Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየትግራይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያልተፈቀዱ ቁሶችን ሳይዙ ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚያካሂዱ አስታወቁ

የትግራይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያልተፈቀዱ ቁሶችን ሳይዙ ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚያካሂዱ አስታወቁ

ቀን:

  • ሰላማዊ የተቃውሞ ሠልፉን ሲቀሰቅሱ የነበሩ የፓርቲዎች አባላት መታሰራቸው ተገልጿል
  • ‹‹ወቅቱ የበዓል ወቅት በመሆኑ የፀጥታ ኃይል እጥረት አለብን››

የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት

በዳንኤል ንጉሤ

በዋናነት በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች በመቀሌ ከተማ ለጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም. የጠሩት ሰላማዊ ሠልፍ ላይ የተጣለውን ክልከላ ባለመቀበል፣ ደጋፊዎቻቸው የተከለከሉ ቁሶችን ሳይዙ በሠልፉ እንዲታደሙ ጥሪ ማድረጋቸውን አስታወቁ።

ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ፣ ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና)፣ ውድብ ናፅነት ትግራይ (ውናት)፣ እንዲሁም ሰላማዊ ሠልፉን ደግፈው አብረዋቸው የቆሙት አሲንባና አረና የተባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በመቀሌ ለማካሄድ የጠሩት ሠልፍ በከተማው አስተዳደር ክልከላ ቢደረግበትም፣ ፓርታዎቹ ግን ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው በማስታወቅ፣ ክልከላውን እንደማይቀበሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል። 

ሰላማዊ ሠልፉን በያዙት ዕቅድ መሠረት እንደሚያካሂዱ የገለጹ ሲሆን፣ በሠልፉ ላይ የሚገኙ ደጋፊዎቻቸውና አባሎቻቸው ምንም ዓይነት የጦር  መሣሪያና ስለት መሰል ነገሮችን ይዘው እንዳይወጡ በቂ ማስገንዘቢያ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

‹‹እኛ በመሣሪያ አናምንም፤›› በማለት ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት የባይቶና ከፍተኛ አመራር አቶ ክብሮም በርኸ፣ የተጠራውን ሠልፍ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማካሄድ የፓርቲያቸው አቋም እንደሆነ ተናግረዋል። ነገር ግን ሠልፉን ከጠሩት ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች ውጪ፣ በስም ካልጠቀሷቸው ሌሎች አካላት የሚገኙ ኃይሎች ሰላማዊ ሠልፉን እንዳያደናቅፉ ሥጋት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

ለሃምሳ ዓመታት የቆየ የአንድ ፓርቲ [ሕወሓት] የበላይነት፣ ጭቆናና ድህነትን በትግራይ ክልል እንዳንሰራፋ የተናገሩት አቶ ክብሮም፣ ይባስ ብሎ ከጦርነቱ በኋላ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከክልሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጣ ጊዜያዊ አስተዳደር ይመሠረታል ቢሉም፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አብዛኞቹ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተቀመጡት የሕወሓት አባላት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በትግራይ ክልል ሁሉን አቀፍ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሠረት የሚል አንቀጽ መያዙን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ ከግንዛቤ ያስገባ አቅጣጫ ቢሰጡም አለመተግበሩን የገለጹት አቶ ክብሮም፣ ይህ አካሄድ የግድ መለወጥ ስላለበት ሰላማዊ ሠልፉ መጠራቱን አስረድተዋል።

በክልሉ የተጠራውን ሰላማዊ ሠልፍ ከደገፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የአሲንባ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ዶሪ አስገዶም በበኩላቸው፣ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ለውጥ ማምጣት አልቻለም ብለዋል።

ለአብነትም በጦርነቱ ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የመድኃኒት፣ የምግብ፣ እንዲሁም መሠረታዊ የሕክምና ቁሳቁሶች ማቅረብ ባለመቻሉ ተጎጂዎች ከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

አቶ ዶሪ በማከል፣ ‹‹ጊዜያዊ አስተዳደሩ የትግራይን ሉዓላዊ መሬት አስከብሬ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው እመልሳለሁ ብሎ በተደጋጋሚ ቃል ቢገባም፣ እነዚህ ቦታዎች እስካሁን በተለያዩ የታጠቁ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ናቸው፡፡ ይባስ ብሎም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለተፈናቃዮች ሲመጣ የነበረው ዕርዳታ በዝርፊያ ምክንያት በመቋረጡ፣ ተረጂዎች በተለያዩ የተፈናቃይ ካምፖች ውስጥ በረሃብና በሞት እየተቀጠፋ ይገኛሉ፤›› ብለዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ዘራፊዎችን ለሕግ አቀርባለሁ ቢልም እስካሁን ያደረገው ነገር እንደሌለ በመግለጽ፣ ለተፈጠረው ችግር ሁሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ተጠያቂ አድርገዋል።

‹‹እነዚህና መሰል የክልሉን ነዋሪዎች ጥያቄዎች መሠረት በማድረግ ነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ለመቀሌ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በሮማናት አደባባይ ሰላማዊ ሠልፍ እንደምናካሂድ በደብዳቤ አሳውቀናል፤›› ያሉት ደግሞ አቶ ክብሮም ናቸው፡፡ በማግሥቱ ነሐሴ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ የተሰጣቸው ምላሽ ጊዜው የበዓል ወቅት በመሆኑና ከተማውም የፀጥታ አስከባሪ ኃይል እጥረት ስላለበት፣ የፀጥታ አካል መመደብ አንችልም የሚል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም  የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት በጋራ በጻፉት ደብዳቤ በሰጡት ምላሽ የትግራይ ሕዝብ በዓል ካከበረ ሦስት ዓመታት እንደሆኑት፣ ሕዝቡ የሚያስፈልገው በዓል ሳይሆን መሠረታዊ ለውጥ መሆኑን፣ ይህንን ሰላማዊ ሠልፍ የሚያስተጓጉል ማንኛውንም ምክንያት እንደማይቀበሉ፣ እንዲሁም የመቀሌ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ አስከባሪዎችን መመደብ ግዴታው እንደሆነ መግለጻቸውን አክለዋል፡፡

የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ማራማዊት ለጋስ ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ወቅቱ የበዓል ወቅት በመሆኑና የከተማ አስተዳጀሩ የፀጥታ ኃይል እጥረት ስላለበት ነው እንጂ ጥበቃ አናደርግም አላልንም፤›› ብለዋል። አክለውም ጽሕፈት ቤቱ ቀደም ሲል በደብዳቤ ከሰጠው ይፋዊ መግለጫ የተለየ አዲስ ውሳኔ ባለማሳለፉ፣ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ነገር ማለት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

በሰላማዊ ሠልፍ ወቅት የፀጥታ አካላት ባለመመደባቸው ችግሮች ቢፈጠሩ ኃላፊነቱን ማን እንደሚወስድ ወ/ሮ ማራማዊት ተጠይቀው፣ ‹‹መጀመሪያ ለቀረበው ጥያቄ መልስ ሰጥተናል፡፡ ከዚያ ውጪ ስለሚሆነው የማውቀው ነገር የለም፤›› ብለዋል።

ይኼው ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበላቸው ሠልፉን የጠሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው፣ ‹‹እነሱ የፀጥታ አካላት አለመሆናቸውን፣ ይህንን ሥራ ማከናወንና ኃላፊነት መውሰድ ያለበት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ነው ብለዋል።

ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ፣ ውድብ ናፅነት ትግራይ፣ ዓረና ለሉዓላዊነትና ለዴሞክራሲ፣ ዓሲምን የተባሉት አምስት የትግራይ ክልል ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጳጉሜን 2 እስከ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በጥምረት ለሚያካሂዱት ሰላማዊ ተቃውሞ ሠልፍ በመቀሌ ከተማ በመኪና በመዞር ሲቀሰቅሱ መታሰራቸው ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...