Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከጃንዋሪ 1 ቀን 2024 ጀምሮ ብሪክስን እንደምትቀላቀል ማረጋገጫ በመሰጠቱ ደስታ ከተሰማቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ኢትዮጵያ ለምን ከሌሎቹ የአፍሪካ ባለኃያል ኢኮኖሚ አገሮች ለምሳሌ ናይጄሪያና አልጄሪያ ቀድማ ዕድሉን እንዳገኘች ምንም ዓይነት መረጃ ባይኖረኝም፣ በአዲሱ የዓለም አሠላለፍ ለውጥ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ለመሆን በመቻሏ ግን ይበል ብያለሁ፡፡ የዛሬን አያድርገውና ኤርትራ ከመገንጠሏ በፊት የቀይ ባህር ተጋሪ አገር በመሆን ሁለት ወደቦች በነበሯት ጊዜ፣ ኢትዮጵያ በጂኦ ፖለቲካ ስትራቴጂነት አንደኛዋ ተመራጭ ነበረች፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አሜሪካ መላውን የአፍሪካ ቀንድና የመካከለኛው ምሥራቅን የምትቃኝበት፣ በአስመራ ቃኘው ስቴሽን የሚባል ትልቅ የግንኙነት ጣቢያ ነበራት፡፡

በመጪው ዓመት በወርኃ የካቲት ሃምሳኛ ዓመቱን በሚደፍነው የ1966 ዓ.ም. ታላቁ ሕዝባዊ አብዮት አማካይነት የዘውድ ሥርዓት ሲገረሰስ፣ በሁኔታው አኩራፊ የነበረችው አሜሪካ ለጊዜያዊው ወታደራዊ አስተዳደር ጀርባዋን ስትሰጥ ነገሮች በፍጥነት መለዋወጥ ጀመሩ፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ገንዘብ ተከፍሎባቸው የተገዙ የጦር መሣሪያዎችን አልሰጥም ስትል፣ ቃኘው ስቴሽን ተዘግቶ አሜሪካውያን ወታደራዊ ሰላዮችና ባለሙያዎች ጓዛቸውን ይዘው እንዲወጡ ተደረገ፡፡ የሶማሊያ ወረራ ያሠጋው የወቅቱ ወታደራዊ መንግሥት በጂሚ ካርተር አስተዳደር የጦር መሣሪያ በመከልከሉ፣ ፊቱን ወደ ሌሎች አማራጮች ለማዞር ዕድል ሳያገኝ ሶማሊያ በምሥራቅ 700 ኪሎ ሜትር፣ በደቡብ ደግሞ 300 ኪሎ ሜትር ድንበር አልፋ ገባች፡፡

በወቅቱ ከሶማሊያ ወረራ በተጨማሪ የኤርትራ ተገንጣይ ቡድኖች አስመራ ዙሪያ ደረሱ፡፡ ኢትዮጵያ አስደንጋጭ የሆነ ጊዜ ውስጥ በመግባቷ ምክንያት የክፉ ጊዜ ወዳጅ ፍለጋ አሰሳ ተጀመረ፡፡ ቀድመው የተገኙት የኩባው ፊደል ካስትሮ ሲሆኑ፣ በእሳቸው አማካይነት በስንት ጥረት ከሶቪዬት ኅብረት አመራሮች ጋር ንግግርና መቀራረብ ተጀመረ፡፡ በከፍተኛ ትጋት ከብዙ ምልልስ በኋላ ሶቪዬት ኅብረት ሶማሊያን መርዳት ትታ ከኢትዮጵያ ጎን ተሠለፈች፡፡ ሶማሊያ የሶቪዬትን ዘመናዊ የአየርና የምድር ኃይል መሣሪያዎችን ከቀላል እስከ ከባድ እስከ አፍንጫዋ ታጥቃ ነበር፡፡ በርካታ ወታደራዊ አማካሪዎችንም ከሶቪዬት ማግኘቷ አይረሳም፡፡

ኢትዮጵያ በወቅቱ ዘመኑን በማይመጥኑ አሮጌ የጦር መሣሪያዎች በጀግኖች ልጆቿ ብርታት እየተከላከለች፣ በታጠቅ ጦር ሠፈር ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተከተቱ ልጆቿን በአጭር ጊዜ አሠልጥና 300 ሺሕ ሚሊሻ ጦር አዘጋጀች፡፡ እነዚያ እንደ ነበልባል የሚነድ ወኔ የነበራቸው ሚሊሻዎች ከመደበኛው ሠራዊት ጋር ተሠልፈው ለማመን የሚከብዱ ጀብዱዎችን ፈጸሙ፡፡ ከእነሱ መካከል በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየን ጀግናው ዓሊ በርኬና መሰሎቹ መቼም ቢሆን አይረሱንም፡፡ እንደ አሜሪካና መሰሎቿ ደባ ቢሆን ኖሮ ይኼኔ ኢትዮጵያ በዚህ ቅርጿና ይዘቷ አትገኝም ነበር፡፡ ዘለዓለማዊ ክብርና ሞገስ ለወቅቱ ጀግኖቻችን በሙሉ ይሁንና እዚህ መድረስ ችለናል፡፡

በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ ኢትዮጵያ በአሜሪካ በግድ ተገፍታ የምሥራቁን ጎራ እንድትቀላቀል ስትደረግ፣ በቀጥታ የገባችው የቀዝቃዛው ጦርነት ዋነኛ ማዕከል ውስጥ እንደነበር ያን ጊዜ የነበሩ ያስታውሱታል፡፡ ዛሬም ያሉ ቢሆኑ ከንባብ ብዙ ነገሮችን እንደቀሰሙ ይታመናል፡፡ እንደ እኔ ዓይነቱ በዚያ አስቸጋሪ ሒደት ውስጥ ያለፈ የጦር መኮንን ደግሞ ብዙ ትዝታ አለው፡፡ የአስመራን ከበባ በማስለቀቅና ተገንጣዮችን ወደ ቆላማ አካባቢዎች በመገፍተር፣ ከዚያም በጀልዴሳ ግንባርና በካራማራ ዓውደ ግንባር በመሳተፍና የጥይት አረርና የከባድ መሣሪያ ፍንጣሪ በአካል ላይ በማስተናገድ ተሳታፊ ስለነበርኩ ያ ሁሉ ተጋድሎ እንደ ትናንት ነው የሚታየኝ፡፡

ወደ ፖለቲካው መለስ ስል በወቅቱ ምንም እንኳ ሁለት ጎራዎች መሀል መገኘት በጣም ከባድ ተግዳሮት የነበረው ቢሆንም፣ በአንድ የዓለም ገዥ መዳፍ ሥር ሆኖ ከመማቀቅ በእጅጉ የተሻለ ነበር፡፡ የውስጥ ችግራችንን በወታደራዊ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ጭምር በመፍታት ሰላም ብናገኝ ኖሮ፣ በቀዝቃዛው ጦርነት ወላፈን ውስጥ ሆነን በርካታ ጥቅሞች ማግኘት የሚያስችለን ስምና ዝና ነበረን፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ገዥዎች ጥላ ሥር ባልወጡበት በዚያ ዘመን ለደቡብ አፍሪካ፣ ለናሚቢያ፣ ለዚምባቡዌና ለሌሎች ያደረግነው ድጋፍና የገነባነው ጠንካራ የጦር ኃይል ኢትዮጵያን ከፍ አድርገው የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ ብዙ የምዕራብ አገሮችም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከኢትዮጵያ ጋር ይሠሩ ነበር፡፡ ለዚህም በሕይወት ያሉ ምስክሮች አሉ፡፡

እኔ ለተወሰነ ጊዜ ከሠራዊቱ ገለል ብዬ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያቋረጥኩትን ትምህርት ስቀጥል፣ በምሁራኖቻችንና በልሂቃኖቻችን አካባቢ የማስተውለው አርቆ ማሰብ የጎደለው ሴረኝነት አይረሳኝም፡፡ በአሜሪካ ፍቅር የተለከፉና ከዚያ በሚላክላቸው ድርጎ ተንደላቀው የሚኖሩ ምሁር ተብዬዎች፣ በኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ወርዶ ሁሉም ወገኖች ወደ ድርድር ጠረጴዛው እንዳይመጡ ያደርጉት የነበረው ጥረት ወደ ሠራዊቱ አመራሮች እንዲጋባ ተደርጎ ነበር፡፡ ሻዕቢያና ወያኔ አሸንፈው ሥልጣን ሲይዙ እነሱም ከሥልጣኑና ከጥቅሙ የሚካፈሉ መስሏቸው፣ አገራቸውን ለእነ ሲአይኤ ሴራ በማጋለጥ ከጅምሩ የከሸፈ መፈንቅለ መንግሥት እንዲካሄድ አመቻቹ፡፡ አሉ የተባሉ የጦር ጄኔራሎች በሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ተፈጅተው አገር ራቁቷን እንድትቀር ተባበሩ፡፡ ብዙ ግፍ ተሠራ፡፡

ሶቪዬት ኅብረት ፈርሳ ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ሲያበቃ ኢትዮጵያ ፈርጣማ አገር ሆና ወደ ዴሞክራሲያዊት አገርነት መቀየር ሲገባት፣ ሻዕቢያ ኤርትራን ገንጥሎ ሲወስድ ወያኔ ደግሞ መላ አገሪቱን ተቆጣጥሮ አሁን የምናየውን ነቀርሳ ተከለብን፡፡ የያኔዎቹ ምሁራንና ልሂቃን አርቀው ማሰብ አቅቷቸው ባመጡት ጣጣ ወያኔ 27 ዓመት ሙሉ አገሪቱን ተጫወተባት፡፡ የአሜሪካና የግብረ አበሮቿ ተላላኪ ሆኖ በደም የተጻፈ ታሪክን አጥፎ የሐሰት ትርክት ፈጥሮ፣ ኢትዮጵያ ከእሱ ውድቀት በኋላ የሥርዓተ አልበኝነት መጫወቻ አደረጋት፡፡ የአንድ ዓለም ጌታ ባሪያ መሆን ያመጣው ውጤት ይኸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰላም ነስቶ እያስለቀሰ ነው፡፡ አሁንም ብሪክስን ስንቀላቀል ካለፉ የጥፋት ታሪኮች እንማር እላለሁ፡፡ ‹‹ከታሪክ የማይማር የታሪክ ማስተማሪያ ይሆናል›› እንደሚባለው፣ ያንን የጥፋት ታሪክ ገጽ እንጠፈው እያልኩም አሳስባለሁ፡፡

(ዘ.እ.፣ ከሲኤምሲ)  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...