Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትሕገ መንግሥቱና ሪፐብሊኩ 28 ዓመት ሞላቸው - የ‹ሚከበር› ነገር አላቸው?

ሕገ መንግሥቱና ሪፐብሊኩ 28 ዓመት ሞላቸው – የ‹ሚከበር› ነገር አላቸው?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ከ28 ዓመት በፊት በዚህ በነሐሴ ወር በአዋጅ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ከነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ ውሏል›› ተባለ፡፡ በሌላ ተከታይ ቁጥር በተሰጠው (አዋጅ ቁጥር 2/1987) የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ ከነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. ጀምሮ ተመሥርቷል፡፡ እንዲሁም የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. ጀምሮ የመንግሥት ሥልጣንን ከሽግግሩ መንግሥት ተረክቧል ተብሎ ታወጀ፡፡ በመደበኛ አሠራር፣ ወግና ‹ደንብ› ልከተል በሚል የተለመደና በመላው ዓለም፣ ወይም በመላው ዓለም ውስጥ በብዙ ጥቂት በማይባሉ አገሮች በሚታወቅ አሠራር ነሐሴ 15 ቀን የሕገ መንግሥት ወይም ሪፐብሊክ ቀን ተብሎ ይከበራል፣ ወይም ይታሰባል ወይም የተቆጠረው፣ የተደረሰበት ዘመን (28 ዓመት) ቀላል አይደለምና ይዘከራል፣ ይከበራል፣ ወዘተ፡፡

ለነገሩ ኢትዮጵያም ነሐሴ 15ን አይደለም እንጂ ኅዳር 29ን/የ1987 ዓመተ ምሕረቱን ኅዳር 29 ማለትም የሕገ መንግሥቱ መግቢያ የመጨረሻ ፓራግራፍ የሚጠቅሰው የሕገ መንግሥት ጉባዔ፣ ሕገ መንግሥቱን ያፀደቀበትን ቀን የሕገ መንግሥት ቀን ብለን ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ‹‹ስናከብር›› ነበር፡፡ ይህ ቀን በዚህ ስያሜና በተጀመረበት መልክ፣ ነገር ግን የሕዝብ በዓል ደረጃ ሳያገኝ ‹ሲከበር› ኖሮ ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ውስጥ ተረስቶ/ቀሪ ተደርጎ ቆይቶ፣ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እየተባለ መከበር የጀመረው ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ ምን የሚከበር ነገር አለው? ሪፐብሊክስ ብሎ ነገር አለን ወይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የሚከበር ነገር ስል ግን በሕግነቱ ሳይሆን በዓልነቱ፣ ክብረ በዓሉ ውስጥ ሆኜ ነው፡፡ እንጂማ የኢትዮጵያ ሕዝብ የእኩልነት፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ትግሉ ሕጉን አክብር፣ ለሕግ ተገዥ ሁን፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተደነገጉ መብቶች የአገርና የሕዝብ መኗኗሪያ ይሁን ብሎ ወጥሮ፣ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ መታገል መጋደል ነው፡፡ እና ሕገ መንግሥቱ የሚከበር ነገር አለው ወይ? ስል የሚደገስለት በዓል አለ ወይ? ከማለት አንፃር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሕገ መንግሥቱን ከማርቀቅ እስከ ማፅደቅ ድረስ በሕወሓት ሥውር ሳይሆን፣ ሥውር መሳይ ቁጥጥር ውስጥ የተከናወነ ነው፡፡ ሕዝብ በነፃና በቀጥተኛ ድምፅ የራሱ ያላደረገው ነው፡፡ ከዚህ ብሶ ሕገ መንግሥቱ ባለፉት 28 ዓመታት ጉዞ ውስጥ (ከዚህ ውስጥ ያለፉትን አምስት ዓመታት እንደ አሎዋንስ ወይም ቃርዳ ማውጣት ያስፈልጋል) ከመልክ ያለፈ፣ በአብዛኛው በብዙ ፈርጅ ተግባራዊነትን አግኝቶ ስለማያውቅ ነው፡፡

የሕገ መንግሥቱ አስኳል ፌዴራላዊ፣ ሪፐብሊካዊ የሕዝብ ሥልጣን ነው፡፡ ይህ ነፃ ዴሞክራሲያዊ ሒደት አንድ ጊዜም ዕውን ሆኖ አያውቅም፡፡ የኖርንበት የሩብ ምዕት ዓመት አገዛዝ በፌዴራላዊነትና በዴሞክራሲዊነት ቅርፅ ይነግድ የነበረ የሕወሓት/ኢሕአዴግ አምባገነንነት ነበር፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ምክር ቤት ደረጃ ሕዝብን ይወክላሉ ተብለው ሲመረጡ የኖሩት ሰዎች የዚህ አምባገነንነት አገልጋዮች ነበሩ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ትናንትም ሆነ ዛሬ ፓርቲና መንግሥት ይቀላቀሉ፣ ፓርቲ የመንግሥት ሥራዎችን ከላይ እስከ ታች ይዋጥ፣ ፓርቲና መንግሥት አንድ ናቸው አይልም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ገዥው ፓርቲ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ገለልተኛ መሆን የሚገባቸውን ሁነኛ የመንግሥት አውታራት ያቦትልካላቸው አይልም፡፡ ስለገለልተኛ አውታራት ብዙ ተብሏል፡፡ ዋናው የአገራችን የዴሞክራሲ ትግል ጉድለትም ይህ መሆኑ ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡ ዴሞክራሲ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ/ቡድን ወገናዊነት ነፃ የሆነ የተቋም ግንባታ ይፈልጋል፡፡ ይህ ቅድም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የተጀመረው፣ ወይም አሁን አገራችን ውስጥ እንደሚታየው የተለያየና ግራ የሚያጋባ የፖለቲካ አቋም ተጀምሮ የነበረው፣ ወይም አሁንም ሌሎች እንደሚሉት ደግሞ ተጀምሮ ነበር የሚባለው የለውጥና የሽግግር ጊዜ ዋና ተግባር፣ አደራና ግዳጅ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚሠራው ተቀዳሚውና አጣዳፊው የሰላምና የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራ፣ ሰላምንና ሥርዓትን ከማስከበር ጋር እዚህ ነፃ ተቋማትን መገንባት ላይ ማተኮርና እዚህ ላይ መረባረብ አለበት፡፡ ከዚህ ጋር እኩል ይህንን ተቀዳሚ ሥራ የሚሾሙና ሊያድሩ የሚችሉ፣ እንዲያውም ራሱን ዴሞክራሲን በቅድመ ሁኔታነት የግድ የሚፈልጉ ጉዳዮችን ከማንሳትና ከማፋፋም መቆጠብ ይፈልጋል፡፡ ከአምባገነንነት ለመውጣት፣ ከአምባገነንነት ወጥቶ ወደ ዴሞክራሲ ለመግባት በመንበረ መንግሥቱ አውታራት ላይ የደረሱ ብልሽቶችን ማደስ፣ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ላይ ሁሉ አፍርሶ እንደገና መሥራትንም ይጠይቃል፡፡ ይህ ሁሉ የሥርዓት ግንባታ ትግል ግን የሁሉንም የተለያየ ሐሳብና የሥልጣን ፍላጎት ያላቸውን ሁሉ ስምምነት፣ በዚህ የጋራ አደራ ላይ መገናኘትን ይፈልጋል፡፡ ከዚህም ጋር የሥርዓት ግንባታ ትግሉ፣ ያኔም በጠዋትና በጊዜ ሳይረፍድ፣ ገና ‹‹ወፎች ሲንጫጩ›› እንዳልነው ለውጡን ከክሽፈት ለማዳን ከመረባረብ ይነሳል፡፡ የለውጥ ጅምሩን ከቅልበሳ ማዳንና ተበታትኖ ከመፋጀት ማምለጥ ጥበብ ያለው እዚያ ውስጥ ነው፡፡

መነሻችን የሕገ መንግሥቱ ዕድሜ፣ በዚህም አማካይነት ሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊነት ነውና በ2011 ዓ.ም. መጋቢት ወር የተጀመረውን ጊዜ ለምን የለውጥና የሽግግር እንደምንለው ወይም እንለው እንደነበር ላስታውስ፡፡ ወቅቱ የሽግግር የሚባልበት ዋናው ምክንያትና ጉዳዩ ሕገ መንግሥት ሲጎሳቆል፣ ሲረገጥ፣ ሲረጋገጥ የገዥዎች መጫወቻ ሲሆን ከነበረበት ምዕራፍ ወደ ሕገ መንግሥታዊነት፣ በራሱ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 8 እንደተደነገገው ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ወደሚሆንበት ምዕራፍ መተላለፍ ማለት ስለሆነ ነው፡፡

ስለሕዝብ ሥልጣን የማወራው ከህልምና ከቅዠት በመነጨ ስሜት አይደለም፡፡ በዓለም ውስጥ የገዥዎች ሹምና ሽረት በሕዝብ ድምፅ መዳፍ ውስጥ የገባበት ወይም ገባ የተባለበት ታሪክ የጀመረው ከታላቁ የፈረንሣይ አብዮት (1789) ጀምሮ ነው፡፡ አሜሪካኖች ከሞላ ጎደል ከሁለት ዓመት ያህል ጊዜ በኋላ በተለያየ የመቆለማመጫ ስም የሚጠሩትን፣ ሁለት መቶ ሃምሳኛ ዓመት የዴሞክራሲና የሪፐብሊክ በዓል የሚያከብሩትም (ለዚያውም ፕሬዚዳንት ትራምፕን ክስ በክስ አድርገው፣ እነሱም እንደ እኛ ‹‹ለካስ ዴሞክራሲ ይሰበራል?›› እያሉ) ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

ዴሞክራሲ ፓርቲዎችን አማርጦ ገዥዎችን ለተገደበ የሥልጣን ጊዜ በሕዝብ ምርጫ መሾም ነው፡፡ ይህ ደግሞ የፓርቲዎችን ነፃ ህልውና፣ የመደራጀት መብት፣ በአጠቃላይ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ መብቶችን ህልውና ማግኘትና መኗኗሪያ መሆን ይጠይቃል፡፡ ዴሞክራሲ እውነተኛ ኑሮ ውስጥ የሚለፉበት፣ ከምርጫ የዘለለ የአቋሞች ብዙነትና ጥል የለሽ ውድድር ኑሮ የሚሆኑበት፣ መብቶችና ኃላፊነቶች የተግባቡበት የአዲስ ሕይወት ግንባታ ነው፡፡ እዚህ ጫካ ውስጥ ተደግሶ የሚመጣ ነገር አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው የመንግሥት አውታራት ፓርቲያዊነት እስካልቀረና እስካለ ድረስ ዴሞክራሲ አይመጣም የሚባለው፡፡ ዴሞክራሲያዊነትና ሕገ መንግሥታዊነት የሚረጋገጠው በመብቶችና በመቻቻል ውስጥ መኗኗርን መሠረት በማስያዝ ላይ በመረባረብና ችግሮች ሲመጡም በሰላማዊ፣ በሕጋዊና በዴሞክራሲያዊ መንገዶች ለመፍታትና ውጤቱንም ለመቀበል መቻልን ኑሮ አድርጎ በማቋቋም ነው፡፡

አገራችን ውስጥ ሲካሄዱ የነበሩት ምርጫዎች፣ ምርጫዎች አልነበሩም የሚባለው፣ 2012 ላይ ‹‹የደረሰው›› የምርጫ ጊዜ፣ እንደተለመደው ለወግ እንስገድ፣ የይስሙላ ትርዒት እናሳይ ካልተባለ በስተቀር እውነተኛና ነፃ ምርጫ ለማካሄድ ቀን ከመቁጠር በላይ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎችን ነፍስ እንዲዘሩ ማድረግ፣ የመንግሥት አውታራትን ፓርቲያዊነት ማፅዳት ያስፈልጋል የተባለው የምናውቀውና ሕይወታችን ውስጥ ከሐውልት በላይ ተገትሮ የሚያሳጣን፣ መሳቂያ ያደረገን እውነት ስለነበር ነው፡፡  የከዚህ ቀደም ምርጫዎች ሁሉ ገዥው ፓርቲ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ እያለ መንግሥትነትን ያለ ነፃ አማራጭና ምርጫ የሚሾምበት፣ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ዓምደ መንግሥት ሆኖ የተደራጀበት ነበር፡፡ ፓርቲው በመንግሥት፣ በሲቪልና በወታደራዊ ቢሮክራሲ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ውጪ ባሉ የኑሮ ዘርፎች ሁሉ ለአገዛዙ ማጎንበስን አረጋግጦ ኖሯል፡፡ የትኛውም ገዥ ቡድንም ሆነ ሌላ ፓርቲ ገዥነትና ተመራጭነት፣ በሥልጣን ላይ መቆየት በነፃና በፍትሐዊ ምርጫ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ መሆኑን ለማረጋገጥ፣ ሥልጣንን በምርጫ ስም በአፅመ ርስትነት መያዝ በጭራሽ እንዳይከሰት፣ ለመከላከል ዋናው መፍትሔና ቅድመ ሁኔታ የመንግሥት አውታራትን ፓርቲያዊነት ማፅዳት ነው፡፡ ገለልተኛ ተቋማትን ማበጀት፣ ማደራት፣ ይህንንም ሥራ ማጥለቅና እንዳይቀለበስ አድርጎ ጠበቅ አድርጎ መጠበቂያ ማበጀት ነው፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 የሚደነግገውን የሕዝብ ልዕልና የማረጋገጥ ተግባር ግን የመንግሥት አውታራትን ከፓርቲ ወገናዊነት ነፃ ከማውጣት፣ የብዙ ፓርቲ ውድድን ከማንተርከክ፣ ባልተጭበረበረ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ትክክለኛ በሆነ ምርጫ የሕዝብ ምክር ቤቶችን ከማደራጀት ያልፋል፡፡ ሕዝብ በአካባቢ ሆነ በፌዴራል ደረጃ በሾማቸው አካላት የመረገጥ ፍዳ ውስጥ ሳያውቁት ከመግባት የሚያመልጡት፣ ከሚዲያዎች አጋላጭነት ባለፈ የራሳቸው የምክር ቤቶች እንደራሴያዊነት መላሸቅና አለመላሸቁን ራሳቸው በራሳቸው መከታተል፣ የላሸቁ እንደራሴዎችን ብዙ ብልሽት ሳያደርሱ ለመቀየር ንቁነቱን የሚያገኙበት እንደ ዕድር በቀዬውና በቀዬዎች አቀፍ ቀበሌዎች ደረጃ ለማንም ተቀጢላ ያልሆኑ መደበኛ ሸንጎዎች ሲኖራቸው ነው፡፡ ማለትም ዴሞክራሲ የሠፈር ኑራቸው እስከ መሆን ድረስ ሲዋሀዳቸው ጭምር ነው፡፡  

የቡድኖች መንግሥታዊ ገዥነት ከነፃና ከትክክለኛ ምርጫ የሚመጭበት አዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት ከዚህ በላይ የተገለጹት የለውጥ ሥራዎች በአንድ ልብና ከሁሉም አስቀድሞ መጀመሪያ መፈጸም አለባቸው ስንል፣ ከዚያ በፊት ሕገ መንግሥቱ መሻሻልና መለወጥ አለበት የሚሉ እንዳሉ ዘንግቼ አይደለም፡፡ በ2012 ዓ.ም. መገባደጃ/መጨረሻ ላይ ምርጫ ‹‹ቀን ቆጥሮ›› ሲመጣ እንደተባለው፣ ሕገ መንግሥት የማሻሻል ሥራ ራሱ ዴሞክራሲ ይጠይቃል፣ ዴሞክራሲን የማደላደል ቅድመ ሁኔታ ይጠይቃል፡፡ ሕገ መንግሥቱ መለወጥ አለበት፣ የችግራችን ሁሉ ምንጭ ሕገ መንግሥቱ ነው የሚሉና ለዚህ የሚተጉ እንዳሉ ሁሉ፣ ከዚህ አኳያ በአንፃራዊነት ሕገ መንግሥቱን የሚደግፉ በተለይም የአገር የግዛት አሸናሸኑ በጭራሽ እንዲነካባቸው የማይፈልጉ፣ እንዲያውም                                                                                                                                                                                                                          የኢትዮጵያን የግዛት አሸናሸን ለምሳሌ ድሬዳዋ የማነው? የማን ይሆን? የሶማሌ ወይስ የኦሮሚያ? ወይስ ሌላ ሦስተኛ አማራጭ አለ? እንዲሁም የአማራና የትግራይ ክልሎች ‹‹የሚፋጁበት››፣ ‹‹የኢትዮጵያ አገር ምድር›› የማን ይሁን የሚለውን ጥያቄ የመፍታት ሥልጣን ያለው ‹‹ባለመብቱ›› የሥልጣን አካል (ወይም የዚህ ጁሪስዲክሽን) በጭራሽ የኢትዮጵያ የማይመስላቸው፣ ከሉዓላዊት ኢትዮጵያ ውጪ ያለ ወይም በጉልበት በጦር በጎራዴ በጦርነት የሚፈታ አድርገው የሚያምኑ አሉ፡፡ ዴሞክራሲን ከማደላደል በፊት ሕገ መንግሥቱን መጀመርያ ልለውጥ ላሻሽል ማለቱ ከንቱ ልፋት ብቻ ሳይሆን፣ መጨራረስን የሚደግስ ቀውስና አዙሪት ውስጥ መግባት ነው፣ ከንቱ ልፋት ነው የሚባለው አሁን ያለው ሕገ መንግሥት የመጀመርያው እንከን፣ ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው ከረቂቅ እስከማፅደቅ ድረስ በባለጊዜው አንድ ፓርቲ ሥውር መሳይ ቁጥጥር ውስጥ፣ ወይም ከሕወሓት ቁጥጥር ውጪ ባልሆነ አሠራር የተከናወነ፣ ሕዝብ በነፃና በቀጥተኛ ድምፅ የራሱ ያላደረገው መሆኑ ነው፡፡ የማንም ፓርቲ ሕገ መንግሥት ያልሆነ፣ ሕዝብ በነፃና በቀጥተኛ ድምፅ የራሱ ያደረገው ሕገ መንግሥት ይኑረን ማለት ደግሞ ከአንደበት ወግ በላይ ዴሞክራሲን ማደላደል ይጠይቃል፡፡

ሕገ መንግሥቱ አሁንና ዛሬ አይደለም መሻሻል ያለበት ሲባል፣ ሕገ መንግሥቱ በጭራሽ መሻሻል የለበትም ማለት አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ መሻሻል ያለበት አሁንና ዛሬ አይደለም የሚል ክርክር ይዤም ሕገ መንግሥቱ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይሻሻል የምልበት ብዙ ምክንያቶች አሉኝ፡፡ መጀመርያ ነገር የሕገ መንግሥት መሻሻል የሚያስፈልገው አገራችን ውስጥ በየትኛውም ምክንያት (መለኮታዊም፣ የታሪክ ኃላፊነትም፣ የሕዝብ ብሶት ወለደው እየተባለም) የጥቂቶችን ፍላጎት ሕዝብ ላይ የመጫን ታሪክ ተዘግቶ፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሞላ ጎል ይሁን ያለው ሕገ መንግሥት ይምጣ ማለት ቀዳሚው ምክንያት ነው፡፡ ይህንን የመሰለ የአገር የበላይ ሕግ የማሻሻል፣ የመለወጥ፣ ቀድዶ የመጣል ተግባር ደርግ እንዳደረገው በመንግሥት ግልበጣ፣ በኢሕአዴግም እንደሆነው በጦርነት አሽንፌያለሁ ብሎ በዚህ ምክንያት ከሚመጣ ከጉልበት በተገኘ ፍላጎት መሆን የለበትም፡፡ ደርግ ‹‹አላወቀበትም››ና ነው እንጂ፣ ኢሕአዴግም ቢሆን እኮ ዝም ብሎ ዴሞክራሲ አወጅሁ፣ ‹‹የሕዝብ ብሶት የወለደው›› ሕገ መንግሥትም በታንክና በአህያ ጭኜ ይዤ መጥቻለሁ አላለም፡፡ መጀመርያ የኢሕአዴግ ጊዜያዊ መንግሥት፣ ቀጥሎም ከ1983 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. የቆየ (በዚህ ረገድም ቢሆን የቻርተሩን/የአገሪቱን የበላይ ሕግ የሦስት ዓመት የጊዜ ገደብ ማክበር የቸገረው) የሽግግር ጊዜና መንግሥት ያስፈለገውም ሕገ መንግሥት የማዘጋጀትና የማፀደቅ ሕገ መንግሥታዊ ጉባዔ የመጥራት ሥራ ማለትም ዴሞክራሲን የማደላደል ሥራ ጫካ ውስጥ ተደግሶ በአህያ፣ በፈረስ፣ በታንክ ተጭኖ የሚመጣ ዕቃ ስላልሆነ ነው፡፡ 

የሕገ መንግሥት ማሻሻያው ዴሞክራሲን ከማደላደል በፊት መቅደም የለበትም የምለው፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያው ሐሳብ ራሱ የሚያመነጨው ከኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ለውጥና ስሜት ውስጥ መሆን ስላለበት ነው፡፡ የአገሪቱን እውነትና የሕዝብን ፍላጎት ከተቆናጠጠ ለውጥ በድርጊቶች፣ በውይይቶች፣ በክርክሮችና በደርድሮች የመግባባትና የኅብረተሰብ ንቃትና ግንዛቤ የመሆን ብርታት እያጎለበተ ከሄደ፣ ለውጥ ዴሞክራሲያዊ ሒደቱን በአስተሳሰብና በድርጊት ሥር እያስያዘ ከመጣ የሚመጡት ማሻሻያ ማለትም የሕዝብ ፍላጎት በሕገ መንግሥት መልክ ይቀረፅ ሲባልም አስቸጋሪ አይሆንም፡፡

የቡድኖች ወይም የገዥዎች መንግሥታዊ ገዥነት ከነፃና ከትክክለኛ ምርጫ የሚመጭበት አዲስ ምዕራፍ ይከፈት ሲባል፣ ‹‹እኔ ብቻ ልክ›› ብለው የቆረቡ ለአንደበት ወግም ቢሆን አገራቸውን ወይም ሕዝቡን ‹‹እኔ እሻልሻለሁ››፣ ‹‹እኔ አሻልሃለሁ›› ያሉ ፓርቲዎችን በነፃ መብቱ እየመረመረ፣ እየተቆጣጠረ ከመመሥረት ጀምሮ እስከ መመረጥ ድረስ የብቃት ማረጋገጫ፣ ‹‹ፈቃድ››ም ጭምር እየሰጠ የሚቆጣጠራቸው የጨዋታ ሜዳ፣ የጨዋታ ሕግ፣ ነፃና ገለልተኛ አጫዋች አለ ማለት ነው፡፡ ምርጫ ይህንን የመሰለ ቅድመ ዝግጅትና መሰናዶ ይጠይቃል፡፡ የሕገ መንግሥት የማሻሻያ ሐሳብም ከየትም ወገን መጣ ከየት የሕዝብን ዳኝነትና ውሳኔ ጠይቆ መቅረቡ ነውና ይህንን ነፃነት ‹ደግሶ› ማቅረብን በቅድሚያ ይፈልጋል፡፡ ጉዳዩን በምሳሌ ለማስደገፍ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 31 እንደ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ ‹‹ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት አለው፡፡ ሆኖም አግባብ ያለውን ሕግ በመጣስ ወይም ሕገ  መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሠረቱ፣ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ›› ናቸው ይላል፡፡ በዚህ መሠረት ሕገ መንግሥቱም፣ ዴሞክራሲም፣ የሚያቋቋሙ ፓርቲዎች ሁሉ፣ የምናማርጣቸው የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ የተወሰነ፣ መነሻ ወይም ሚኒማ የዴሞክራሲያዊ አመለካከትና የድርጅት አኗኗር መለኪያን ያለፉ እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡ የሕዝቡም ፈቃድና ፍላጎት ይኼው ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ከተወጣ በኋላም ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ያሸነፈው ፓርቲ ማንም ይሁን ማን ሳይነኩ የሚከበሩ መሆናቸው የዴሞክራሲ ወግ ነው፡፡ የአገር የዓለም የሥልጣኔ ሕግ ነው፡፡ ፓርቲን ከፓርቲ አማርጦ ወደ ሥልጣን የማውጣት ጉዳይ መሠረታዊውን የሰውነት፣ የዜግነት፣ የማኅበረሰብ መብቶች የሚያስከብርና የማያስከብር ፓርቲ ወይም ቡድን የማማረጥ ጉዳይ ሳይሆን፣ ከዚህ ውጪ የሆኑ ጥቅሞችን ወይም ‹‹ተጨማሪ እሴቶችን›› የማግኘት ጉዳይ መሆኑ የሕዝብም፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የፖለቲከኞችና የፓርቲዎች ግንዛቤ አልሆነም፡፡

የአገር አንድነት ነገም ተመሳሳይ ጣጣ አለበት፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 52/2/ሀ ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳደር ያዋቅራል፣ የሕግ የበላይነት የሠፈነበት ዴሞክራሲዊ ሥርዓት ይገነባል፣ ይህንን ሕገ መንግሥት ይጠብቃል፣ ይከላከላል ይላል፡፡ አዎ ሕገ መንግሥቱ ራስን በራስ ማስተዳደርንና የብሔረሰቦች መብት መረጋገጥን ይደነግጋል፡፡ ራስን በራስ ለማስተዳደርና ለብሔረሰቦች መብት መረጋገገጥ የየብቻ መሬት መለየት፣ መሬትን የብሔረሰብ ማንነት ገጽታ አካል ማድረግ፣ አካባቢያዊ ሥልጣን የተወሰነ ማኅበረሰብ ርስት ነው ማለት፣ ወሰን የውስጣዊ አገር ድርሻ ማረጋገጫ ነው ይላል ወይ? ልብ አድርጉ ዛሬ ይህንን መጠየቅ ያስገርም ይሆናል፡፡ በኢሕአዴግ አፍላ የሥልጣን ዘመን ውስጥ እኮ በክልል ውስጥ አይደለም በማዕከላዊ መንግሥት ግዛት ውስጥ የተወሰነ የሥልጣን መደብን እንደ ርስት ከተወሰነ ብሔረሰብ ጋር ማቆራኘት የአገር ‹‹ሕግ›› ነበር፡፡ ይህንን የመሰለ ዛሬ ድረስ፣ ሌላው ቀርቶ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ምናልባትም ይለይለት ተብሎ ስለክልል ‹‹የግዛት አንድነት›› ሲወራና ‹‹ዳኝነት›› ሲጠየቅ የምንሰማው ሕገ መንግሥቱ ይህንን ስለሚደነግግ ነው ወይ? (ለምሳሌ ብሔርተኛ አደረጃጀት አንዱ ችግር ነው፡፡ እውነትን ፍርጥ አድርጎ ለመናገር ደግሞ የብሔር ፓርቲ የጭቆና መሣሪያ ነው፡፡ ለምን? በአደረጃጀቱና በዓላማው አንድን ዓይነተኛ ማኅበረሰብ የእኔ ብሎ ሌላውን ስለሚያገል፣ ማብለጥ፣ ማድላት ለብሔርተኛ ፓርቲ ውስጣዊ ባህርይው ስለሆነ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ፓርቲ ‹‹መብት››ነት ምንጭ ግን ሕገ መንግሥቱ አይደለም)፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ጀርባ ያለው ፖሊሲ ሕገ መንግሥቱን አምጦ የወለደው ፖሊሲ የዚህ ሁሉ ችግር ምንጭ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አንድ ላይ መሆንን፣ አንድ ላይ መያያዝ እንዲያቅተን  ያደረገንን፣ ሕገ መንግሥቱንም ሆነ ከሕገ መንግሥቱ በስተጀርባ የነበረውን ፖሊሲ፣ ወይም በእነዚህ ላይ ለውጥ ለማምጣትና ማሻሻያ ለማድረግ ወደ ሕግ ሥራ (የሕግ የማሻሻያ ሐሳብ በማቅረብ የሚጀምር፣ ወደ ሕግ ማሻሻል ሥራ) ከመግባታችን በፊት መጀመርያ መነጋገርን ማወቅ፣ መለማመድ፣ የጋራ መግባባት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከምርና ከልብ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

እናም የሕገ መንግሥቱንና የሪፐብሊኩን 28ኛ ዓመት በምናስታውስበት በዚህ ወቅት፣ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ውስጥ ዘለን እንግባ ከማለታችን በፊት እስኪ መጀመርያ መነጋገርን እንነጋገር፣ መነጋገገርን እንወቅ፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...