ምነዋ እዚህ አገር
አነሰ የእብዱ ቁጥር።
ተከልክሎ ነው በውድ
ሰዉ የተወው ማበድ
ሰው ባገሩ በወንዙ ማበድ መወፈፍ ካልቻለማ
ምን አገር ሆነ ያማ!
እብድ የሌለውስ አገር
ምኑን አገር ነው ከምር።
ዜጋ አብዶ ገዱ ተንጋዳ
ነካ ነካ ካላረገው፣ በገዛ አገሩማ ጓዳ፣
ቢሻው ካልተሸማቀቀ፣ እገዛ ቤቱ እንደ እንግዳ፣
ወይ ከት ከት ብሎ ካልሳቀ፣ አሊያም ድንገት ካልተቆጣ፤
ወፈፍ ወፈፍ ካላረገው፣ የእብደት አብሾ እንደጠጣ፤
እንዲህ እንዲያ ካልሆነማ
ምን አገር አለው እሱማ።
እብድማ ካልተዋጣላት
አገሩሳ ምን ሰው አላት!
አገሩሳ ምን አገር ናት!!
እብድ የሌለውስ አገር
ምኑን አገር ነው ከምር።
ሁላችን አንዴ ብናብድ፣
አይኖርም ነበር እብድ።
ኧረ እንበድ እንበድ
ኧረ ጎበዝ እንበድ!!!
(ነፃነት ለጠማቸው ተባብረው ማበድ ለተሳናቸው ያገር ልጆች) ጥር 1984 ዓ.ም.
– ነቢይ መኰንን ‹‹ጥቁር ነጭ ግራጫ››