በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲኖራቸው ከሚፈለጉ ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ነው፡፡ ዘርፉ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንዲሆንና ኢትዮጵያ ያላትን ያልተነካ የቱሪዝም ሀብት እንድትጠቀምም፣ መንግሥት የተለጠጡ ዕቅዶችን ሲያወጣ ይታያል፡፡ ምንም እንኳን መንግሥት ዕቅድ በማውጣት ከዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ከፍተኛ ቢያደርገውም፣ በርካታ ችግሮች ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ማነቆ ሆነዋል፡፡
በተለይም በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ ግጭቶችና የመሠረተ ልማት ችግሮች ከቱሪዝም መዳረሻዎች የሚገኘው ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ምክንያት ሆነዋል፡፡
የዘርፉ ባለሙያዎችም፣ በአገሪቱ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በአግባቡ ለመጠቀምና ውጤታማ ሥራ ለማከናወን የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበር ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ሙሉጌታ እንደገለጹት፣ የማኅበሩ መቋቋም በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን በአግባቡ ለመጠቀምና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ክህሎት ለማሳደግ ያግዛል፡፡
ከዚህ ቀደም ከ300 በላይ በመሆን ‹‹ሙያዬ ለአገሬ የበጎነት ማኅበር›› ብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አሁን በጋራ በመሆን ማኅበሩን መመሥረታቸውን ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡
ማኅበሩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተጎዳውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ታስቦ የተቋቋመ መሆኑን የተናገሩት አቶ አሸናፊ፣ ማኅበሩ በ228 አባላት መመሥረቱንና የአባላቱም ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
ማኅበሩ በዘርፉ በጥናትና ምርምር፣ በሥልጠናና በማማከር ሙያዊ አበርክቶውን ለመወጣት መነሳቱን ጠቅሰው፣ ከዚህም ባሻገር በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ምቹ የሥራ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን በማስተባበር ለአባላት የሥልጠና እንዲሁም የትምህርት ዕድሎችን ማቅረብና በሙያዊ ሥነ ምግባር የታነፁ ባለሙያዎችን መገንባት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባ ከኒውዮርክና ከጄኔቫ በመቀጠል ሦስተኛዋ የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ በመሆኗም፣ በከተማዋ የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች የሚመጥን ሙያዊ ብቃት እንዲኖር ማኅበሩ የበኩሉን ድርሻ የሚወጣ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከአገሪቱ አምስት የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ውስጥ አንዱ ሆኖ ከመመደቡ ጋር ተያይዞም፣ የፖሊሲ ግብዓቶች ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል እንደሚያቀርብ፣ እንደሚያወያይ፣ ካወያየም በኋላም ተፈጻሚነቱን አቶ አሸናፊ ተናግረዋል፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሰፊ እንደመሆኑ የተለያዩ ሥራዎችን ተደራሽ ለማድረግ ማኅበሩ እንደሚሠራ፣ ሥራው ተፈጻሚ እንዲሆን በዘርፉ ያለ ማንኛውም ባለሙያ አባል መሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
በአገሪቱ የተለያዩ ማኅበሮች እንዳሉ፣ እነዚህም የየራሳቸውን ድርሻ በመወጣት ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ማኅበራቸው በዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮችን በመፍታት የተሻለ እንደሚሠራ አስታውሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ሪዞርቶች፣ የቱርና የተለያዩ ተቋማት የማኅበሩ አባል መሆን እንደሚችሉና አባል ከሆኑ በኋላ የአካባቢውን ሁኔታ በማየት ክፍያ እንዲከፍሉ የሚደረግ መሆኑን አክለዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ሰዎች እንዳሉና እነዚህን በሥነ ምግባር ለማነጽ ማኅበሩ የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በፊት ‹‹በሙያዬ ለአገሬ›› በተሰኘው የበጎነት ንቅናቄ ባለሙያዎች ላሊበላ ድረስ በመሄድ 37 ሆቴሎችን ምን ዓይነት ችግር አለባቸው? ምንድነው የጎደለው? የሚለውን በመለየት የሙያ፣ የግብዓት እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገላቸው አቶ አሸናፊ አብራርተዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም ማኅበሩ ወደ ተለያዩ ክልሎች በመሄድ ከሙያዊ ሥልጠና በተጨማሪ፣ የተለያዩ ድጋፎች የሚያደርግ መሆኑንና ይህንን ከአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ማኅበሩ በተለይም በመሠረተ ልማት ማሻሻያዎችና በከተማዋ መዳረሻ የሚጎለብቱ ጅምር ሥራዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ይሆናል ብለዋል፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች፣ የኢንዱስትሪ ተዋናዮችና ባለድርሻ አካላት የሚሰባሰቡበት ዝግጅቶችና ኮንፈረንሶች ተግባራዊ እንደሚያደርግ ገልጸው፣ መድረኮችም የዕውቀትና የተለያዩ ልምድ ልውውጦች እንዲኖሩ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል፡፡