በመናኸሪያዎች ውስጥ ቢቶፕያ ቴክኖሎጂ ሶሉውሽን በተሰኘ የሶፍትዌር ሥርዓት በመዘርጋት ከታሪፍ በላይ የሚወስድ ክፍያን በማስቀረት አንድ ቢሊዮን ብር የሕዝብ ገንዘብ እንዳይባክን መደረጉ ተገለጸ፡፡
የቢቶፕያ ቴክኖሎጂ ሶሉውሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክርስቲያን ተሾመ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በትግበራው አማካይነት ሕገወጦች ከታሪፍ በላይ በማስከፈል ኅብረተሰቡን ይዘርፉት የነበረውን እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ድረስ የሕዝብ ገንዘብ እንዳይባክን ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በቴክኖሎጂው አማካይነት ትኬት እንዲቆረጥ በማድረግ በተሳፋሪና በሾፌር መካከል የሚካሄደው የጥሬ ገንዘብ ልውውጥ ማስቀረት መቻሉን አቶ ክርስቲያን ገልጸዋል፡፡
ቢቶፕያ ቴክኖሎጂ ሶሉውሽን ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመት ውስጥ በአገሪቱ የሚታዩ የትራንስፖርት ዘርፍ ክፍተቶችንና ብልሹ አሠራሮችን በማስተካከል መነኸሪያዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማዘመን ላይ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ተናግረዋል፡፡
ከየክልሉ የትራንስፖርት ቢሮዎች ጋር በዋናነት እንደሚሠራ የገለጹት አቶ ክርስቲያን ከትራንስፖርት ሚኒስትር ጋር የተለያዩ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመናኸሪያ አካባቢ ያሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ሒደቶች በርካታ ሕዝብን ለብዝበዛና ለምሬት ሲዳረግ የነበረው የአሠራር ሒደት የተሻሻለ እንዲሁም ዘመናዊ መንገድን የተከተለና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ለክትትልና ለቁጥጥር የተመቸ እንዲሆን ለማድረግ ቢቶፕያ ቴክኖሎጂ ያበለፀገውን ዲ-ትሪፕ የተሰኘ መተግበሪያ ወደ ሥራ አስገብቶ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ቴክኖሎጂው ወደትግበራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በአዳማ፣ በሻሸመኔ፣ ዶዶላ፣ ባቱ፣ ቢሾፍቱ፣ ጅማ፣ አሰላ፣ ባሌ ሮቤ፣ በቆጂ፣ በፊቼ፣ በአምቦ፣ በወሊሶ፣ በሆለታ፣ አጋሮ፣ ጭሮ፣ ቡሌ ሆራ፣ ያቤሎ፣ ሞያሌ እንዲሁም በሲዳማና ደቡብ ክልል ሐዋሳ፣ ሆሳዕናና ወልቂጤን ጨምሮ ከ25 በላይ የሚሆኑ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ አቶ ክርስቲያን ተናግረዋል፡፡
በመናኸሪያ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በወጣላቸው የደረጃ ታሪፍ ብቻ እንዲጭኑ የሚያዘውን ታሪፍ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ሆነው ወደ ሥምሪት የማይገቡና በቂ አገልግሎት የማይሰጡ ተሽከርካሪዎች በሲስተሙ አማካይነት ተገደው ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ የትራንስፖርት እጥረትን ለመቅረፍ አስተዋጽኦ ማድረጉን ክርስቲያን ተናግረዋል፡፡
ተሽከርካሪዎች በተመዘገቡበት ተራ መሠረት ብቻ እንዲሠማሩ በማድረግ መናኸሪያዎች ውስጥ ከሚስተዋሉ ግርግሮችና ደላሎች ነፃ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን አቶ ክርስቲያን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በየደረጃው ለሚገኙ የመንግሥት ኃላፊዎች የመናኸሪያዎች ሙሉ እንቅስቃሴ አንድ በአንድ መከታተልና ሪፖርት እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ ከ350 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ክርስቲያን ተናግረዋል፡፡
በቅርቡም ይህንን ቴክኖሎጂ ወደ መቀሌ፣ ነገሌ ቦረናና አርሲ ለመተግበር ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ብለዋል፡፡
በቀጣይ ተሳፋሪዎች ትኬት የሚቆርጡት በቴሌብርና በሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት አማካይነት መጠቀም እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡