ራንድ ‹‹አትላስ›› (Atlas) የሚለውን ቃል የወሰደችው ከጥንታዊ ግሪክ አፈ ታሪክ ነው፡፡ አፈ ታሪኩም እንደዚህ ነው፡- በጥንታዊ ግሪክ አፈታሪክ ውስጥ በፍልስፍና፣ በሒሳብና በአስትሮኖሚ ሊቅ የነበረ ‹‹Atlas›› የሚባል ከቀደምት አማልክት (Titans) መካከል ነበር፡፡ ዓለምን ለማስተዳደር በቀደምቶቹ አማልክት (Titans) እና በወጣቶቹ አማልክት (Olympian Gods) መካከል አሥር ዓመታት የፈጀ የTitanomachy ጦርነት ይካሄዳል፡፡ በስተመጨረሻም፣ በዚየስ (Zeus) የሚሩት ወጣቶቹ አማልክት ጦርነቱን ያሸንፋሉ፡፡ ዚየስም ቀደምቶቹን አማልክት (Titans) በሙሉ ያስራቸዋል፡፡ ከቀደምቶቹ አማልክት መካከል የጦርነቱ መሪ የነበረውን አትላስ ላይ ግን አንድ ለየት ያለ ቅጣት ይጥልበታል፤ ይሄውም በምድር ምዕራባዊ ጫፍ ሄዶ መሬትንና መላውን ጠፈር ለዘልዓለም እንዲሸከም ይፈርድበታል፡፡ አትላስም በፅናትና በጥንካሬ ይሄው ዓለምን ተሸክሟት ይኖራል፡፡ ይሄ የአትላስ አፈታሪክ በሆሜርና በሒሲየድ አፈ ታሪኮች ውስጥ የሰፈረ ሲሆን፣ ይሄንን አፈ ታሪክ መሠረት በማድረግም ዓለምን የተሸከማት አትላስ በተለያዩ ሥዕሎችና ቅርፃቅርፆች ተሠርቶ ይገኛል፡፡ በኪነ ጥበብና ሥነ ፅሁፍ ሥራዎች ውስጥም ‹‹አትላስ›› የፅናትና የጥንካሬ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ አየን ራንድም ‹‹አትላስ›› ን ‹‹The heavy lifter of the society›› በማለት ለታዋቂ ሥራዋ ‹‹Atlas Shrugged›› ርዕስ አድርጋዋለች፡፡
- ዮናስ ታደሰና አሞን በቀለ ‹‹የፍልስፍና ትምህርት››