‹‹መጫኛው ወፊቾ ቀርቀባው ወፊቾ
የጉራጌ ነጭ ጤፍ እንዴነህ አሚቾ›› የሚል መንቶ ግጥም በኅብረተሰቡ ዘንድ ይታወቃል፡፡ የእንሰት ዋና ተክል ሥር የሆነው አሚቾ በቤተ ጉራጌ ዘንድ ተወዳጅ የሆነና በተለያየ መልኩ ለምግብነት የሚቀርብ ነው፡፡
ደጀኔ ደንደና፣ የጉራጌ ብሔረሰብ የሀገር በቀል ዕውቀቶች ትግበራ ጥናት በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ የአሚቾን ምንነትና ይዘት አብራርተዋል፡፡
የእንሰት ተክል ዋና ሥር አሚቾ ሲሆን፣ ከሌሎች ሥሮች የሚለየው ይህኛው ወደ ጥልቅ የሚገባ ሳይሆን፣ በጣም በመወፈርና በመስፋት አጫጭር ሌሎች ሥሮችን በማውጣት የዕድገት ደረጃውን ይጨርሳል፡፡ አጫጭር ሥሮች ጠቀሜታቸው ውኃና ማዕድናት ከመሳብ ውጪ ዋናውን ተክል ደግፎ እንዲቆም የሚደርገው አሚቾ መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹ስለዚህ ግንድ ሲፋቅ አሚቾ ደግሞ ይጨፈጨፋል፡፡ የተጨፈጨፈውን አሚቾ ከተፋቀው ግንድ ጋር በቅርጫት ውስጥ በመጭመቅ ውኃን በማጠራቀም ቡላ ይመረታል፡፡ ከዚህ የተረፈው ሥር አሚቾ ደግሞ ተቆራርጦና ተቀቅሎ ይበላል፡፡››
‹‹ኩችኩቻ የሚባልን ባህላዊ ምግብን ለማዘጋጀት አሚቾ ተፈላጊ ሲሆን፣ ቀድሞ ይቀቀልና ይከተከታል፡፡ በደቦ ሥራም ባህላዊ ቤት በሚሠራበት ወቅት ቅቤና ሚጥሚጣ ከሌሎች ቅመማ ቅመም እንደ ኮረሪማ፣ ነጭና ጥቁር አዝሙድ፣ ኮሰረት ተጨምሮ የሚዘጋጅ ባህላዊ ምግብ ነው፡፡
የጉራጌ ዞን ባህል መምርያ ባዘጋጀው ጉራጌና የባህል እሴቶች መጽሐፉ ከአሚቾ የሚዘጋጁ ምግቦች ብሎ ከጠቀሳቸው ዓይነቶች መካከል ፍንካች፣ ጥብስና ፍርፍር ይገኙባቸዋል፡፡
የተቀቀለው አሚቾ ተቆራርሶ በገበታ በማቅረብ በትኩስ ወተት፣ በእርጎና በአጓት የሚበላው ባህላዊ ምግብ የአሚቾ ፍንካች ሲሆን፣ የተቀቀለው አሚቾ በቀጭኑ በቢላ ተሸንሽኖ በምጣድ እያገላበጡ በመጥበስ በወተትና በወተት ተዋጽዖ የሚበላው ደግሞ የአሚቾ ጥብስ ነው፡፡ ሦስተኛው ዓይነት የአሚቾ ፍርፍር ሲሆን፣ የተቀቀለው አሚቾ በመከትከቻ መሣሪያ ተከትክቶ በትልቁ ገበቴ በማኖር በሚጥሚጣና በቅቤ ታሽቶ ይበላል፡፡ በተለይ የተለመደው በደቦ ትልልቅ ባህላዊ ቤቶች ሲሠሩና የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች ሲዘጋጁ የሚበላ ነው፡፡ አሚቾ ከመብልነት ባለፈም ለመድኃኒትነት ይውላል፡፡
የእንሰት ተክል በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ ሁሉም ነገር መሆን ይችላል፡፡ ቁርስ፣ ምሣ፣ እራት፣ እንደ ጊዜውና እንደ ወቅቱ ሁኔታ መባያውን ወይም አሠራሩን እየቀያየሩ መመገብ የተለመደ ነው የሚለው ብርሃነ ዓለሙ ገሣ ነው፡፡
እንሰት ‹‹አያ ልበ ጥኑ›› በጉራጌ በሚለው ጥናታዊ መጣጥፉ እንደገለጸው፣ የጉራጌ ብሔረሰብ በላቡ፣ በጥረቱ ኑሮን መቀየር እንደቻለ ሁሉ ባህላዊ ምግቦቹን በማስተዋወቁ ረገድም ከኢትዮጵያ እስከ ዓለም ዳርቻ አዳርሷል፡፡ ቆጮ፣ ክትፎና ቡላ በብዙዎች መዘውተር ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ጉራጌ ከእንሰት (ቆጮ)፣ ከክትፎና ከጎመን ጋር የረዥም ጊዜ ታሪክ አለው፡፡ አተር፣ ባቄላ፣ በቆሎ፣ ገብስ፣ ስንዴና የመሳሰሉት እንዳሉ ሆነው፡፡
እንደ እንሰቱ ዓይነት ባይበዛም የቆጮ ዓይነቶችም አሉ፡፡ ለአብነት ያህል ዘወትር የሚበላው አሻሻት፣ ለበዓልና እንግዳ ሲመጣ የሚዘጋጀው ዳፑዋ (ዳቡየ)፣ አልቧቦጫት፣ ብዙውን ጊዜ በጾም ወቅትና ለመንገድ ስንቅ የሚሆነው በቅመም የሚሠራው ቅሙስ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
እንደ ብርሃነ ዓለሙ ገሣ ሐተታ የእንሰት ዓይነቶች ከ50 በላይ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አስታራ፣ ባደዴት፣ አንቀፉየ፣ የሽራ ቅንቅይና፣ አጋዴ፣ ቅብናር፣ ጓርየ፣ እምርየ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከምግብነቱ በተጨማሪ እንደ እንሰቶቹ ዓይነት ለስብራት፣ ለሕመም መድኃኒትነት ያገለግላሉ፡፡ አንድ እንሰት ከመፋቁ በፊትም ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ለቤት መሥሪያና ለከብቶች ማሠሪያ ገመድ፣ ለከብቶች ቀለብ፣ ለተለያዩ ምግቦች ማዘጋጃ፣ ለመኝታ ቁሳቁሶች (ካፑዋት፣ ቀጭቀጨ)፣ ለሳሎንና ለወፈንቻ ምንጣፍነት (ጂፐ)፣ የደረቀው ክፍሉም እንጨት በሌለበት ለማገዶነት ያገለግላል፡፡
ቆጮ
ከቤተ ጉራጌ አልፎ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅ የሆነው ከእንሰት ተክል የሚዘጋጀው ቆጮ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለይ ክትፎ ሲበላ ለማባያነት በቀዳሚነት ይቀርባል፡፡
የደጀኔ ደንደና ጥናታዊ መድበል እንደሚገልጸው፣ ቆጮ ከእንሰት የሚገኝ ዋና ምርት ሲሆን የእንሰት ግንድን በመፋቅና በመቅበር ለምግብ ዋስትና የሚውል ዋና ባህላዊ ምግብ ነው፡፡ አሠራሩም መጨረሻ የዕድገት ደረጃ ላይ የደረሰውን እንሰት ግንዱን ቆራርጦ በመፋቅ እዚያው በተዘጋጀለት እንሰት ማሳ ውስጥ በተን ተደርጎ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ቅጠል ለብሶ እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ በመቀጠል የተበተነውን ከሰባት እስከ አሥር ቀናት ውስጥ ሰብሰብ ተደርጎ ባለበት ይከመራል፡፡
‹‹እንደ ምርቱ ብዛት ጉድጓድ ተመጥኖ ከጎርፍና ከቤት እንስሳት ንከኪ ውጪ ሆኖ ጓሮ በቅርብ ርቀት ላይ የሚቆፈር ሲሆን፣ በአሥራ አምስተኛው ቀናት በተዘጋጀለት ጉድጓድ የእንሰት ቅርጫፍ ያለ ኮባ ቅጠል በጥንቃቄ ድርድር ተደርጎ በሠልፍ ይነጠፋል፡፡ ቀጥሎ በላዩ ላይ የኮባ ቅጠል በወፍራሙ ይነጠፋል፡፡ መጨረሻ ላይ እነዚህ ሒደቶች ከተጠናቀቁ በኋላ ምርቱ ተከድኖ ዝናብና ውኃ እንዳይገባ ድንጋይ በላዩ ላይ ይጫናል፡፡ የቆጮ ምርት አቀባበር በዚህ መልኩ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ከሁለት ወር በኋላ በስሎ ለምግብነት ይውላል፡፡
የቆጮ ዋና ዋና ማባያዎች ደግሞ ክትፎ፣ ወተት፣ ጎመን፣ አሬራ፣ ዓይብና አጓት ሲሆኑ ለነዚህም በማባይነት ልዩ ልዩ የቆጮ ዓይነቶች በተለያየ የዕድሜ ዕርከን ለሚገኙ ይቀርባሉ፡፡
እንደ አጥኚው ገለጻ፣ አሻሻት ለበዓላት በኮባ ቅጠል፣ በአዘቦት ያለ ኮባ ቅጠል ተጋግሮ የሚበላ ቆጮ ሲሆን፣ በዕድሜ ለገፉ ሰዎች ለስለስ ተደርጎ ይዘጋጃል፡፡ ዳፐየ/ዳፑየ/ዳፗ፣ እርጥብ ወፍቾ ተጎዝጉዞ ከላይ እንደ ድፎ ዳቦ በመክደን የሚጋገር ቆጮ ነው፡፡
አልባቦጨት፣ ለበዓላት ብሎ በስሱ የሚዘጋጅ የቆጮ ቂጣ ነው፡፡ ቅመ/ሙስ/ቅርመስዮ/፣ ቆጮው ውኃ ሳይነካው በደረቁ የቆጮ ሊጥ ወፈር አድርጎ መጋገር ነው፡፡ ይህንን ምግብ ለታመመ ሰው፣ ለስብራት፣ ለአራስና በዕድሜ ለገፉ ሰዎች ለፈውስ ይሆናል ተብሎ ይበላል፡፡
ብራፕራት፣ ሴት ልጅ እንደወለደች ለደስታ ተብሎ ቤተሰብና ጎረቤት ጠያቂዎች የሚበሉት የቆጮ ዓይነት ነው፡፡ አጥርቁየ/ዬ፣ ለሕፃናት ተብሎ እንሰት ሲፋቅ ለቆጮ የተዘጋጀውን በቃጫ በመጭመቅ ከረጋ በኋላ ወዲያው ተጋግሮ የሚበላ ነው፡፡
ቡላ እና ዓይነቶቹ
በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የጥናትና ምርምር የባህል ጥናት ተመራማሪው አቶ ደጀኔ ደንደና ሐተታ መሠረት የቡላ መገኛው ለቆጮ ተብሎ ከሚፋቀው ግንድ ውስጥና አምቾ ተጨፍጭፎ ከሚወጣ ፈሳሽ ውኃ ነው፡፡ ባለሙያዎቹ ግንዱን በሚፍቁበት ወቅት መሬቱ ጎርጐድ ተደርጎ የኮባ ቅጠል ይነጠፍና ፍሳሹ እንዲጠራቀም ይደረጋል፡፡ በዚህ መልክ ተጠራቅሞ የረጋውን ፈሳሽ በኮባ ቅጠል ተጠቅልሎ ቆጮ ጉድጓድ ውስጥ በቆጮ መሀል ይገባል፡፡ ይህም እንዳይደርቅና እንዳይበላሽ ለማድረግ ነው፡፡ በእንዲህ ሁኔታ የተዘጋጀው የቡላ ምርት ከወተት ጋር በገንፎ፣ በሙቅ መልክና በሌላ የአመጋገብ ዘዴ ለአገልግሎት ይውላል፡፡
ቡላ በተለይ ለበዓላት፣ ለወለደች ሴት፣ በስብራት ለታመመ ሰው ፍቱን መድኃኒት ነው ተብሎ እንደሚታሰብ ልዩ ልዩ ምግቦችም ከቡላ በገንፎ፣ በፍርፍርና በቂጣ መልክ እንደሚዘጋጁም ጠቅሰዋል፡፡
ገንፎው ለበዓላት፣ በዕድሜ ለገፉ ሰዎች፣ ለስብራት፣ ለአራስና ለሕፃናት ጠዋት ጠዋት በባዶ ሆድ የሚበላ ሲሆን፣ ፍርፍሩ ደግሞ ለእንሰት ተከላ ለደቦ፣ ለአራስ፣ ታዋቂ ሰዎች ሲሞቱ ለጉድጓድ ቆፋሪዎች ተብሎ ይዘጋጃል፡፡ ለመስቀል በዓል ከሩቅ ለሚመጡ የቤተሰብ አባላት ከዓይብ ጋር ተዘጋጅቶ የሚበላው ቂጣው ይሆናል፡፡
አዲሱ ዓመት የዘመን መለወጫ ሲመጣ ከሚበሉት ባህላዊ ምግቦች መካከል ብራፕራት /ብራብራት፣ እርግፎን ይገኙበታል፡፡
እንደ አጥኚው ሐተታ፣ ቡላ ደርቆ ጠፈፍ ካለ በኋላ ምጣድ ላይ እንደ እንኩሮ በሰል ተደርጎ ከታመሰ በኋላ የተፈረፈረው በቅቤ ይታሻል፡፡ ለመብልም ይሁን ለሌሎች ዝግጅቶች በተለይ ለአዲስ ዓመት አቀባበልና ለእንሰት ተከላ በደቦ ለተሳተፉት ከቆጮ ጋር የሚዘጋጅ ባህላዊ ምግብ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ከእንሰትና እንሰት ተዋጽኦ የሚዘጋጁ በርካታ ባህላዊ ምግቦች የእንሰት ተክል አምራች በሆኑ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ አንዱ አታካኖ የሚባል ባህላዊ ምግብ ከቡላ የሚዘጋጅ ሲሆን ቅቤና ዓይብ ይጨመርበታል፡፡
ሔኖክ ሥዩም ባዘጋጀው ቱባ መጽሔቱ እንደተገለጸው፣ በወላይታ ብሔረሰብ ዘንድ የሚታወቀው ሙቾ ከተጨመቀ ቡላ የሚሠራ ባህላዊ ምግብ ነው፡፡ እንዲሁም ባጭራ በዳውሮዎች የሚታወቀውና ከቡላ የሚዘጋጀው ይህ ባህላዊ ምግብ በተመሳሳይ በቅቤና በዓይብ ይበላል፡፡ በጋሞዎች ተወዳጅ የሆነው ፌቴላ ደግሞ ከቆጮ ታሽቶ በሚገኝ ቡላ የሚዘጋጅና ከበሰለ ጎመን ጋር በዳጣ ወይም በሚጥሚጣ የሚበላ ነው፡፡
የእንሰት ተክል ከምግብነት ከቆጮና ቡላ ውጪ ቅጠሉ ለክትፎ፣ ለጎመንና ለዓይብ መብያነት፣ ለዳቦ መጋገሪያነት፣ ለመተኛነት፣ ለልዩ ልዩ ዝግጅት ለማስዋቢያነት እንደሚጠቅም፣ ቅርንጫፉ ሲደርቅ በወፍጮ መልክ ለቤት መሥሪያነትና ለገመድ እንደሚያገለግል፣ ከሚፋቀው ግንድ የሚወጣ ቃጫ ደግሞ ለጂባና ለሌሎች ቁሳቁሶች መሥሪያነት እንደሚውል በመጽሐፉ ተገልጿል፡፡
እንሰት (ቆጮ) ከጉራጌ ሕዝብ ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ከሚገልጹት መካከል ምሳሌያዊ አነጋገሮቹ ይገኙበታል፡፡ ብርሃነ ዓለሙ ገሣ እንዲህ ከትቧል፡፡
‹‹ኧሰት አሸኹ ባባኔ – ቲረቁሪ በሲፍ፣ ቲጫፑሪ በሣራ›› (እንሰት አየሁ አባቴ ጋ ሲነቀል በወስፌ፣ ሲጫር በሰንጢ)፣ ‹‹አማት ተመራት፣ ኧሰት ተዋራት›› (አማትና ምራት፣ እንሰትና ዋርያት)፣ ‹‹ኦዥወት፣ ተብና ቤት፤ ተዝራብ ኧሰት›› (ሰነፍ ሴት ዝናብ በሌለበት እቤት፣ እየዘነበ ግን የእንሰት ሥራ ልትሠራ ወጣች)፣ ‹‹አስታራ ጭዛንሁ የባሬ፣ ሰንዳ በሣወም›› (አስታራ /ለመድኃኒትነት የሚፈለግ የእንሰት ዓይነት ነው/ መድኃኒት እሆናለሁ ብሎ ቢላዋ በዛበት)፣ ‹‹ያንጨነዊ ትከ ኤኸር፣ በዘር የፏቊ ውሣ ኤኸር›› (ያልወለዱት ልጅ አይሆን፣ በክረምት የፋቁት ውሣ (ቆጮ) አይሆን)፡፡