‹‹ተለያይተናል! አትረብሽኝ›› የሚለው መልዕክትህ ደርሶኛል። ስትጽፈው በቁጣ ተሞልተህ የነበረ ትመስላለህ። መቼ ነው የተለያየነው? ለመለያየት ሁለት ሰዎች መስማማት አልነበረባቸውም? እስከማስታውሰው ድረስ በመለያየታችን እኔ አልተስማማሁም። ስለዚህ አልተለያየንም! አንተ ግን መቼ ይሆን የመለያየት ትክክለኛ ትርጉሙ የሚገባህ? ፍቅር በየቀኑ በመተያየት፣ አብሮ በመዋልና ማዕድ በመጋራት ብቻ ይለካል ያለህ ማነው? … መኮራረፍን መለያየት ያደረገውስ? ‹‹ሀፒይ አንቨርሳሪ የኔ ፍቅር ስትመጣ እንቅልፍ ወስዶኝ ካገኘከኝ የምትወደውን ላዛኛ ሠርቼ ፍሪጅ ውስጥ አድርጌልሃለሁ›› ማለት ይኼን ያህል ያስቆጣል?
ዛሬ ከተጋባን አንድ ዓመት ስለሞላን ‹‹እንኳን አደረሰህ›› ባልኩህ ተለያይተናል ትለኛለህ አንዴ? በእርግጥ ድምፅህን ከሰማሁት ቆይቻለሁ። በዓይነ ሥጋ ከተያየን ሰንበትበት ብለናል። በእኔ በኩል እስከ ዕለተ ሞታችን አብረን ልንሆን አምላካችን ፊት ቃል በገባነው መሠረት ለቃሌ ታምኜ እየኖርኩ ነው።
ትዳር ማለት ተስፋ አለመቁረጥ ነው። ትዳር ማለት ለሁለተኛ ዕድል በርን ገርበብ አድርጎ ማደር ነው። አትሳሳት አልተለያየንም። ተለያይተን ቢሆን ኖሮ በሬን እንደጭኔ ቆልፌው እተኛ ነበር?
አንተስ ብትሆን እስካሁን ባይቆርጥልህ ነው’ንጂ፤ አንድ ላይ ባንሆን ኖሮ አዲስ ሴት መልመድ ያቅትሃል? አየህ ውዴ! … ይህች አብረን የኖርንባት የመጀመሪያው የትዳር ዓመታችን የፈተና ጊዜያችን ናት። ግዴለህም … ለመጋባት የሁለት ሰው ፍቃድ አንዳስፈለገን ሁሉ፤ ለመለያየትም የሁለታችን ውሳኔ ይሁን።
- እስከዳር ግርማይ ‹‹ናፍቆት››