በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር)
አሁን አሁን በኢትዮጵያ በርካታ ዜጎች በማናቸውም ሰዓት በታጠቁ አካላት ይታገታሉ። በሕይወት ተርፈው እንዲለቀቁ እስከ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ክፍያ ይጠየቅባቸዋል። ሌላው ይቅርና በስደተኛ ጣቢያዎች ተጠልለው የሚገኙ ሕፃናት እንኳ የዕገታ ሰለባ ናቸው። ከዕገታው ሒደት በኋላ በሕይወት የማይመለሱም አሉ። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ አቅሙን ማጎልበት የቻለ ግለሰብም ሆነ ቤተሰብ በዕገታ ወረርሽኝ ሳቢያ ወደ ድህነት አረንቋ እየዘቀጠ ይገኛል።
ዕገታ ቀድሞ ከመሀል አገር ርቆ በጥቂት የውጭ አገር ዜጎችና የዕርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ላይ ይከሰት ነበር። ዛሬ ዕገታ ተዘውታሪ ኩነት ሆኖ እንደ ሰደድ እሳት ቢዛመትም፣ ሁሉም ሥፍራ በእኩል መጠን እየተለበለበ አይደለም። ዕገታ በኢትዮጵያ ከመደበኛ ዜናነት ባሻገር አሥጊ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመላክተው የበለፀጉ አገሮች (ለምሳሌ ካናዳና አሜሪካ) ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይሄዱ መምከራቸው ነው።
ዕገታ የዘፈቀደ ክንውን አይደለም
ዕገታ በረቀቀ ዕቅድና በተመረጡ ተዋንያን የሚተወን ነው። ቢያንስ ‹‹የተነቃቃና የታጠቀ አጋች››፣ ‹‹ገንዘብ አስገኝ ታጋች›› እና ‹‹ምቹ የማገቻ ሥፍራ›› ስለሚኖረው የሶስት ማዕዘናዊ የወንጀል ቅርፅ (Crime Triangle) ይፈጥራል። ሁሉም ሥፍራ ለማገቻነት እኩል አያመችም። አካባቢው በተለይ በአማፂና በመንግሥት ኃይሎች ግጭት ሥር ሲውል፣ የተቀናቃኝ ቡድኖች በአካባቢው ላይ የይገባኛል ጥያቄ ሲያነሱበት፣ ወይም ሥፍራውን የባላንጣ ታጣቂዎች የሚያዘወትሩት ሲሆን ለዕገታ ወንጀል መበራከት አመቺ ይሆናል።
የዕገታ ዓላማም ሆነ አድራሻ ተለዋዋጭ ነው
ኢትዮጵያ አልፎ አልፎ ለፖለቲካ ዕውቅና ሲባል የሚተገበሩ ዕገታዎችን ታስተናግድ ነበር። ባለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት (እ.ኤ.አ. ከ1970 እስከ 2020) በርካታ የኢትዮጵያ አማፂዎች በአጋችነት ተመዝግበዋል። በዝርዝሩም ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ፣ የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር፣ አልሸባብ፣ የቴፒ ወጣቶች፣ የግንቦት ሰባት አርበኞች ግንባር፣ የሙሩሌ ታጣቂዎች፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የሳምሪ ሚሊሻና የአማራ ሚሊሻዎች ይገኙበታል።
የዕገታ ዓላማ በጊዜ ሒደት ተቀያያሪ ነው። በበርካታ አገሮች ታጣቂ ቡድኖች ነፃነትን ወይም የፖለቲካ ግብን ለማስገኘት የዕገታ ስትራቴጂን ያስቀድማሉ። በሒደት ግን ዕገታን እንደ ኢኮኖሚያዊ የጥቅም ምንጭነት ይጠቀሙበታል። ለምሳሌ በ1970ዎቹ በናይጄሪያ አካባቢያዊ ብክለትን ለማስቆም ተቋቁመው የነበሩ ተዋጊ ቡድኖች፣ በሒደት ዓላማቸውን ቀይረው ወደ ገንዘብ አስመጪ የዕገታ ዓይነት አሸጋግረውታል።
ገንዘብ አስከፋይ ዕገታ (Kidnapping for Ransom) ሁሌም አንድ ቦታ አይረጋም። የታጋቹ ቁጥርና ሀብት መጠን ሲሟጠጥ፣ የአጋቾቹ መውጫና መግቢያ ሚስጥራዊነት ሲያበቃ፣ እንዲሁም አዲስና አመቺ ሥፍራ ሲገኝ ዕገታው ‹‹ሥልታዊ ሽግሽግ›› ያካሂዳል። መንግሥትና ኅብረተሰቡ ፀንተው በቁርጠኝነት ሲታገሉት ደግሞ ከናካቴው ይከስማል።
ዕገታው ምን ያህል ተሠራጭቷል?
ባለፉት 26 ዓመታት በዓለማችን የተከሰቱ ግጭቶችን ከሚሰንደው ‹‹ACLED›› ከተሰኘ የመረጃ ተቋም መገንዘብ እንደሚቻለው፣ በኢትዮጵያ 10,075 የግጭት ጥቃቶች ተከስተው ወደ 65,810 ዜጎች ለአደጋ ተጋልጠዋል። ከዚህ ውስጥ 89 የሚሆኑት የዕገታ/አፈና ሰለባዎች ናቸው። እስከ 80 በመቶ የሚሆኑ ዕገታዎች ለሚዲያም ሆነ ለመንግሥት የፀጥታ አካላት ይፋ አይደረጉምና ይህ ቁጥር ከነባራዊው ሁኔታ አንፃር እጅግ ያነሰ ነው።
እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ድረስ በኢትዮጵያ የተዘገበው የዕገታ ኩነት ኢምንት ነበር። ሆኖም ከ2020 ጀምሮ ዕገታ ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል፣ ከ2020 እስከ 2021 ብቻ የ600 በመቶ፣ ከ2021 እስከ 2022 ደግሞ የ136 በመቶ ዕድገት ተከስቷል (ምሥል 2)። የ2023 ገና ያልተጠናቀቀ ቢሆንም በዓመቱ መጨረሻ ቁጥሩ በ78 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል መተንበይ ተችሏል።
ለአብነት በሰሜን ሸዋ ፍቼ አካባቢ የሚከናወኑ ዕገታዎች ሦስት ቁልፍ ሥፍራዎች አሏቸው። አንደኛው የግል፣ የዘመድ፣ ወይም የተመዘበረ የመንግሥት/የሕዝብ ገንዘብ ይኖረዋል ተብሎ የተገመተ ግለሰብ የመኖሪያ አድራሻ ነው። ዒላማ የተደረገው ግለሰብ በታጣቂዎች ታግቶ በጨለማ ለሰዓታት በእግር እንዲጓዝ ይገደዳል። ሁለተኛው ገንዘብ እስኪከፈል ለቀናት ወይም ለሳምንታት ታጋቹ የቤት ውስጥ እስረኛ ሆኖ የሚቆይበት ሥፍራ ነው። ሦስተኛው ሥፍራ ደግሞ የገንዘብ መቀባበያው ነው። የተጠየቀው ገንዘብ ተከፍሎ ታጋቹ ዕድለኛ ከሆነ በሕይወት ሊለቀቅ ይችላል።
ምሥል 1፡ የኢትዮጵያ የዕገታ ቦታዎች ሥርጭት። ሦስቱ ክበቦች ከፍተኛ የዕገታ ክምችት የተስተዋለባቸው ሲሆኑ ሥርጭታቸው ግልጽ እንዲሆን ሲባል ጎልተው ቀርበዋል።
ዕገታ የበረከተው የት ነው?
ዕገታዎች በመላው ኢትዮጵያ በእኩል መጠን አልተሠራጩም። በኦሮሚያ 58 በመቶ፣ በአማራና በሶማሌ 10 በመቶ፣ በትግራይና በአፋር 6 በመቶ የዕገታ ክምችት ተከስቷል። በኦሮሚያም ቢሆን ዞኖች እኩል የዕገታ ተጋላጭነት የላቸውም። በምሥል 1 እንደሚታየው የዕገታ ክምችት የተከሰተው በአዲስ አበባ ከተማ አቅራቢያ፣ በምዕራብ ኦሮሚያና በማዕከላዊው ሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል ነው። በተጠቀሱት ሦስት ሥፍራዎች ዕገታ የመከማቸቱ ፀባይ ‹‹የወንጀል ክምችት ሕግን›› (Law of Crime Concentration) ያመላክታል።
ምሥል 2 በማያሻማ ሁኔታ (Statistically Significant) ዕገታ የተፋፋመባቸውን ሥፍራዎች ያሳያል። ቦታዎቹ የከፍተኛ ዕገታ ቁጥርን ከሚሸፍኑት ሥፍራ ጋር አቆራኝቶ ነው። ለምሳሌ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ በርካታ ዕገታዎች ቢመዘገቡም ዕገታ የተፋፋመበት ሥፍራ ሆኖ አልተገኘም። ምክንያቱም በዕገታዎቹ ቦታዎች መሀል ያለው ክፍተት በሰሜን ሸዋ ከታየው በዕገታዎች ክፍተት መጠን በላይ የሰፋ ነውና።
ምሥል 2፡ በኢትዮጵያ የዕገታ ሥርጭት የተፋፋመባቸው (Hotspot) ሥፍራዎች።
በሌሎች አገሮች እንደታየው ዕገታ በክልል ድንበሮች አካባቢ ይበረክታል። በኢትዮጵያ ወደ 80 በመቶ የሚሆኑት ዕገታዎች ከክልል ድንበር ወሰኖች በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ተከስተዋል።
በምሥል 3 ዕገታ እንዴት በሒደት ወደ መሀል ኢትዮጵያ እየተከማቸ መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል። እ.ኤ.አ. በ2020 ምንም ዕገታ በክበቡ ውስጥ ሳይዘገብ በ2023 ብቻ 78 በመቶ የሚሆነው ዕገታ ተከማችቶበታል። ዕገታ ወደ መሀል አገር የመበርከቱ ጉዳይ ወረርሽኙ ወደ መላው ኢትዮጵያ በቀላሉ ለመስፋፋት የሚኖረውን ሰፊ ዕድል ያመላክታል።
ለዕገታ መበራከት በርካታ መንስዔዎች አሉ
ለዕገታ መበራከት የሕገወጥ የጦር መሣሪያ ድንበር ኬላዎችን እያለፈ በገፍ ወደ አገሪቱ መግባቱ፣ ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር መኖሩ፣ በበርካታ ሥፍራዎች የመንግሥት መዋቅርና ቁጥጥር ደካማ መሆኑ፣ አንዳንድ የመንግሥት የፀጥታ አካላትና ባለሥልጣናት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከወንጀለኞቹ ጋር መጣመራቸው፣ ክልሎች ሚሊሻና ልዩ ኃይልን በገፍ እየመለመሉ ማሠልጠናቸውና ጥቂት የማይባለው ምሩቅ ደግሞ ከእነ ታጠቀው መሣሪያ ክህደት (Defection) በመፈጸም ወደ ዘራፊነት ወይም አጋችነት መቀየሩ፣ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል። የተጠቀሱት ምክንያቶች በርክተው የታዩባቸው አንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ‹‹የሞት ቀጣና›› ለመባል በቅተዋል።
ምሥል 3፡ እ.ኤ.አ. ከ2020 በኋላ በመሀል ኢትዮጵያ የተከሰተ ዓመታዊ የዕገታ ሥርጭት። ቢጫ ቀለም ያላቸው ክበቦች ከአዲስ አበባ ድንበር በመነሳት 125 ኪሎ ሜትር ርቀትን ይሸፍናሉ። በክበቦቹ ዙሪያ የሚታየው ቁጥር በየዓመቱ ከአጠቃላይ የዕገታ ውስጥ ስንት መቶኛው በተጠቀሰው ራዲየስ ውስጥ እንደሚገኝ ያሳያል።
ለዕገታ ተጋላጭ የሆኑትን አካባቢዎች መለየት ይቻላል
የድንበር ወዝግብ ያለባቸውን አካባቢዎች ከሠራዊት ተቀናሽና ከዳተኞች የሚበዙበትን አካባቢዎች፣ የመንግሥት ተቋማት የተዳከሙባቸውን አካባቢዎች፣ የጦር መሣሪያ ዝውወር የሚበረክትባቸውን አካባቢዎች ‹‹ለዕገታ ተጋላጭ አካባቢ›› ብሎ መሰየም ይቻላል። አካባቢዎቹ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንቅስቃሴ መጀመር የነበረበት ትክክለኛ ጊዜ ትናንት ሲሆን፣ ዘገየ ከተባለ ደግሞ ዛሬ ነው። ነገን መጠበቅ ግን ትልቅ ስህተት ነው።
ምን ይደረግ?
ለዕገታ መስፋፋት አመቺ ሁኔታዎች እየበረከቱ በመሆኑ ችግሩ ወደ ባሰ ቀውስ መሸጋገሩ አይቀርም። ብሔር፣ ሃይማኖትና ዕድሜ ሳይለይ ሁሉም ዜጋ ይጎዳል። የአገሪቱ ገጽታ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም፣ ወዘተ በእጅጉ ይላሽቃል። ሌላው ይቅርና የመንግሥት ባለሥልጣናትም የዕገታ ሰለባ ይሆናሉ። የዕገታ ወረርሽኝን ለመግታት መንግሥትና ማኅበረሰቡ በቅንጅት መሥራት ቢኖርባቸውም፣ በተለይም መንግሥት አወዛጋቢ የክልል ድንበር የተከሰተባቸው አካባቢዎች ለዕገታ መስፋፋት አመቺነታቸው ታውቆ ውዝግቡ በፍጥነት ሊፈታ ይገባል፡፡ የአገሪቱ ድንበር ኬላዎች ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በመጨረሻም የራሱን ባለሥልጣናት ንፅህና መፈተሽ ይኖርበታል። ሕግና ሥርዓት እንዲተገበር ቆፍጠን ብሎ ካልተንቀሳቀሰ ችግሩ እየከረረ ከመጣው የዘርና ሃይማኖት ውጥንቅጥ ጋር ተወሳስቦ፣ ኮሎምቢያም ሆነ ናይጄሪያ ካስተናገዱት የዕገታ ሰቆቃ የከፋ ነው የሚሆነው።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው daniel.kassahun@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡