Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትምህርት ሚኒስቴር የመማርያ መጻሕፍት ለማሳተም ያወጣውን ጨረታ የጃፓን ኩባንያ አሸነፈ

ትምህርት ሚኒስቴር የመማርያ መጻሕፍት ለማሳተም ያወጣውን ጨረታ የጃፓን ኩባንያ አሸነፈ

ቀን:

  • ኅተመቱ ሰባት ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሏል

ባለፈው ዓመት የተከሰተውን የመማርያ መጻሕፍት አቅርቦት ችግር ለመፍታት፣ ወጥቶ የነበረውን ጨረታ ባሸነፈው የጃፓን ኩባንያ አማካይነት 40 ሚሊዮን መጻሕፍት በኅትመት ላይ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚነስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ነሐሴ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የመጻሕፍት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ኃላፊነቱ የትምህርት ሚኒስቴር መሆኑንና በአገሪቱ የኅትመት ድርጅቶች ብቃት ማነስ ምክንያት የመማርያ መጻሕፍት ኅትመት ለውጭ ድርጅት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ ከጃፓኑ ኩባንያ ቶፕሀም ጋር በጋራ የመሥራት ስምምነት (joint venture) መደረጉን፣ ድርጅቱ ኢትዮጵያ በመግባት ማምረት እስከሚጀምርበት ወቅት ድረስ ለቀጣይ ዓመት ግማሽ ዓመት የሚሆኑ 40 ሚሊዮን የመማርያ መጻሕፍት እንዲያቀርብ መደረጉን ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት የመጻሕፍቱ ኅትመት እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

በአገር ውስጥ ለሚገኙ የኅትመት ድርጅቶች ዕድል መሰጠቱን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ የድርጅቶቹ የማተም ብቃት በሚፈለገው ደረጃ ባለመሆኑና የአገር ውስጥ ድርጅቶች የሚያቀርቡት የኅትመት ዋጋ በጣም ውድ ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡

የጨረታ ሒደቱ ሲከናወን የአገር ውስጥ አታሚዎች አነስተኛ ያቀረቡት የማምረቻና መጻሕፍቱን ክልሎች ድረስ የማሠራጫ ዋጋ 27 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ቶፕሀም የተባለው የጃፓን ኩባንያ የኅትመትና ክልሎች ድረስ ለሚያሠራጫቸው መጻሕፍት ዋጋ ሰባት ቢሊዮን ብር በማቅረቡ መመረጡን ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ለ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ ጥቂት መጻሕፍት፣ እንዲሁም እስከ ግማሽ ሴሚስተር ድረስ የተቀሩትን ለማስገባት ታቅዷል ተብሏል፡፡

በአገር ውስጥ ከሚገኙ የኅትመት ድርጅቶች ጋር በነበረው ውይይት የኅትመት ዋጋ መወደድ እንደ ችግር የተነሳው፣ የወረቀት ታክስ ከፍሎ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጨረታ የሚያሸንፉ የአገር ውስጥ ድርጅቶችም ቢሆኑ ጨረታ ሲያሸንፉ ውጭ አገር የሚያሳትሙበት ዋነኛ ምክንያት፣ የመማርያ መጻሕፍት ከውጭ ሲገቡ ታክስ ስለማይደረጉ፣ ወረቀት ሲገባ ደግሞ ከፍተኛ ታክስ ስለሚጣል የአገር ውስጥ አታሚዎችን አቅም እንዲቀንስ ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት የትምህርት ሚኒስቴርና የገንዘብ ሚኒስቴር በካቢኔ ደረጃ ባደረጉት ውይይት የወረቀት ታክስ መነሳቱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ በመሆን ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ማዕከል እንዲሆኑ በተያዘው ዕቅድ መሠረት፣ ሁሉም ራስ ገዝ እንደሚሆኑ ብርሃኑ (ፕሬፌሰር) ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያ ራስ ገዝ የሚሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለማስተዳደር ስምንት አባላት ያሉት ቦርድ ከነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ መቋቋሙ ተገልጿል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ እንዲሆን ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት የሚፈጅ የሽግግር ሥራውን የሚያከናውነው ቦርዱ ሲሆን፣ ለቦርዱ ሊቀመንበር ሆነው እንዲያገለግሉ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ተሹመዋል። 

የትምህርት ሚኒስትር ደኤታው ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ደግሞ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር እንዲሆኑ፣ በጠቅላይ ሚኒሰትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሹመት ማግኘታቸውም ተገልጿል። 

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ ራስ ገዝ እንዲሆን በአዋጅ የተፈቀደ ቢሆንም፣ ሙሉ በሙሉ ራስ ገዝ ሆኖ ሥራ የሚጀምረው የሚተዳደርባቸው መመርያዎች ከተዘጋጁ በኋላ ከ2017 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚሆን ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል።

በተጨማሪም በ2015 ዓ.ም. በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፈተናቸውን ሲወስዱ የነበሩት የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች፣ የመጨረሻዎቹን ሦስት ፈተናዎች ባለመፈተናቸው ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ተፈትነው እንዲያሚያጠናቅቁ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በ2016 ዓ.ም. መስከረም አጋማሽ ድረስ ውጤት ይፋ በማድረግ በጥቅምት ወር የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እንዲጀመር የማድረግ ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዙ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ለመገንባት መታቀዱን አክለዋል።

በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የኢንተርኔት አገልግሎት ባለባቸው አካባቢዎች በኦንላይን እንደሚሰጥም፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) አስታውቀዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...