Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

እያደገ የመጣው በኅብረት ሥራ ማኅበር የተደራጁ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በዋናነት ከሚጠቀሱ የፋይናንስ ተቋማት በተጨማሪ፣ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተው አገልግሎት የሚሰጡ የፋይናንስ ተቋማት ቁጥራቸው እያደገ መጥቷል፡፡  

የኅብረት ሥራ ማኅበር አዋጅን መሠረት አድርገው የሚቋቋሙት እነዚህ የቁጠባና የብድር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በፌዴራል ደረጃ ቁጥራቸው ከ21 ሺሕ በላይ ስለመድረሱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት መደበኛ የሚባለውን የፋይናንስ አገልግሎት ከሚሰጡ እንደ ባንክና ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት በተለየ አደረጃጀትን በመከተል የሚቋቋሙና የገንዘብ አቅርቦት ምንጫቸውንም ከአባሎቻቸው የሚሰበስቡትን ቁጠባ አድርገው፣ መልሰው ለአባሎቻቸው የብድር አገልግሎት የሚያቀርቡ ናቸው።

እንደሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ለሌሎች ብድር የሚያቀርቡ መሆናቸው መሠረታዊ መለያቸው እንደሆነም ይጠቀሳል፡፡ ባለፈው እሑድ ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በይፋ ምሥረታውን ያካሄደው የጳጉሜን የገንዘብ፣ ቁጠባና የብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበር ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ መኮንን እንደገለጹትም፣ የቁጠባና የብድር የኅብረት ሥራ ማኅበራት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አባሎቻቸው ፋይናንስ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል፡፡ የቁጠባ ባህልን በማዳበር ረገድም የእነዚህ ማኅበራት ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑም ይጠቅሳሉ፡፡  

የቁጠባና የብድር የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከባንክና ከማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብድር ለማግኘት ያልቻሉ አባሎቻቸውን ወይም የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚፈልጉትን ብድር በቀላሉ እንዲያገኙ ከማመቻቸት ባለፈ፣ ማኅበራቱ ከሚያገኙት ትርፍም ተቋዳሽ የሚያደርጋቸው በመሆኑ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

እነዚህ የቁጠባና የብድር የኅብረት ሥራ ማኅበሮች ከአባሎቻቸው የሚያሰባስቡትን የባለድርሻነት መዋጮ በካፒታል መልክ በማሰባሰብ መልሰው ለአባላት ብድር ማቅረብ ዋነኛ ተግባራቸው መሆኑን የገለጹት፣ የጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘለዓለም ጌታነህ በበኩላቸው፣ እንዲህ ያሉት ተቋማት ጠቀሜታቸው ዘርፈ ብዙ ነው ይላሉ፡፡ 

ከባንክና ከማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብድር ማግኘት ለማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመድረስ ቀዳሚው መሆናቸውንና፣ ዜጎች ሀብት እንዲያፈሩ ዕድል የሚሰጡና ዋጋን በማረጋጋት ጭምር የየራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

በአሁኑ ወቅትም በመላ አገሪቱ የተቋቋሙ የቁጠባና የኅብረት ሥራ ማኅበራት አቅማቸው እየጎለበተ የአባሎቻቸውን ቁጥር እያሳደጉ በሚሊዮች የሚቆጠር ገንዘብ ወደማበደር ስለመሸጋገራቸው ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፋይናንስ ተደራሽነት አሁንም እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑና ወደ ባንክ በመሄድ ብድር ማግኘት እጅግ ፈታኝ በመሆኑ፣ ተጨማሪ የቁጠባና የብድር የኅብረት ሥራ ማኅበራት መስፋፋት አስፈላጊ በመሆኑ እነሱም ይህንን ማኅበር ሊመሠርቱ መቻላቸውን አመላክተዋል፡፡ 

አዋጅ ቁጥር 985/2009ን መሠረት አድርገው የሚቋቋሙት እነዚህ ማኅበራት፣ ዜጎች በጋራ ሆነው የሚያስፈልጓቸውን የፋይናንስ ፍላጎቶች ለማሟላት ጠቀሜታ የሚሰጡ ናቸውም ብለዋል፡፡  የእሳቸውም ተቋም ይህንኑ መሠረታዊ ዓላማ በመመርኮዝ ሰዎች በፈቃደኝነት ኢኮኖሚዊና ማኅበራዊ ችግሮቻችን በጋራ ለመፍታት ያቋቋሙትና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚያስተዳድሩት ራስ አገዝ ድርጅት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡  

በዋናነት ግን ዜጎች በአቅማቸው ቆጥበው፣ በአቅማቸው ተበድረው እንዲሠሩ ለሚፈልጉት አገልግሎትም በቀላሉ ብድር ለማግኘት የሚያስችላቸው መሆናቸው የተለየ እንደሚያደርጋቸው ጠቁመዋል፡፡ 

ለምሳሌ በአገሪቱ ያሉት ንግድ ባንኮች ይልቅ እነዚህ ማኅበራት አነስተኛ ብድር ዝቅተኛ ለሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል በማቅረብ ረገድ ተመራጭና ተደራሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል። የእነዚህ ማኅበራት መኖር ሌላው ጠቀሜታ ብድር ለማግኘት በሌሎች የፋይናንስ ተቋማት የሚጠየቀው የብድር ማስያዣ ዓይነት የተለየና ቀላል መሆኑ ነው፡፡ 

እንደ አቶ ዘለዓለም ገለጻ፣ ለምሳሌ የእሳቸው የኅብረት ሥራ ማኅበር አባል የሆነ ሰው አባል የሆነበትን ደብተር አቅርቦ  ለሌለው አባል ዋስ በመሆን አነስተኛ መጠን ያለውን ብድር በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል በመሆኑ አሠራሩን ለየት ያደርገዋል ይላሉ፡፡ አንድ ተበዳሪ የማኅበሩ አባል ከሆነበት ጊዜ  ጀምሮ በሦስት ወራት የቆጠበውን ገንዘብ ከእጥፍ በላይ መበደር የሚችልበት ዕድልም አለው፡፡ ለአብነትም 100 ሺሕ ብር የቆጠበ አባል እስከ 400 ሺሕ ብር ብድር ሊገኝ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ እንዲህ ያለው አሠራራቸው እነዚህን ማኅበራት ከባንክና ከማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ልዩ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል፡፡ የማኅበራቱ አባላትም በዚህ ዓይነት መንገድ ከሚቀርብላቸው ብድር በተጨማሪ አባል የሆኑበት ማኅበር የሚያገኘውን ትርፍ መልሰው የሚከፋፈሉበት በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን አንደሚጨምርላቸው ገልጸዋል፡፡ 

እንደ ጳጉሜን ያሉ ተቋማት ሌላው መሠረታዊና ልዩነታቸው ብድር የሚሰጡት ለአባላት ብቻ በመሆኑ እርስ በእርሳቸው ዋስ በመሆን ለኮንዶሚየም ክፍያ ለሕክምናና ለትምህርትና ለመሳሰሉ አስቸኳይ ብድር እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራርም አለው፡፡ ይህ በተቋማት ውስጥ ለማኅበራዊ አገልግሎት በሚል የሚሰጥ ነው፡፡ 

እንዲህ ያለው የብድር አሰጣጥ ብድሩ እንዳይመለስ እንቅፋት ሊሆን አይችልም ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ዘለዓለም፣ ሥጋቱን የሚያስቀር አሠራር ስላለ ችግር እንደማይኖረው አመልክተዋል፡፡ አልከፍልም ቢል ቀጥታ ወደ ሕግ የማይኬድ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ወደ ሕግ ከመሄዱ በፊት መጀመርያ በማኅበሩ ሥር በሚገኘውና ለዚሁ ተብሎ በተዋቀረው የሽምግልና የግልግል ኮሚቴ ጉዳዩ እንዲታይ ይደረጋል፡፡ ከተበደረው ጋርም ውይይት በማድረግ ይታያል፡፡ ብድሩ የሚመለስበትን አማራጮች በጋራ የማፈላለግ ሥራ የሚሠራ በመሆኑ፣ ወደ ሕግ ከመሄድ በፊት በቅድሚያ ብዙ ጉዳዮች ዕድል የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩንም አስገንዝበዋል፡፡  ስለዚህ አንድ ተበዳሪ ካልመለሰ ቀጥታ ወደ ንብረት መሸጥ አይሄድም፡፡ 

የቁጠባና የብድር የኅብረት ሥራ ማኅበራት አገልግሎት የሚሰጠው ከሕዝብ ከተሰበሰበ ገንዘብ ነውና እንዳይባክን ቁጥጥር የሚያደርገው አካል ማነው? ለሚለው ጥያቄ  አቶ ዘለዓለም፣ ቁጥጥሩ ፈቃዱን በሰጠው የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የሚካሄድ ይሆናል ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ለተመሳሳይ ሥራ የተቋቋመው ማኅበራትን የሚቆጣጠረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ነው፡፡ ኤጀንሲው በየወረዳው ክፍለ ከተማው የኅብረት ሥራ ማደራጃዎች ያሉት በመሆኑ እነዚህ ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡ ማደራጃዎቹ በየወሩ ሪፖርት ይቀርብላቸዋል፡፡ እነሱ ደግሞ ለብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ የቁጥጥሩን ሥራ የሚሠራው አካል የብድር አሰጣጥንና የብድር አመላለሱን ጭምር በአግባቡ መፈጸሙን ሁሉ የሚያይ ነው፡፡ ጳጉሜን  የገንዘብ ቁጠባን ብድር የኅብረት ሥራ ማኅበር በአገልግሎቱ ዙሪያ ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል? ለሚለውም ጥያቄ አቶ ዘለዓለም የሰጡት ምላሽ፣ በርካታ አዳዲስ ነገሮችን ይዘው የሚመጡ መሆኑ ነው፡፡  ዘግይተው ወደ ገበያ መግባታቸው ጠቅሞናል የሚሉት አቶ ዘለዓለም እንዲህ ባሉ ተቋማት ያልተለመዱና አዳዲስ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እንደሚያስችላቸው ጠቅሰዋል፡፡

ከእነዚህ አዳዲስ አሠራሮቻቸው መካከል ከ50 ሺሕ ጀምሮ ብድር ለማቅረብ የሚያስችል አሠራር መዘርጋታቸው አንዱ ሌላው ይለየናል የሚሉ ተግባራቸው ነው፡፡ ለሕክምና ለትምህርትና ለመሳሰሉት አስቸኳይ ጉዳዮች ፈጣን ብድር በአነስተኛ ወለድ ለማቅረብ መዘጋጀቱ ነው፡፡ ሌላው እንለይበታለን ብለው የጠቀሱት ጉዳይ ደግሞ የቡድን ቁጠባ ሲሆን፣ ይህ የቡድን ቁጠባ ለምሳሌ ለስፖርተኞች በተለይ ለስፖርት ክለቦች አባላት የሚሰጥ ነው፡፡ ጳጉሜን ከሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት በተለየ ይዞት የመጣው አገልግሎቱ ለመጀመርያ ጊዜ ከወለድ ነፃ ቁጠባ የሚጀምር መሆኑ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ አገሪቱ ከወለድ ነፃ ቁጠባ የሚጀምር ነው፡፡ እስካሁን ድረስ አገሪቱ ከወለድ ነፃ ቁጠባ የሚያሰባስበው ፋይናንስ የሚያደርጉ (ብድር የሚያቀርቡ) ባንኮች ላይ ብቻ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ጳግሜን ይህንን አገልግሎት ይዞ መቅረቡን አቶ ዘለዓለም ጠቅሰዋል፡፡ 

ከወለድ ነፃ ቁጠባ በኅብረት ሥራ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ እየተሰጠ ባለመሆኑ፣ ይህንን አገልግሎት መጀመሩ በእምነታቸው ምክንያት ተጠቃሚ ሳይሆኑ የቆዩን ተገልጋይ ያደርጋል፡፡ 

አገልግሎቱን የሚሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያን ተከትሎ እንደሆነ፣ ነገር ግን አሠራሩ ትንሽ ከበድ ስለሚል ተቋማት ወደ እዚህ አልገባም፡፡ እኛ ግን ዓላማችን አገልግሎት መስጠት ስለሆነ ለመጀመርያ ጊዜ ከኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ከወለድ ነፃ ቁጠባና ብድር መስጠት ይጀምራል ብለዋል፡፡ 

ሌላው የተለየ አገልግሎት ብለው የጠቀሱት አገልግሎት አባላት የክብረ በዓላት ቁጠባ ሲሆን፣ ለምሳሌ የክርስትና እምነት ተከታዮች ለጥምቀት በዓል የሚሆን የክብረ በዓል ቁጠባ ከመስከረም ወር ጀምሮ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ጥር ወር ላይ በአካውንታቸው ቁጠባቸው ከእነ ወለዱ ይሰጣቸዋል፡፡ 

የእስልምና እምነት ተከታዮችም በተመሳሳይ የሚሰጡ እንቅስቃሴዎች የሚኖሩ ሲሆን፣ ለምሳሌ ለሃጅ ጉዞ የሚሆናቸውን ገንዘብ ቆጥበው በሚፈልጉበት ጊዜ ገንዘቡ ይሰጣቸዋል፡፡ 

ማኅበሩ በአኃዱ ስብስብ በ2016 የሒሳብ ዓመት ለማከናወን ያቀዳቸውን ሥራዎች ሥራ አስኪያጁ በሪፖርታቸው አቀርበው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በ2016 የሒሳብ ዓመት ከሁለት ሺሕ በላይ አዳዲስ አባላትን ለማፍራት ዕቅድ የያዘ ሲሆን፣ ይህም አጠቃላይ የአባላቱን ቁጥር ከ2329 በላይ ደርሷል፡፡ እነዚህ አባላትም ከሚደረግ ዕጣ (ሼር) ሽያጭ ከ10.8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የሚገኝ እንደሆነ ታሳቢ ተደርጓል፡፡

ከብድር አቅርቦት አንፃርም ማኅበሩ ከ23.1 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ለአባላቱ ለመስጠት ያቀደ ሲሆን ለንግድ፣ ለመኪና ለቤት ግዥና ለመሳሰሉ  ብድር የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል፡፡ የብድር ወለድ ምጣኔውም ከ13 እስከ 15 በመቶ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ በሒሳብ ዓመቱ 42 ሚሊዮን ገቢ የማግኘትና ስምንት ሚሊዮን ብር ለማትረፍ ዕቅድ ይዟል፡፡ 

የፋይናንስ ተዛማጅ አገልግሎቶችን ለመስጠት እንደ ተቋቋመ፣ መሥራች አባላቱም 329 ሲሆኑ፣ የእነዚህም አባላት መዋጮም አሥራ ሁለት ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ወደ ሥራ የሚገባውም ይህንን ካፒታል በመያዝ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ 

ጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበር አዋጅ ቁጥር 985/2009 መሠረት በማድረግ የተቋቋመ ሲሆን፣ የካቲት ወር  በ2015 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማደራጃ ፈቃድ በመውሰድ ምሥረታውን ሊያካሂድ ችሏል፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ እስከ 2015 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ከ1180 በላይ የሚሆኑ መሠረታዊ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተቋቁመው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ከተማ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሥራ ማኀበራት ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል፡፡

ከእነዚህ ማኅበራት ሌለ ሁለት የገንዘብ ቁጠባና የብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየኖችን አንድ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ማኅበራት ፌዴሬሽን ተደራጅቶ አገልግሎት እየሱጡ መሆኑንም ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች