚ እንደምትሆን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የእኛ ቦታ አፍሪካ ኅብረት ነው፤›› የሚሉት አቶ ያሬድ፣ አፍሪካ ኅብረት አጠናክሮ በዚያ መጠቀም ማሻል መሆኑን ያምናሉ፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ እኛ የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ነን፤›› የአፍሪካ ዩኒየንን መመራት እንችላለን፡፡ የቆየና የሚከበር ነገር አለን፡፡ እሱን ተጠቅመን የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን ማጠናከር መቻል ለአፍሪካ ትልቅ ሀብት ነው፡፡ ለእኛም የሚያስከብረን ይሆናል በማለት ይገልጻሉ፡፡

‹‹ብሪክስ ውስጥ የገባነውም የአፍሪካ ኅብረት ይመስለኛል፤›› የሚሉት አቶ ያሬድ፣ እኛ ከናይጀሪያ ኢኮኖሚ ጋር አንወዳደርም፡፡ አመራረጣቸውን ስታየው ሞር ኦፍ ጂኦ ፖለቲካል ኢንተረስት ይመስለኛል፡፡ ግብፅ የዓረብ ሊግ መሪ ናት፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መሪ ነች እንጂ ኢኮኖሚዋ ትንሽ በመሆኑ በዚህ ትጠቀማለች ማለት ይከብዳል፡፡

በመሆኑም ይህ ጉዳይ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያመጣ አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም ፈተናውን የሚያበዛብን ይመስለኛል የሚሉት አቶ ያሬድ፣ እንደ አሜሪካ ካሉ አገሮች ጋር ላያስማማን ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን ከዓለም ባንክ ገንዘብ እየለመንን ነው፡፡ አጎዋ ተጠቃሚነታችንን ለማስቀጠል እየጠየቅን ነው፡፡ ስለዚህ የአሜሪካ ተቀናቃኝ ቡድን ውስጥ ከሆንክ ዕርዳታውንም ብድሩንም ሊከለክሉ ስለሚችል ነው የብሪክስ አባል መሆናችን ፍዳችንን ሊያበዛው ችላል የሚል ሥጋት ያሳደረባቸው አቶ አበባየሁና ቆስጠንጠንዮስ ግን ኢትዮጵያ ሁሉንም አማራጮች መጠቀም ይጠቅማል ይላሉ፡፡ ከብሪክስም ሆነ ከብሪክስ በተቃራኒ ካለው ጎራ ጋር በስምምነት መሥራት ይጠቅማል ይላሉ፡፡  አቶ ያሬድ በዚህ አይስማሙም፡፡ ‹‹ከጠቀመ ግን ጥሩ ነው፤›› የሚሉት አቶ ያሬድ፣ ውጤቱን በቅርብ የምናየው ስለሚሆን ያኔ ሊታይ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ግን እንደ ፖለቲካ አሊያንስ የብሪክስ ቡድን ውስጥ መግባት ትክክል ሊሆን ይችላል የሚሉት አቶ ያሬድ፣ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት አሜሪካኖች ጭልጥ ብለው ሲሄዱ ሩሲያና ቻይና ብዙ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ውሳኔዎችን አስቀርተዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ አገሮች ትልቅ አደጋ ሊፈጥሩብህ የሚችሉ አደጋዎችን ይከላከሉልሃል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ሰላም ፈጥረህ የምታደርግ ከሆነ ከአንድ ቡድን ጋር ባትታይ የተሻለ ይሆናል የሚል ምልከታ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ አበባው በዚህ አባልነታችንም ተጠቃሚ እንሆናለን ብለው ያምናሉ፡፡

‹‹ከብሪክስ ጋር በተያያዘ የተደረሰበት ደረጃ የኢትዮጵያን የዲፕሎማቲክ አቅም ከፍ ማለቱን የሚሳይ ነው፤›› ያሉት አቶ አበባው፣ ነገሩን እንዲህ በቀላሉ ማየት ተገቢ ያለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ ሎቢ አድርጎ በዓለም ደረጃ ትልልቅ የሚባል ኢኮኖሚ ካላቸው አገሮች ቅቡልነት አግኝቶ ተቀባይነት ማግኘት ትልቅ ውጤት ስለሆነ መታሰብ ያለበት ከዚህ አባልነታችን እንዴት እንጠቀማለን ብሎ መሥራት ብቻ ነው፡፡

የብሪክስ አባል በመሆናችን ብቻ የሚፈጠር የገበያ ዕድል ይኖራል፡፡ ወደ አገር ውስጥ ኢንቨስትመንትም የሚጨመርበት ዕድል ስላለ የግሉ ዘርፍም ተጠቃሚ እንደሚሆን ይስማሙበታል፡፡ እኔ እንደ ነጋዴ አንድ ምርትን በብቸኝነት አምርቼ ለ100 ሺሕ ሕዝብ አከፋፍላለሁ፣ የማከፋፍልበትን ዋጋ ወስኜ ነው የማከፋፍለው፡፡ ሁለት ብንሆን ደግሞ አማራጭ ይፈጠራል፡፡ ከአንድ ብቻ መሆኑ ግን ሲፈልግ ይሰጥሃል፣ ሳይፈልግ ይነሳሃልና ኢትዮጵያ አማራጭ አጋዥ ማግኘቷ ትልቅ ውጤት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ያምናሉ፡፡  

አያይዘውም ‹‹ወደፊት ዓለምን ማን ይቆጣጠራል? ብትል እነ ቻይና ናቸው፡፡ በአፍሪካ ኢንቨስት እያደረጉ ያሉት እነ ቻይና ናቸው፤›› የሚሉት አቶ አበባየሁ ደግሞ ቴክኖሎጂም አላቸው፡፡ እንደ እኛ ያሉ አገሮች ደግሞ ቴክኖሎጂዎችን በቀላሉ ለመላመድ እየቻልን ያለነውም የቻይናን ነው፡፡ ቴክኖሎጂውንም አፎርድ አድርገን የምንገዛው የቻይናን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አድቫንቴጅ አለው፡፡ አንዱ ጋር የሙጥን ከማለት ሁለቱም ጋር መሥራት ጥሩ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የትኛውንም ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንደ መልካም ዕድል ቆጥሮ ተጠቃሚ ለመሆን የግል ዘርፍ ያለበትን ችግር መቅረፍ ወሳኝ ሊሆን ይገባል፡፡ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጀምሮ ያሉ ችግሮች ከውድድር የሚገቱ ናቸው፡፡ መንግሥት ይጠቅመኛል ያላቸውን ስምምነቶች መድረጉ እንደተጠበቁ ሆነው ስምምነቶቹንም ሆነ አጠቃላይ የአገር ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የግሉ  ዘርፉን ማጠንከር እንደሚኖበትም አቶ አበባው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከብሪክስ አባል መሆን ጋር በተያያዘ ለአገርም ሆነ ለግሉ ዘርፍ ይጠቅማል ተብሎ የተጠቀሰው ሌላው ጉዳይ የብሪክስ አባል አገሮች ከዶላር ሌላ አማራጭ መገበያያ ገንዘብ የሚፈጥሩ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ አማራጭ መፈጠሩ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የሚገልጹት አቶ አበባው፣ እንደ ነጋዴ ኢንፖርት ኤክስፖርት ላይ ያለው ችግር መሠረቱ ከዶላር ጋር የተያያዘ ይላሉ፡፡ ዓለም ላይ የሚመረቱ ብዙ ዓይነቶች ምርቶች ቻይናና ሩሲያ ይመረታሉ፡፡ ግብይታችን ግን የሚፈጸመው በዶላር ነው፡፡ ይህንን መለወጥ ከቻልን ከአሜሪካ ጋር የምንጓተትበት ነገር አይኖረንም፡፡ ከእነዚህ አገሮች የንግድ ሲስተማቸው በቀላሉ መሥራት ያስችላል፡፡ መርካቶ በትሄድ ነጋዴው የንግድ ትስስሩ ከቻይና ጋር ነው፡፡ ሸማቹም አፎርድ የሚያደርገው የቻይናን ስለሆነና ቴክኖሎጂያቸው ቀላል ስለሆነ፣ እንዲሁም በፈለከው መጠን የሚያቀርቡ በመሆኑ ብዙ ከዶላር ሌላ የእነሱን ምርት የምትገበያይበት ገንዘብ ከተፈጠረ ብዙ ይጠቅማል ይላሉ፡፡

ለዚህ አባባላቸው በምሳሌነት ያነሱት ጉዳይ ብዙ ጊዜ በዶላር ዕጦት በርካታ ኢንቨስትመንቶች የሚስተጓጎል መሆኑን ነው፡፡ ‹‹በመቶ ሚሊዮን ያፈሰስክበት የደከምክበት አንድ ኢንቨስትመንት አንድ ሺሕ ዶላር ዋጋ ያለው የተበላሸ ዕቃ ለመለወጥ የሚያስፈገውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ስድስት ወርና አንድ ዓመት ልትጠብቅ ትችላለህ፤›› ብለዋል፡፡

ዕቃውን ለመግዛት ግን የግድ የምትጠቀመው የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡ ስለዚህ የብሪክስ አባል ከሆንን በኋላ ግን በቻይና ገንዘብ ወይም አዲስ ሊፈጠር በሚችል መንገድ ገንዘብ ሳትጠቀም ግን የቻይናን ዕቃ በቻይና ገንዘብ ትገዛለህ፡፡ ስለዚህ ለነጋዴውና ለአምራቹ ትልቅ ጥቅም ይሰጣል ብለው ያምናሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡት አቶ ያሬድ ደግሞ ሁለተኛ ከረንሲ መፈጠሩ ጥሩ ነው፡፡ በሩብል፣ በብር፣ በሌሎችም መገበያየት ከቻልን ጥሩ ነው፡፡ ግን የእኛ የፖሊሲ ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብር እኮ ምሥራቅ አፍሪካ ከረንሲ መሆን ይቻላል፡፡ ጂቡቲ፣ ሶማሌ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ኤርትራና የመሳሰሉ አገሮች ተቀባይነት አለው፡፡ በእነዚህ አገሮች ተቀባይነት ቢኖረውም በኢትዮጵያ ሕግ ከአንድ ሺሕ ብር በላይ ይዘህ መውጣት አትችልም፡፡ ስለዚህ የእኛ የፖሊሲ ድክመት ነው እንጂ የከረንሲ ወይም የመገበያያ ችግር እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ በብር ብዙ አገሮች ሊገበያዩ ይችላሉ፡፡ ዶላር የምንጠቀመው በፓርላማ ተወስኖ አይደለም የሚሉት አቶ ያሬድ ተቀባይነት ስላለው እየተገለገልንበት ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ ብር ምሥራቅ አፍሪካ ላይ ከረንሲ መሆን ይችላል፡፡ ግን ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ብር ይዞ መውጣት እንደ ወንጀል ነው የሚታየው፡፡ ጠቃሚ መሆኑ ቀረና እንደ ኔጌቲቭ ነገር ታይቶ በሕግ የሚያስጠይቅ ዓይነት በመሆኑ የተፈጠረ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

በመሆኑም የእኛ የራሳችን የፖሊሲ ድክመት ነው እንጂ የመገበያያ ከረንሲ አይደለም፡፡ እኛ ብዙ የምናቀርብና የምንነግድ ከሆነ ከእኛ ብዙ የሚገዛ ሰው በብርም ይገዛል፡፡ ግን አሁን ቻይናም በለው ሌላም አገር እኛ የሚገዛው ነገር ከሌለ ብር አይቀበልህም፡፡ ጂቡቲ ብር የሚቀበለው ከእኛ የሚፈልጉት ነገር ስላለ ነው፡፡ ኬንያ፣ ኤርትራም ሆነ ሶማሊያ በተመሳሳይ የሚፈልጉት ነገር ስላለ በብር ሊገበያዩ ይችላሉ ብለዋል፡፡ ከዶላር ሌላ መገበያያ መፈጠሩ ላለው የግል ዘርፉ ይጠቅማል በሚለው ዙሪያ ላይ ቆስጠንጢኖስ ግን አማራጭ መገበያያዎች መኖር ጠቀሜታ የሚኖረው የወጪ ንግድን በማሳደግ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ አሜሪካ ከአንድ አገር በተጣለች ቁጥ ማዕቀብ ታደርጋለች፡፡ ማዕቀብ የምታደርገው ዶላር የእርስዋ ገንዘብ ስላልሆነ ነው፡፡ አሁንም ብሪክስ አማራጭ መገበያያ ገንዘብ ለመቆጣጠር ሊወስን የቻለው ከአሜሪካ ማዕቀቦች ለመላቀቅ እንጂ ሌላ አንድምታ አለው ብለው አያምኑም፡፡

ዋናው ነገር መሆን ያለት የውጭ ምንዛሪ አበረታቶ የተለያዩ አገሮችን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ነው፡፡

ይህ ለሆነው የኢትዮጵያ ብር ከተለያዩ ገንዘቦች ጋር መቀያየር የሚያስችለው በማለት አማራጭ መገበያያው ቢፈጠርም መገበያያውን ለማግኘት የወጪ ንግድን አሁንም ማጠንከር ወሳኝ ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡ አሁን ባለው የዶላር ጥንካሬ ሌላ መገበያያም መጠቀም ከባድ ስለመሆኑም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዩሮ ዶላርን ይተካል ተብሎ የታሰበውን ያህል አለመሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡

እንዲህ ባሉ ስምምነቶች ውስጥ የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ ተወደዳሪ ሊሆን ይችላል ወይ? አቅምስ አለው ወይ? ለሚለው ጥያቄ አቶ ያሬድ አቅም የለውም ይላሉ፡፡ በአጭሩ የእኛ የግል ዘርፍ ድክመት የመንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ዳኛ መሆኑ ቀርቶ ሁሉ ቦታ ተጫዋች ሆኖ ይቀርባል፡፡ ከግሉ ዘርፍ ጋር ተፎካካሪ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ይህንን ፓራዳይዝድ ሽፍት ፈጥረህ ካልተቀየረ ውጤት አይመጣም፡፡

የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ አሁን ደካማ ነው በሚባልበት በዚህ ወቅት የብሪክስ አባልም መሆን ሆነ አፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን መተግበር ሊጎዳ አይችልም ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ቆስጠንጠኒዮስ (ዶ/ር)፣ የግል ዘርፉ ደካማ ነው፡፡ ደካማ ያደረገው ግን የመንግሥት አሠራር ነው ይላሉ፡፡ በፖሊሲ ደረጃ መንግሥት የግል ዘርፉን እናበረታታለን ቢልም በተግባር የማይታይ ነው፡፡ ለምሳሌ የዓለም ባንክ ዱይንግ ቢዝነስ በሚለው መመዘኛ ስንመለከተው ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ለመጀመር በጣም ከባድ መሆኑን ነው፡፡ የዛሬ አምስት ዓመታት ዶ/ር ዓብይ ወደ ሥልጣን ሲመጡ በቀላሉ ቢዝነስ ለመሥራት የሚያስችሉ ዕድችን ለመፍጠር ቢሞከርም አሁን ላይ ነገሮች ሲታዩ የታሰበውን ያህል ያለመሆኑን ነው፡፡

መሬት አግኝተህ ሥራ ለመሥራት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ከዚህ አንፃር ሥራ ለመሥራት ከባድ ከሚባሉ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ከሙስና ጋር ተያይዞ ያለውም ችግር በተያያዥ የሚታይ ስለሆነ፣ የግል ዘርፉ በተሰማራበት ሥራ እንኳን ማደግ እንዳልቻለ ቆስጠንጠኒዮስ በረሃ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ ብሪክስ ውስጥ ትልቁ ፈተና የሚገጥመው ሙስና ነው፡፡ የብሪክስ የሙስና ኮሚቴ ብራዚል ውስጠ ባደረገው ስብሰባ አንድ አባል አገር ተጠቃሚ የምትሆነው ሙስናን መቆጣጠር ሲችል ነው ብሎ የገመገመ በመሆኑ ይህም ጉዳይ ሊታይ ይገባል ሙስና የመንግሥት ችግርም በመሆኑ መንግሠት ይህንን መቆጣጠር የሚችልበት መንገድ ሊፈጠር ይገባል፡፡ በመሆኑ ይህም ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚታየውም የካፒታል ችግር የግል ዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚቀንስ በመሆኑ እንዲህ ያሉ ችግሮችንም መቅረፍ ለጥሩ ተወዳዳሪነት የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ስለዚህ ውጭ ካፒታል መግባት በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናም ሆነ የብሪክስ በመሆን የምናገኘውን ጥቅም ከፍ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር ለመገበያት ብሎም ተወዳዳሪ ለመሆን ማድረግ ይገባታል ብለው ቆስጠንጠኒዮ (ዶ/ር) የጠቆሙ አበይት ጉዳይ የካፒታል ገበያ ላይ መሥራት ነው፡፡ ሊብራላይዜሽን ሲባል አገር መሸጥ የሚመስላቸው ያሉ በመሆኑ ይህ አመለካከት ተቀይሮ ከየትኛውም ዓለም ኢትዮጵያ ውስጥ ላለ ኢንቨስመንት አክሲዮን እየገዙ አገር ሊያሳድጉ ይችላሉና ይህ ጉዳይ በደንብ ሊሠራበት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡       

በመሆኑም መንግሥት የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ወጥተው እንዲሠሩ ኮንትራት እንዲወስዱ ብታግዛቸው እንደ ቴሌ ያሉትም የመንግሥት ተቋማት ወጥተው እንዲሠሩ ቢደረግ ባንኩንም በተመሳሳይ መንገድ ማሠራት ቢቻል መልካም ይሆናል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት አንዱን የግል ባንክ ይዞ፣ ኬንያ ቅርንጫፍ እንዲኖረው ይዞ ለመሄዱ እጠራጠራለሁ፡፡ እንደ ራሱ አያስባቸውም፡፡ ምናልባት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ይዞ ሊሄድ ይችላል መሀል ላይ የእኛና የእነሱ የሚል ሥነ ልቦና አለ፡፡ ስለዚህ መንግሥት እንዲህ ያለውን አመለካከት ከቀየሩና ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች ሁሉ የኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እና በዚህ ዕሳቤ ከተሠራ ውጤት ይኖረዋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች