በራያና ወልቃይት አካባቢዎች ያለው የይገባኛል ውዝግብ ከሰሞኑ ግለቱ የጨመረ ይመስላል፡፡ ሁለቱ አካባቢዎች ወደ ትግራይ መካለል አለባቸው፣ እንዲሁም ወደ አማራ ክልል ሊጠቃለሉ ይገባል የሚሉ በተቃራኒ ጎራ የተሠለፉ ወገኖች ቃላት እየተወራወሩ ነው፡፡ የራያና የወልቃይት ጉዳይ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከሰሞኑም የተጋጋለ ሽኩቻ የሚያስነሳ ጉዳይ አላጣም፡፡
የውዝግቡ ዋና መነሻ ደግሞ የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ነሐሴ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. የአሸንዳ በዓልን አስታከው ያሠራጩት መረጃ ነበር፡፡ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሠራጩት የትግርኛ ቋንቋ መረጃ፣ የወልቃይትና የራያ አካባቢዎችን አስመልክቶ ያለው ውዝግብ ስለሚፈታበት መንገድ አጨቃጫቂ ነጥቦችን አንስተዋል ተብሏል፡፡
ሚኒስትሩ አብርሃም (ዶ/ር) ለአሸንዳ በዓል ምኞታቸውን አስፍረው በዚሁ አጋጣሚ፣ ‹‹በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት ከአጨቃጫቂዎቹ የትግራይ አካባቢዎች የተፈናቀለው ሕዝባችን ወደ ቀዬው ተመልሶ ሰላማዊ ኑሮን እንዲመራ እየተሠራ ነው፤›› የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ ‹‹የሁለቱም ክልሎች አመራሮች በተገኙበት በፌዴራል ደረጃ ያሠለፍነውን ውሳኔ ለመተግበር እየተሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሕግና ሕገ መንግሥታዊ አሠራርን በመከተል የወልቃይትና የራያ ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ እንዲፈታ እየተሠራ መሆኑን፣ ከዚህ ጎን ለጎን ሕዝቡ ወደ መኖሪያ ቀዬው ተመልሶ የራሱን አስተዳደር እንዲያቋቁም እንደሚደረግም ሚኒስትሩ ገልጸው ነበር፡፡
ችግሩ በፌዴራል መንግሥት ትኩረት እንደተሰጠው የአካባቢውን መዋቅራዊ ችግርም ተከታትሎ የሚያስፈጽመው የፌዴራል መንግሥቱ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ የአካባቢዎቹን ሰላም ለማደፍረስ የሚሞክሩ ኃይሎች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው ያሉ የታጠቁ ኃይሎችን የመተካት ሥራ መከላከያ እንደሚሠራ፣ እንዲሁም ተቋቁመው የነበሩ መዋቅሮችንም የመተካት ሥራ እንደሚያከናውን ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው በግልጽ አብራርተዋል፡፡
ይህ የመከላከያ ሚኒስትሩ መልዕክት ደግሞ በተቃራኒው ያሉ ኃይሎችን ክፉኛ አስቆጥቷል፡፡
በትግራይ ጦርነት ማግሥት ተቋቁሞ የቆየው በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስተዳደር በሚል የሚጠራው መዋቅር ባወጣው መግለጫ፣ በአካባቢው ‹‹የሚጠናከር እንጂ የሚፈርስ ተቋም የለም›› በማለት የአጸፋ መግለጫ አውጥቷል፡፡
አስተዳደሩ በዚህ መግለጫው የሚኒስትሩን በማኅበራዊ ትስስር ገጽ የወጣ መረጃ፣ ‹‹አገሪቱ የምትገኝበትን መንታ መንገድ ያላገናዘበና ጠብ አጫሪ›› መልዕክት ብሎታል፡፡ ሚኒስትሩ ሆን ብለው የአማራ ክልል ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ታሳቢ አድርገው ያስተላለፉት አደገኛ መልዕክት ስለመሆኑም በመግለጫው አስታውቋል፡፡ መልዕክቱ ኃላፊነት የጎደለውና ክልሉን ወደ ለየለት ቀውስ የሚከት መሆኑን መግለጫው ያትታል፡፡ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የመንግሥት አመራር ሆነው ሳለና አገርን ያለ አድልኦ ማገልገል ሲገባቸው፣ በተቃራኒው ግን ለወጡበት ማኅበረሰብና ክልል ብቻ የወገነ መልዕክት ማሰራጨታቸው በእሳቸው ደረጃ ከሚገኝ አመራር የማይጠበቅ ተግባር መሆኑን ነው በመግለጫው አጠንክሮ ያስታወቀው፡፡
የወልቃይት አካባቢ መዋቅር አስተዳዳሪዎችም ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለያዩ መንገዶች የተቃውሞ መግለጫዎች ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡ የወልቃይት አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው፣ ‹‹የሚፈርስ መዋቅርም ሆነ የሚፈታ ትጥቅ የለም›› የሚል ምላሽ በጉዳዩ ላይ ሰጥተዋል፡፡
የወልቃይት አካባቢ ምክትል አስተዳዳሪና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በበኩላቸው፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ የሰጡት መረጃ የአካባቢውን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ መረጃ በአካባቢው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጣ አስነስቷል ብለዋል፡፡ የወልቃይት አካባቢ ጉዳይ በሰላምና በሕግ እንጂ በጉልበት ይፈታል ብለው እንደማይጠብቁ ተናግረዋል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ሪፖርተር ተጨማሪ ማብራሪያ የጠየቃቸው ኮሎኔል ደመቀ፣ የወልቃይት ጉዳይ የሕግ ሥርዓትን ተከትሎ እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄው መድረሱንና ምላሹን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል አካባቢው (ወልቃይት) ሰላማዊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ኮሎኔል ደመቀ ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው የተለየ ግጭት አለመከሰቱን የተናገሩት ኮሎኔል ደመቀ፣ ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የልሳነ ግፉአን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አብዩ በለው ስለሰሞነኛው ውዝግብ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ትስስር መረጃ እንደ ግለሰብ አስተያየት ብቻ እንደማይወሰድ ተናግረዋል፡፡ በወልቃይት የሚፈርስ መዋቅር እንደሌለ አጠንክረው የገለጹት አቶ አብዩ፣ በጠለምት አካባቢ የነበረውን አስተዳደር የማፍረስ ሙከራዎች እንደነበሩ የአስተዳደር ሰዎች ሥራቸውን እንዳይሠሩ የማድረግ ጥረት እንደነበረም አክለዋል፡፡ ‹‹የወልቃይት ጉዳይ ከዚህ ይልቅ በሕግ ነው መፈታት ያለበት፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የፕሪቶሪያውን ስምምነት እየጣሰ ያለው ራሱ ሕወሓት ነው ሲሉ የገለጹት አቶ አብዩ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሕወሓት ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑንና ይህንንም ራሳቸው የሕወሓት አመራሮች፣ ‹‹በአደባባይ ፉከራ አማራ ክልል ዘምተን በኃይል ወልቃይትን እናስመልሳለን እያሉ›› መግለጻቸውን አስረድተዋል፡፡
በሕወሓት በኩል በግልጽ የሚታይ የጦርነት ቅስቀሳና ወታደራዊ ዝግጅት መኖሩ እየታየ፣ እሱን ወደ ጎን ብሎ የወልቃይትን ሰላማዊ ሁኔታ የሚያደፈርስ መግለጫ ማውጣት ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሰላማዊ የትግራይ ተወላጆች አሁንም ቢሆን በወልቃይት በሰላም እየኖሩ መሆኑን ያመለከቱት አቶ አብዩ፣ ችግሩ በሕጋዊ መንገድ ዕልባት ሳያገኝ ‹‹ወንጀል ሠርተው የሸሹ ሰዎችን ጭምር በተፈናቃይ ስም መልሶ ለማስፈር የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት የለውም፤›› በማለት ነው ሐሳባቸውን ያጠቃለሉት፡፡
ከወልቃይት በመለስ አጨቃጫቂ የሆነው የራያ አካባቢ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ አስተያየት የተጠየቁትና የአካባቢውን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖችም ቢሆኑ፣ ከሰሞኑ የተፈጠረው ሁኔታ ግራ እንዳጋባቸው ነው የተናገሩት፡፡
በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር አቶ በላይ ደሳለኝ፣ የፌዴራል መንገሥቱ የራያን ሕዝብ ያማከለና ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም የሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መሥራት አለበት ብለዋል፡፡ ‹‹የቀድሞ የወሎ ጠቅላይ ግዛት አካል የነበሩትን ራያ ኦፍላ፣ ራያ አላማጣ፣ አላማጣ ከተማ፣ ራያ ባላ የሚባሉ አካባቢዎች ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ እየመራ ይገኛል፡፡ ነገር ግን በቅርብ ጊዜ ከአካባቢው አስተዳደርና ከሕዝቡ በኩል ሕዝበ ውሳኔ ይደረጋል የሚል መረጃ እየተሰማ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በእሳቸው እምነት ወደ አካባቢው ይመለሳሉ ከሚባሉት ተፈናቃዮች ጋር በጦርነቱ ወቅት ወንጀል ሠርቶ የሸሸ ሰውም ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ ሳይጠራና አካባቢውን በሚመለከት የመጨረሻ ዕልባት ሳይሰጥ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሰን እናሰፍራለን የሚል ቃል መግባቱ ለአካባቢው እንደማይበጅ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የአካባቢው ኅብረተሰብ በተፈናቃዮች ስም የሕወሓት ታጣቂዎች ወደ አካባቢው ገብተው ቀጣናውን ብጥብጥ ውስጥ እንዳይከቱት ሥጋት አለው፤›› በማለትም አቶ በላይ አክለዋል፡፡
በኮረም ዙሪያ አፍላ ወረዳ ወደ ስድስት ቀበሌዎች አሁንም ድረስ በሕወሓት ታጣቂዎች እጅ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ በላይ፣ ነዋሪው በእነዚህ አካባቢዎች የማንነት ጥያቄ አለው ይላሉ፡፡ በራያ ቀጣና የተመሠረተው ጊዜያዊ አስተዳደር ሳይፈርስ መከላከያው የፀጥታ ሥራውን ቢይዘው ኅብረተሰቡ ብዙም ችግር የለበትም በማለት ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ በተፈናቃይ መልሶ ማስፈር ስም አካባቢው ለሕወሓት ተላልፎ ከተሰጠ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል በማለት ነው ሥጋት ያሉትን ጉዳይም ያከሉት፡፡
የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አብርሃም አረፈዓይኔ በበኩላቸው፣ አሁን የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት አካባቢውን ተቆጣጥረውታል ይላሉ፡፡ በአካባቢው የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደርም መፍረሱን ይናገራሉ፡፡
‹‹ተፈናቃዮችን መልሶ የማስፈር ሥራ ለማከናወን ዝግጅት አለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መከላከያ ኃይሉ ሰነድ አዘጋጅቶ ጭምር ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢው ከተመለሱ በኋላ ከሁሉም አካል የተውጣጣ ጊዜያዊ አስተዳደር በአካባቢው ይመሠረታል የሚል ዕቅድ መንግሥት አውጥቷል፡፡ ይህ ከተከናወነ በኋላ ሕዝበ ውሳኔ በአካባቢው ይካሄዳል የሚል መረጃም አለ፤›› በማለት የራያን ወቅታዊ ሁኔታ አስረድተዋል፡፡
ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በተደረገ አስቸኳይ የምክር ቤት ስብሰባ ነበር፣ የአማራ ክልል የክልሉ አዲስ ፕሬዚዳንት አቶ አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የቢሮ ኃላፊዎችን ሹመት ያፀደቀው፡፡ ክልሉ ባለመረጋጋት ውስጥ ሆኖ አዳዲስ አመራሮችን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ይህ አለመረጋጋትና የፀጥታ ችግር ደግሞ ገና አለመስከኑ ነው የታወቀው፡፡ ክልሉ ከቀውስ ውስጥ ሳይወጣ ነባሮቹን የወልቃይትና የራያ ይገባኛል ቀውሶች ለመሸከም መገደዱ ፈተና እንደሚሆንበት እየተገመተ ነው፡፡
በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ስለአማራ ክልል መሠረታዊ ጥያቄዎች ያነሱት አዲሱ ርዕሰ መስተዳደር፣ የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደርና ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በጋራ ለመኖር የማይቸገር ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በየጊዜው በሚያጋጥሙ የፖለቲካ ሴራዎች ክልሉ ለዘርፈ ብዙ ችግሮች እየተዳረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ክልላችን በቆዩና በወቅታዊ ችግሮች ውስብስብ ችግር ውስጥ ገብቷል፡፡ በአገሪቱ የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ ተቃርነው የቆሙ የፖለቲካ ኃይሎች ከውስጥም ከውጭም ክልሉን ተጋላጭ አድርገውታል፡፡ የአማራን ክልል ወደ የማያባራ ግጭትና ብጥብጥ ለማስገባት በየተገኙበት መድረክ ከሕግና ከሥርዓት ውጪ የአማራን ክልል ሕዝብ ጥቅምና መብቶች በተመለከተ አንዳንዶች መርዘኛ ንግግር ሲረጩ ተስተውሏል፤›› ብለዋል፡፡
የአማራን ክልል መሠረታዊ ጥያቄዎች አፈታት በተመለከተ በፌዴራል መንግሥቱ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከቱ ወገኖች መኖራቸውንም አቶ አረጋ ተናግረዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ክልሉ ከሌሎች ጋር ተባብሮ እንደሚፈታም ቃል ገብተዋል፡፡