Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኢትዮጵያ አጠቃላይ የመሬት ፖሊሲ እንዲወጣ የዘርፉ ባለሙያዎች መንግሥትን እንዲወተውቱ ተጠየቀ

በኢትዮጵያ አጠቃላይ የመሬት ፖሊሲ እንዲወጣ የዘርፉ ባለሙያዎች መንግሥትን እንዲወተውቱ ተጠየቀ

ቀን:

ኢትዮጵያ በተለያዩ አዋጆች፣ ፖሊሲዎችና መመርያዎች ላይ የመሬት አጠቃቀም ሥርዓትን ብታስገባም፣ የመሬት አስተዳደርን አጠቃሎ በአንድ ላይ የሚይዝ የመሬት ፖሊሲ ባለመኖሩ የሚታዩ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ መንግሥት አጠቃላይ የመሬት ፖሊሲ እንዲያወጣ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲወተውቱ ተጠየቀ፡፡

ላንድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ፣ የመሬት ቀንን አስመልክቶ በኢትዮጵያ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ተግዳሮቶችና ዕድሎች በሚል ባዘጋጀው የባለሙያዎች ምክክር መድረክ፣ ከዓመታት በፊት ጀምሮ በመሬት አጠቃቀምና ሥርዓት ዙሪያ ሥር የሰደዱ ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላሉ የተባሉ፣ ሙያዊ የፖሊሲ ግብዓቶች እንዲሁም ጥናቶች ቢቀርቡም፣ ወደተግባር መለወጥ እንዳልተቻለ ተገልጿል፡፡

በመሬት ፖሊሲና ተቋም ላይ ዳሰሳ ያቀረቡት በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈጻሚና የመሬት ሕግ ባለሙያ አቶ አበባው አበበ እንደሚሉት፣ የሕዝብ ፖሊሲ፣ የግብርና ፖሊሲና ሌሎችም ስለመሬት ቢያወሩም፣ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የመሬት ፖሊሲ ካለመኖሩም በተጨማሪ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 የተቀመጡት የፖሊሲ ሐሳቦች፣ ከትግበራ ጋር ችግሮች አሉባቸው፡፡

ለአብነትም፣ ሕገ መንግሥቱ መሬት በነፃ ሊያገኙ የሚችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ብቻ እንደሚል፣ ነገር ግን ከዚህ ዘለል ያለና ተቃርኖ ያለበት ትግበራዎች እንደሚስተዋሉ አንስተዋል፡፡

ከእነዚህ ኅብረተሰብ ክፍሎች ውጪ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሬት በተለያየ መንገድ እንደሚያገኙና በመሬት ሕጎች ላይ በግልጽ ያልተመለሱ ጥያቄዎች እንደሚነሱም ያክላሉ፡፡

የመሬት አስተዳደር፣ የካሳ ክፍያና ሌሎችም መሬትን በሚመለከት የወጡ ሕጎች የፖሊሲ ሐሳብ ቢኖራቸውም፣ ባለይዞታ በተለያዩ ሕጎች የተሰጠው መብት በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግለት አይስተዋልምም ብለዋል፡፡

ለአርሶ አደሩ የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ሠርተፍኬት ከመስጠት ጀምሮ ወደፊት ለሚታሰበው የመሬት ፖሊሲ ሐሳብ ለማመንጨት የሚያግዙ ሥራዎች በሚኒስቴሩ በኩል እየተከናወኑ መሆኑን፣ በአጠቃላይ ለደን፣ ለግብርና፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለልማት፣ ለመኖሪያና ለሌሎችም ጥቅም የሚውሉ መሬቶችን አጠቃሎ የሚይዝ የመሬት ፖሊሲ ያስፈልጋል ሲሉ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙ የሕግ፣ የግብርናና የመሬት ነክ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

አጠቃላይ የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ፖሊሲ ባለመኖሩ የኢትዮጵያ የመሬት አጠቃቀም እየተበላሸ መሆኑ፣ ለም መሬት ለግንባታ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ መሬት ለሰብል የሚውልበት አካሄድ አደገኛ ነው የሚል አስተያየት ቀርቧል፡፡

የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት ካልተበጀለት ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአድአ ጤፍ የሚባል እንደማይኖር፣ እንዲህ ያሉና በርካታ መሬት ነክ ችግሮችም እንደሚገጥሙ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የገጠር ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እንደሚያስፈልግ፣ የመሬት አስተዳደርም ራሱን የቻለ መሪ ተቋም እንደሚያስፈልገው የመድረኩ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል፡፡

የላንድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ የቦርድ ሊቀመንበር መለሰ ዳምጠው (ዶ/ር)፣ በተለያዩ ጊዜያት በመሬት ዙሪያ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ በባለሙያዎች የመፍትሔ ሐሳቦች መቅረባቸውን አስታውሰው፣ መንግሥት በዘርፍ ያለውን ችግር የሚቀርፍ አጠቃላይ የመሬት ፖሊሲ እንዲያወጣ ምሁራንና ባለሙያዎች መንግሥትን እንዲወተውቱ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...