Saturday, July 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት የተደረገበት የሠራተኞች የኢኮኖሚ ጥያቄ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ለዓመታት ሲጠይቋቸው የነበሩ ጥያቄዎች ሰሚ አጥተው ስለመቆየታቸው በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ሠራተኞች አንገብጋቢ ጥያቄዎች ናቸው ተብለው በኢትዮጵያ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በኩል ለቀረቡ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ መንግሥታዊ አካል እንኳን ማግኘት አቅቷቸው ‹‹የሰሚ ያለህ!›› በማለት ድምፃቸውን ሲያስተጋቡም መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡

በተለይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እየከፋ የመጣው የዋጋ ንረት በሠራተኛው ላይ እያሳረፈ ያለውን ተፅዕኖና መለስተኛ መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን በማመላከት መንግሥት ዕርምጃ ይወስድ ዘንድ ኢሠማኮ በተደጋጋሚ ውትወታ ቢያደርግም ሰሚ ጆሮ ማግኘት አልቻለም ነበር ወይም በዝምታ ለማለፍ ተመርጧል።

ኢሠማኮ መሠረታዊ የሚባሉ የሠራተኞች ጥያቄዎችን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ባለሥልጣናት ከማቅረብ ባሻገር፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በዚሁ ዙሪያ ለመወያየት በተደጋጋሚ በደብዳቤ ጭምር መጠየቁን ያስታውሳል፡፡ ባሉ ችግሮች ዙሪያ መፍትሔ ለመፈለግ ቢያንስ የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ያቀረባቸው ተደጋጋሚ ጥያቄዎች በዝምታ በመታለፋቸው፣ ከጥቂት ወራት በፊት የተከበረውን የሠራተኞች ቀን የሠራተኞች ድምፅ እንዲሰማ ጫና ለማድረግ የአደባባይ ሠልፍ እስከ መጥራት ደርሶ ነበር።

ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ ሰሚ ያጣው የኢሠማኮ ውትወታ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ ያልተጠበቀ ምላሽ አግኝቷል። በዚህም የኢትዮጵያ ሠራተኞች መሪዎች የዓመታት ውትወታቸው ሰምሮ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ተገናኝተው በችግሮቻቸው ዙሪያ ለመምከር ዕድል አግኝተዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ለመጀመርያ ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ለመምከር የቻሉበት ዕድል የተፈጠረው ረቡዕ ነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር፡፡

ረቡዕ ዕለት የነበረውን መድረክ አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ የሠራተኞች ጉዳይን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገ የመጀመሪያው የምክክር መድረክ ሲሉ ገልጸውታል፡፡ የኢሠማኮ አመራሮችና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የባለሥልጣናት ቡድን ያደረጉት ውይይት ሦስት ሰዓታትን የፈጀ ነበር፡፡ ውይይቱ ታሪካዊና ባልጠበቁት መንገድ የተካሄደ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ካሳሁን፣ አሉ የሚባሉ የአገሪቱ ሠራተኞች ጥያቄዎችን በሙሉ አንስቶ ለመወያየት ዕድል የሰጠ መድረክ እንደነበር ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም በመንግሥት ምላሽ እንዲያገኙ ሲያቀርቧቸው የነበሩ ጥያቄዎች በሙሉ በተጠናቀቀው ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረው የውይይት መድረክ ላይ ሰፊ ጊዜ ተሰጥቷቸው መደመጥ የቻሉበት መሆኑና የውይይቱ አጠቃላይ ሁኔታም እንዳረካቸው አቶ ካሳሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል።

ኢሠማኮ ከዚህ በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የጻፍናቸው የተለያዩ ደብዳቤዎች የነበሩ ቢሆንም፣ በተጠናቀቀው ሳምንት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ይሁንታ አግኝቶ ውይይት ሊደረግ የቻለው በሐምሌ 2015 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈ ደብዳቤን መሠረት በማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል። የመጨረሻው ደብዳቤ፣ ‹‹መንግሥት የውይይት መድረክ አላመቻች አለ፣ በሩ ተዘጋብን፤›› የሚል አቤቱታን ያዘለ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፣ በስተመጨረሻ ይህ ደብዳቤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን በር አስከፍቶ ባለፈው ረቡዕ ለተካሄደው የውይይት መድረክ ዕድል እንደፈጠረ ተናግረዋል።

በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ኢሠማኮ ያቀረባቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ አቶ ካሳሁን በሰጡት ምላሽ፣ የውይይት መድረኩ ኢሠማኮ ከዚህ ቀደም ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ለመንግሥታቸው በተደጋጋሚ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ተራ በተራ በዝርዝር ለመመልከት ያስቻለ እንደነበር ጠቁመዋል።

በደመወዝ የሚተዳደረው ሠራተኛ በአገሪቱ ከተቀሰቀሰው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት አንፃር ችግር ውስጥ መውደቁን አስመልክቶ ኢሠማኮ በተደጋጋሚ ሲያቀርብ የነበረው የመፍትሔ ጥያቄ በውይይት መድረኩ በቅድሚያ የተነሳ አጀንዳ እንደነበር አቶ ካሳሁን ገልጸዋል። ዝቅተኛ ደመወዝ የሚከፈለው ሠራተኛ የከፋ የዋጋ ንረት ታክሎበት ችግር ውስጥ እየወደቀ በመሆኑ መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጥበት ኢሠማኮ ምክረ ሐሳቦችን ያቀረበበት የውይይት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

ከመፍትሔ ሐሳቦቹ መካከል በሠራተኞች የቅጥር ደመወዝ ላይ የተጣለው ግብር እንዲቀነስ በውይይት መድረኩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡት ምክረ ሐሳቦች አንዱ እንደነበር አቶ ካሳሁን ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰንና በሠራተኛ አዋጁ መሠረት የደመወዝ ቦርድ ተቋቁሞ ወደ ሥራ እንዲገባም መጠየቃቸውን አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጥበት በኢሠማኮ አመራሮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረበው ሌላው ጉዳይ ለሁለት ዓመት የተቋረጠው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አማካሪ ቦርድ ሥራውን እንዲጀምር የሚል ነው፡፡  

የዚህ ቦርድ ሥራ ማቆም የሠራተኞች ጉዳይ ትኩረት እንዳያገኝ ከማድረጉ በላይ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ አፈጻጸም ተግባራዊ እንዳይሆን አድርጎት ስለቆየ ቦርዱ ዳግም ሥራ እንዲጀምር ማድረግ አስፈላጊነቱን በማብራራት መፍትሔ እንዲሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥያቄ መልክ ቀርቧል፡፡ የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲን በተመለከተ ተግባራዊ መሆን ያልቻሉ የአዋጁ ድንጋጌዎች ምክንያት እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች በኢሠማኮ ሰፊ ማብራሪያ የሰጠበት ጉዳይ ነበር፡፡ በመሆኑም የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ መመርያ እስካሁን ተግባራዊ ያልተደረገ በመሆኑ ይህ መመርያ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆንላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን አንደጠየቁ አቶ ካሳሁን ገልጸዋል።

የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ጋር ተያይዞ የወጣው መመርያ ከያዛቸው ድንጋጌዎች መካከል ‹‹20/80›› በሚል የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህም ኤጀንሲዎቹ ለሠራተኞች መክፈል ያለባቸው ክፍያ የሚወሰነው ውሳኔውም ኤጀንሲዎቹ ከድርጅቱ ከሦስተኛ ወገን ከሚያገኙት ገንዘብ 80 በመቶ ለሠራተኞች እንዲከፍሉ፣ 20 በመቶውን ለራሳቸው አስተዳደራዊ ወጪ እንዲያስቀሩ የሚደነግግ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ መመርያ መሠረት በፍርድ ቤት ውሳኔ ተሰጥቶበት እንኳ ተግባራዊ ባለመሆኑ መመርያው በትክክል እንዲተገበርላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄያቸውን እንዳቀረቡ አስረድተዋል።

የሠራተኛው በነፃ የመደራጀትና የመደራደር መብት በየቦታው ተግዳሮት እየገጠሙት መሆኑንና አንዳንድ ድርጅቶች ሠራተኞች እንዳይደራጁ እንደሚከላክሉ፣ እንዲሁም ከተደራጁም በኋላ የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎቹ ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድና ሠራተኞች ከተደራጁ በኋላ አንዳንድ ድርጅቶች ለድርድር ፈቃደኛ እንደማይሆኑም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስረዳታቸውን ገልጸዋል። እንዲህ ላሉት ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተራ በተራ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ የዕለቱ የውይይት አካሄድም ከዚህ በፊት ከተለመደው የውይይት መንገድ በተለየ የተካሄደ እንደነበር አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎቻቸውን ከሰሙ በኋላ በእያንዳንዱ ጉዳይ መልስ ከመስጠት ባሻገር በጉዳዩ ላይ ዳግም ውይይት ማድረግ የተቻለበት እንደነበር ገልጸዋል። 

‹‹በአጠቃላይ ሲታይ ውይይቱ በመግባባት የተካሄደ እንጂ እንደ ባለሥልጣንና ጥያቄ አቅራቢ አልነበረም፡፡ ጉዳዩ ላይ እየተነጋገርን እሳቸውም መልስ እየሰጡ እኛም እያስረዳን የተካሄደ ውይይት ነበር፤›› ብለዋል፡፡ 

በዚሁ መንፈስ ኢሠማኮ የቀረቡትን ሁሉንም ጥያቄዎች በአዎንታዊ መንገድ ተቀብለው መልስ እንደተሰጠባቸው የጠቆሙት አቶ ካሳሁን፣ ለእያንዳንዱ ጥያቄዎች የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ተፈጻሚ ሊያደርጉ ይገባል ያሉትን አቅጣጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡  በተለይ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልና የደመወዝ ግብርን በተመለከተው ጥያቄ ዙሪያ እንዲሁም የአማካሪ ቦርድን ዳግም ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሶ፣ በዚህ መልኩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጉዳዩ ተፈጻሚ እንዲሆን አቅጣጫ መስጠታቸውን ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹እንዲያውም በጠየቃችኋቸው ጥያቄዎች ላይ እኛም እየሠራንባቸው ነው፤›› እንዳሉዋቸው አቶ ካሳሁን ገልጸዋል። በተለይ ዝቅተኛው የሠራተኛ ክፍልና ደሃው የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ መሆን የሚችልበትን መንገድ ለማየት የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጽንኦት መናገራቸውን አቶ ካሳሁን ገልጸዋል።

ተቋርጦ የነበረው የአማካሪ ቦርዱ መድረክ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በአስቸኳይ እንዲጀመርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እዚያው አቅጣጫ የሰጡ በመሆኑ ኢሠማኮ ካቀረባቸው ጥያቄዎች ውስጥ አይቻልም የተባለበት ነገር እንደሌለ ይጠቁማል፡፡ ጥያቄዎቹ ጥናትን መሠረት አድርጎ የሚመለስ በመሆኑ፣ በዚሁ አግባብ ጥያቄዎቹ ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የአቶ ካሳሁን ማብራሪያ ያመለክታል፡፡ አንዳንዶቹ ሒደት የሚፈልጉ ስለመሆኑ እኛም እንገነዘባለን ያሉት አቶ ካሳሁን፣ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ግን የለም፡፡ ነገር ግን የተቋረጠው የአሠሪና ሠራተኛ አማካሪ ቦርድ ሥራውን ከጀመረ ከመንግሥት ጋር የሚኖረንን ውይይትና ምክክር የሚያስቀጥል በመሆኑ በቦርዱ የሠራተኛውን ጥያቄዎች እንዲታይ ይደረጋል፡፡ ‹‹በአጠቃላይ በዚህ ውይይት ላይ ምን አገኘን ብላችሁ ታምናላችሁ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ካሳሁን፣ በመግባባት ላይ የተመሠረተ ውይይት በማድረግ ጥያቄዎቻችንን ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ በተለይ አንድም ጥያቄ ‹‹ይህ አይሆንም›› ተብሎ የቀረ ባለመሆኑ ስኬታማ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ በጥናት ላይ ተመሥርቶ በሒደት ምላሽ የሚያገኝ ስለመሆኑ ማረጋገጫም የተሰጠ መሆኑ ጥሩ ውይይት አድርገናል ብለው እንደሚምኑ አቶ ካሳሁን አመልክተዋል፡፡ 

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን በሚገባ መገንዘባቸውን፣ ከመገንዘብም በላይ ጉዳዩን አይተውልናል፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ‹‹እኔ እንዲህ ያለውን መድረክ ስላላገኘን ውጪ ሆኜ የማስብበት መንገድና በአካል ካገኘናቸው በኋላ እኛን የተቀበሉበትና ያስተናገዱበት መንገድ ፍፁም የተለየ ሆኖብኛል፤›› በማለት የውይይት መድረኩ ድባብና አጠቃላይ አካሄዱ ያልጠበቁት እንደሆነባቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ የትኛውም የመንግሥት ባለሥልጣናት ያደርጉታል ተብሎ በማይታመን ደረጃ አክብረው ተቀብለው ጥያቄያችንን በአግባቡ ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ውጤቱንም በዚሁ ልክ እንደሚጠብቁ አመልክተዋል፡፡ ኢሠማኮ ካቀረባቸው ጥያቄዎቹ እንዲስተካከሉ የተባሉ ጉዳዮች ይኖሩ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ካሳሁን በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በጣም የሚገርመው ነገር ተቃውሞ አይደለም ጥያቄያችሁ በዚህ መንገድ መስተካከልና መቅረብ አለበት፣ ወይም ይህንን እንደገና እዩት እንኳን አልተባልንም፡፡  በዚህ ምክንያት ይህ ይሆናል ብለው እንኳን አልተገለጸልንም። ይህ የሚያሳየው ጥያቄውን በሙሉ መቀበላቸውን ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ኢሠማኮ ማድረግ አለባችሁ ብለው እንደ ምክር ያነሱት ነገሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ እንደ ሲቪክ ማኅበር የሰዎችን አመለካከት በመቀየር ረገድ ኢሠማኮ መሥራት አለበት ብለውናል፤›› ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል። 

ለአገር የተሻለ ነገር ለማምጣት የሰዎች አመለካከት ላይ መሥራት፣ እንዲሁም በጋራ የመሥራት ባህልን ማዳበር ስለሚያስፈልግ ኢሠማኮ በዚህ ዙሪያ ሊሠራ ይገባል መባላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ከድህነት እንደምንወጣ እርግጠኛ ሆኖ መሥራት እጅግ አስፈላጊ ስለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገነዘቧቸው ሲሆን፣ ሌሎች የሠለጠኑ የምንላቸው አገሮች የእኛን ያህል ሪሶርስ ያልነበራቸው ሲሆን፣ እኛ ሁሉ ነገር ያለን በመሆኑ ይህንን ከተጠቀምንበትና የአመለካከት ለውጥ አድርጎ ሁሉም ተሳታፊ የሆነበት ሥራ ከተሠራ በአጭር ጊዜ አገራችንን እናሳድጋለን፡፡ ቢያንስ ለቀጣይ ለትውልድ የሚመች ነገር ለመፍጠር ኢሰማኮ ሊሠራ ይገባል፣ ከማለት ውጪ አንዳችም ጥያቄ በእኛ ላይ አላቀረቡም ብለዋል፡፡ በእኛ በኩል ግን አገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲህ ስለሆነ፣ ወይም ኢኮኖሚው እንዲህ ስለሆነ ጥያቄውን አዘግዩ ይሉናል ብለን ጭምር ሠግተን የነበረ ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ነገር ግን ከገመትነው ውጪ በአግባቡ ጥያቄያችን ተስተናግዷል፤›› በማለት የተፈጠረው ግንኙነት እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ 

እንዲህ ባለው ሁኔታ የኢሠማኮን አመራር ያሰደሰተው ውይይት መድረክ በእርግጥ ተግባራዊ ስለመሆኑ ምን ያህል እምነት እንዳላቸው የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፣ ‹‹ያቀረብናቸው ጥያቄዎች በአግባቡ እንደሚመለሱ እኔ በሙሉ ተስፋ  ነው የምጠብቀው›› ብለዋል፡፡ ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላም የተገነዘቡት ይህንኑ እንደሆነ በመጥቀስ የውይይት መድረኩን አወድሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች