የዘጠኝ ቀናት የቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን ድግስ ተጠናቆ ተሳታፊዎችም ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ለሻምፒዮኑ በቂ ዝግጅት ማድረጓ የተመሰከረላት ሃንጋሪ፣ እንግዶቿን እንደ ዕንቁላል ስትንከባከብ ቆይታለች፡፡ ረብጣ ቢሊዮኖች አፍስሳ ለሻምፒዮናው አዲስ የአትሌቲክስ ማዕከል የገነባችው ሃንጋሪ፣ የዓለም ሻምፒዮናውን በስኬት መወጣቷ በዓለም አትሌቲክስ ሳይቀር ተመስክሮላታል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀጣይ የኦሊምፒክ ጨዋታ ለማሰናዳት ጥያቄዋን እግረ መንገድ አቅርባለች፡፡
ሆኖም በሃንጋሪ የነበረው ተለዋዋጭ የአየር ንብረት የሻምፒዮናውን ድምቀት ማቀዝቀዙ አልቀረም፡፡ በተለይ በከፍተኛ ቦታ ልምምድ ሲያደርጉ የቆዩ ኢትዮጵያውያኑን አትሌቶችን ሲፈትን ነበር፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በ35 አትሌቶች፣ በ11 የተለያዩ ርቀቶች መካፈል የቻለ ሲሆን፣ በሴቶች 10 ሺሕ ሦስት ሜዳሊያ፣ እንዲሁም በወንዶች 10 ሺሕ ነሐስ ሜዳሊያ፣ በወንዶች 3000 መሰናከል የብር ሜዳሊያ፣ በሴቶች 1500 ሜትር ነሐስ እንዲሁም በሴቶች ማራቶን ወርቅ፣ በወንዶች ማራቶን ነሐስ ማሳካት ችሏል።
አትሌቶች ስለ ሻምፒዮናው ምን አሉ?
በተለያዩ ርቀቶች ኢትዮጵያን ወክለው በሻምፒዮናው የተካፈሉ አትሌቶች ስሜታቸው ከውድድር በፊትና በኋላ ለሪፖርተር ሲያካፍሉ ሰንብተዋል፡፡ ሪፖርተር በቡዳፔስት በነበረው ቆይታ የአትሌቶችን ስሜት ለመጠየቅ ጥረት አድርጓል፡፡
አብዛኛዎቹ አትሌቶች ሃንጋሪ ለሻምፒዮናው ጥሩ ዝግጅት እንዳደረገች መስክረዋል፡፡ በአንፃሩ ከዝግጅቱ ይልቅ የኢትዮጵያ በመድረኩ ማሳካት ያለባትን ውጤት አሳክታለች ወይ? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ያሻው ነበር፡፡ በዚህም አትሌቶች ለሻምፒዮናው ያደረጉት ዝግጅት ጥሩ እንደነበር ጠቅሰው፣ ያቀዱትን እንዳላሳኩ ግን አልሸሸጉም፡፡ ይህም የአገሪቱ ተለዋዋጭ የአየር ሁኔታ ፈተና መሆኑን ያነሳሉ፡፡
ሪፖርተር በሻምፒዮናው የማጣሪያ ውድድሮችን ጨምሮ እስከ ፍፃሜው በቦታው ተገኝቶ ከውድድራቸው በኋላ አብዛኛዎቹን አትሌቶች ማናገር የቻለ ሲሆን፣ ‹‹ሙቀት፣ ሙቀት›› የሚል ተደጋጋሚ አስተያየት ተቀብሏል፡፡ አትሌቶቹ በስታዲየሙ ካለው ወበቅ በዘለለ ውድድሩ ላይ እያሉ ሙቀቱ ልባቸውን እንደሚያፍን በተደጋጋሚ ያነሱ ነበር፡፡
የሴቶች ማራቶን ገድል
ቅዳሜ ነሐሴ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በቡዳፔስት ከተማ የሚሌኒየም የጀግኖች ሐውልት አደባባይ የተከናወነው የሴቶች ማራቶን የሚረሳ አይደለም፡፡ አራት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዕለቱ ከነበረው ሙቀት ጋር እየታገሉ ገድል ፈጽመዋል፡፡ ርቀቱን ተቆጣጥረው መምራት ከጀመሩበት ሰዓት አንስቶ ከፍተኛ ሙገሳ የተቸሩበት የቡድን ሥራ ማሳየት ችለዋል፡፡ በውድድሩ አማኔ በሪሶ አሸንፋ ወርቅ ስታመጣ፣ የዓምናዋ አሸናፊ ጎተይቶም ገብረ ሥላሴ ሁለተኛ ሆና ብር አጥልቃለች፡፡ የሞት ሽረት ስታደርግ የነበረው ያለም ዘርፍ የኋላዋ አምስተኛ መውጣቷን ያወቀችው ዶክተሯ ነግሯት ነው፡፡
ከ40 ኪሎ ሜትር በኋላ ምን እንደተከሰተ እንደማታውቅ የተናገረችው ያለም ዘርፍ፣ ወርቅ መገኘቱ እንዳስደሰታትና በቀጣይ አገሯን እንደምትክስ ተናግራለች፡፡
ሌላዋ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረገችው ፀሐይ ገመቹ ስትሆን፣ ውድድሩ ለመጠናቀቅ እየተቃረበች በነበረበት ወቅት ከፍተኛ የጎን ሕመም እንዳጋጠማትና ለማቋረጥ መገደዷን ለሪፖርተር አስረድታለች፡፡ በነጋታው በተደረገው የወንዶች ማራቶን ኢትዮጵያ በልዑል ገብረ ሥላሴ፣ ታምራት ቶላ፣ ሜልኬሳ መንገሻና ፀጋዬ ጌታቸው ተወክላለች፡፡
ከንጋቱ 11፡30 ወደ ሒሮስ አደባባይ ያቀኑት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች፣ አሠልጣኞች፣ እንዲሁም አጠቃላይ የልዑካን ቡድኑ በዕለቱ የነበረውን የአየር ንብረት ሁኔታ አንፃር የሴቶቹ ውጤት ይደገማል የሚል ግምት ነበር፡፡
ሪፖርተር ከውድድር አስቀድሞ ከአሠልጣኝ ሃጂ አዴዮ ጋር ስለ ሁኔታው የተወያየ ሲሆን፣ የአየር ንብረቱ ጥሩ መሆኑንና የተሻለ ውጤት ሊመጣ እንደሚችል ገምቶ ነበር፡፡
በአንፃሩ ውድድሩ 38 ኪሎ ሜትር እስኪደርስ ድረስ ልዑልና ታምራት ጥሩ መጓዝ ችለው ነበር፡፡ በመጨረሻም ታምራት 38 ኪሎ ሜትር ላይ ለማቋረጥ ተገዷል፡፡ ሚልኬሳና ፀጋዬም ውድድሩን ማጠናቀቅ አልቻሉም፡፡
ልዑል አምስት ኪሎ ሜትር እስኪቀረው ድረስ ቢታገልም፣ የነሐስ ሜዳሊያን አሳክቷል፡፡

ገብረሥላሴና ያለም ዘርፍ የኋላውና ፀሐይ ገመቹ ጎልተው ታይተዋል
በወረቀት ላይ የቀረው የቡድን ሥራ
ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮንና እንዲሁም በኦሊምፒክ ውድድሮች በተለይ በረዥም ርቀት የቡድን ሥራ የተዋጣላት ነበረች፡፡ ይህ በጋራ ለውጤት የመሥራት ባህል ግን በሒደት እየተሸረሸረ ሄዷል፡፡ ለቡድን ሥራው መሸርሸር የተለያዩ ምክንያቶች ይዘረዘራሉ፡፡ ይህም ከሪዮ ኦሊምፒክ በኋላ ቀድሞ በብሔራዊ ቡድን ይዋቀር የነበረው የአትሌቲክስ ቡድን መቅረቱና አትሌቶች በግላቸው ልምምድ መሥራት እያካበቱ መምጣታቸውን ተከትሎ እንደሆነ ይነሳል፡፡
በግል የመሥራቱ ልምድ አገር ወክለው ከሚያከናውኑት ውድድር ይልቅ በግል ውድድሮች ውጤቱም ጥቅሙም የጎላ ያደርገዋል፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን አትሌቶች የማናጀሮቻቸውን ትዕዛዝ መቀበሉና መተግበሩ ላይ መጠመዳቸው መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ከዚህም ባሻገር አትሌቲክስ ከፍተኛ ገንዘብ የሚገኝበት መድረክ እየሆነ መምጣቱን ዋነኛ ተጠቃሽ ምክንያት ተደርጎ ይነሳል፡፡ ከዚህም ባሻገር የግል ውድድሮች ተለክተውና ተመጥነው፣ እንዲሁም የግል አሯሯጭ የተመደበላቸው በመሆኑ ሥራውን ያቀልላቸዋል፡፡
በአንፃሩ በዓለም ሻምፒዮና ሆነም በኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ ከፊት ቀድሞ ዙሩን የሚያከር ወይም የሚመራ አትሌት ባለመኖሩ የቡድን ሥራው ከሽፋል፡፡
በቡዳፔስት ሻምፒዮና በተለይ በሴቶችና በወንዶች 5000 ሜትር ውድድሮች ከፍተኛ ስህተት የታየበትና ኢትዮጵያ ልታገኘው የሚገባውን ሜዳሊያ ያጣችበት ሆኖ አልፏል፡፡
ሪፖርተር በቡዳፔስት ከአሠልጣኞችና ከአትሌቶች ጋር ባደረገው ቆይታ የተለያዩ አስተያየቶችን አዳምጧል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ለሻምፒዮናው የተዘጋጀው በሁሉም ርቀት የተለያዩ አሠልጣኞችን ይዞ ነው፡፡ በልምምድ ወቅት ሁሉም አሠልጣኝ የየራሱን አትሌቶች ብቻ ይዞ ነው የተለማመደው፡፡
ወደ ቡዳፔስት እንዲያመሩ የተመረጡት አትሌቶች እንደ ርቀታቸው የተለያዩ አሠልጣኞችን ይዘው ተጉዘዋል፡፡ በአዲስ አበባ በነፍስ ወከፍ ሲሠለጥኑ የሰነበቱት አትሌቶች በቡዳፔስትም ደግመውታል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም የውድድሩ ዕለት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ቡድን የሚሳተፉትን አትሌቶች አሠልጣኞች ጠርቶ ሲያማክርና ምን ዓይነት ታክቲክ መከተል እንደሚገባቸው ሲያወያይ ነበር፡፡ በአንፃሩ አትሌቶቹ ውድድራቸውን አጠናቀው ሲገቡ የተማከሩትን አለመተግበራቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡ ከዚያም ባሻገር አንዱ አንዱን ሲወቅስ ሪፖርተር መታዘብ ችሏል፡፡
ሆኖም ግን ቀድሞ አሠልጣኞቹ ከፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ቡድን ጋር የሚያደርጉትን ውይይት ጆሮ ዳባ ልበስ እንደሚሉትና ይልቁንም አትሌቶቹ የየግላቸውን እንዲተገብሩ ያዟቸው እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ ለዚህም ማሳያነት በሴቶች 5000 ጉዳፍን የሚያግዛት ማጣቷና በወንዶች 5000 ሜትር በሪሁ አረጋዊ ተመሳሳይ ስህተት መታየቱ ማሳያ ነው፡፡
አትሌቶቹ ከውድድር በኋላ ዙሩን ተከፋፍለው ለመምራት ቀድመው ተነጋግረው የገቡ ቢሆንም፣ በውድድሩ ላይ ግን የሚተገብረው መጥፋቱን ያነሳሉ፡፡
የ5000 ሜትር ወንዶች ምርጫ ውዝግብና የአትሌቶቹ ዕይታ
በቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና አነጋጋሪ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የጥላሁን ኃይሌ በመጨረሻ ሰዓት መቀነስ ነበር፡፡ አትሌቱ ውሳኔ በልምምድ ቦታ የሰማ ሲሆን፣ መጨረሻም ከአሠልጣኙ ሲሰማ በለቅሶ ስሜቱን ገልጿል፡፡ ይህም የአትሌቶችን ስሜት የረበሸ ነበር፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ በተለይ በ5000 ሜትር ተሳታፊዎችን በመጠኑም ቢሆን የጎዳ ነበር፡፡ ይህም አትሌቱ አለመመረጡን አዲስ አበባ እያለ ሊነገረው ይገባል የሚለው አስተያየት ሚዛን ይደፋል፡፡ ከዚህም በላይ አብዛኛው አትሌት እንዲሁም አሠልጣኝ ፌዴሬሽኑ የጠራ አሠራር አለመከተሉና ማብቂያውስ መቼ ነው? የሚለው ተነስቷል፡፡ ሻምፒዮናዎች ሆኑ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ሲከናወኑ ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚነሱ አወዛጋቢ ጉዳዮችም እንዲሁም ክርክሮች አሳሳቢ መሆናቸው ተነስቷል፡፡
አሠልጣኞችም በበኩላቸው ውሳኔያቸው ላይ ፌዴሬሽኑ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ውዝግቦችን መቅረፍ ካልቻለና ግልጽ አሠራር መዘርጋት ካልቻለ፣ በየሻምፒዮናው መሰል ክርክሮችና ውዝግቦችን ማስተናገድ መቀጠሉ እንደማይቀር ይነሳል፡፡
ከአንድ ዓመት ያነሰ ጊዜ የቀረው የፓሪስ ኦሊምፒክ፣ ከቡዳፔስቱ ጋር ተመሳሳይ የአየር ሁኔታ እንደሚኖረው የሚገመት ሲሆን፣ ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ያነሳሉ፡፡
በሌላ በኩልም በመካከለኛና በረዥም ርቀት ብቻ የተወሰነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን፣ በሜዳ ተግባር እንዲሁም የአጭር ርቀት አትሌቶችን ማፍራት እንደሚገባው አስተያየት የሚሰጡ በርካቶች ናቸው፡፡
ሪፖርተር በቡዳፔስት በነበረው ቆይታ ኢትዮጵያ ለምን የአጭር ርቀት ተወዳዳሪዎችን ይዛ አትቀርብም የሚል አስተያየት ሲቀበል ሰንብቷል፡፡
ሆኖም በማዘውተሪያ ሥፍራ ዕጦት እየተፈተነ የሚገኘውና የመንግሥት ትኩረት የተነፈገው አትሌቲክስ የአጭር ርቀት አትሌቶችን ማፍራት ቅንጦት መሆኑ የማይቀር ነው የሚል አስተያየት ተበራክቷል፡፡
በዳዊት ቶሎሳ (ከሃንጋሪ ቡዳፔስት)