- ቆይ አንቺ ምን አሳሰበሽ?
- እንዴት አያሳስበኝም?
- አንቺን የገጠመሽ ችግር በሌለበት ለምንድነው ስለ አገሪቱ ፖለቲካ የምትጨነቂው?
- እኔን የገጠመኝ ችግር እንደሌለና እንደማይኖር በምን አወቅህ?
- ባለቤትሽ የመንግሥት ሰው ሆኖ እንዴት አንችን ችግር ሊገጥምሽ ይችላል?
- እስኪ አትቀልድ።
- አልቀለድኩም!
- እንዴት? አገሪቱ ችግር ውስጥ መሆኗ የእኔ ችግር አይደለም ማለት ነው?
- እንደዚያ ማለቴ አይደለም።
- እና ምን እያልክ ነው?
- በቀጥታ አንቺ ጋር የሚደርስ ችግር አይኖርም ማለቴ ነው።
- የአገሪቱ ፖለቲካ ከዛሬ ነገ ይሰክናል ብንልም አልሆነም። ሁሉ ነገር ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደ እየተመለከትኩ ነገ ችግሩ እኔ ጋር እንደማይደርስ ምን ማረጋገጫ ይኖረኛል?
- አይ… እንደምትይው የተፈጠረ ነገር የለም።
- እንዴት? ችግር የለም እያልከኝ ነው?
- ፈተና አልገጠመንም ወይም ችግር የለም አላልኩም።
- ምን እያልክ ነው ታዲያ?
- ፈተና ቢገጥመንም ፈተናዎችን ወደ ዕድል እየቀየርን መጓዛችን ይቀጥላል እያልኩ ነው።
- ይህን ነገር አንተም መንግሥትም ትሉታላችሁ እንጂ አንዲት ፈተና ወደ ዕድል ተቀይራ አልተመለከትንም።
- በእኛ በኩል፣ ማለቴ በመንግሥት በኩል ያለው ትልቁ ችግር እሱ ነው።
- ምኑ?
- ያጋጠሙንን ፈተናዎችን እንዴት ወደ ዕድል እየቀየርናቸው እንደሆነ የሚያሳይ መረጃ ለሕዝብ እየሰጠን አለመሆኑ በእኛ በኩል የሚስተዋል ትልቅ ክፍተት ነው።
- እኔ ግን ከግጭት ወደ ግጭት፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስንገባ እንጂ ወደ ዕድል የተቀየረ ነገር አላየሁም።
- በእኛ በኩል በቂ መረጃ እየቀረበ ባለመሆኑ አንቺም ሆንሽ ሌላው ማኅበረሰብ ዕድሎቹን ለማየት እንደተቸገረ ይታወቃል።
- እናንተ መረጃ ካልሰጣችሁ የአገሪቱ ችግሮች ወደ ዕድል ሲቀየሩ ለማኅበረሰቡ አይታዩም ማለት ነው?
- እንደዚያ ማለቴ ሳይሆን…
- ወይስ ለእኛ የሚታየው ለእናንተ አይታይም?
- እንዴት?
- ለእኛ የሚታየው የሰው ሕይወት እያጠፋ ያለ ግጭት ከቦታ ቦታ ሲስፋፋ ነው። ለእናንተ ግን የሚታያችሁ ሌላ ነገር ይሆን?
- ፈተናዎች አሉ ቢሆንም ፈተናዎቹን ወደ ዕድል እየቀየርናቸው ነው ወደፊት የሚገጥሙን ፈተናዎችም ወደ ዕድል ይቀየራሉ።
- እሱ ነገር እኮ ነው የሚገርመኝ?
- ምኑ?
- ሰዎች እየታሠሩና እየተሰወሩ ነው።
- ይህንንም ወደ ዕድል እንቀይረዋለን።
- ሰዎች መታሠራቸው ሲቆም ሳይሆን ከተፈቱ በኋላ አገር ጥለው ሲሰደዱ ነው የምናየው።
- እሱን እኮ ነው የምልሽ?
- ምን?
- ወደ ዕድል እየቀየርነው ነው።
- የሰዎች መታሰርን?
- እህ…!
- የታል የቀየራችሁት?
- ይኸው ራስሽ ተናገርሽው አይደል እንዴ?
- ምን አልኩኝ?
- የታሠሩ ሰዎች ከአገር እየወጡ ነው አላልሽም?
- ከአገር እየተሰደዱ ነው ያልኩት።
- ያው ነው።
- አሃ… እንዲህ ነው ወደ ዕድል የምትቀይሩት?
- እንደዚያ አላልኩም።
- እና ምና እያልክ ነው?
- ቢታሠሩም ሲፈቱ የውጭ ዕድል ይገጥማቸዋል እያልኩ ነው።
- እህ… ታሥረው የነበሩ አንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ከአገር ከወጡ በኋላ ፖለቲካ በቃኝ ማለታቸውንስ እንዴት ነው የምታየው?
- እንደ ዕድል!
- አሁን ዕድል የምትሉት ምን እንደሆነ በደንብ ገብቶኛል።
- ምኑን ነው ዕድል የምንለው?
- ፈተናዎቹን !
- Advertisment -
- Advertisment -