Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው ግጭት ለሽግግር ፍትሕ ትግበራ አዳጋች እንደሚሆን ተገለጸ

በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው ግጭት ለሽግግር ፍትሕ ትግበራ አዳጋች እንደሚሆን ተገለጸ

ቀን:

በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ የፖሊሲ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ትግበራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የሽግግር ፍትሕ፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልል ባለው ግጭት ለትግበራ አዳጋች ይሆናል የሚል ሥጋት መኖሩ ተገለጸ፡፡

መንግሥት በተለይ በአማራና በኦሮሚያ፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችን ትግበራው ከመጀመሩ በፊት በሰላማዊ መንገድ መፍታት አለበት ሲል የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን ተናግሯል፡፡

የባለሙያዎች ቡድኑ ከተቋቋመ ወዲህ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ፣ ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በፍትሕ ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ቡድኑ የሽግግር ፍትሕ አተገባበር የሚያትተውን ፖሊሲ ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሲያሰባስብ የቆየውን ሥራ ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

በአገሪቱ ወደ 50 የሚጠጉ መድረኮችን በማዘጋጀት ግብዓቶችን የሰበሰበ ቢሆንም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ግን ግብዓት የማሰባሰብ ሥራውን አለማጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

‹‹በግጭቶች ምክንያት በኦሮሚያና አማራ ያላደረግናቸው አራት መድረኮች ይቀራሉ፡፡ እነዚህ ግጭቶች ካልተፈቱ የሽግግር ፍትሕ ትግበራውን የበለጠ አዳጋች ያደርገዋል፤›› ሲሉ የሽግግር ፍትሕ ቡድን አባል ማርሸት ታደሰ (ዶ/ር)፣ገልጸዋል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ቀረፃ በሚቀጥለው ወር ጥቅምት እንደሚጠናቀቅ አክለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ሌላኛው የቡድኑ አባል ታደሰ ካሳ (ዶ/ር) ግን በእነዚህ ክልሎች ሳይካሄድ በቀረ መድረክ ሳቢያ ፖሊሲውን ማርቀቅ አይቻልም ብለዋል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ከዚህ ቀደም ባለፈው ሐምሌ ወር ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ በግጭቶቹ ምክንያት መዘግየቱ ተመላክቷል፡፡

በሽግግር ፍትሕ ሥርዓቱ በኢትዮጵያ እስካሁን የተፈጸሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መርምሮ ፍትሕን፣ ካሳን፣ ዕርቅንና ተጠያቂነትን በማስፈን ለአገር ግንባታው አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ፣ የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት በተጠናቀቀ ማግሥት በኢትዮጵያ መንግሥት አነሳሽነት የተጀመረ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የትኞቹን ጥሰቶችና ከመቼ እስከ መቼ የተፈጸሙትን እንደሚያይም በፖሊሲው እንደሚወሰን የቡድኑ አባላት ገልጸዋል፡፡

የሽግግር ፍትሕ የሚያያቸው በደሎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡበት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ወይም ከ1983 ዓ.ም. ወይም ከዚያም ዘልቆ ሊጀምር እንደሚችል የቡድኑ አባላት አስረድተዋል፡፡ የተሰበሰበውን ግብዓት የመተንተንና የመጀመርያውን የፖሊሲ ረቂቅ የማዘጋጀት ሥራ በሚቀጥሉት ሳምንታት እንደሚጀመር የቡድኑ የባለሙያ አባላት ተናግረዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ አሁንም በግጭት ውስጥ ናት፤›› ያሉት ማርሸት (ዶ/ር)፣ ‹‹በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ግዙፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመደበኛ የፍርድና ፍትሕ አሠራር ለመፍታት አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

ፖሊሲው ከፀደቀ በኋላ የምርመራ፣ የዳኝነት፣ የካሳ፣ የዕርቅ፣ ብዙ ተያያዥ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ኮሚሽኖች ይቋቋማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የቡድኑ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሽግግር ፍትሕ የዓላማ ወሰንና አፈጻጸም በተመሳሳይ ጊዜ ለመተግበር፣ ዝግጅት ላይ ካለው አገራዊ ምክክር ጋር የሚጋጭባቸውና የሚወራረሱባቸው ቦታዎች መለየት እንዳለባቸው ባለሙያዎቹ አስረድተዋል፡፡

የሽግግር ፍትሑ በመንግሥት በመጀመሩ ተዓማኒና ከገዥው ብልፅግና ፓርቲ ገለልተኛ ሆኖ ይፈጸማል ወይ ለሚለው ጥያቄ ቡድኑ የባለሙያዎች ስብሰባ ብቻ እንደሆነ አባላቱ ተናግረዋል፡፡ ከገዥው ፓርቲ ፍላጎት ይልቅ የውጭ አካላት በሽግግር ፍትሕ ላይ ያላቸው የጥቅም ፍላጎት የጎላ እንደሆነ ቡድኑ ገልጿል፡፡

ተመድ፣ የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ እስካሁን ድረስ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ሳይሆን፣ ገለልተኛ በሆኑ በዓለም አቀፍ ተቋማት ሊጣራ ይገባል ሲሉ ይወተውታሉ፡፡ ለዚህም ተግባር ያቋቋሙት የባለሙያዎች ኮሚሽን ከጥቂት ወራት በኋላ ዓላማውን ሳያሳካ የተራዘመው የአንድ ዓመት ቀነ ገደብ ያበቃል ተብሏል፡፡

አገር በቀል የሽግግር ፍትሕ እንቅስቃሴ መጀመሩ ግን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከደረሰው የዲፕሎማሲ ኪሳራ በመጠኑ እንዳያገግም ማድረጉን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...