Tuesday, September 26, 2023

የወልቃይትና ራያ ጉዳይ በሕግ የሚፈታበት አግባብና ፈተናዎቹ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በወልቃይትና የራያ ጉዳዮች ላይ የሚነሳው ሙግት ሁለት ዓይነት የውዝግብ ምንጭ ያለው ነው፡፡ አንዱ ጥያቄው በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ያለ የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ነው የሚል ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ከአስተዳደር ወሰን ወይም ከድንበር ይገባኛል ጋር በተያያዘ ሳይሆን፣ የጉዳዩ መነሻ የማንነት ጥያቄ ነው የሚል ነው፡፡ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ በጥያቄው ምንነት ላይ የሚነሱ ሙግቶችን ብቻ ሳይሆን፣ በአፈታት ሒደቶችና ቅደም ተከተሎች ላይም ተጨማሪ ውዝግብ የሚያስነሳ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

የአማራና ትግራይ ክልሎችን ሲያወዛግብ የኖረው የወልቃይትና የራያ ጉዳይ በሕግ ይፈታ በሚለው ላይ ብዙዎች ቢስማሙም፣ በየትኛው የሕግ ቅደም ተከተል መፈታት እንደሚችል ግን የሚያስማማ ሐሳብ ብዙም አይደመጥም፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዋጅ በሚደነግገው ቅደም ተከተል? ወይስ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 ድንጋጌ? የሚለው ገና አልለየለትም፡፡

በሌላ በኩል ጉዳዩ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መጋቢት 2014 ዓ.ም. በፀደቀው የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰንና የግጭት አፈታት አቤቱታ አቀባበል፣ አያያዝና ምላሽ አሰጣጥ መመርያ ዕልባት ያግኝ የሚለው ገና አልታወቀም፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ኃላፊነትን ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1261/2013 የወልቃይትና የራያ ውዝግብን ለመገላገል አመቺ መንገዶች አሉት የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በብዙዎች ዘንድ ተደጋግሞ የሚጠቀሰው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 የአከላለል ለውጦች ተብሎ በተቀመጠው አንቀጽ ዕልባት ማግኘት የሚችል ጉዳይ ስለመሆኑም ይነገራል፡፡

እስከ ደም አፋሳሽ ጦርነት የደረሰው የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ዛሬም ቢሆን የበረደ አይመስልም፡፡ ሁለቱ አካባቢ በቀጣይም የሌላ ዙር ግጭት ምንጭ እንዳይሆን በእጅጉ ሥጋት አለ፡፡ የግጭት መንገዱ ተሞክሮ ዘላቂ መፍትሔ አለማምጣቱ ላይ መግባባት የተፈጠረ ቢመስልም፣ በሁለቱም ወገን የቃላት ውርወራውና መገባበዙ አሁንም አለመቆሙ ብዙዎችን ያሠጋል፡፡ ከግጭት በመለስ ጉዳዩ በሕግ ዕልባት ያግኝ ወደሚለው ሲመጣ ደግሞ፣ በዚህ መንገድ ሊኖር የሚችለው የችግሩ አፈታት ሒደት ብዙ እያከራከረ ነው፡፡

በምንም መንገድ ቢሆን ጉዳዩ የአገሪቱን ሕጎችና ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች የሚፈትን እንደሆነ ብዙዎች ይገምታሉ፡፡ ለአብነት ያህል የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ኃላፊነትን ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1261/2013 ክፍል አራት አለመግባባቶችን ስለመፍታት በሚል ርዕስ ሥር፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሎች መካከል ወይም በፌደራል መንግሥትና በክልል መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሔ እንደሚፈልግ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ከአንቀጽ 33 ጀምሮ የአወዛጋቢ ጉዳዮች ጥያቄ እንዴት መቅረብ እንዳለበትና በምን አግባብ እንደሚፈታ አዋጁ በሰፊው ይዘረዝራል፡፡ የውዝግብ ምንጭ በሆኑ ጉዳዮች ተወዛጋቢዎቹ አካላት ውይይትን በማስቀደም በንግግር ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አዋጁ በተዋረድ ያስቀምጣል፡፡ በተወዛጋቢዎቹ መካከል ውይይት ችግር መፍቻ ካልሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በጉዳዩ ጣልቃ እንደሚገባ ሕጉ ይጠቅሳል፡፡

አዋጁ ወደ አንቀጽ 37 ሲሸጋገር ደግሞ የአስተዳደር ወሰን ውዝግብን ስለሚዳኝበት መንገድ ይገልጻል፡፡ በተራ ቁጥር አንድ ላይ የቀረበው ጥያቄ የአስተዳደር ወሰን ውዝግብን የሚመለከት ከሆነ ምክር ቤቱ የሕዝብን አሠፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይወስናል ተብሎ ተቀምጧል፡፡ በተራ ቁጥር ሁለት ደግሞ ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 በተቀመጠው ቅደም ተከተል መሠረት ውሳኔ ይሰጣል የሚል ድንጋጌ ሠፍሯል፡፡

በተከታዩ አንቀጽ 38/1 ደግሞ ምክር ቤቱ የሕዝቡን አሠፋፈር በማጥናት አካባቢው ወደየትኛው ክልል መካለል እንዳለበት ለመወሰን የሚያስችል በቂ መረጃ እንዳለው ካመነ በዚያው መሠረት ይወስናል ይላል፡፡ በአንቀጽ በ38/2 ደግሞ ምክር ቤቱ የሕዝቡን አሠፋፈር በማጥናት አከራካሪው አካባቢ ወዴት መካለል እንዳለበት ለመወሰን የማይቻል መሆኑን ካመነ፣ የሕዝቡን ፍላጎት መጠየቅ ይኖርበታል በሚል ተደንግጎ ይገኛል፡፡  

ሕዝበ ውሳኔ የሚለውን የግልግል መፍትሔ በተከታዮቹ አንቀጾች በዝርዝር የሚያብራራው አዋጁ ሒደቱ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደሚካሄድ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ በአንቀጽ 40 ሥር ደግሞ ማን በሕዝበ ውሳኔው እንደሚሳተፍ በዝርዝር ያሠፈረ ሲሆን፣ በድንበር ውዝግብ ተገደው አካባቢውን የለቀቁ ሰዎች ድምፅ የመስጠት መብታቸው እንደሚከበር ነው የሚደነግገው፡፡

ይህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዋጅ በተጨባጭ የወልቃይትና የራያ ጉዳዮችን ስለሚዳኝበት ሁኔታ ብዙ አሻሚ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ የወልቃይትና የራያ ጉዳይን ለመፍታት የትግራይና የአማራ ክልሎች በውይይት ጥረት ያደረጉበት ሁኔታ የለም፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የራሱ ሕግ ባስቀመጠው መሠረት ጉዳዩን አጥንቶ መረጃ አሰባስቦ ለመወሰን የቱን ያህል ርቀት እንደሄደ የሚታወቅ ነገርም የለም፡፡ አሁን ስለሕዝበ ውሳኔ ጉዳይ ብዙ ሲባል ቢሰማም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በዚህ መንገድ ይፈታ ስለማለቱም የተጨበጠ ነገር የለም፡፡

በቅርቡ የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የአሸንዳ በዓልን አስታከው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ላይ የሁለቱም ክልሎች አመራሮች፣ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት በጋራ ሆነው ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ችግሩ በሕጋዊ መንገድ እንደሚፈታ ገልጸው ነበር፡፡ ሚኒስትሩ አክለውም የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቦታቸው እንደሚመለሱና ችግሩን በሕዝበ ውሳኔ ለመፍታት እየተሠራ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በቅርቡ የአማራ ክልል አዲስ አስተዳደር ሲደራጅ ወደ ኃላፊነት የመጡት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አረጋ ከበደ ይህን ውድቅ የሚያደርግ አስተያየት ሲሰጡ ተደምጠዋል። አንዳንዶች በየሚዲያውና በአገኙት መድረክ የአማራ ክልል ሕዝብን ጥቅም የሚጎዳ ያልተጨበጠ መረጃ እያሠራጩ መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ በበዓለ ሲመታቸው መናገራቸው አይዘነጋም።

ከወልቃይትና ከራያ ጉዳዮች የሕግ ዳኝነት ጋር በተገናኘ ጥያቄ የቀረበላቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የሕግ ባለሙያ፣ ጥያቄው ሁለቱንም ማለትም የወሰንና የማንነትን ጥያቄዎች ይዞ መቅረቡን ገልጸዋል። ጥያቄው የአስተዳደር ወሰንንም የማንነት ጥያቄንም ይዞ ከቀረበ እንዴት ይፈታል የሚለው ጉዳይ በጥንቃቄ እንዲታሰብበት ያሳስባሉ፡፡

የወልቃይትና የራያ ጥያቄ ሁለቱንም ይዞ የተነሳ መሆኑን ያሰመሩበት የሕግ ባለሙያው፣ ሕጉ ሁለቱንም ዓይነት ጥያቄ ተቀብሎ የሚያስተናግድበት የራሱ አግባብ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በእሳቸው ግምት ጥያቄዎቹ እንዳቀራረባቸው በአንድ ላይም ሆነ በተናጠል ሊፈቱ የሚችሉበት የሕግ አግባብ መኖሩን ይሞግታሉ፡፡ በየትኛው መንገድ ጉዳዩን መፍታት የተሻለ እንደሆነ መጠየቅ ያለበት ግን የፌደሬሽን ምክር ቤት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ አሁን ላይ ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በዚህ መንገድ ልፍታው ብሎ ግልጽ ባለማድረጉ በዚህ ላይ ሐሳብ መስጠት እንደሚቸገሩ ነው ያከሉት፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕዝበ ውሳኔ ችግሩን ለመፍታት አቅጣጫ ስለመቀመጡ በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ሁለቱ አካባቢዎች ገብቶ ተቋቁመው የነበሩ የአስተዳደር መዋቅሮችን ማፍረሱና አካባቢውን በሥሩ ማስተዳደር ስለመጀመሩ በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡ በራያም ሆነ በወልቃይት የታጠቁ ኃይሎች በመከላከያው ስለመተካታቸው ብዙ ሲወራም ነበር፡፡ መከላከያ ሠራዊቱ በተረከባቸው በእነዚህ ቦታዎች የሥልጠና ሰነድ አዘጋጅቶ ከአካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ ለማስፈር ዝግጅት እያደረገ መሆኑም ተነግሯል፡፡ በአካባቢው ከሁሉም የተውጣጣ ጊዜያዊ የሽግግር ጊዜ አስተዳደር የመፍጠር ፍላጎት እንዳለም የተነገረ ሲሆን፣ በሒደት ደግሞ በቀጣናው ሕዝበ ውሳኔ ለማደራጀት ዕቅድ መያዙ ሲነገር ሰንብቷል፡፡

ይህን ሁሉ ያልተጨበጠ ወሬ ነው የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ በአካባቢው ተቋቁሞ የነበረው አስተዳደር በአማራ ክልል ስለተቋቋመ እሱ ተቀይሮ በቦታው ሁሉንም ያማከለ ጊዜያዊ አስተዳደር ይመሥረት የሚል አቅጣጫ ነው ያለው ይላሉ፡፡ ከዚህ ውጪ የአካባቢው አስተዳደር ከመከላከያው ጋር ተግባብቶና ተናቦ እንደሚሠራ የተናገሩት ባለሙያው፣ የአካባቢውን አስተዳደር በተመለከተ ሕጋዊ ርክክብ ከተደረገ በኋላ በቦታው ሁሉን አቀፍ አስተዳደር ተመሥርቶ ጥያቄውን በሕግ ወደ መፍታት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ሕጋዊ መፍትሔ ብሎ ሲያስቀምጥ፣ ያን ጊዜ ያስኬዳል አያስኬድም በሚለው ጉዳይ ላይ መወያየት ይቻላል ብለው ነው ሐሳባቸውን ያጠቃለሉት።

ስለዚሁ ሁኔታ ጥያቄ የቀረበላቸው የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ በላይ መንግሥቴ (ዶ/ር)፣ በቅርበት በሚከታተሉት የራያ አካባቢ ሕዝበ ውሳኔ የመደራጀቱ ጉዳይ ጎልቶ መነሳቱን አረጋግጠዋል። ‹‹ሕዝቡ በሕጋዊ መንገድ እስከሆነ ሕዝበ ውሳኔ እንደ አማራጭ መቅረቡን አይጠላውም። በሕዝበ ውሳኔ ይዳኝ መባሉን የራያ ሕዝብ አያሠጋውም፣ እንዲያውም ሲጠይቀው የነበረ ነው። ሕዝበ ውሳኔ ሲባል በተፈናቃይ መልሶ ማስፈር የአካባቢው ነዋሪ ያልነበሩ ሰዎች መጥተው ድምፅ በመስጠት ውሳኔውን ሊያፋልሱት የሚችል ሥጋት አለ። ነገር ግን በራያ አካባቢ ይህ አያሠጋም። ምክንያቱም በእያንዳንዱ ቀበሌ ማን ይኖር እንደነበርና እንደተፈናቀለ በጥንቃቄ በሕዝቡ ተሳትፎ ተመዝግቧል። የአካባቢው ሕዝብ በተፈናቃይ ተከልሎ ከውጪ የሚመጣውን ሰው ይለያል። ስለዚህ በራያ ተፈናቃይ መልሶ ማስፈርም ሆነ ሕዝበ ውሳኔ የሚያሠጋ ጉዳይ አይሆንም፤›› በማለት ምልከታቸውን አጋርተዋል።

አሁን የአካባቢው መዋቅር እንዳልፈረሰ ያረጋገጡት በላይ (ዶ/ር)፣ ከመከላከያ ጋር ተናቦ እየሠራ መሆኑንም አመልክተዋል። መዋቅሩ ሁሉንም ባካተተ መንገድ እንደ አዲስ ይደራጅ መባሉን ያወሱ ሲሆን፣ ይህም በሕዝቡ ዘንድ የፈጠረው ቅራኔ አለመኖሩን አስረድተዋል። ስለራያ ጥያቄ ምንነት ወደ ትግራይ ልግባ፣ ወደ አማራ ልካለል ወይም የራሴ ራያ ማንነት ያለኝ ስለሆነ ራሴን ችዬ ልደራጅ የሚል ሦስት ዓይነት መንገዶችን የተከተለ ስለመሆኑ የተጠየቁት በላይ (ዶ/ር)፣ ‹‹የራያ ማኅበረሰብ ቀድሞ በወሎ አስተዳደር ሥር ነኝና ወደ አማራ ክልል ልካለል፤›› የሚል ጥያቄን በሰፊው ማንሳቱን ተከራክረዋል፡፡ የራያ ማንነት አለን ወይም ወደ ትግራይ መግባት አለብን የሚሉት ወገኖች አላማጣ ገብተው እንኳን በነፃነት መንቀሳቀስ የማይችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ 

‹‹የወልቃይት ጉዳይ ሊዘገይና ጊዜ ሊያስፈልገው እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ በራያ በኩል ግን በሕጋዊ መንገድ እስከመጣ ድረስ ተፈናቃዮችን የማስፈሩም ሆነ ሕዝበ ውሳኔ የማድረጉ ጉዳይ መፍትሔ መሆን ይችላል፡፡ ሁለቱ ክልሎች በድርድር ችግሩን ቢፈቱት ኖሮ ለሁሉም ወገን አትራፊ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ባለመሆኑ ጉዳዩ ሄዶ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ደርሷል፡፡ አሁን የሚጠበቀው ምክር ቤቱ የሚሰጠው ሕጋዊ መፍትሔ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስለአካባቢው ሁኔታ ያጠናበትን አጋጣሚ እንደሚያስታውሱ ገልጸው፣ ከወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ጋርም በመተባበር ስለሁኔታው መጠናቱን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ወደ ሕዝበ ውሳኔ ሳይገባ ተጨባጩን ሁኔታ አገናዝቦ እስካሁን አለመወሰኑን አክለዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የደረሰው የወልቃይትና የራያ ጉዳይ በምን የሕግ አግባብ ዕልባት እንደሚያገኝ በጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡ ሕዝበ ውሳኔ የሚለው ከሰሞኑ ገዝፎ እየተነገረ ያለ ጉዳይ ቢሆንም፣ ነገር ግን በራሱ የአካባቢዎቹን ተጨባጭ ሁኔታ አጥንቶ ውሳኔ የሚሰጥበት ዕድልም መኖሩ በተለያዩ ሕጎች ላይ ተቀምጧል፡፡

ይህ ጥያቄ ሙግቱ ከቀጠለ ግን በሒደት የሕገ መንግሥት አተረጓጎም ጥያቄ ያስነሳል ተብሎም ይገመታል፡፡ የሕገ መንግሥት አተረጓጎም ጥያቄ ከሚያስነሱ ጉዳዮች ተብለው ከተቀመጡት አንዱ፣ በፌደራል መንግሥትና በክልሎች መካከል አለመግባባቶች ሲፈጠሩ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ ሌላው ደግሞ በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች መሆኑ ሠፍሯል፡፡

ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሕግ ውዝግብ ያስነሳል ተብሎ የሚጠበቅ ጉዳይ ሲሆን፣ በሒደት የሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ጥያቄን የሚያስነሳ ስለመሆኑ በአንዳንዶች ዘንድ እየተገመተ ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 የአከላለል ለውጦች ተብሎ እንደሠፈረው የክልሎችን ወሰን ጥያቄ በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት ይፈጸማል ተብሎ ተቀምጧል፡፡ ክልሎቹ መስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝቡን አሠፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ እንደሚወስንም አንቀጹ ይገልጻል፡፡ ይህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ደግሞ ከሁለት ዓመት ጊዜ በላይ ሊወስድ እንደማይችል ነው አንቀጹ የሚገልጸው፡፡ የወልቃይትና የራያ ውዝግብ ሁለት ዓመት ያለፈው ቢሆንም፣ ይህን ቁርሾ በሕግ ዕልባት ለመስጠት እስካሁን የተቻለም አይመስልም፡፡ ለዚህ ይመስላል አንዳንድ ወገኖች ጉዳዩ ሆን ተብሎ ለፖለቲካ ትርፍ መግዣ በመንግሥትና በሚመለከታቸው ወገኖች ተጓቷል የሚል ክስ ሲያቀርቡ የሚደመጠው፡፡ ኢትዮጵያ አጨቃጫቂ የድንበርም ሆነ የማንነት ጥያቄ መፍታት የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች እንዳላት በሰፊው ቢነገርም፣ ይህ የሕግ ማዕቀፍ ግን በወልቃይትና በራያ ውዝግብ አፈታት ሊፈተን የቀረበ ይመስላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -