Sunday, July 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየማኅበራዊ ሚዲያው መንታ መንገዶች

የማኅበራዊ ሚዲያው መንታ መንገዶች

ቀን:

ከሰላም ግንባታ ጋር ተያይዞ ቴክኖሎጂና ዲጂታል መድረኮች አዎንታዊና አሉታዊ ሚና አላቸው፡፡ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የሆኑት ፌስቡክ፣ ኤክስ (ቲዊተር)፣ ቲክቶክና ሌሎችም በኅብረተሰቡ ዘንድ ጤናማ ለውጦችን ለማነሳሳት በተለያዩ አገሮች ውስጥ ጥቅም ላይ ሲውሉ ተስተውሏል፡፡ በተቃራኒው ከግለሰብ አንስቶ በተቋም ደረጃም ሐሰተኛ፣ ግጭት ቀስቃሽና ጥላቻን የሚነዙ መረጃዎች በከፍተኛ ፍጥነት ለማሠራጨትም ይውላሉ፡፡

ዲጂታል ሚዲያ በተለይም ማኅበራዊ ሚዲያዎች አሁናዊ ገጽታና አጠቃቀማቸውን መገንዘብ ለሰላም ግንባታ ያላቸው ሚና በሚል በሜታ (ፌስቡክና) በኢትዮጵያ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በተዘጋጀ መድረክ የተነሳውም፣ በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያው ለአሉታዊ ይዘት መጠቀሚያ መሆኑ ነው፡፡

በምክር ቤቱ የፕሮግራምና ልማት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሀና ወልደ ገብርኤል፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ የዲጂታል ትሩፋቶችን በመጠቀም ድርጀታዊ አቅምን ለመገንባት፣ እየሠራበት ቢሆንም፣ አሉታዊ ይዘቶች የሚለቀቁበት በመሆኑ፣ ከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብ ሕይወት በማሳጣትና ውድመት በማስከተል ለሰላም ግንባታው እንቅፋት ሲሆን ተመልክተናል ብለዋል፡፡

ሲቪክ ማኅበረሰቡ ዲጂታል ቴኖሎጂዎችን በመጠቀም ኅብረተሰቡን በማስተማር፣ ጤናማ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲኖር በማስቻልና ማኅበረሰቡ ራሱን ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ተፅዕኖ እንዲጠብቅ በማድረግ በስፋት መሥራት እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል፡፡

በዲጂታል ሚዲያ የሚሠራጩ ግጭት ቀስቃሽ ይዘቶችን በመጠቆም ከሚመለከተው አካል ጋር በቅንጅት መሠራት እንዳለበት፣ በሌሎች አገሮች የሲቪክ ማኅበራት ቴክኖሎጂን ለሰላም በመጠቀም ግጭት የሚከሰትባቸውን ቦታዎች እንደሚለዩ፣  የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት እንደሚተገብሩና ግጭትን የመከላከል ሥራ እንደሚሠሩበት ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤቱ፣ ግጭት በሚከሰትበት ጊዜ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ወደ ሰላም ለመለወጥ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ሲሠራ መቆየቱን፣ በድኅረ ግጭትም  የተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሰንዶ በማዘጋጀት የሽግግር ፍትሕ ይሰፍን ዘንድ ውትወታ ማድረጉንና ሒደቱ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን ቴክኖሎጂንና ማኅበራዊ መድረኮችን መጠቀሙን አስታውሰዋል፡፡

የዲጂታል መድረክ አጠቃቀምን አስመልክቶ፣ ዜጎች በአክብሮትና በሂሳዊ አስተሳስብ እንዲሳተፉ፣ ለውይይትና በሰላማዊ መንገድ አብሮ ለመኖር ምቹ የዲጂታል አካባቢ እንዲፈጠር ሲቪክ ማኅበረሰቡ፣ መንግሥትና ሌሎችም ተቋማት አብረው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የሴንተር ፎር አድቫንስመንት ኦፍ ራይትስ ኤንድ ዴሞክራሲ (ካርድ) ዋና ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉ፣ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በተለይ ፌስቡክ በፊት ከነበረው  በጣም ጥቂት የተማሩ (ኢሊት) የምንላቸው ከሚጠቀሙበት ዓውድ፣ የማይታዩና የማይደመጡ የነበሩ ድምፆች ቦታ ሚያገኙበትን ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

መረጃ ከአንድ ወገን ብቻ እንዳይጫን፣ የማይሰሙ የነበሩ ድምፆች አንፃራዊ ድምፅ እንዲያገኙ ማስቻሉን፣ የሰዎችን ግንኙነትና የውትወታ ሥራን ቀላል ማድረጉን አክለዋል፡፡

 ከ2018 በኋላ የታየው ለውጥ በተለይ አፍላ የለውጥ ስሜት የነበረበት ሁኔታ ‹‹የፌስቡክ ሪቮሊውሽን›› እስከመባል አድርሶት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች የፖለቲካ መሣሪያም ሆመሆናቸውን፣ የተዛባ መረጃና የሸፍጥ ትርክቶች እንዲጨምሩ ማድረጋቸውን፣ ቀድሞም ሐሳብ በመሰንዘር ጠንካራ የነበሩት እንዲጠነክሩ፣ ዕድል ያልነበራቸውም እንዲያገኙ ማስቻሉን አክለዋል፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ኢንተርኔት/ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን እንዲዘጋ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

‹‹ኢንተርኔት መዝጋት የመንግሥትን ተጠያቂነት ይቀንሳል እንጂ ችግሮችን አይፈታም፤›› ሲሉም፣ መንግሥት መረጃ መስጠት  ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ጠቁመዋል፡፡

የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውና ነውጥን እንደ ትግል አማራጭ የወሰዱ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ማኅበራዊ ሚዲያውን ለተሳሳተ መረጃና ለጥላቻ ንግግር እንደሚጠቀሙበት፣ በዲጂታል (ማኅበራዊ ሚዲያ) ያለው ግንዛቤና ዕውቀት ዝቅተኛ መሆንና በኢትዮጵያ አደገኛ ይዘቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

ነውጥን እንደ ትግል አማራጭ የወሰዱ የፖለቲካ ኃይሎች ማኅበራዊ ሚዲያውን ለጦርነት መድረክ የሚጠቀሙበት በመሆኑም፣ ሲቪክ ሶሳይቲው ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠት ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅበት፣ እውነትን በማረጋገጥና ትክክለኛውን መረጃ በማሠራጨት ረገድ መሥራት እንደሚገባም አክለዋል፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም፣ ይዘቶችን ለመረዳትና እዚያ ውስጥ ለመሳተፍ  የዕውቀትና ክህሎት ክፍተት መኖሩ፣ በተሳሳተ መረጃ ውሳኔ የመስጠት ዕድልን መፍጠሩን፣ ይህ አሳሳቢነቱ የሚጎለው በፖለቲካው ዘርፍ ቢሆንም፣ ችግሩ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችም እንደሚስተዋል ገልጸዋል፡፡

የተዛቡ መረጃዎችንና የጥላቻ ንግግሮችን ለመቀነስና ጤናማ ንግግሮች እንዲዳብሩ ለማድረግ የዲጂታል ዕውቀት ከማስፈለጉም በተጨማሪ፣ መንግሥት ግልጽ መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት ማኅበራዊ መድረኮችን ከመዝጋት ይልቅ መረጃ በመስጠት ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በተለይም ማኅበራዊ ትስስር ገጾች አጠቃቀም ላይ ለተማሪዎች ማስተማርና ዕውቀት ማስጨበጥ እንደሚያስፈልግም መክረዋል፡፡

እንደ አቶ በፍቃዱ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዓለም አቀፍ ሕግ እንዲኖር መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች (ኩባንያዎች) አሠራራቸውን በማሻሻል ግጭት የሚያነሳሱ መረጃዎችንና ይዘቶችን ማስቀረትም ይኖርባቸዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ድኤታ ወ/ሮ ሁሪያ ኢብራሂም በበኩላቸው፣ የሰላም ግንባታ ሒደት ጊዜና ትዕግሥትን እንደሚጠይቅ ገልጸው፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዕውቀት እንዲዳብር መንግሥት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የዲጂታል (የማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች) ግንዛቤ ዙሪያ የሚሠሩ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችን  ማግኘት ከባድ እንደሆነ በማስታወስም፣ መንግሥት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በአግባቡ የመጠቀም ዕውቀት ስለሌለው፣ ዕውቀት ለማስጨበጥ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሰላም ሚኒስቴር የአገር ግንባታ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አስማ ረዲ እንደሚሉት፣ 67 በመቶ የዓለም ሕዝብ የኢንተርኔት ተጠቃሚ በመሆኑ አጠገቡ ካለው ማኅበረሰብ ይልቅ ከመድረኩ በሚያገኘው መረጃ የሚታነፅበት መንገድ ሰፍቷል፡፡   

በኢትዮጵያ 21 ሚሊዮን ሕዝብ የኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆኑን፣ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ አንፃር ትንሽ ቢመስልም፣ ሕዝቡን ለማንቃት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ልጆች የበለጠ በተማሩና መረጃ ባገኙ ቁጥር ዕውቀታቸው ይሰፋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ የሰው ልጅ ተስፋ የሚኖረውም ዓለም ላይ ሰፊ ዕድል እንዳለ ሲገነዘብ እንደሆነ አክለዋል፡፡

‹‹አካባቢ ላይ ባሉ ነገሮች ብቻ መታጠር ግጭት ያሰፋል፡፡ ዓለምን ባወቁ ቁጥር ወጣ ብሎ የሥራ ዕድል እንዳለም ይገነዘባሉ፤›› የሚሉት ወ/ሮ አስማ፣ ትልቁ ፈተና 21 ሚሊዮን ሕዝብ የሚጠቀመው ለምንድነው? የሚለው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አብዛኛው የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳታፊ ለመረጃ ብቻ እንደሚጠቀምበት፣ ነገር ግን የመረጃውን እውነተኛነት የማያጠራ በመሆኑ ለሰላም ግንባታ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  

ዲጂታል ሚዲያው ለሰላም ግንባታ ወሳኝ ቢሆንም፣ ያለ ምንም ቁጥጥር መረጃ የሚለቀቅበት፣ አጠቃቀሙ ላይ የዕውቀት ክፍተት ያለበትና ለግጭት የሚያነሳሱ ይዘቶች  የሚጽፉ አካላትም ራሳቸውን ደብቀው  የሚሠሩበት  መሆኑ የዘርፉ ፈተና እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በሕግ የሚገኝ ተጠያቂ  ባለመኖሩም ኢንተርኔት መዝጋትና መገደብ  አማራጭ ነው ብለዋል፡፡

‹‹አብዛኞቹ የኢትዮጵያ አክቲቪስቶች የሚያሠራጩት መረጃ ጥላቻ የሚሆነው ስላላስተማርን፣ ዕውቀት ስላልሰጠን ነው፤›› ብለው፣ ሰላም ሚኒስቴር ከሚሰጣቸው ሥልጠናዎች ውስጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንደሚገኝበትና ይህ ወደ ማኅበረሰቡ ሲዘልቅ ችግሮችን እንደሚያቃልል ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ በነበረው ውይይትም፣ በኢትዮጵያ ደረጃ ሰፊ ተጠቃሚ ያለው ፌስቡክ  በተቋምም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ሪፖርት ደርሶት ልጥፉን ወዲያውኑ እንደማያነሳና የሚያነሳው ችግሩ ከተከሰተ በኋላ መሆኑ አስተችቶታል፡፡  

ዲጂታል ሚዲያ መጠቀም ሰብዓዊ መብት ተደርጎ ይቆጠር እንጂ በተጠቃሚው ዘንድ መብትና ግዴታ እንደማይታወቅ፣ ችግሩን ለመፍታት እየተሠራ ቢሆንም፣ ችግሩ እየቀደመ እንደሚሄድም ከመድረኩ ተነስቷል፡፡

የሜታ በአፍሪካ የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ የፐብሊክ ፖሊሲ ዳይሬክተር ሜርሲ ናግዎ በበኩላቸው፣ ሜታ የጥላቻ ንግግርና ግጭት ቀስቃሽ ይዘቶችን እንደሚያነሳ፣ በአፍሪካም ይሁን በሌሎች አገሮች መድልኦ እንደሌለ ነገር ግን መጠናከር ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...