Tuesday, September 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የአስመሳይነትና የአታላይነት ፖለቲካ አገር እያጠፋ ነው!

አስመሳይነትና አታላይነት የተፀናወተው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ ፖለቲካ የአገር፣ የአኅጉርና የዓለም ውስብስብ ችግሮች የሚፈቱበት ጥበብ እንጂ፣ አስመሳዮችና አታላዮች በአወዛጋቢ ትርክቶች የንፁኃንን ደም ለማፍሰስ የሚተውኑበት የጥፋት መድረክ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ያለፉትን ሃምሳ ዓመታት ውጣ ውረዶች ታሪክ የሚታዘብ ማንም ዜጋ፣ በፖለቲካው ምኅዳር ውስጥ ካለፉት ውስን ቅን ዜጎች በስተቀር ብዙዎቹ ለደረሱ ጥፋቶች ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በቀላሉ ይገነዘባል፡፡ እነሱን እያዩ ያደጉ የዘመኑ አፍለኛ ፖለቲከኞችም ካለፉት አርዓያዎቻቸው ጥፋት ለመማር ፈቃደኛ ባለመሆን፣ ፖለቲካን የአገር ችግር መፍቻ መሣሪያ ከማድረግ ይልቅ የሴራ ማቀነባበሪያ ማድረግ መርጠዋል፡፡ በአገርና በሕዝብ ስም ደጋግመው ቢምሉም ግብራቸው ግን ከአንደበታቸው ተቃራኒ ነው፡፡ ማስመሰልና ማታለል የተካኑበት ስለሆነ ለሕዝብ ደኅንነትና ሰላም በአደባባይ ቢደሰኩሩም፣ ብዙ መቶ ሺዎች አልቀው ሚሊዮኖች ቢፈናቀሉ ደንታቸው አይደለም፡፡ ሥልጣናቸውን ለማደላደል ወይም የሚያልሙትን ሥልጣን ለመቆናጠጥ በሚያደርጉት መቅበዝበዝ፣ አገር ምስቅልቅሏ ወጥቶ ሕዝብም ሰላሙ ተናግቶ እሪታውን ቢያቀልጥ ምንም አይመስላቸውም፡፡ በስሙ ለመነገድና ለመቆመር ግን ማንም አይቀድማቸውም፡፡

ኢትዮጵያ ሰላም የምታገኘው ልጆቿ በእኩልነት፣ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት መንፈስ፣ በመከባበርና በመፈላለግ ስሜት ለብሔራዊ ደኅንነቷና ጥቅሟ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል መደላድል ሲፈጠር ነው፡፡ ይህንን ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረ አኩሪ የኢትዮጵያዊነት ስሜት በመናድ በብሔር፣ በእምነት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት ሕዝቡን መከፋፈልና ደም ማቃባት የዘመኑ ፖለቲከኞች ተግባር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ይህንን እኩይ ፍላጎት ለማሳካት ደግሞ አስመሳይነትና አታላይነት እንደ ግብዓት እያገለገሉ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ከ80 በላይ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ድንገት ዛሬ የተገኙ ይመስል፣ በቂ መረጃና ማስረጃ በማይቀርብባቸው አወዛጋቢ ትርክቶች አንዱን የሌላው ጠላት በማድረግ የተፈጠረው ቀውስ የብዙዎችን ንፁኃን ሕይወት ቀጥፏል፣ አሁንም እየቀጠፈ ነው፡፡ ሕዝቡን በብሔር ከፋፍሎ እርስ በርሱ ለማባላት የተወጠነው ፕሮጀክት አዋጭ ሳይሆን ሲቀር፣ የእምነት ልዩነቶችን በመታከክ የሚከናወነው ደባ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በአልባሌ የፖለቲካ አመለካከት በመከፋፈል የደረሰው ድቀት በዋጋ የሚተመን አይደለም፡፡

አንዴ በወለጋ፣ ሌላ ጊዜ በደቡብ፣ ትንሽ ቆይቶ በቤኒሻንጉል፣ ከዚያ በጋምቤላ፣ እያሉ እያሉ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋርና በሌሎች ሥፍራዎች የተከናወኑ ግጭቶችና ጦርነቶች ለመግለጽ የሚያዳግት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ አስከትለዋል፡፡ አሁን ደግሞ በሌሎች አካባቢዎች ከሚስተዋሉ ግጭቶች በተጨማሪ፣ በአማራ ክልል መጀመር ያልነበረበት ውጊያ እየተካሄደ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ካለው ብልፅግና ፓርቲ ጀምሮ ሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ኢትዮጵያ ከገባችበት የጥፋት አዙሪት ውስጥ በፍጥነት እንድትወጣ ለምን ቁጭ ብለው መምከር አቃታቸው? በተለይ ደግሞ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና ከማንም በፊት ተነሳሽነቱን በመውሰድ ይህ የጥፋት ጉዞ እንዲገታ ለምን ፈር ቀዳጅ መሆን አቃተው? ከብልፅግና ፓርቲ ጋር በቅርበት የሚሠሩ ፓርቲዎችም ሆኑ በርቀት ያሉት ጭምር የተያዘው የጥፋት መንገድ እንዲቆም ለምን ድምፃቸውን አያሰሙም? ማዶ ለማዶ በመሆን ፋይዳ በሌላቸው የመግለጫ ጋጋታዎች ለማስመሰል የሚተውኑትን ደካማ ድራማ ለምን አያቆሙም? እንዲህ ዓይነቱ አስመሳይነትና አታላይነት ከሥልጣንና ከጥቅም በላይ ለአገርና ለሕዝብ አለማሰብን ነው የሚያሳየው፡፡

ኢትዮጵያ በታሪክ መዝገብ ውስጥ ድንቅ ክንውኖች የተስተናገዱባት ታላቅ አገር ናት፡፡ በረጅሙ አንፀባራቂ የነፃነት ታሪኳ ስማቸውን ከመቃብር በላይ ትተው የሄዱ እጅግ በጣም በርካታ ዜጎችን ያፈራች ናት፡፡ እነዚህ በታሪክ የሚታወሱ ወገኖች በአርበኝነት፣ በአገር አስተዳደር፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በሆቴል፣ በቱሪዝምና በሌሎችም በርካታ ዘርፎች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በሕይወታቸው መስዋዕትነት ጭምር ታላቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ እነዚህ በአራቱም ማዕዘናት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ውስጥ የተገኙ ባለደማቅ ታሪኮች፣ በብሔርና በእምነት ልዩነቶች ሳይከፋፈሉ አገራቸውን በክብር ሲጠብቁም ኖረዋል፡፡ የኮሎኒያሊስቶችን ቅስም የሰበረው አንፀባራቂው ታላቁ የዓድዋ ድል ሲታወስ፣ አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ጥቁሮች ጭምር የጀግኖቹን ኢትዮጵያውያን ውለታ የሚዘክሩት በከፍተኛ አክብሮት ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ የነፃነታቸው እናት እንደሆነች በአደባባይ በኩራት ሲናገሩ የሚደመጠው፡፡ ይህንን የመሰለ አኩሪ ታሪክ ያላትን አገር በአስመሳይነትና በአታላይነት ከንቱ ፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የሚከቱ ፖለቲከኞች፣ ከገቡበት አደገኛ የጥፋት ጎዳና በፍጥነት እንዲወጡ ግፊት መደረግ አለበት፡፡ ድርጊታቸው ለታላቋ ኢትዮጵያ አይመጥንምና፡፡

ከፖለቲከኞች ጀርባ ተለጥፈው በሃይማኖት ጭንብል በአገርና በሕዝብ ላይ የማያባራ መከራ የሚያመጡ፣ በቤተ እምነቶችና በአማኞች መካከል ቅራኔ የሚፈጥሩና ከሰማያዊው አስተምህሮ አፈንግጠው ምድራዊ የንዋይና የሥልጣን ጥም ማርኪያ መንገዶችን የሚያማትሩ በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡ የነገውን አገር ተረካቢ ትውልድ በአስመሳይና በአታላይ ትርክቶች በማደናገር፣ ተምሮና ሠርቶ ከመለወጥ ይልቅ የማይታይና የማይዳሰስ ተስፋ ላይ እየጣዱት ነው፡፡ አንዳንዶቹ በግላጭ ለማመን የሚከብዱ የሀብት ማግኛ አጓጉል ቅዠቶችን በመጋት፣ ከአቋማሪ ድርጅቶች የባሰ የትውልድ ማምከኛ ፕሮጀክቶችን ደቅነዋል፡፡ አስመሳዮቹና አታላዮቹ ይህንን ሁሉ ደባ የሚፈጽሙት የማኅበረሰቦችን ደካማ ጎኖች ማለትም ይሉኝታ፣ ዓይነ አፋርነት፣ የዕውቀትና የክህሎት አለመደርጀትና ሌሎች ተዛማጅ ምክንያቶችን በመጠቀም ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አገራዊ ኪሳራ በስፋት እየታየ፣ በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በክልሎች በየደረጃው ያሉ መዋቅሮችና የሚመለከታቸው አካላት ዝም ሲሉ ያስደነግጣል፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት በሕግ በተለያዩባት አገር ውስጥ ሁሉም ቅጥሩን አስከብሮ መተዳደር ቢቻል፣ በሃይማኖት ስም የሚነግዱ አስመሳዮችና አታላዮች በአገርና በሕዝብ ላይ አይቀልዱም ነበር፡፡

በአስመሳይነትና በአታላይነት ከተካኑት መካከል የሚጠቀሱት ደግሞ፣ በሥልጣናቸው ከሚባልጉ ሹማምንት ሥር የማይጠፉ የንግድ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ጥገኞች ግብር በማጭበርበርና በመሰወር፣ ሕገወጥ ደረሰኞችን በመጠቀም፣ በኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ በስፋት በመሰማራት፣ የመንግሥት የግዥ ሥርዓትን በመደርመስ ያለ ጨረታ ኮንትራቶችና ግዥዎችን በመቀበል፣ በጥቁር ገበያ ውስጥ ዋነኛ ተዋንያን በመሆን፣ የመንግሥት ተቋማትን በጉቦ በመበከል፣ የምርቶችን አቅርቦትና ሥርጭት በመቆጣጠር፣ የግብይት ሥርዓቱን ምስቅልቅሉን በማውጣትና የሕዝቡን ሕይወት በሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ሲኦል በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ እነሱ በተካኑበት የማስመሰልና የአታላይነት ጥበብ የፋይናንስ ተቋማትን ጭምር እንደ ግል ንብረታቸው በመጠቀም፣ ብድርና የውጭ ምንዛሪ እንደ ልባቸው ያጋብሳሉ፡፡ አብረዋቸው በተሠለፉ ሙሰኛ ሹማምንቶች አማካይነት መሬት፣ ከቀረጥ ነፃ ዕድልና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን በቀላሉ ያገኛሉ፡፡ የእነሱ ዋና ሥራ ሹማምንት በተቀያየሩ ቁጥር እያስመሰሉ በአታላይነት መተወን ነው፡፡ በዚህ መሀል ግን ሕዝብና መንግሥት በመካከላቸው ሊጠገን የማይችል ቁርሾ እየተፈጠረ አገር መከራዋን ታያለች፡፡ የአስመሳይነትና የአታላይነት ፖለቲካ አገር እያጠፋ እንደሆነ ይታወቅ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...