Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

እንይ ሪልስ ስቴት ገንብቶ ባስረከበው ግቢ ውስጥ አዲስ ግንባታ መጀመሩ ውዝግብ አስነሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

እንይ ሪል ስቴት ኩባንያ በቦሌ ቡልቡላ ገንብቶ ለገዥዎች ባስተላለፈው የመኖሪያ ቤቶች ግቢ ውስጥ አዲስ ግንባታ መጀመሩ ውዝግብ አስነሳ፡፡

ሪል ስቴቱ ከገነባቸው ሕንፃዎች ቤት ገዝተው የሚኖሩና የጋራ ሕንፃ ቤት ባለቤቶች ማኅበራት መሪዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሪል ስቴቱ ሕንፃውን ገንብቶ ካርታ ቢያስረክባቸውም፣ የሕዝብ ይዞታ በሆነውና በግቢው ውስጥ ባለው የነዋሪዎች የጋራ መሬት ላይ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በ1997 ዓ.ም. 50 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት በሊዝ ተቀብሎ የመኖሪያ ሕንፃ ግንባታ ካካሄደው እንይ ሪል ስቴት ቤት የገዙ ባለንብረቶች፣ በግቢው ውስጥ የጋራ አረንጓዴ ቦታ፣ የሕፃናት መጫዎቻዎች፣ የጋራ አገልግሎት መስጫዎችና የመሳሰሉ የነበሩ ቢሆንም፣ ሪል ስቴቱ አዲስ ዲዛይን ሠርቶ ግንባታ መጀመሩን የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ኢዮሲያስ አራጌ ተናግረዋል፡፡

በ1997 ዓ.ም. መሬቱን ተቀብሎ ሲያለማ የነበረው ሪል ስቴቱ፣ ቤቱን ገንብቶ በአብዛኛው ቤቱን ያስተላለፈው በ2009 ዓ.ም. አካባቢ መሆኑን፣ አሁን የግለሰቦች ካርታ የመጨረሻ ርክክብ እየተደረገ ስለመሆኑም አቶ ኢዮሲያስ አክለው ገልጸዋል፡፡

የቤት ባለቤቶቹ ምንም እንኳ የግቢውን አጠቃላይ ካርታ ባይረከቡም ቤታቸውን ተረክበው በእያንዳንዳቸው ስም ሥር ከተካተቱት የአረንጓዴ፣ የመጫወቻ፣ የፓርኪንግና መሰል የጋራ አግልግሎት መጠቀሚያ ቦታዎች መካከል ግቢው መግቢያ በር አካባቢ የከርሰ ምድር ውኃ ቁፋሮ አድርገው ለመጠቀም ማጠናቀቂያ ላይ ቢደርሱም፣ የከርሰ ምድር ውኃውን እንዳይጠቀሙ መከልከላቸውን ተናግረዋል፡፡

የቦሌ ቡልቡላ ዘንባባ የጋራ ሕንፃ ባለንብረቶች ማኅበር የተሰኘው የነዋሪዎች ኅብረት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ውስጥ የተገነቡ የመኖሪያ ቤቶች ግቢ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የውኃ እጥረት በመኖሩ፣ ችግሩን ለመቅረፍ የጉድጓድ ቁፋሮ ከእያንዳንዱ የቤት ባለቤት ገንዘብ ተሰብስቦ ስለመከናወኑ ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ማኅበሩ የከርሰ ምድር ውኃ ቁፋሮውን እንዲያካሂድ ከአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ፈቃድ የተሰጠው መሆኑን፣ ቁፋሮው ተጠናቆ የማጠናቀቂያ ፈቃድ እንዲሰጣቸውም ቢጠይቁም ውኃውን እንዳይጠቀሙ መከልከላቸውን የገለጹት የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አበራ ታደሰ ናቸው፡፡ 

በአጠቃላይ በዚህ የመኖሪያ ግቢ ውስጥ ቤቱን የገዙ ነዋሪዎች ግዥውን ከመፈጸማቸው በፊት፣ በሳይት ፕላኑ ላይ የተካተቱ የጋራ መገልገያዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ለቤቱ አጠቃላይ ዋጋ መክፈላቸውን አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

ሪል ስቴቱ የፕላን ማሻሻያ የሕግ ሽፋን በማድረግ ያለ ነዋሪዎች ፈቃድና ዕውቅና፣ የልጆች መጫዎቻና አረንጓዴ ልማት ቦታ ላይ አዲስ ፕላን አውጥቶ ግንባታ ማካሄዱን አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በግቢው ውስጥ ከሳይት ፕላን ውጪ ትንንሽ ቤቶችን ገንብቶ ከነዋሪዎች ዕውቅና ውጪ ሽያጭ ማካሄዱን አክለዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የእንይ ሪል ስቴት የሕግ አማካሪ አቶ ክንፈ ሚደቅሳ እንደገለጹት፣ በዘርፉ ያሉ ሕግጋትን መሠረት በማድረግ አዋጭ ነው ያለውን መንገድ በመከተል ግንባታ ማካሄድ ይቻላል፡፡ ይህም ማለት ግንባታው ከመካሄዱ በፊት የተዘጋጀውን የሳይት ፕላን አንቀይርም፣ አንነካም ወይም የሚለወጥበት አግባብ የለም የሚል ድንጋጌ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ለውጥ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ መኖሩን የቤት ባለቤቶች ያውቃሉ ብለዋል፡፡

የሳይት ፕላን ሊቀየር የሚችለው ከጊዜ ወደ ጊዜ ከደንበኞች ፍላጎት ወይም ከገበያና ከቴክኖሎጂ መቀያየር ጋር አብረው የሚለወጡ ሁኔታዎች በመኖራቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በግቢው ውስጥ መኖር ያለባቸው የአረንጓዴ፣ የሕፃናት መጫወቻ፣ የጋራ መጠቀሚያና ሌሎችም አገልግሎት መስጫ ቦታዎች መጀመሪያ ከታሰቡበት ቦታ ሊቀያየሩ ይችላል እንጂ በግቢው ውስጥ አሉ ብለዋል፡፡

አክለውም ይህ የመለወዋጥ ጉዳይ ሕገወጥ ሊሆን የሚችለው ግን ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ፈቃድ ካላገኘ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሪል ስቴቱ ቤቱን ገዝተው ለገቡ የቤት ባለቤቶች ግዴታ እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ሳይት ፕላን መሠረት ግንባታ ያካሂዳል እንጂ ከዚህ ውጪ ምንም ዓይነት ግንባታ ማካሄድ አይችልም የሚል ግዴታ አልተጣለም ብለዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው የመዋኛ ገንዳ ተብሎ ተይዞ የነበረው በስፖርት ማዘውተሪያ መተካቱን፣ የልጆች መጫወቻም ግቢው ውስጥ መገንባቱን ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በአንድ ሳይት ውስጥ የአረንጓዴ ቦታ ኪራይ ለትርፍ እንደተቋቋመ ኩባንያ ሕጉን በጠበቀ መንገድ ግንባታውን ያካሂዳል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የቤት ባለንብረቶች ለገነቡት የውኃ ጉድጓድ፣ የይዞታው ባለቤት እንይ ሪል ስቴት በመሆኑ ራሱ መጨረስ ሲገባው፣ ተገንብቶ በመገኘቱ እንዲቆም መደረጉን የሕግ አማካሪው ተናግረዋል፡፡ የቤት ባለቤቶቹ ያቀረቡት ደብዳቤ እንደሚያሳየው ግን ቁፋሮውን ፈቃድ ለማካሄድ ሕጋዊ ዕውቅና በማኅበሩ በኩል አግኝተዋል፡፡ የሕግ ባለሙያው የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮው ፈቃድ በአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን መሰጠቱን አምነው፣ ነገር ግን የማኅበሩ አካሄድ ሕገወጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ፈቃዱን አግኝተው ከቆፈሩ በኋላ መጠቀም ለምን ተከለከሉ በሚል ሪፖርተር የጠየቃቸው የእንይ ሪል ስቴት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ከጀምሩ ፈቃድ የሰጠው የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 በጻፈው ድብዳቤ መሠረት መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በስህተት በእንይ ሪል ስቴት ጥያቄ እንደቀረበለት ተደርጎ በመስጠቱ ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ጉዳዩን በተመለከተ የጻፈው ደብዳቤ፣ የቤት ባለቤቶች በተረከቡት ግቢ ውስጥ ባለ ክፍት ቦታ ያስቆፈሩትን የከርሰ ምድር ውኃ ለመጠቀም፣ የግቢው ካርታ ባለቤትነት የሪል ስቴቱ በመሆኑና የቀረበውን የሕጋዊ ባለቤትነት ጉዳይ ይገባኛል የሚለው አካል ጉዳዩን በፍርድ ቤት አስወስኖ ሲመጣ ለተወሰነለት አካል የመጠቀሚያ ፈቃዱን እንደሚሰጥ ይገልጻል፡፡

በሌላ በኩል የቤት ባለቤቶቹ ያቀረቡት ሌላኛው ቅሬታ በግቢው ውስጥ ከተገነቡት ሕንፃዎች መካከል አንዱ ሕንፃ የመዛነፍ ችግር እንደገጠመው ባለቤቶቹም፣ ከሪል ስቴት ኩባንያውም የተሰማ ሲሆን፣ ሪፖርተርም በቦታው ተገኝቶ እንዳየው ሕንፃው ከተገነባ በኋላ ከሥሩ ተጨማሪ ማጠናከሪያ ተደርጎበታል፡፡

ቤት ገዥዎቹ እንደሚሉት ሕንፃው ሊያስከትል የሚችለው ጉዳትና አደጋ ካለ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ይደረጋል ተብሎ የተገለጸላቸው ቢሆንም፣ እስካሁን ተጠንቶ የመጣ ውጤት አለመኖሩን፣ ነገር ግን ከከተማ አስተዳደሩ ባለሙያዎች ሕንፃው ከፍተኛ የሆነ ችግር እንዳለበት መገለጹን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሪል ስቴቱ የሕግ አማካሪ እንደሚሉት፣ በጉዳዩ ላይ ለአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች 1.8 ሚሊዮን ብር በመክፈል ጥናት እየተደረገ ነው፡፡ ጥናቱ የተለየ ሊያመጣው የሚችለው ውጤት ባይኖርም፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ ግን በሕንፃው ላይ ያለው ችግር የከፋ አለመሆኑንና አደጋ ሊያመጣ የማይችል መሆኑ ማረጋጫ እንደተሰጠበት አቶ ክንፈ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የግንባታ ፈቃድ ባለሙያ አቶ አዲሱ ደመቀ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሪል ስቴቱ በግቢው ውስጥ ለአረንጓዴ ቦታም ሆነ ለሕፃናት መጫወቻ የቤት ለውጥ ሊኖር እንደሚችል እንጂ የተወሰነ ቦታ ላይ ለይቶ እንዲያስቀምጥ ሕጉ አያስገድደውም፡፡ ሪል ስቴቱ አሁንም ግንባታ ለማካሄድና የሳይት ፕላን ለመከለስ ሕግ እንደማይከለክለው አክለዋል፡፡

ኩባንያው አሁንም ግንባታ ለማካሄድ ብዙ ቦታ እንዳለው የተናገሩት አቶ አዲሱ፣ ይሁን እንጂ መንግሥት የሚያውቀውና ዳኝነት ሊሰጥ የሚችለው የተናጠል ካርታ አልቆ የሳይት ካርታ ሲመክን መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም የመንግሥት ሚና የሪል ስቴቱን ባለቤት በወሰደው አምስት ሔክታር መሬት ላይ ባለው የሳይት ካርታ መሠረት የግንባታ ሕግጋቱን መጠበቅ አለመጠበቁን መከታተል ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጉዳዮች የሚወሰኑት በራሱ በሪል ስቴቱና ቤት በገዙት ባለንብረቶች መካከል በመሆኑ፣ ሁሉም ጉዳይ ወደ መንግሥት ሊያስኬድ የሚያስችል አይሆንም ሲሉም ጠቁመዋል፡፡  

እንይ ሪል ስቴት በ1997 ዓ.ም. የወሰደውን መሬት እስካሁን ግንባታውን አጠናቆ ለነዋሪዎች አለማስረከቡንና መሬቱንም ለታለመለት ዓላማ ወቅቱን ጠብቆ አለመልማቱን፣ እንዲሁም ቤት ደርሷቸው የገቡ ባለቤቶች በጋራ የነዋሪዎች ነፃ ቦታ ላይ በፈለጉት መንገድ መገልገል አለመቻላቸውን በተመለከተ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ምክትል ኃላፊ አቶ እንዳለ ይመርን ሪፖርተር አነጋግሯቸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ በወሰነው መሠረት የተለያዩ የቤት አልሚዎች በተሰጣቸው መሬት ላይ ማካሄድ ያለባቸውን ግንባታ በወቅቱ እንዲያጠናቅቁ ተለይቶ የአንድ ዓመት ዕድሜ በማስጠንቀቂያ ስለመሰጠቱ አቶ እንዳለ ተናግረው፣ እንይ ሪል ስቴትም ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሁለቱ አካላት ውዝግብ መሥሪያ ቤታቸው ስለመድረሱ፣ ችግሩን አልሚው ከደንበኞቹ ጋር በመመካካር እንዲፈታ ጥረት መደረጉን አክለዋል፡፡

በመሆኑም በርካታ ችግሮች በአልሚውና በቤት ገዥዎች ስምምነት መካከል መፈታት ያለባቸው በመሆኑ፣ አሁንም ሊደረግ የሚገባው ከሪል ስቴቱ ጋር በነበራቸው ውል መሠረት ቁጭ ብለው መነጋገርና መፍታት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ሪል ስቴቱ ከሕግ ውጪ ያልተገባ ድርጊት ላይ ከተገኘ መንግሥት ዕርምጃ እንደሚወስድ የገለጹት አቶ እንዳለ፣ በግቢው ውስጥ የተቆፈረውን የውኃ ጉድጓድ ሁለቱ አካላት በመነጋገር መፍትሔ መፈለግ፣ ካልቻሉ ያዋጣኛል በሚሉት የሕግ አግባብ ሊቀጥሉበት ይችላሉ ሲሉ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች