Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኤርትራ ወታደሮች ከስምምነቱ በኋላ ከትግራይ ክልል አለመውጣታቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ አደረገ

የኤርትራ ወታደሮች ከስምምነቱ በኋላ ከትግራይ ክልል አለመውጣታቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ አደረገ

ቀን:

በአጥናፉ አበራ

የኤርትራ ወታደሮች ከስምምነቱ በኋላ ከትግራይ ክልል እንዳልወጡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰሞኑ ባጠናቀረው ሪፖርቱ ይፋ አደረገ፡፡

በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሳቢያ፣ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው የገቡ የኤርትራ ወታደሮች ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላም ከትግራይ ክልል አለመውጣታቸውን አምነስቲ አመልክቷል። 

ወታደሮቹ ድንበር ጥሰው ከገቡበት ሥፍራ አለመውጣት ብቻ ሳይሆን፣ በተለይ ኮከበ ፅባህና ማርያም ሸዊቶ በተባሉት የትግራይ ክልል ወረዳዎች በንፁኃን ላይ ያነጣጠረ ግድያ፣ ዝርፊያና አስገድዶ መድፈር መፈጸማቸውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ቲገሬ ቻጉታህ ተናግረዋል።

ማርያም ሸዊቶ በምትባል ወረዳ ብቻ 20 ያህል ነዋሪዎች በተለይ ወንዶች ከጥቅምት 15 እስከ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ባለው ወቅት በኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን ከዓይን እማኞች፣ ከጥቃቱ ከተረፉና በጥቃቱ ሕይወታቸውን ካጡ ቤተሰቦች መስማቱን አምነስቲ በሪፖርቱ ገልጿል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በርከት ያሉ የጥቃት ሰለባዎችንና የዓይን ምስክሮችን አናግሬ አጠናቀርኩት ባለው ሪፖርቱ፣ የኤርትራ ወታደሮች በተጠቀሱት ሥፍራዎች የትግራይ ታጣቂዎችን በማደን ሰበብ በሚያደርጉት የቤት ለቤት አሰሳ ንፁኃን በተደጋጋሚ አስገድደው በመድፈር፣ በመዝረፍና በመግደል የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸውን ጠቅሷል። ወታደሮቹ ሴቶችን በካምፓቸው ውስጥ በማገት በተደጋጋሚ አስገድዶ መድፈር ይፈጽሙባቸው እንደነበርም አብራርቷል።

የኮከብ ፅባህ ወረዳ ነዋሪና የአስገዶዶ መድፈር ሰለባ ከሆኑት አንዷና የ37 ዓመቷ ቤዛዊት፣ ‹‹ብትጮሂም ሊያድንሽ የሚችል የለም እያሉ ለሦስት ወራት ያህል በቡድን ይደፍሩኝ ነበር፤›› ስትል የኤርትራ ወታደሮች ይፈጽሙባት የነበረውን ግፍ ለሰብዓዊ መብት ተከራካሪው አምነስቲ ኢንተርናሽናል መናገሯ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ ቤዛዊት ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት መሆኗም ታውቋል።

የከፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ አምነስቲ በኮከብ ፅባህ ያናገራቸው አንድ የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኛ፣ የአካባቢው ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችና ከጥቃቱ ያመለጡ ሴቶች የምስክርነት ቃላቸውን መስጠታቸውን አስታውቋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግሥትም በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ሕግ የተጣለበትን ንፁኃንን የመጠበቅ ግዴታ እንዳልተወጣ በሪፖርቱ ጠቅሶ ወቀሳውን ሰንዝሯል። አክሎም በንፁኃን ላይ እነዚህን የከፉ የመብት ጥሰቶች የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስቧል።

ለሁለት ዓመታት የቆየውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የቋጨው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ ክፍተቶች እንዳሉበት ‹አፍሪካንስ ፎር ዘ ሆርን› የተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ጥምረት አስታውቆ የነበረ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሒዩማን ራይትስዎች በበኩሉ ‹‹የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላም በምዕራብ ትግራይ የዘር ማፅዳት ወንጀል እየተፈጸመ ነው፤›› ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርቱን ይፋ ቢያደርግም፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የኤርትራም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥታት የሰጡት ምላሽ የለም።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...