Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሕዝብን ጤና አደጋ ላይ የሚጥሉ ምርቶችን ሲሸጡ በተያዙ ተቋማት ላይ ዕርምጃ መወሰዱ...

የሕዝብን ጤና አደጋ ላይ የሚጥሉ ምርቶችን ሲሸጡ በተያዙ ተቋማት ላይ ዕርምጃ መወሰዱ ተገለጸ

ቀን:

የሕዝብን ጤና አደጋ ላይ የሚጥሉ ምርቶችን ሲሸጡ በተያዙ ተቋማት ላይ ዕርምጃ መወሰዱን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

በተቋማቱ ላይ ዕርምጃ የተወሰደው በ2015 ዓ.ም. በተደረገ የክትትልና የቁጥጥር ወቅት መሆኑን፣ ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. መጪው አዲስ ዓመትን በማስመልከት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

ተገቢውን የምግብ ማቀነባበር ሥርዓት ያልተከተሉ ተቋማት ላይ በተደረገ ቁጥጥር መሠረት ዕርምጃ የተወሰደ መሆኑን፣ በአሰሳው ወቅት የተገኘው 10.2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ 110,097 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ምግቦች መያዛቸውን የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙሉ እመቤት ታደሰ ተናግረዋል፡፡

በተቋማቱ ላይ ከተወሰደባቸው ዕርምጃዎች መካከል ለ243 የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ12 ያህሉ ደግሞ በጊዜያዊነት የማሸግ/የማገድ እንዲሁም፣ በአንድ ተቋም ላይ የገንዘብ ቅጣት ከተላለፉት ውሳኔዎች ውስጥ ይገኙበታል ብለዋል፡፡ የተቀሩት ደግሞ በባለሥልጣኑ በይፋ ያልተነገረ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው ተገልጿል፡፡

ከምግብ ነክ በተጨማሪ መጠጥ የሚያዘጋጁ ተቋማት ላይ ቁጥጥር የተደረገ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጇ፣ በዚህም ቁጥጥር ከ8.8 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው 173,201 ሊትር የተለያዩ መጠጦች መወገዳቸውን አስረድተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ጥራታቸውን ያልጠበቁ፣ ከባዕድ ጋር የተቀላቀሉና የተለያዩ ችግሮች ያሉባቸው ከ19.6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ምግቦች መጠጦች፣ ማብሰያዎችና ማሸጊያዎች መወገዳቸውን ወ/ሮ ሙሉ እመቤት ገልጸዋል፡፡

ከበዓል ጋር ተያይዞ ከሕገወጥ ዕርድ፣ በዋጋ ቅናሽ ቤት ለቤት ከሚሸጡ ምርቶች፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ካበቃ ምርቶች፣ ኅብረተሰቡ መጠንቀቅ እንዳለበት አስረድተው፣ እነዚህን ምርቶች የሚሸጡ ሕገወጦችን ደግሞ በ8864 ነፃ ስልክ መስመር ለባለሥልጣኑ በማሳወቅ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ሲል አሳስበዋል፡፡

ባለሥልጣኑ መጪውን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሕገወጥ ድርጊቶች ከወዲሁ መለየቱን የገለጹት ወ/ሮ ሙሉ እመቤት፣ ሕገወጥ ዕርድ በየቦታው መኖሩ፣ ምንጫቸው የማይታወቁ ምርቶችና የንፅህና ጉድለት በስፋት መኖራቸውን ከታዩ ዋና ዋና ክፍተቶች ጥቂቶቹ መሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡

እነዚህን ሕገወጥ አሠራሮችን መሠረት በማድረግ በተለያዩ ቦታዎች ባለሙያዎች ተሠማርተው ቁጥጥር እንደሚያደርጉ ጠቁመው፣ ቁጥጥርና ክትትል ከሚደረግባቸው ቦታዎች መካከል የበዓል ዋዜማ ገበያዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ለሚያደርገው የቁጥጥርና የክትትል ሥራ የከተማው ነዋሪዎች ዕገዛ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ በአዲሱ ዓመት ዋዜማም የኅብረተሰቡ ትብብር እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...