- አገልግሎት እየሰጡ ያሉት መንገዶች 247 ቢሊዮን ብር ተገምተዋል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመጪዎቹ አሥር ዓመታት በከተማዋ ማስተር ፕላን መሠረት ለሚያካሂዳቸው የመንገድ ግንባታዎች፣ 500 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው አስታወቀ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 1,114 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታና ጥገና ያካሄደ መሆኑንና በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት 11.6 ቢሊዮን ብር መመደቡን፣ የከተማ አስተዳደሩ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሞገስ ጥበቡ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ አሁን ያለው የመንገድ መሠረተ ልማት በወቅቱ የገበያ ዋጋ መሠረት አጠቃላይ ግምቱ 247 ቢሊዮን ብር የሚገመት እንደሆነ፣ በቀጣይ የተሻሉ የመንገድ መሠረተ አውታሮችን መገንባት አማራጭ የሌለው መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስና የከተማ ገጽታን ለመቀየር የማይተካ ሚና ይኖራቸዋል የተባሉ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከ2.7 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ አጠቃላይ ርዝመታቸው 2.3 ኪሎ ሜትር የሆነ ስድስት ተሻጋሪ ድልድዮች እየተገነቡ ነው ብለዋል፡፡
ለቃሊቲ-ቱሊ ዲምቱ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት ለሚያስፈልገው በጀት አበዳሪ የነበረው የቻይና ኤግዚም ባንክ፣ ብድሩን ለአምስት ዓመታት መልቀቅ ባለመቻሉ ምክንያት ተስተጓጉሎ የነበረ ቢሆንም፣ የከተማ አስተዳደሩ ወስኖ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ግንባታው እየተከናወነ ለትራፊክ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በ2.4 ቢሊዮን ብር እየተከናወነ መሆኑን፣ ከጥር 2016 ዓ.ም. በፊት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ የቻይናው ኤግዚም ባንክ ብድሩን በማቆሙ ምክንያት ቆሞ የነበረው የቃሊቲ-ቂሊንጦ የመንገድ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ለዚህ ፕሮጅክትም ውሳኔ ተላልፎ ግንባታው እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ የሚገነቡ መንገዶችን በተመለከተ በዓለም ባንክ ድጋፍ አማካይነት የትራንስፖርት ማስተር ፕላን እየተዘጋጀ መሆኑን፣ ዕቅዱ የግንባታ ፕሮጀክትና የቅደም ተከተል አፈጻጸም ምን መሆን እንዳለበት በግልጽ የሚያሳይ የአሥር ዓመት ዲዛይን እየተሠራላቸው እንደሆነ የተናገሩት ሞገስ (ኢንጂነር)፣ መንገዶቹ በአጠቃላይ ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃሉ ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ለካፒታል ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት መስጠቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከአጠቃላይ የከተማዋ በጀት 60 በመቶ የሚሆነው ለካፒታል ፕሮጀክት እየተመደበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው ያሉ ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለሚዲያ ባለሙያዎች ነሐሴ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. አስጎብኝቷል፡፡
በጉበኝቱ በፒያሳ አራዳ አካባቢ እየተገነባ ያለውን የዓድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም፣ 455 የልማት ተነሽ አርሶ አደሮችን ያቀፈውና በ14 ሔክታር መሬት ላይ የተገነባውን የኢንቨስትመንት ልማትና ልህቀት፣ ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተገነባ ያለውን የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከልና የትራንስፖርት ቢሮ ሕንፃ፣ የማሳለጫ መንገዶችን፣ በሃያት አካባቢ እየተገነባ የሚገኘውን የሃያት ሳይት ግብርና ምርቶች ማከማቻና መሸጫ ማዕከል፣ በ1.5 ቢሊዮን ብር የተገነባውን የለሚ እንጀራ ፋብሪካ፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ኮንቬንሽን ማዕከልን በተመለከተ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡