Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሆድና የሆድ ነገር (ክፍል አሥራ አራት)

ሆድና የሆድ ነገር (ክፍል አሥራ አራት)

ቀን:

በጀማል ሙሐመድ ኃይሌ (ዶ/ር)

‹‹እንጀራ በማየት አያጠግብም፡፡››

ስለእንጀራ የተነገረው አንዳንዱ አባባል አስገራሚ ነው፡፡ ሐበሾች ‹‹ለምን እንዲህ አሉ?›› ብለን ሰናስበው ደግሞ ይበልጥ ግርም ሊለን ይችላል፡፡ እስኪ ከላይ የተጠቀሰውን አባባል ልብ ብላችሁ እዩት፡፡ ነገሩ ይህ ከሆነ (እንጀራ በማየት የማያጠግብ ከሆነ)፣ በማየት የሚያጠግበው ምግብ የትኛው ነው? ዳቦ፣ ቂጣ፣ ጨጨብሳ፣ ገንፎ፣ ፓስታና ማካሮኒ…? ከቶ ለመሆኑ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ በሌላውም ዓለም ጭምር በመታየቱ ብቻ የሚያጠግብ ምግብ አለ ወይ?

ይህማ ቢሆን ኖሮ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕዝቦች በየቀኑ በር መጋዝ ከመገዝገዝ፣ በጠኔ ጥርስ ከመላመጥ ነፃ በወጡ ነበር፡፡ እንዴት ከተባለ፣ ምርጥ ምርጥ ምግቦች ከተበሰሉ በኋላ፣ በመስታዎት ውስጥ ወይም ያለምንም ግርዶሽ ይደረደሩና የምግብ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሠልፍ ይዘው በመቆም ምግቦቹን ለተወሰኑ ሰኮንዶች ወይም ለደቂቃ ያህል ትክ ብለው እያዩ እንዲያልፉ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ፣ የኢትዮጵያውያን የምግብ ዋስትና ከስንትና ስንት ዓመታት በፊት በተረጋገጠ – የለም-የለም፡፡ ሲጀመር የምግብ ዋስትና ችግር የሚባል ነገር በየትኛው በር ወደ ጎጇቸው መግባት ይችልና? (‹‹የምግብ ዋስትና›› የሚባል አገላለጽ ራሱ ባልትፈጠረ ነበር)፡፡

 በማየት ብቻ ሊያጠግብ የሚችል ምግብ በዓለማችን ላይ የሌለ ሆኖ እያለ፣ ታዲያ ሐበሾች ለምን ይሆን ‹‹እንጀራ በማየት አያጠግብም›› ማለታቸው? እንዴት ‹‹እንጀራ በማየት አያጠግብም›› ለማለት ቻሉ? አንዳንድ ሰዎች ከሰው ቤት ተጋብዘውም ሆነ ከቤታቸው፣ የተዘጋጀው ምግብ ከመሶቡ ወይም ከትሪው ላይ በብዛት ወይም በገፍ ቀርቦ ማየት አይፈልጉም፡፡ የተዘጋጀው ምግብ በዓይነትም፣ በመጠንም በዝቶ መቅረቡን ሲያዩ፣ ‹‹በዓይናችን አታጥግቡን›› ይላሉ፡፡ ወይም ገና ብዙም ሳይበሉ፣ ከዚህ በኋላ የመብላት ፍላጎት የሌላቸው መሆኑን የሚያመላክት ነገር ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ በጣም ዝግ ብለው ቆረስ፣ ጠቀስ፣ ጎረስ ማድረግ… ‹‹እንዴ ብላ’ንጂ›› ወይ ‹‹ብይ’ጂ›› ሲባሉ፣ ‹‹ዓይኔ ጠግቦ፣ አልበላኝ አለኮ›› የሚል መልስ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡

ከዚህ አንፃር፣ ‹‹እንጀራ በማየት አያጠግብም›› የሚለው አባባል ሊሠራ ይችላል፡፡ ማለትም ተዘጋጅቶ በብዛት የቀረበን ምግብ በማየት ዓይን የሚጠግብ ቢሆንም፣ ያ የቀረበው ምግብ እንጀራ ከሆነ ግን አቶ ዓይን ፍፁም ሊጠግብ አይችልም፡፡ ‹‹እንጀራን በተመለከተ ሊኖር የሚችለው ጥጋብ፣ እሱን በመብላት ብቻና ብቻ ነው፤›› ለማለት የተፈለገ ይመስላል፡፡ ከዚህ አንፃር የእንጀራን ደረጃ ከፍ ማድረጋቸው ይሆን?

‹‹ባይኔ ጠገብኩ›› የሚሉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ‹‹ዓይኑ ይሳሳል›› የሚባሉ ሰዎችም አሉ፡፡ (‹‹ዓይኔ ይሳሳል›› የሚል ሰው ግን የለም፡፡ ማን እጁን ይሰጣል?) እነዚህ የቀረበው ምግብ ከመሶቡ ካፍ እስከ ገደፍ የሞላም ይሁን፣ በጣም አነስተኛ ወደ ቀረበው ምግብ ሊሰነዘሩ የተዘጋጁ እጆችን ቁጥር በማሰብ ማለትም፣ ሊመገቡት ከቀረቡት ሰዎች ብዛት ጋር በማነፃፀር ‹‹ምግቡ ሊያንሰን ይችላል›› ወይም ‹‹ሳልጠግብ እቀራለሁ›› ብለው የሚሠጉ ናቸው፡፡ ይህ ሥጋታቸው ወይም ሥነ ልቦናዊ ግፊታቸው የሚገልጸው በአጎራረሳቸው ሊሆን ይችላል – የመቁረስ፣ የማጥቀስና የመጉረስ ዑደትን ከመደበኛው ፍጥነት በላይ ሲያስኬዱትና የሚያነሱት የጉርሻ ጥቅል እብጠቱ የጨመረ ሲሆን፡፡ አንዳንድ ጎራሾች፣ በእጃቸው ሰቅስቀው ያነሱትን ለመጉረስ ሲሞክሩና ከአፋቸው የመከፈት አቅም በላይ ሲሆንባቸው፣ ጉርሻውን ጠቅልሎ በያዘ እጃቸው ጣቶች አፋቸውን ከግራና ከቀኝ በኩል ወደ ውጭ ፈልቀቅ አድርገው እስከመጉረስና በሁለት ‹‹ጉንጫቸው›› (በአራቱም መንጋጋቸው) እስከማላመጥም ጭምር ይደርሳሉ፡፡ አይ የሆድ ነገር! (በሁለት ጉንጫቸው የሚያመነዥጉ ጫት ቃሚዎችም አሉ፡፡ አይ የሱስ ነገር!)

ዓይን የመሳሳቱ ነገር በሕፃናት ላይ ከተከሰተስ? መጀመርያ ነገር ብዙ ጊዜ ይከሰታል፡፡ ሁለተኛ ነገር መገለጫው በጣም ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ አፋቸውን ሞልተው ከመብላትም፣ ምግቡን ወደ ፊታቸው ከመሰብሰብም አልፈው ተርፈው ሊናጠቁና ሊጣሉ ይችላሉ፡፡ አይ የልጅ ነገር! (እዚህ ላይ መባል ያለበት አይ የሆድ ነገር አይደለም)፡፡  

‹‹ዓይን አዋጅ› የሚባልም ነገር አለ፡፡ አባባሉ በዛ ብሎ ከቀረበ ነገር ውስጥ መምረጥ ወይም መርጦ ለማንሳት ወይም ለመውሰድ መቸገርን የሚያመላክት ሲሆን፣ ከምግብ አንፃር ያለውን ቦታ ብናየው አይከፋም፡፡ የምግብ ዓይነት መሶቡን ሞልቶ ሲቀርብ፣ ‹‹ዓይኔ ጠገበ›› የሚሉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ዓይን አዋጅ የሚሆንባቸው ሰዎችም አሉ – በተለይ የብፌ ምግብ ሲሆን፡፡ የብፌ ምግብ ካለበት ድግስ ወይም ግብዣ ላይ የተገኘ አንድ ሰው፣ መጀመርያ ላይ ‹‹የቱን አንስቼ የቱን ልተወው›› የሚል ስሜት ሊዘይረው ይችላል፡፡ መጨረሻው ግን ከዚህም፣ ከዚያም፣ ከዚያም፣ ከዚህም ምናልባትም ከሁሉም ወይም ከአብዛኛው ዓይነት በማንሳት የምግብ ሰህኑን በጭንቀት መግደል ይሆናል፡፡ አንዳንዴ በተለይም ብፌው ላይ የቀረበው አማራጭ ብዛት ያለው ከሆነ፣ አቶ ተጋባዥ ከተወሰነው ዓይነት ሳያነሳ ሳህኗ ጢም ትልበታለች… አንዳንዴ በሳህኗ ማነስ የሚናደድ የመኖሩን ያህል፣ ቆልሎ ያመጣውን ሳይጨርስ የሚተውም ሰው አለ – ሆዱ በመሙላቱ፡፡ እንዲያ ነው የሆድ ነገር!

ስለእንጀራ ወደተነገሩ አስገራሚ አባባሎች እንመለስ፡-

‹‹እንጀራን ምን ይጨርሰዋል መጉረስ››፡፡ ወይም አባባሉ በምልልስ ሊቀርብ ይችላል – እንዲህ በማለት፡-

‹‹’እንጀራን ምን ይጨርሰዋል?’ ቢሉት ‘መጉረስ!’›› አለ፡፡

እዚህም ላይ ከፍ ሲል ያነሳነውን ዓይነት ጥያቄ ማንሳት ግድ ይለናል፡፡ ከቶ ለመሆኑ መጉረስ የማይጨርሰው ምግብ አለ’ንዴ? ዳቦ ነው ወይስ ቂጣ? ገንፎ ነው ወይስ ጨጨብሳ? ፓስታ፣ ማካሮኒ ነው ወይስ ሩዝ? የትኛው ወይስ የትኞቹ ናቸው መጉረስን የሚመክቱና ሊጨርሳቸው የማይችሉት? ፓስታ፣ መኮረኒና ሩዝ በእጅ በሹካና ማንኪያ ሊበሉ ይችላሉ፡፡ ለውጡ የእጅ ጣቶች በሹካ ጣቶችና በማንኪያ መተካታቸው ነው፡፡ አፍላ ላይ ሲደርስ ሁሉም መጉረስ ነው፡፡

 በሌላ በኩል መጉረስ የማይጨርሰው ምግብ ቢኖር ኖሮ፣ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ባልተራብን ነበር – ቢያንስ የእንጀራ እህል (ጤፍ፣ ማሽላና ገብስ)  እጥረት ሲያጋጥመን፣ ያንን መጉረስ የማይጨርሰውን ምግብ እየበላን የምርት እጥረት ጊዜን፣ በረሃብ ሳይሆን በጥጋብ እናሳልፍ ነበር፡፡ (ለነገሩ ምርታችን ከዝናብ መኖር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለው እነዚያም ከእንጀራ ውጭ ያሉትና መጉረስ የማይጨርሳቸው ምግቦች የት ይገኛሉ?)  

ዋናው ጥያቄ፣ ማንኛውም ምግብ ሊያልቅ የሚችለው በመበላቱ (እየተጎረሰ በመበላቱ) ሆኖ እያለ፣ ሐበሾች እንጀራን መጉረስ እንደሚጨርሰው መናገር ለምን አስፈለጋቸው? ደግሞ’ኮ ‹‹እንጀራን ምን ይጨርሰዋል መጉረስ›› የሚሉን፣ ‹‹እንጀራ በማየት አያጠግብም›› ባለን አፋቸው ነው፡፡ ‹‹እንጀራ በማየት አያጠግብም›› በማለት፣ መጥገብ ከፈልግን ልንበላው ወይም ልንጎራርሰው እንደሚገባ ካበሰሩን በኋላ፣ ይሄው መብላታችን ወይም መጎራረሳችን የሚጨርሰው ወይም የሚፈጀው መሆኑን እያረዱን ነው፡፡ ነገሩ፣ ‹‹ላም እሳት ወለደች፡፡ እንዳትልሰው እሳት ሆነባት እንዳትተወው ልጅ ሆነባት›› ዓይነት ሆነ እኮ!

ሁለቱን አባባሎች ለማስታረቅ ስንሞክር፡- ‹‹እንጀራን ምን ይጨርሰዋል፡፡ መጉረስ›› በሚለው አነጋገር ማስተጋባት የተፈለገው መልዕክት፣ የቁጠባን አስፈላጊነት ማሳየት ይመስላል፡፡ እንጀራ በማየት ስለማያጠግብ፣ ለመጥገብ እንጀራውን መብላት አስፈላጊ የሆነውን ያህል፣ ሲበሉ ግን በየቀኑ እንብርት እስከሚገለበጥ መብላት ሳይሆን፣ ልክን ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን ‹‹እንጀራን ምን ይጨርሰዋል፡፡ መጉረስ፤›› የሚለው ብሂል ይመክራል፡፡ ባጭሩ፣ እንጀራ በማየት ስለማያጠግብ፣ ለመጥገብ የሚበላ ሰው፣ ‹‹ነገም ሆድ አለ›› የሚለውን ተረትና ምሳሌያዊ ምክር ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ‹‹ለምን?›› ቢሉ፣ እንጀራን የሚጨርሰው መጉረስ ነዋ! 

ስለእንጀራ ከተነገሩ አስገራሚ ተረትና ምሳሌዎች አንድ እንጨምር – ባለፈው ዕትም የጠቀስነው ‹‹አንድ እንጀራ የጣለውን፣ አምስት እንጀራ አያነሳውም›› የሚለውን ‹‹ጉደኛ›› አነጋገር፡፡ (በነገራችን ላይ አባባሉ ‹‹አምስት እንጀራ አያነሳውም›› ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹አሥር እንጀራ አያነሳውም›› ተብሎም ይነገራል፡፡ እናም በዚህ በሁለተኛው አባባል ላይ መሠረት አድርገን ነው የምንነጋገረው)፡፡

ይህ ተረትና ምሳሌ ሁለት፣ ሦስት ወይም አራት ቀናት እንጀራ ሳይበላ ስለቀረ ሰው አይደለም እየነገረን ያለው፡፡ ቁርስ ወይ ምሳ ወይ እራት ባለመብላቱ፣ ስለወደቀ (ጉዳት ስለደረሰበት) ሰው ነው እየነገረን ያለው – ሳይበላ የቀረውና የጣለው አንድ እንጀራ ነውና፡፡ በሌላ በኩል በዚያው እንጀራ ባልበላበት ወቅት (ምሳ፣ ቁርስ ወይም ራት)፣ በእንጀራው ምትክ ሌላ ምንም ዓይነት ምግብ (ለምሳሌ ቆሎ፣ ንፍሮና በሶ…) ሳይበላ ስለመቅረቱ አባባሉ የሚነግረን ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ሰውዬው ሌላ ምግብ በልቶም ሊሆን ይችላል፡፡

ሆኖም አመክኗዊ ክርክራችን ደንደን ብሎ ይበልጥ ጉልበት እንዲያገኝ፣ ሰውዬው ‹‹ምንም ነገር አልበላም›› ብለን እንውሰድ፡፡ ትልቁ ጥያቄ፣ እንዴት ሆኖ ነው፣ አንድ እንጀራ ስለጣለው አሥር እንጀራዎች ‹‹እሱን ማንሳት የሚሳናቸው?›› የሚለው ነው፡፡ ኧረ እንዴት ሆኖ ነው፣ ቁርሱን አንድ እንጀራ ሳይበላ የቀረን ሰው፣ አሥር እንጀራዎችን ከዚያ በኋላ ባሉት ተከታታይ አሥር የምግብ ወቅቶች (ምሳውን፣ ራቱንና ቁርሱን… ለሦስት ተከታታይ ቀናት) ሲበላ፣ መነሳት የማይችለው ማለትም ብርታትና ጥንካሬው ወደ ነበረበት የማይመለሰው?

‹‹…አሥር እንጀራ አያነሳውም›› ሲባል፣ መቼም አሥሩም እንጀራዎች አንዴ ቀርበውለት ‹‹ጨርግዶ-ጨርግዶ ቢተዋቸው›› ለማለት አይደለም – ይህ ሊሆን የሚቻል አይደለምና፡፡ ወይስ ደግሞ ሦስቱን (ወይም መቅሰስን የሚጨመር ከሆነ አራቱን) የምግብ ወቅቶች ሳይጠብቅ፣ በቀን ወይም በሁለት ቀናት ውስጥ በተለያየ ሰዓት አሥሩን እንጀራዎች አከታትሎ ቢበላ ለማለት ይሆን? እንዴት ሊሆን ይችላል? (ነው ወይስ እንጀራ በሐኪም የታዘዘ መድኃኒት ሆነና አረፈው?) 

አባባሉ ‹‹አሥር እንጀራ የጣለውን፣ መቶ እንጀራ አያነሳውም›› ቢሆንልን ኖሮ (በምን ዕድላችን?)፣ ይህን ያክል ከዚህ አባባል ጋር ‹‹ባልተነታረክን›› ነበር፡፡ አባባሉ እንዲህ ቢሆንልንማ ኖሮ፣ ሰውዬው በቀን ሦስት ጊዜ የሚመገብ ቢሆን፣ አሥር እንጀራ ሲጥለው (ማለት አሥር እንጀራ ሳይበላ ሲቀር)፣ ከሦስት ቀን በላይ ተርቧል ማለት ነው፡፡ በቀን ሁለት ጊዜ የሚመገብ ከሆነ ደግሞ፣ አምስት ቀናት ሙሉ ተርቧል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ መቶ እንጀራ ቢሰጠው፣ በቀን ሦስት ጊዜ እየበላ ለአንድ ወር ከሦስት ቀናት ወይም በቀን ሁለት ጊዜ እየበላ ለአንድ ወር ከሃያ ቀናት አካባቢ ይቆያል… በጣም አሳማኝ! አባባሉ እንዲያ ቢሆንልን ኖር፣ በዚሁ ተገላገልን ነበር ግን አልሆነም… 

የአባባሉ (‹‹አንድ እንጀራ የጣለውን፣ አሥር እንጀራ አያነሳውም›› የሚለው) መልዕክት ሲጠቃለል፣ ‹‹አንድ ሰው ለሦስትና ከዚያ በላይ ቀናት ይቅርና ለአንድም ቀን በእንጀራ ዕጦት ረሃብ ከደረሰበት የረሃብ ዱላ ምቱ አደገኛ በመሆኑ፣ ለሦስት ቀናትና ከዚያም በላይ እንጀራን ቢመገብም ወደ መጀመርያ ጥንካሬውና ጤንነቱ መመለስ አይችልም፤›› የሚል ዓይነት ነው፡፡ ይህ ተረትና ምሳሌ በራሱ ከግነትም አልፎ ከኩሸት የደረሰ ነው፡፡ የኳሸ ቢኳሽም እንጀራ በሐበሾች ባህል መደነቅ፣ መሞገስና መሞካሸት ያለበት ምግብ ነውና ‹‹መርሀባ›› ብለን በአዕምሯችን ደጅ ጎምለል-ጎምለል የሚለውን አመክኒዮ በእምቢተኛ ትከሻችን ገፋ አድርገን ለመቀበል እንችል ነበር፡፡ ግን ነገሩ መች እንደዚያ ሆነ? አባባሉ ሳንካ የበዛበት ነው፡፡   

አንደኛ ነገር፡- ይህ አገላለጽ (‹‹አንድ እንጀራ የጣለውን፣ አሥር እንጀራ አያነሳውም››) የሚለው በቀጥታ የሚናገረው ችግሩን እንጂ መፍትሔውን አይደለም፡፡ ‹‹አንድ እንጀራ የጣለውን›› ሰው ስንት እንጀራ ‹‹እንደሚያነሳው›› አይነግረንም፡፡ ባጋጣሚ አንድ እንጀራ የጣለው ሰው ቢኖር፣ ይህን ሰው በስንት እንጀራ ማንሳት እንደሚቻል የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ድህነት እንደ ዋርካ ዛፍ በተንሰራፋበት አገር፣ አንድ ብቻ ሳይሆን ሁለትም፣ ሦስትም፣ አራትም… እንጀራ የሚጥላቸው ሰዎች በሽበሽ ናቸው፡፡ እናም ጥያቄው ‹‹እንዴት ይነሱ?›› ነው፡፡

በሌላ አነጋገር እስከ ኩሸት በደረሰ መንገድ የተነገረው የዚህ ብሂል መሠረታዊ ጭብት ወይም መልዕክት፣ እንጀራን ያለማቋረጥ/ያለማሰለስ መብላት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግድ መሆኑን ጭምር መንገር እንጂ፣ ሳይበላ በመቅረቱ ‹‹እንጀራ የጣለውን›› እንዴት ማንሳት እንደሚቻል የሚጠቁመው ነገር የለም፡፡ የአባባሉ ባለቤቶች ሰውን እንጀራ እንዳይጥለው ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በማሰብና በመጨነቅ ምክራቸውን ያለ ስስት የለገሱ ቢሆንም፣ ምክራቸው የሚጠቅመው ግን ሁሉም ነገር በእጁና በደጁ ላለው ሰው ብቻ ነው፡፡ ምሳ ቢበላ፣ ራት፣ ራት ቢበላ ቁርስ ለማይደግመው የአገሬ ደሃ ሕዝብ የሚሆን ምክር አይደለም፡፡ ምናልባት ሀብታሞች ወይም ኑሯቸውን በቅጡ ያሸነፉ ሰዎች ‹‹መቼም ሞልቶኛል›› ብለው በመዘናጋት ከእንጀራ ውጭ ሌላ እንዳይመገቡና የእንጀራ ፍቅራቸው እንዳይቀንስ ከሆነ፣ ‹‹ሊያስማማን›› ይችላል… 

ሁለተኛ ነገር፡- አባባሉ አቅም የሌላቸው ሰዎች ሆድን ለመሙላት ከእንጀራ ውጭ ያሉ አማራጮችን እንዳያስቡና ለረሃብ አዋጭ የመፍትሔ መንገዶች አድርገው እንዳይዙ ሥነ ልቦናዊ ጫና ይፈጥራል፡፡ ተመጋቢዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ አምራች ገበሬዎችም የተፅዕኖው ሰለባ ከመሆን አይተርፉም፡፡ ለእንጀራ በሚሆን ምርት ላይ አብዛኛውን ወይም ሁሉንም ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ይፈጃሉ፡፡ እናም ሰዎች በማንኛውም አጋጣሚ የተመጣጠነ ምግብ ሊያገኙ የሚችሉበትን ዕድል የሚዘጋ በመሆኑ፣ የራሱ የሆነ ጉዳትና አደጋ ያለው ነው፡፡

ሦስተኛ ነገር አቅሙ ያላቸው ሐበሾች የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን አፈራርቀው ከመመገብ ይልቅ፣ የምግብ ምርጫቸውን አጥብበው እንዲኖሩ በፅናት የሚገፋፋ ነው፡፡ (ደግሞም ተሳክቶለታል፡፡ ሌላን ዓይነት ምግብ ጨጓራው ‹‹በቃኝ›› እስከሚል ድረስ ግጥም አድርጎ በልቶ፣ ‹‹እንጀራ ካልበላሁ፣ የበላሁ አይመስልኝም›› ማለትን ምን አመጣው?)

አርሶ አደሮች ወተት አልበው ቅቤ እየሸጡ፣ ንብ አንብተው ማር እየሸጡ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አልምተው አላባውን አየሸጡ፣ ዶሮ አርብተው እንቁላልና ዶሮ እየሸጡ… ምግባቸውን (እንጀራቸውን) በአብዛኛው የሚበሉት ግን ወይ በሽሮ ወይ በክክ ወጥ ብቻ ነው፡፡ እናም ልጆቻቸው የመቀጨጭና የመቀንጨር ሰለባ የሆኑባቸው የአርሶ አደር ቤተሰቦች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

አቅሙም፣ አማራጩም እያላቸው በተመጣጠነ ምግብ ዕጦት የተነሳ እጅግ በርካታ የገጠር ሰዎች ለመቀጨጭና እልፍ ሲልም ለመቀንጨር እየተዳረጉ ባለባት አገር፣ የዚህን ዓይነት አባባሎች ዳፋቸው ቀላል አይደለም (በክፍል አሥራ አምስት እንገናኝ – ኢንሻ አሏህ!)፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  jemalmohammed99@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...