Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ምን ይዘን እንሻገር?

ዛሬም ጉዞ ለማድረግ የታክሲ ወረፋ ይዘናል። ለአዲስ ዓመት በዓል ሸመታ ከወጣው ጀምሮ፣ የዕለት ኑሮው እስከሚያጣድፈው ድረስ ታክሲ ጥበቃ ተሠልፈናል። በወዲያ በኩል ደግሞ አበዳሪና ባለዕዳ ተፋጠዋል። ‹‹የሦስት ቡና ሒሳብ አለብህ ታመጣ እንደሆነ አምጣ…›› ፔርሙዝ የያዘች ባለቡና ወያላው ላይ ታፈጣለች። ‹‹ታዲያ ብቻዬን ስሆን አትጠይቂኝም? ደንበኞቼ ፊት የምታፋጥጪኝ ማንን ለማሳነስ ነው? ግቡ ግቡ ቆነጃጅት አትስሟት ያማታል…›› ይላል ወያላው ሽቅርቅር፣ ብርቅርቅ ላሉ ሦስት ቀዘባዎች እየተነጠፈ። ‹‹ኧረ ግባ ሞልቷል። ደግሞ አንተን ብሎ ቁንጅና ለኪ?›› ትላለች ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመች ሃምሳ የተጠጋች የምትመስል ወይዘሮ። ‹‹ምነው እማማ? እኛ እኮ ልጆች ነን በጊዜያችን እንጫወትበታ፡፡ ውብ የሆኑት ደግሞ የእርስዎ ልጆች ስለሆኑ ነው…›› ወያላው ወይዘሮዋን ለማበሳጨት ሽሙጥ ጀመረ። የነገር ያለህ!

‹‹አንተ እንዴት ተናግረህ ልብህ ወልቋል? ደግሞ እኔን ነው እማማ? ቁንጅናን ለእኛ ተወው። አፍ አስከፍተን ሳናስከድን ነበር ቀጭ ቋ ያልንባት አዲስ አበባን። እንደ አሁኑ መንገዱ ሁሉ ጉድጓድ አልነበረም። ገደል ለገደል እንደ ዝንጀሮ እየዘለላችሁ በምትጓዙበት የእንቅፋት ጫካ ደግሞ ጊዜ ምናምን ትላለህ? አታውቀንማ… አላየኸንማ…›› ወይዘሮዋ ነገር ከያዘች የምትለቅ አትመስልም። ወያላው፣ ‹‹በገዛ እጄ…›› እያለ እጁን ፀጉሩ ላይ ጥዶ ራቀ። ቀጥላለች ወይዘሮዋ፣ ‹‹ቁንጅና ውስጥ ነው ያለው። መጀመርያ ከውስጥ ነው የሚጀምረው። ውስጥ ሰላም ሲሆን አዕምሮ ከራሱ ጋር ሳይጣላ ውሎ ሲያድር ያን ጊዜ ገላ ቢለበስበት፣ ቢቀባባ ነውር የለውም። የዛሬ ልጆች ግን አብዛኞቻችሁ ከራሳችሁ ተጣልታችሁ፣ ለራሳችሁ ሳትሆኑ፣ በራሳችሁ እየፈረዳችሁ፣ መንፈሳችሁ ሞቶ፣ ከላይ ከላይ ማማር ትወዳላችሁ። በዚያ ላይ ደግሞ አስከሬን ማስዋብ ብቻ፡፡ ሰው ከሞተ ወዲያ ሳጥኑ በወርቅ ቢንቆጠቆጥ ምን ይፈይዳል?›› ስትል ከኋላ ወንበር የያዙት ሦስቱ ዘናጮች ከጣራ በላይ አሽካኩ። የመንገዱ ፀባይ ነዋ!

ጉዟችን ተጀምሯል። አሁን ቀልባችን ሦስተኛው ረድፍ ላይ ወደ ተሰየሙት ወጣቶች ሸፍቷል። ‹‹ተረረም… ተረረም… ኧረ እንዲያው ተረረም… የተዘፈነው ለአንቺ ነው አይደል?›› ይላታል ልዕልት መሳይዋን ወጣት በቀኟ የተሰየመው። ‹‹ሰምቼው አላውቅም…›› ትለዋለች ኮስተር ብላ። ‹‹እንዴ እሱን ካልሰማሽማ ጆሮሽን እስካሁን ተጠቅመሽበት አታውቂም ማለት ነው። ‹አንቺ ልጅ አንቺ ልጅ የቬነስ እመቤት፣ በምድር የማትገኝ አንቺ ነሽ በእኔ ቤት…›  ብሎ በዜማ አንጎራጉሮ ሲያበቃ አፍጥጦ ያያታል። ‹‹አሁን በአንተ ቤት ተላክፈህ ሞተሃል፡፡ በዚህ ድምፅህ ለምን አይዶል ላይ አትወዳደርበትም?›› መሽኮርመም ጀምራለች። ‹‹ለውድድር የሚጋብዘኝ ሳጣ ምን ላድርግ ብለሽ ነው?›› ሲላት አንዱ ከአጠገቤ፣ ‹‹ምን ዓይነቱ ‹ፋራ› ነው? ገና ከአሁኑ ዕድል የለኝም ብሎ ይጀምራል እንዴ? አትሰማውም በቃ ከዚህ በኋላ…›› ይላል ተንሿኮ። ይኼን የማይሰማው ‹ጀንጃኝ› ነኝ ባይ መተርተሩን ቀጥሏል፣ ‹‹እኔ ምልሽ? ለምን እኔና አንቺ አንደራጅም?›› ይላታል። ‹‹እንዴ ምን ለመሆን?” ትጠይቃለች በግንባሯ ፀዳል ዓይን የምታባርረው ቆንጆ። ‹‹ዋናው እኔና አንቺ እንደራጅ እንጂ የምንሆነው አናጣም። ከዚያ ዕድላችንን መሞከር ነው። ከሆነልን ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ እንሠራለን። ካልሆነልን ትውልድ እንተካለን…›› ሲላት ከት ብላ ሳቀች። ጨዋታው ደራ ማለት አሁን ነው!

መሀል ወንበር ያሉት አዛውንት ሊናደዱ ፈልገው ሳይናደዱ፣ ሊቆጡ ፈልገው የሚከተለውን መገመት ከብዷቸው፣ ‹‹ሆ… ሆ…›› አሉ በረዥሙ። ልጅት ለአመል ያሳየችውን ግንባር መከስከስ ትታ፣ ‹‹ቆይ አንተ እንዴት እስካሁን ተደራጅቶ ዕድል መሞከር ትዝ ሳይልህ ኖሮ ኖሮ… አሁን አሰብከው?›› ስትለው፣ ‹‹ምን ላድርግ አንቺን የመሰሉ ወርቀ ዘቦዎች ታክሲ መጠቀም አቆሙዋ…›› ብሎ እጇን ይዞ ከአንገት በላይ ሳቀ። ጊዜና ታክሲ ከአንገት በላይ አነጋግሮ ይኼው እንዲህ ከአንገት በላይ ያሳስቃል። ደግሞ ትንሽ እንደ ተጓዝን ዓይኑን በጨው ባጠበው ወጣት ጋባዥነት ሻይ ልትጠጣ ያቺ የፀዳል ክንፍ አብራው ወረደች። ገና ከመውረዳቸው አጀብ ባዩ በዛ። ‹‹ወይ ዘንድሮ? እንዲህ ስፈራ ስባባ ቆሜ ልቅር? ምን አለ አምላኬ ወይ ድፍረት ብትሰጠኝ? ወይ ወደ ጭልፊትነት በሆነ ምትኃት ብትለውጠኝ?›› አለ ከመጨረሻ ወንበር አንዱ። ‹‹ሆኖ መገኘት እንጂ መለዋወጥ መቼ ከበደን ዘንድሮ? በተቀመጡበት መገኘት አልችል ብለን አይደል እንዴ ባስቀመጥነው ሥፍራ የምናጣው ነገር የበዛው…›› ሲል ጋቢና የተሰየመ፣ ‹‹እንዴ ቆይ… ቆይ… የተጨባበጠ ሁሉ ይጣመራል ያለህ ማነው?›› አሉ አዛውንቱ። ‹‹ኧረ ተውኝ አባት። ብቻ አንዴ ላግባና ከዚያ የመጣው ይምጣ…›› ይላል ያ ብቸኝነት የሰለቸው። ምን ያድርግ ታዲያ!

‹‹እንዴት ያለ ጊዜ ነው እናንተ? እናንተ ልጆች ምንድነው የሆናችሁት? ፍቺ ይኼን ያህል ቅልል ያለባችሁ ምን ነክቷችሁ ነው? የገነቡትን መናድስ፣ የደከሙበትን ማፍረስ እንዲህ ከጥፍራችሁ ቆሻሻ አልቆጥር ብላችሁ የከፋችሁትስ ምን ቢለክፋችሁ ነው?›› ብለው እየተገረሙ አዛውንቱ አፋቸውን ሲይዙ ወጣቱ ብቻውን ያወራል። ‹‹በነገራችን ላይ ሰሞኑን ያም እየደወለ፣ ያም እየጠራኝ የሚለኝ ተፋታሁ ሆኗል። አይገርምህም?›› የሚለኝ ያ ዝም የማያውቅ ከጎኔ የተሰየመ ወጣት ነው። ይኼኔ፣ ‹‹አቁምለት…›› ብሎ ድንገት ወያላው ታክሲዋን አስቆማትና አንድ ጎልማሳ ገባ። ‹‹ሳበው…›› ከማለቱ ወያላው ጎልማሳው፣ ‹‹ይኼው ስበን፣ ስበን፣ በጥሰን አረፍነው። ከዚህ በላይ ምኑ ይሳባል?›› እያለ ነገር ቀላቅሎ ጨዋታውን አቆረፈደው። ለነገሩ ምን ያልቆረፈደ ጨዋታ አለ? ተሳፋሪ ይወርዳል፣ ተሳፋሪ ይጫናል። ወያላው በወረዱት ፋንታ ታክሲዋን ለመሙላት ይጣራል። ሲገኝም ትርፍ ይደርባል። ‹‹ይቅርታ እዚህ ጋ ጠጋ ትሉላት…›› መሀል መቀመጫ ያሉትን ያስቸግራል። ‹‹ደርብብን ኧረ… ‹ላለው ይጨመርለታል› አይደል የሚባለው…›› አለው ጎልማሳው። የምትደረበዋ ልጅ ቀበል አድርጋ፣ ‹‹ታዲያስ እንዲህ ታክሲ ወንበር ላይ ካልተለማመድነው ነገ ከነገ ወዲያ አብረን እየኖርን መዝለቃችን ይሰምርልናል?›› ብላ ፈገግ አሰኘችን። ‹‹ጨዋታ ትችያለሽ ማለት ነው፣ ለእንዳንቺ ዓይነቷስ እንኳን መጠጋት ብነሳም አይቆጨኝ…›› አለ ጎልማሳው። ‹‹አመሠግናለሁ…›› ከማለቷ ጎልማሳው ወዲያው ቀጠል አድርጎ፣ ‹‹አሉ እንጂ ወይ ጨዋታ አያውቁ፣ ወይ ጨዋታ አይወዱ፣ በሕዝብ ወንበር የባለ ንብረትነት ስሜት የሚሰማቸው። አጋጥመውሽ አያውቁም?›› አላት። ድንገቴ በሉት!

ጉዞ ሊገባደድ ነው፡፡ ‹‹ፍርድ እንደ ራስ ነው። የአንዳንዱ ሰው የታክሲ ውስጥ አቀማመጥ ካሳለፈው ኑሮና ካሳለፈው አድካሚ ሕይወት ጋር ሲገጣጠም ታዝቤያለሁ…›› አለችው። ‹‹እሱስ ልክ ነሽ። እኛም የሰውን አቀማመጥ ከአመጣጡ ጋር አገናዝበን መቀበል አበዛን መሰለኝ፣ በሰላም ተሳፍሮ በሰላም እንዳይወርድ፣ በሽብር ተሳፍሮ በነውጥ መውረድ የሚመኘውን እናበረታታለን…›› ሲል ጎልማሳው ግራ ገብቶን መላው የታክሲ ተሳፋሪዎች እርስ በርስ ተያየን። ‹‹በቀኝ አሳይቶ በግራ ታጠፈ ማለትስ አሁን ነው…›› የምትለው አንዲት ጠይም ቆንጆ ናት። አዛውንቱ በበኩላቸው፣ ‹‹አላድለን ብሎ እንጂ እስኪ አሁን ስለወንበር ይኼን ያህል ዘመን መንገዋለል ነበረብን?››› ይላሉ። መንገዱ በተሽከርካሪዎች ተጨናንቋል። ሁሉም አሽከርካሪ ጥሩንባው ላይ ‹ለሽ› ብሎ የተጋደመ ይመስል መንገዱ በእሪታ ተሞልቷል። ‹‹አይለቁንም እንዴ? ነው መብራቱ ‘ስታክ’ አደረገ?›› ወያላው ሾፌሩን ያናግራል። ‹‹ምን ‘ስታክ’ ያላደረገ ነገር አለ?›› ይላል ዝምተኛው ሾፌራችን። ‹‹በቃ እዚህ ጋ እናውርዳቸዋ…›› ወያላው አንዴ ወደ እኛ አንዴ ወደ ሾፌሩ እያየ ለውሳኔ ቸኩሎ ይቁነጠነጣል። ‹‹እንዴ? እዚህ መንገድ መሀል ልታወርደን? ነውር አይደለም እንዴ?›› አዛውንቱ ተቆጡት። ‹‹ታዲያ አረጓዴው መብራት አልበራ አለ እኮ። በእግራችሁ ብታዘግሙ ለእናንተም ጤና ነው…›› ሲላቸው፣ ‹‹መሀል መንገድ ዘርግፈኸን ስለምን ዓይነት ጤና የምታወራው?›› ብሎ ከመጨረሻ ወንበር አንዱ ጮኸ። ንዴት!

‹‹እኔ ምን ላድርግ መብራቱ ነዋ፣ እንቢ ካላችሁ የሚያስገድዳችሁ የለም…›› ወያላው ማጉተምተም ሲጀምር ጎልማሳው፣ ‹‹እሱ ምን ያድርግ ብላችሁ ነው። የታየውን መፍትሔ ነው ያቀረበው። ይህንችስ ማን አየብን? መፍትሔ ማጣታችን ሳያንስ መፍትሔ ሲገኝም አላዳምጥ እያልን ችግር መደራረብ… በበኩሌ ታክቶኛል። እኔን አውርደኝ…›› ብሎ ወረደ፡፡ ቀስ በቀስ አንዱ አንዱን እያየ ዱብ ዱብ አለ። ቢያንስ ስድስት ሰዎች ያህል እንደ ወረዱ ትራፊክ ፖሊሱ መጥቶ ሥምሪቱን ያስተናብር ጀመር። መብራቱን አልፈን ጥቂት ተጉዘን ስናበቃ ታክሲያችን ጥጓን ያዘች። ወያላው፣ ‹‹መጨረሻ…›› ብሎ በሩን ከፈተው። ‹‹ከጨረስከውማ ቆይተህ ነበር…›› እያሉ አዛውንቱ ሲወርዱ በጨረፍታ እያየሁ ጆሮዬ የገባው፣ ‹‹መድረሳችን ላይቀር መሀል መንገድ የቀረው መብዛቱ…›› ያሉት ነው። ‹‹መልካም አዲስ ዓመት ይሁንላችሁ›› እየተባባልን ስንለያይ ከመድረሻችን ይልቅ፣ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ምን ይዘን ይሆን የምንሻገረው የሚለው የብዙዎቻችን ልብ ውስጥ የተሰነቀረ ሐሳብ ይመስል ነበረ፡፡ መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት