የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በተፈለገው ልክ እንዳያድግ የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ተደራሽ አለመሆናቸው እንቅፋት መሆኑን የኢትዮጵያ የኢኖቬሽ ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው ነሐሴ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. የዲጂታል ኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ‹‹የዲጂታል ኢትዮጵያ›› 2025 የግማሽ ዘመን አፈጻጸም ግምገማ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡
የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ/ር)፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ከተጀመረ በኋላ በኢትዮጵያ ጥሩ ለውጦች ቢኖሩም፣ ስትራቴጂው በተፈለገው ልክ እንዳይተገበር የሚያደረጉ ማነቆዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ለዲጂታል ኢኮኖሚውና ቴክኖሎጂ ተደራሽ ለማድረግ የቴሌኮምና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተደራሽ አለመኖር፣ ለስትራቴጂው መተግበር እንቅፋት መሆኑናቸውን አማካሪው አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም ያነሱት የኤሌክትሪክ ኃይል ዝርጋታ 54 በመቶ የደረሰ መሆኑን ጠቁመው፣ አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚኖርባቸው አካባቢዎች ወይም 6 በመቶ ዝርጋታ አለመኖረን ጠቁመዋል፡፡
ይህ ደግሞ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ከተደራሽነት አኳያ ገዳቢ ምክንያት መሆኑን ጠቁመው፣ የቴሌኮም ዝርጋታም ውስንና ለዕድገቱ ሌላው እንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን ያነሱት አብዮት (ዶ/ር)፣ ኅብረተሰቡ የስማርት ቀፎ የመግዛት አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሉ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ መሳለጥ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. ከ2020 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ የስማርት ቀፎ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍ ቢልም፣ ከዜጎች ገቢ አንፃር የመግዛት ፍላጎት ጋር አኳያ ግን በአቅም ምክንያት መገደቡን አልሸሸጉም፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያ ፀድቆ ወደ ሥራ ከገባ ሦስተኛ ዓመቱ እየመጣ መሆኑን ገልጸው፣ የዲጂታል መታወቂያ፣ ከክፍያ ሥርዓትና ለእነዚህ ተግባሮች የሕግና ሥርዓት መዘጋጀት በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ተብሏል፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ ተግባሮችም ቢሆኑ በተፈለጉት ልክ ያልተሠሩ መሆናቸውን ጠቁመው፣ አሁንም የዲጂታል ልማቶች በሁሉም አካባቢዎች መተግበርን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
‹‹በዋናነት የዲጂታል ልማት ስኬታማ የሚሆነው ግለሰቦች ጋ ውጤት ሲያመጣ ነው፤›› ያሉት አማካሪው፣ ይህም እያንዳንዱ የግለሰብ ሕይወት ያመጣውን ለውጥ መመዘንና መገምገም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ገጠራማ አካባቢዎች እንደሚኖር ገልጸው፣ የዲጂታል ልማቶች እነዚህ ማኅበረሰብ ክፍሎች ጋ መድረሳቸውን መፈተሽ ይገባል ብለዋል፡፡
በስትራቴጂው የታዩት በርካታ ክፍተቶች አንዱ ከተሞች ላይ ያተኮሩና በጥልቀት ወደ ማኅበረሰቡ እንዳልሄዱ የሚያሳዩ መሆኑናቸውን ገልጸው፣ ከግምገማው በኋላ ያለውን ውጤትና ችግሮች ታይተው መፍትሔ እንደሚሰጥባቸው ተናግረዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በዋናነት የዲጂታል መሠረተ ልማቶች በማልማት ላይ ያተኮረ መሆኑን፣ በሦስት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን መገምገምና በቀሪው ሁለት ዓመታት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ ነው ብለዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ዕቅድና ትግበራ ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ከፍ ለማድረግና ሁሉን አቀፍ አካታች ማኅበረሰብ ለመገንባት ወሳኝ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጸዋል፡፡
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬታማ የሚሆነው ውጤታማ በሆነ መንገድና በባለድርሻ አካላት ሙሉ ድጋፍ ተግባራዊ ከሆነ ብቻ መሆኑን የገለጹት በለጠ (ዶ/ር)፣ የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት በማረጋገጥ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች መፍጠር አገራዊ ገቢን ማሳደግ በስትራቴጂው ከተቀመጡ ግቦች መካከል ይገኙበታል ብለዋል፡፡