Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስደተኞችንና ተፈናቃዮችን ለመታደግ የቆመው ተራድዖ

በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከሰተው ግጭት በርካታ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፣ ንብረታቸውም ወድሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ልጆቻቸውም ከሜዳ ቀርተዋል፡፡ እነዚህንም የማኅበረሰብ ክፍሎች የምግብ፣ የመጠጥ፣ የአልባሳት፣ እንዲሁም የጤና እክል ገጥሟቸው ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ሆነዋል፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች የችግሩ ሰለባ ሆነው የማቀቁ ወገኖች በርካቶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን ወገኖች ለመደገፍ መንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋሞች እየሠሩ ቢሆንም፣ ችግሩ ግን አሁንም አልተፈታም፡፡ አክሽን ፎር ዘ ኒዲ ኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች የችግሩ ገፈት ቀማሽ ለሆኑ ሰዎች ድጋፍ በመስጠት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ አቶ ሳሊህ ሡልጣን የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የድርጅቱን ሥራ አስመልክቶ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹አክሽን ፎር ዘ ኒዲ ኢን ኢትዮጵያ›› መቼ ተመሠረተ?

አቶ ሳሊህ፡- አክሽን ፎር ዘ ኒዲ ኢን ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2012 ሊቋቋም ችሏል፡፡ ተቋሙም ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች፣ እንዲሁም ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች በርካታ ድጋፎችን ሲያደረግ ቆይቷል፡፡ አሁንም እያደረገ ይገኛል፡፡ ተቋሙም ገና ሥራውን ሲጀምር በኬንያ ቦረና በካምፕ ተጠልለው ለሚገኙ ስደተኞች ድጋፍ በማድረግ ነው፡፡ በተለይም በውኃ በግልና በአካባቢ ንፅህና እንዲሁም በመጠለያ ላይ ተደራሽ በመሆን ሰፊ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋሙ ምን ዓይነት አገልግሎቶችን ይሰጣል?

አቶ ሳሊህ፡- ተቋሙ ለመጀመርያ ጊዜ ሥራውን ሲጀምር የኬንያ ቦረና ላይ ለሚገኙ ስደተኞች ድጋፍ በማድረግ ነው፡፡ በዚህ ቦታ ለሚገኙ ወገኖች የጤና፣ የምግብና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተቋሙ ድጋፉን በማስፋት በጋምቤላ ክልል የኦፕሬሽን ሥራ ማከናወን ችሏል፡፡ በጋምቤላ  ዋሽ፣ ሼልተር፣ እንዲሁም የመሠረተ ልማት ላይ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ትልቁን ሚና ሊጫወት የቻለ ተቋም ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ በርካታ የስደተኛ ቁጥር ያለው በጋምቤላ ክልል በመሆኑ፣ እነዚህን ድጋፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት በክልሉ  ከ300 ሺሕ በላይ ስደተኞች በመጠለያ ካምፕ ውስጥ አሉ፡፡ እነዚህንም ስደተኞች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ ተቋሙ የበኩሉን መወጣት ችሏል፡፡ ተቋሙም ይህንን መሠረት በማድረግ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ሶማሌ ጅግጅጋና በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረት ተቋሙ እንቅስቃሴውን ሰፋ አድርጎ በውኃ አቅርቦት፣ በጤና በትምህርትና በሌሎች የመሠረተ ልማቶች ከፍተኛ  ወጪ በማውጣት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋሙ በዓመታት ጉዞው በሥራቸው ላይ ምን ዓይነት ችግር ገጥሞታል?

አቶ ሳሊህ፡- ተቋሙ ከተቋቋመ አሥራ ሁለት ዓመታትን አስቆጥራል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ይህንን ያህል የተጋነነ ችግር ገጥሞናል ማለት ትንሽ ይቸግራል፡፡ ተቋሙም ትልቁንና ዋነኛ የሚባለውን 87 በመቶ የሚሆነውን ድጋፍ የሚያገኘው ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር በኩል መሆኑ ችግር እንዳያጋጥመን አድርጎናል፡፡ ይሁን እንጂ በመተከል፣ በመተማ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አዳዲስ የሱዳን ስደተኞች በመኖራቸው፣ የተጣጣመ ድጋፍ ለማድረግ ተቸግረናል፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋሙ መሠረት አድርጎ የሚሠራው ተፈናቃዮች ላይ እንደመሆኑ ምን ዓይነት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል?

አቶ ሳሊህ፡- ተቋሙ በዚህ ችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች ሁለት ዓይነት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ አንደኛ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ሲወጡ የጤና፣ የመጠለያና የምግብ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ወደ ቀዬአቸው ሲመለሱ መልሶ የማቋቋም ሥራ ይሠራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወጥ በሆነ መንገድ በምግብም ሆነ በሌሎች ነገሮች ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት ከዚህ በፊት በኦሮሚያ ክልል፣ በቦረና እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወጥ የሆነ ሥራ መሥራት ችለናል፡፡ ሌላውና ዋነኛ ደግሞ ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ዋሽ፣ መጠለያና መልሶ ማቋቋም ላይ በቋሚነት የሚሠራ ይሆናል፡፡ ተቋሙ እስካሁን 4.8 ሚሊዮን ወገኖችን በተለያዩ ነገሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ችሏል፡፡ በቀጣይም ይህንን ታሳቢ በማድረግ ወጥ የሆነ ሥራ የምንሠራ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርብ ከኢጋድ ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት አድርጋችኋል፡፡ የስምምነቱ ትኩረት ምንድን ነው?

አቶ ሳሊህ፡- ተቋሙ በኢትዮጵያ ሞያሌ አካባቢ ላሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለያዩ የመሠረተ ልማቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከኢጋድ ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡ ከኢጋድ ጋር ለ34 ወራት አብሮ ለመሥራት የተስማማነው የሞያሌ ሶማሌና የሞያሌ ኦሮሚያ ማኅበረሰብን ተደራሽ የሚያደርግ ነው፡፡ ስምምነቱም የውኃ፣ የትምህርት፣ የመሠረተ ልማትና ሌሎች ሥራዎችን ተደራሽ ለመሆን ነው፡፡ እነዚህን ሁለቱን የድንበር አካባቢዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፣ ለዚህም ፕሮጀክት ከ230 ሚሊዮን በላይ ወጪ ፈሰስ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ይህም ፈንድ የጀርመን ኢኮኖሚ ዴቨሎፕመንት በተሰኘ ተቋም በኩል የተደረገ ድጋፍ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሌሎች ተቋሞች ጋር ቅንጅት ፈጥራችሁ እየሠራችሁ ይገኛል፡፡ በሥራችሁ ምን ዓይነት ለውጥ አምጥታችኋል?

አቶ ሳሊህ፡- አክሽን ፎር ዘ ኒዲ ኢን ኢትዮጵያ ከተለያዩ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በሰፊው እየሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የመንግሥት ተቋም ከሆኑት ጋር ቅንጅት ፈጥረን እየሠራን ነን፡፡ በተለይም ከጤና፣ ከትምህርት፣ ከውኃና ከሌሎች ተቋሞች ጋር ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ክልል ካሉ ተቋሞች ጋር ቅንጅት ፈጥረን እየሠራን ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከእነዚህም ጋር ስንሠራ በሥራችን ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ማምጣት ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

አቶ ሳሊህ፡- በቀጣይ በአገር አቀፍ ደረጃ የልማት ክፍተት ያለባቸው ቦታዎች ላይ ሄዶ ለመሥራት ዕቅድ ይዘናል፡፡ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በሌሎች ቦታዎች ለመሥራት ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ በእነዚህም ቦታዎች ስንሠራ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር ስለሚሆን ሥራችንን ያቀልልናል፡፡ ለአብነት ያህል ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ለመሥራት ዕቅድ ይዘናል፡፡ በተለይም የመሠረተ ልማት ክፍተት ያለባቸውን ቦታዎች ላይ ወጥ የሆነ ሥራ የምንሠራ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ በግጭት ውስጥ ለነበሩ አካባቢዎች ድጋፍ አድርጋችኋል?

አቶ ሳሊህ፡- ተቋሙም በዋናነት የሚሠራው በእነዚህ ዓይነት ችግር ለተጎዱ ወገኖች መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በፊትም በቦረና አካባቢ በተከሰተው ድርቅ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ተቋሙ ድጋፍ ማድረግ ችሏል፡፡ በሌሎች አካባቢዎችም እንዲህ ዓይነት ድጋፍን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ወደፊትም የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ለሶማሌ ስደተኞች ድጋፍ ማድረግ ችለናል፡፡ በአፋርም፣ በሶማሌ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ምግብ ነክ ነገሮችም ሆነ ሌሎች የመሠረተ ልማት ነገሮችን ድጋፍ በማድረግ ስደተኞችን መታደግ ችለናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...