Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩል ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ...

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩል ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተነገረ

ቀን:

ባለፈው አንድ ወር ውስጥ የሱዳንን ጦርነት በመሸሽ ኢትዮጵያውያንና የሱዳን ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡና ቁጥራቸውም እየጨመረ እንደሆነ ታወቀ፡፡ ስደተኞቹ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሥፈራቸውም ተነግሯል፡፡

በአንፃሩ ቀደም ሲል በመተማ በኩል ወደ አማራ ክልል ይገቡ የነበሩት ስደተኞች ቁጥር በእጅጉ እየቀነሰ መሆኑን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ከሚያዝያ ወር አጋማሽ ጀምሮ ጦርነቱን በመሸሽ በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ፣ በርካታ ሰዎች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ በመተማ በኩል ወደ አማራ ክልል ይገቡ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እየገቡ እንደሆነ ነው የተመድ ጽሕፈት ቤት በሪፖርቱ የገለጸው፡፡

‹‹በመተማ በቀን እስከ አንድ ሺሕ ሰዎች ድንበር ያቋርጡ ነበር፡፡ ባለፈው ጥቂት ቀናት ግን ወደ 200 ገደማ ነው እየገቡ ያሉት፤›› ሲል ጽሕፈት ቤቱ ነሐሴ 26 ቀን 2015 ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡

ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን የሚገኘው ኩርሙክ ወደ ተባለ ሥፍራ የሚሰደዱት ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር፣ በነሐሴ መጀመርያና ከዚያ በፊት ያልታየ ነው ብሏል፡፡

እስከ ነሐሴ መጨረሻ ድረስ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር የሸሹ ሰዎች ቁጥር 78,598 ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 46 በመቶው በሱዳን ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው ተብሏል፡፡ ሱዳናውያን 34 በመቶ ሲሆኑ፣ የሌላ አገሮች ዜጎች ደግሞ 20 በመቶ ያህል እንደሚሸፍኑ ተመልክቷል፡፡

ስደተኞቹ ድንበር ተሻግረው ሲገቡ በአማራ ክልል መተማ በኩል፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩርሙክ በኩል ቁጥጥር ይደረግ እንደነበር በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 17 ሺሕ የሚጠጉ አባወራዎች በሁለቱ ቦታዎች ሰፍረው የሚገኙ መሆናቸውና ቁጥራቸውም ከ35 ሺሕ በላይ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ከሰፋሪዎቹ መሀል 18,558 ያህሉ መተማ፣ እንዲሁም 15,960 ያህሉ ደግሞ በኩርሙክ ሲገኙ በጋምቤላ ክልል ባሉ ሁለት ቦታዎች ደግሞ 700 ያህል ሰዎች መጠለላቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን መረጃ በመውሰድ ሪፖርቱ ይፋ እንዳደረገው፣ 16 የተረጋገጡ የኮሌራ ሕመሞች በመተማ ተከስተዋል፡፡ በኩርሙክ ደግሞ 190 የተጠረጠሩ የኮሌራ ሕመምተኞች ሊኖሩ እንደሚችሉና አራት ሰዎችም ሳይሞቱ እንዳልቀሩ ተገልጿል፡፡

ለስደተኞቹ ድጋፍ ማቅረብን በሚመለከት ከተመድ ማዕከላዊ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ፈንድ ከተገኘ አምስት ሚሊዮን ዶላር ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡት የመጠለያ ግንባታና መሰል ድጋፎች እየቀረበ መሆኑን፣ ተጨማሪ ድጋፍም እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል፡፡

የተመድ እ.ኤ.አ. የ2023 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ምላሽ ዕቅድ አራት ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ እስካሁን የተገኘው ፈንድ ግን 26 በመቶ ብቻ መሆኑንም ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...