Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጠቅላይ ሚኒስትሩ የዩኒቨርሲቲ መምህራን የመኖሪያ ቤትን በሚመለከት ‹‹ጥሩ እንቅስቃሴ›› እንዳለ ተናገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዩኒቨርሲቲ መምህራን የመኖሪያ ቤትን በሚመለከት ‹‹ጥሩ እንቅስቃሴ›› እንዳለ ተናገሩ

ቀን:

የዩኒቨርሲቲ መምህራንን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ በጥሩ ሁኔታ እየተሠራ መሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ሥራ አስፈጻሚዎች መግለጻቸውን የማኅበሩ አመራሮች ተናገሩ፡፡

ማኅበሩ የዚህ ጥያቄ ምላሽ ውጤታማ ይሆናል ብሎ እንደሚያስብና ‹‹ጥሩ እንቅስቃሴ›› ላይ ነው ብሎ እንደሚያምን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዮሐንስ (ዶ/ር) የተመራና ሰባት አባላትን የያዘ የማኅበሩ የሥራ አስፈጻሚ ቡድን በትናንትናው ዕለት ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በመገኘት፣ ለሰዓታት የፈጀ በመምህራንና በአገር ጉዳይ ውይይት አድርገው ነበር፡፡

ከማኅበሩ አመራሮች ጋር ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ  (ዶ/ር)፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞትዮስ (ዶ/ር)፣ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ እንዲሁም ከሁለት የጽሕፈት ቤታቸው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን ነው፡፡

የመምህራኑን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ በሚመለከት የተወሰኑት ተጨባጭ ውሳኔዎች ምን እንደሆኑ ከሪፖርተር ለተነሳላቸው ጥያቄ ዮሐንስ (ዶ/ር) መልስ ሲሰጡ፣ እንደተለመደው አሠራር የአጠቃላይ ትምህርት መምህራን በሚሠሩበት አካባቢ የመኖሪያ ቦታ የማግኘት አሠራሩ የሚቀጥል ሆኖ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን መኖሪያ ቤት በሚመለከት ግን ውይይት እየተደረገበትና ጥሩ ምላሽ ሊገኝ እንደሚችል እንደተረዱ ተናግረዋል፡፡

‹‹የዩኒቨርሲቲ መምህራን የቤት ጥያቄን በሚመለከት ከዚህ በፊት የተነሳ ጉዳይ አለ፡፡ ውይይት እየተደረገበት ሲሆን፣ ዕልባት እንዲያገኝ እየተሠራበት እንደሆነ ነው የተገለጸልን፤›› ሲሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላገኙት ምላሽ አስረድተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከዚህ በፊት ሲያነሱት ስለነበረው የደመወዝ ጥያቄን በሚመለከት ማኅበሩ አንደኛው ይዞት የሄደው ጉዳይና የተወያየበት ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለደመወዝና መሰል ጥያቄዎች በየደረጃው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እንዳደረጉባቸው እንደነገሯቸው ገልጸዋል፡፡

የደመወዝ ጭማሪውን በሚመለከት፣ የኑሮ ውድነትን በአጠቃላይ የማቅለል ሥራ እንደሚሠራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹላቸው፣ ይህንንም ለማስተካከል ጥረት እንደሚያደርጉ በውይይታቸው ላይ እንደተነሳ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ የማኅበሩ አመራሮችም ስለ ደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ቁርጥ ያለ ምላሽ ለማግኘት ጠብቀው እንዳልሄዱም ተናግረዋል፡፡

‹‹ማናችንም ደመወዝ በሚመለከት ‹ከዛሬ ጀምሮ ይህን ያህል ጨምረናል› የሚል መልስ አንጠብቅም፡፡ ችግሩ እንዳለና ትኩረት ተሰጥቶ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲፈጽም ነው ያነሳነው፤›› ሲሉ ዮሐንስ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የማኅበሩ አመራሮች ከመምህራን ጥያቄዎች በተጨማሪ የሙያ ጥያቄና የመምህርነት ሙያ ምንነትን በሚመለከት፣ የትምህርት ቤቶች አቅምና ግብዓት በሚመለከት፣ እንዲሁም ለመምህራን ምቹ የሥራ ከባቢ መፍጠርንና የተለያዩ ጉዳዮችን አንስተው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያይተዋል፡፡

‹‹በቶሎ ይሄ ነው የሚሆነው ወይም ያ ነው የሚሆነው ሳይሆን፣ ጊዜ ተወስዶ በአቅምና በፕሮግራም የሚሠራ ነው የሚሆነው፤›› ሲሉ የጥያቄዎቹ ምላሾች ስለሚወስዱት ጊዜ ተናግረዋል፡፡

የማኅበሩ አመራሮች ስለ ማኅበራቸውና ማኅበሩ ለማስገንባት ስላቀደው ሕንፃም ከተወያዩባቸው ጉዳዮች አንደኛ መሆኑን ሪፖርተር መረዳት ችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...