Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የማዕበል ናሙና!

ሰላም! ሰላም! ‹‹ለሰላም የምንሰጠው ዋጋ ወደድ ቢል ኖሮ እንዲህ የግጭት መጫወቻ አንሆንም ነበር…›› የሚለኝ ምሁሩ ወዳጄ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ወንድሜ እውነትህን ነው፡፡ ለማንኛውም እንዴት ሰነበታችሁ ወገኖቼ? አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ሊተካ የሳምንት ያህል ጊዜ ቀርቶታል፡፡ ‹‹መቼም ልማድ ሆኖብን ለአዲሱ ዓመት መልካም ምኞት መለዋወጥ ወግ ቢሆንም፣ እኛ አስተሳሰባችንን ዘመኑ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ አኳያ ለማዘመን ካልቻልን ሁሉም ነገር ከንቱ ነው፡፡ አዲስ ዓመት ሲቃረብ ቃላት ቀምረን እርስ በርስ በመልካም ምኞቶች ለመመራረቅ ስንዘገጃጅ፣ አፋችን ብቻ ሳይሆን ልባችን ጭምር ንፁህ ቢሆን ኖሮ ‹የሰላም ምንቸት ግባ የግጭት ምንቸት ውጣ› ለማለት አያቅተንም ነበር፡፡ ግና ከላይ እስከ ታች መታደስ ካላደረግን ምኞታችንም ሆነ ግብራችን ታጥቦ ጭቃ መሆኑ አይቀሬ ነው…›› እያለ ምሁሩ ወዳጄ ሰፋና ጠለቅ ካለው ዕውቀቱ ሲያካፍለኝ በአንክሮ እያዳመጥኩት ነበር፡፡ አባትየው አዛውንቱ ባሻዬም፣ ‹‹የዘመኑን ነገር ለዘመኑ ሰው መተው ድሮም የነበረ ልማድ ቢሆንም፣ አላፊው ትውልድ ለተቀባዩ አዲስ ትውልድ ከሕይወት ተሞክሮ የተቀዳ ማሳሰቢያ መስጠቱ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ምክሩም ሆነ ማሳሰቢያው አዳማጭ ጆሮና አስተዋይ ህሊና ያስፈልገዋል…›› ሲሉኝ አንድ የቆየ ነገር ትዝ ብሎኝ በህሊናዬ ውስጥ አቃጨለ፡፡ የህሊና ጉዳይ ቀላል አይደለም!

ጊዜው ራቅ ቢልም አንድ ነገር አይረሳኝም፡፡ ከበርካታ ዓመታት በፊት አንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ በቴሌቪዥን ሲናገሩ በአንክሮ እያዳመጥኳቸው ነበር፡፡ ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይማርና እኚያ አንጋፋ ምሁሩ፣ ‹‹ሁላችንም በየተሰማራንበት መስክ በምናከናውናቸው ሥራዎች የምንመዘነው በሕዝብ የህሊና ዳኝነት እንደሆነ መዘንጋት የለብንም…›› ነበር ያሉት፡፡ የህሊና ዳኝነት ትልቅ ግምት ሊሰጠው የሚገባ እሴት መሆን እንዳለበት ጭምር ነበር ያብራሩት፡፡ ዛሬ አዛውንቱ ባሻዬ በሌላ ምልከታ ሲያመጡት ግርም ነበር ያለኝ፡፡ የህሊና ነገር ሲነሳ ደላላ ሠፈር ምን ህሊና አለ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ በአንድ በኩል ነገሩ እውነት ሲሆን በሌላ በኩል ግን ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አይኖረውም እላለሁ፡፡ ምክንያቱ ምንድነው ብትሉኝ ሁላችንም የምንመዘነው በግላችን በምናከናውነው ጉዳይ ሲሆን፣ የጋራ ተጠያቂነት ባለበት ደግሞ እንደ ተሳትፏችን ይሆናል ማለት ነው፡፡ የግልና የወል ተጠያቂነት መኖሩን ለማወቅ ግን አስተዋይ ህሊና ያስፈልገናል እላለሁ፡፡ እኔ በዚህች እዚህ ግባ በማትባል ዕውቀቴ ይህንን የምለው፣ ስህተት ሠርቻለሁ ብዬ ባሰብኩ ቁጥር የሚቆነጥጥ ህሊና ስላለኝ ነው፡፡ ለዚህም ፈጣሪዬን አመሠግነዋለሁ፡፡ ተመሥገን!

በቀደም ዕለት አንዱ ወሮበላ ባንክ ውስጥ ስልኬን መነተፈኝና አዲስ ሲም ካርድ ላወጣ ቴሌ ጎራ ብዬ ያጋጠመኝን ላጫውታችሁ። የስልኬ መሰረቅ ብዙም እንዳላበገነኝ የታዘቡ እንደ ደርቢ የሰው ሕይወት አፍጥጠው ሲከታተሉ የሚውሉ ምስኪኖች፣ ‹እሱ ምን አለበት? ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ የያዘውን ይዞ ነው። ዕድሜ ለዚህ አቀባባይ ድለላው…› ብለው እየተቀባበሉ ሲያሙኝ ሰማሁ። እኔ ሻጭና ገዥን የማገናኝ ደላላ እንጂ መሬት በካሬና በሔክታር እየለካሁ የማድል ሹም አይደለሁም፡፡ አንድ ተራ ደላላን ትልቅ ምቾት ያለው ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ከተቀመጠ ሹም፣ ወይም በርካታ ኮንቴይነሮች እያንጋጋ ከሚነግድ ሲራራ ነጋዴ፣ አለበለዚያም ኮንትሮባንድ ከሚነግድና ግብር መክፈል እርሙ ከሆነ ሕገወጥ ጋር እያወዳደሩኝ ያሉትን ምስኪን ሐሜተኞች እንዳልሰማ ሆኜ ‹ፎርጂ› ሲም ካርዴን ተቀብዬ ውልቅ አልኩ፡፡ ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ የሰማሁትን ሐሜት ስነግረው፣ ‹‹የእኛ ሰው ከመንጋ አስተሳሰብ ወጥቶ ለሐሳብ ጥራት ቦታ ካልሰጠ ብሪክስን በመቀላቀል ብቻ የሚኖር ለውጥ የለኝም…›› አለኝ፡፡ ይህም እውነት ነው!

ውዴ ማንጠግቦሽ በስልኬ መጥፋት ሳቢያ ልታፅናናኝ ፈልጋ ነው መሰል በቅቤና በቅመም ያበደ ዶሮ ወጥ ሠራችልኝ፡፡ ነገር ግን በርበሬው በዛ ብሎ ኖሮ የስልኬን መጥፋት ሰምቶ ሊያፅናናኝ የመጣ ወዳጅ ዘመድ ሳይቀር ሁለቴ ሦስቴ ጎርሶ፣ ‹አንበርብር የበርበሬ እርሻ ጀመርክ እንዴ?› ብሎ ሲጠይቀኝ ከስልኩ ሐሜት ጋር ተደምሮ ሰማይ ጠቀስ ትችት እንዳይጀመር ተሳቅቄ ነበር። ለነገሩ በተወደደ ኑሮ በርበሬ የረከሰብን መሰለኝና ማንጠግቦሽን በዓይኔ ገረመምኳት፡፡ እሷም ጥፋቷ ገብቷት ኖሮ በዝምታ ነበር ያለፈችኝ፡፡ ይገርማችኋል ያደለው ያልታደለውን አፈናቅሎ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ይገነባል፣ አዳሜ ሰማይ ጠቀስ የሐሜት ብሎኬት ይደረድራል፡፡ ለነገሩ ይኼም አለመታደል ነው። ወደ ቁምነገሩ ስመልሳችሁና ዘንድሮ ከሰው ልጅ በስተቀር ሁሉም ነገር ተወዷል፡፡ የሰው ልጅ ብቻ ነው እያደር ዋጋው እየቀነሰ ያለው፡፡ በቀደም ሠፈር ውስጥ ያለ ከሰል ሻጭ ዘንድ ሄጄ አንድ ከረጢት ከሰል ስጠኝ ስለው፣ ‹‹ጋሼ አንበርብር ከሰል ከጠፋ ሰነበተ እኮ…›› ብሎኝ ጠጋ በማለት፣ ‹‹ለአንተ እንደምንም ብዬ አንድ አላጣም ዋጋው ግን 900 ብር ነው…›› ሲለኝ ይኼ ኑሮ ሳይሆን ሲኦል ነበር የመሰለኝ፡፡ ኧረ ጎበዝ ወዴት እየሄድን ነው!

ለዚህ አሳረኛ ኑሮአችን ዋነኛ ምክንያቶቹ እኛ ነን ብል የሚቀየም ይኖር ይሆን? ለማንኛውም እኛ ማለት በአስመሳዮችና በአሳሳቾች አፈጮሌነት የምንበለጥ ስለሆንን፣ የአጭር ጊዜ ጉዳዮች ላይ እንጂ እንደነዚያ አስተዋይ አያት ቅድመ አያቶቻችን አርቀን ማሰብ የተውን ይመስለኛል፡፡ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ይህንን ጉዳይ አንስተን ስንነጋገር፣ ‹‹አንበርብር ምን መሰለህ ዕውቀት ያልሰነቀ ማኅበረሰብ የድህነትና የክፋት ሰለባ ይሆናል፡፡ ዕውቀት ሲኖርህ ማንንም ሰው የምትወደውም ሆነ የምትጠላው በአስተሳሰቡ ወይም በሚደግፈው ቡድን ምክንያት ሳይሆን፣ በተግባራዊ እንቅስቃሴው በሚያከናውነው አዎንታዊ ወይም አሉታዊ አስተዋጽኦ ነው…›› ያለኝ አይረሳኝም፡፡ እኔም ይህንን በዚህች የደላላ ዕውቀቴ ስተነትን ብልጭ የሚልልኝ ሐሳብ አለ፡፡ ጠብሰቅ ያለ ዕውቀት ከምግባር ጋር የተላበሱ አንቱ የተባሉ ሰዎችን ተመልከቱ፡፡ አይዋሹም፣ አይሰርቁም፣ ሴራ አይጎነጉኑም፣ ወጣቱን እያታለሉ እሳት ውስጥ አይማግዱም፣ ሐሰተኛ ወሬ እያሠራጩ የሕዝብ አዕምሮ አያስጨንቁም፣ የአገር ህልውናን ችግር ውስጥ የሚከት ድርጊት አይፈጽሙም፡፡ ህሊናቸው ንፁህ ስለሆነ የትም ቦታ ቢሄዱ አያፍሩም፡፡ እንዲያ ነው!

የጀመርኩትን ወግ ቶሎ ጨርሼ ካልተሰናበትኳችሁ ቀኑን ሙሉ በርካታ ህፀፆችን ሳወጋ ውዬ ባድር ግድም አይሰጠኝ ነበር። ሲያዩኝ ግን ብሶት ያለብኝ አልመስልም አይደል? ይህች እንደገና ተሻሽላ የተጠገነች ካፖርቴና ስቄ ማሳቅ አለመቻሌ ተባብረው እየሸፈኑልኝ እንጂ፣ የአገሬን ጉዳይ ሳስበው በጣም ብዙ የሚያቃጥሉ ነገሮች ውስጤን ይፈጁታል። ያው መሸት ሲል የብቅል ጭማቂ ቀዝቀዝ እስኪያደርገው አትሉም? ጥቂት ወዲያ ወዲህ እንዳልኩ ታዲያ ቶዮታ ኤግዘከቲቭ አውቶሞቢል ላሻሽጥ መደለል ጀመርኩ። የመሰንበቻው ኃይለኛ ዝናብ ነገር መቼም እንደ አዲስ አይነገርም። ደመናው ዞር ሲል ሰማዩ ሲጠቁር የዓለም መጨረሻ መምሰሉ ብቻ ሳይሆን፣  ዶፉ ከወረደ በኋላ አውራ ጎዳናውን የሚያጥለቀልቀው ጎርፍ የኢንዶኔዥያን ሱናሚ እየመሰለ ሲያስፈራራኝ ሰነበተ። የአውራ ጎዳናዎቻችን በጎርፍ መጥለቅለቅ ሚስጥሩ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ሲስተም ዜሮ መሆኑን ማሳያ ነው ብል ሐሰት የሚለኝ እንደማይኖር እርግጠኛ ነኝ፡፡ ወጣ ብሎ መንገዶቹን በዓይን ዓይቶ መፍረድ ይቻላል፡፡ ህሊና በአስመሳይነት ካልተጋረደ በስተቀር የአዲስ አበባ ጎዳናዎች የጀልባ ቀዘፋ ውድድር ሊካሄድባቸው የተዘጋጁ መሆናቸውን ለመረዳት ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ይኸው ነው!

እንዲህ እንዲህ እያልኩ ቶዮታውን የሚገዛ ደንበኛ ሳገኝ ለሚከፍለው ክፍያ ጥቂት እንደሚጎድለው በጆሮዬ ሹክ አለኝ። መኪናዋን አስፈትሸን ከጨራረስን በኋላ፣ ‹‹ምን ይሻላል?›› ስለው እንዲያመልጠው እንደማይፈልግ ነግሮኝ የሚያበድረው ወዳጅ ያፈላልግ ጀመር። ‹‹ማን አለ? እከሌም ለራሱ አራጣ ተበድሮ ጭንቅ ላይ ነው፣ ማን ነው ያም አይሰጠኝም። እሱ ሲበልጡት አይወድም…›› እያለ ረጅም ጊዜ ወሰደ። ‹‹እጅህ ላይ ያለው ገንዘብ እኮ ሌላ መኪና ይገዛል፣ በቃ ይኼን ተወውና ሌላ ልፈልግልህ?”›› ስለው በጣም ተበሳጭቶ፣ ‹‹ለምን ተብሎ? እኔ ከማን አንሳለሁ? ጓደኞቼ ሁሉ ከኮሮላ አልፈው ቱሶንና ራቫ ፎር እየነዱ?›› ብሎ መልሶ አፈጠጠብኝ። በኋላ ከባሻዬ ጋር ስለኑሮና አኗኗራችን ስንጫወት፣ ‹‹የእኛ ነገር እኮ አያስተማምንም። ሥራችን ከላይ ከላይ፣ አስተሳሰባችን ከላይ ከላይ፣ መሪም ተመሪም ስፋት ላይ እንጂ ጥልቀትን ችላ ብለን መንጎድ ዋና ሥራችን ከሆነ ቆየ እኮ?›› ያሉኝ ትዝ እያለኝ፣ ይህች በጨበጣ ከማን አንሼ እያልን የምኖራት ኑሮ እኔኑ መልሳ አስመረረችኝ። ደንበኛዬ እንደ ምንም ብሎ የጎደለውን 130,000 ብር ከሞላ በኋላ መኪናውን ተቀበለ። እኔም ኮሚሽኔን ተቀብዬ ሽው አልኩ። ደግሞ የነዳጅ መቅጃ አበድረኝ እንዳይለይ ብዬ ነዋ። እንዲህ የሽሽት ፊታውራሪ ካልሆንማ የሚባለውን አንችለውም!

በሉ እስኪ እንሰነባበት። የያዝኳትን ይዤ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር መሸት እስኪል እያወራን የእግር መንገድ እንጓዛለን። ሁለታችንንም አንድ ነገር አስደንግጦናል፣ አስገርሞናል። ሌላ ጊዜ በግልምጫ ብቻ ዘቅዝቆ ሊሰቅለን ምንም የማይቀረው ሰው ዛሬ ከልቡ የእግዜር ሰላምታ ይሰጠናል። ሁለታችን በመገረም ደጋግመን እንተያያለን። ሰላምታ እንደ ዶላር ብርቅ የሆነበት ዘመን ላይ ነዋ የደረስነው። ‹‹ምን ተገኝቶ ነው ዛሬ የእኛ ሰው መሬት የሆነው?›› ስለው፣ ‹‹የአዲስ ዓመት በዓል እየተቃረበ ስለሆነ ለመልካም ምኞት መግለጫ ልምምድ ላይ ይሆናል እንጂ፣ መቼም ይኼ ሁሉ ሰው አድማስ ሎተሪ ወይም ቶምቦላ ደርሶት አይደለም…›› ብሎ ሳቀ። እሱ እኮ በል ሲለው ነገረኛ ነው፡፡ ብዙም ሳንርቅ ድካም ይሰማን ጀመር። ‹‹ሮጠው የማይደክሙት ጀግኖች አትሌቶችን በምታፈራ አገር እኛ ይህችን ታህል ተራመድን ብለን ሲደክመን አናሳዝንም?››› አልኩት። ‹‹‹ስታይላችን› ነው፣ በዘር ከምንወርሰው በጎ ነገር ክፋቱ፣ መሰላቸቱ፣ መዳከሙና መሳነፉ ማየሉ እንዳልከው ያሳዝናል…›› እያለኝ ወደ ግሮሰሪያችን አመራን። ግሮሰሪያችን ስንደርስ በምናየው ነገር ግራ ተገባን። ሌላ ጊዜ ከምናውቃቸው ምራቃቸውን ከዋጡ ታዳሚዎች ይልቅ አፍላ ታዳጊዎች ቤቱን ሞልተውታል። ሴቶቹ ወንዶቹ ላይ በሙዚቃው ሥልት ወድቀው ይነሳሉ። ወንዶቹ በምዕራባዊያን የሙዚቃ ክሊፖች ላይ እንደሚያዩዋቸው ራፐሮች አቀማመጣቸውን እያሳዩ ከእኛ በላይ ላሳር ይላሉ። ሁናቴያቸውና አጠጣጣቸው ፍፁም አስደንጋጭ ነው። ተቆጪና ገላማጭ እንዳይኖር ሁኔታቸው ያስፈራል፡፡ አሁን ነው መፍራት!

የግሮሰሪዋ ባለቤት ልጆቹ እየደጋገሙ መጥተውበታል መሰል ምንም ሳይመስለው ‹ቅዳ!› ሲሉት ጂኑን ይቀዳል፣ ‹ክፈት!› ሲሉት ጠርሙሱን ይከፍታል። እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ተጠቃቅሰን ግሮሰሪውን ጥለን ወጣን። ስሜታችን ግን በእጅጉ ተረባብሿል። ‹‹አንበርብር አሁን ያየነው እኮ የማዕበሉን ናሙና ነው…›› አለኝ። ‹‹የምን ማዕበል?›› አልኩት። ‹‹አሟረትክ አትበልና የጥፋት ማዕበል። አሁንማ እኛ ራሳችን ብዙውን ነገር ተላመድነውና ችላ ማለት ጀመርን። ቀስ በቀስ ለችግሮቻችን እጅ መስጠታችን ሳያንስ፣ ጭራሽ በአጭሩ መቀጨት የሚችል የትውልድ ነቀርሳ ሲዛመት ዝም ብለን እናያለን…›› እያለኝ እሱም ቤቱ እኔም ቤቴ ገባሁ። ምንድነው ባሉበት ተቀምጦ ከጥፋት፣ ከውድመትና ከዝቅጠት ጋር መላመድ? አንዳንዴ ሳስበው በርካታ ጉድለቶች እንዳሉብን ይገባኛል፡፡ ጉድለቶቻችንን መርምረን ችግራችንን ነቅሰን ካላወጣን በስተቀር መፍትሔ አናገኝም፡፡ ለመፍትሔው ደግሞ ራሳችንን መመልከት ይኖርብናል፡፡ ማን ነበር የተድበሰበሰ ችግር መጀመርያ የሚያጠፋው ባለቤቱን ነው ያለው? እባካችሁ ችግሮቻችንን አናድበስብስ፣ ችግሮች ሲድበሰበሱ አጥፊ ይሆናሉ፡፡ ይህንን ለመረዳት ግን ከአስመሳይነት የራቀ አስተዋይ ህሊና ሊኖረን ይገባል፡፡ አለበለዚያ የማዕበል ናሙና ወደ ጥፋት ውኃ ላለመቀየሩ ማስተማመኛ የለም፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት