Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እኛ ለእኛ!

እነሆ ከካዛንቺስ ወደ ፒያሳ ልንጓዝ ነው። ‹ጎዳናው መንገዱ…› እያለ በሆዱ የሚያዜመው በሐሳብ ተጠምዶ ይነካዋል፣ ማንን? መንገዱን፡፡ ‹እከሌን ምሰል፣ እንደ እከሌ ካልሆንክ›፣‹እንደ እከሊት ተድረሽ ወልደሽ ካልከበድሽ› እየተባልን አድገን፣ የሆኑትን ለመምሰል በምንደፋፈርበት የ‹ሞዴሎች› ምድር ያየሱልንን ጎዳና ዛሬም ያለ መታከት ይዘነዋል። አጥብቀው ያሸከሙንን የማስመሰል ሸክም የትኛው ፌርማታ አውርደን እንደምንጥለው እንጃ ያሰኛል። የራሳችን ያልሆነውን ዛሬም በባለአደራነት ጫንቃችን ላይ ተሸክመን አላወረድነውም። ‹ይህ የእኔ አይደለም፣ ይህ ያንቺ አይደለም› እንዳንባባል፣ ‹አጥብቆ ያሰረ ዘቅዝቆ ይሸከማል› የሚል ሸባቢ የተረት ዘብ አስቀምጠውብናል። ማጥበቃችንን እንጂ አስተሳሰራችንን እንዳናጤን፣ ከረጢታችን መሙላቱን እንጂ በምን እንደሞላናው እንዳናስተውል ያደረገን ይህ ሸክም፣ አበረታች ተረት እንደሆነስ ማን ያውቃል? ሲተረክ ዘበት መሳዩ ኑሯችን ከጫፍ እስከ ጫፍ ቢበረበር ያለ ፈቃዳችን የተሸከምናቸው አቁማዳዎች ስብስብ ነው። ይህን አስበው አንዳንድ አፈንጋጮች ‹ዘራፍ› ሲሉ ‹ማንም ያሰበውን የሆነ የፈለገውን ያገኘ የለም› በምል አፅናኝ መሳይ፣ በሥውር ከንቱነትን ባዘለ ተስፋ አስቆራጭ ንግግር ወደ ቦታው ይመለሳል። ሕይወት እንዲህ ከሆነ ቆየ!

ጉዟችን ተጀምሯል። ከሾፌር ጀርባ ያለው መቀመጫ ላይ እንዳሻቸው የሚናገሩ ገራገር እናት ተሰይመዋል። እንደ ነገሩ ሸብ ያደረጓትን ወደ መሀል አናታቸው የሸሸች ሻሽ እያስተካከሉ ይበሰጫጫሉ። ከእሳቸው ንጭንጭ የወያላው ይብሳል። ‹‹ቆይ እኔምለው ዘንድሮ ኑሮውም ጠቡም አንድ ላይ ነው እንዴ አድመው የተነሱብን?፡፡ ይላል። እኚያ እናት ቀበል አድርገው፣ ‹‹ኧረ የዘንድሮን ነገር እንጃ፡፡ ኢትዮጵያ የፆምና የፀሎት አገር ብትሆንም ፈጣሪ አልሰማት ያለ ነው የሚመስለው፡፡ እዚህ እኛ ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ጭምር ብንፆምም ብንፀልይም ሰላም ከራቀን ቆየ፡፡ ለበረከት ብንማድልም ረሃብና ስደት ያሉት እዚህ ነው፡፡ ምን ዓይነት መርገምት እንደመጣብን እንጃ…›› አሉት። ‹‹የገዛ ሥራችን ነው ለዚህ ሁሉ መከራ የዳረገን፡፡ ፀሎታችንም ሆነ ምልጃችን የልብ ንፅህና ቢኖረው ኖሮ እንዲህ የችጋርና የግጭት መጫወቻ አንሆንም ነበር፡፡ እንደ አገርም ሆነ እንደ ማኅበረሰብ ራሳችንን ኦዲት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ያለበለዚያ የራሳችንን ጥፋት ዘመን ላይ ማላከክ አያዋጣም…›› የሚለው ኮስተር ያለ ጎልማሳ ነው፡፡ መልካም ሐሳብ ነው!

‹‹የባሰ አታምጣ፣ የሚናገሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው። እኛ ጊዜ የሰጣቸው በየተራ መንበሩን እየተቆጣጠሩ ሲገዙ ያለ ምንም ተቃውሞ በሰላምና በፍቅር አስተዳድሩን ስንል፣ ማን ሰሚ ተገኝቶ ነው ጥፋትን ማላከክ አይገባም ተብለን የሚነገረን…›› በማለት አንዱ አጉተመተመ። ‹‹ድሮም ከእናንተ ጋር መከራከር…›› እያሉ እኚያ እናት ወደ ሻሻቸው እጃቸውን ሰደው፣ ‹‹ይኼ ሻሽ ደግሞ በሽበቴ የማፍር መሰለው እንዴ እንደ ዘመኑ ሰው የሚንሸራተተው? ነገራችን ሁሉ እንደዚህ ሻሽ ሆነ እኮ…›› ብለው ሻሻቸውን አውልቀው ቦርሳቸው ውስጥ ከተቱት። ተጎንጉኖ ለሦስት እየተገመደ የሚወርደው ጥጥ የመሰለ ፀጉራቸው ክፉና ደጉን በወግ ያሳለፉበት ዕድሜ ቀላል እንዳልሆነ ይናገራል፡፡ ‹የእርጅና በረከት ከርስ በመሙላት ብቻ አይገኝም። ቀናውን ከጠማማው በመለየት እንጂ› የሚለን ይመስላል። ‹‹ሽበት መኩሪያ መሆኑ ቀርቶ በቀለም ለዛውን እንዲያጣ በተደረገበት በዚህ ከንቱ ጊዜ…›› ከማለቱ አንዱ ቀውላላ፣ ‹‹ወንድሜ ተው እንጂ ጊዜን ለምን እየኮነንክ ራስህን ነፃ ለማውጣት መከራ ታያለህ…›› ብሎ ያ ኮስታራ ጎልማሳ ሲመልስለት ለጊዜው ፀጥታ ሰፈነ፡፡ አንዳንዴ ፀጥ ሲል ደስ ይላል፡፡

‹‹እስኪ የንብረት ግብር በሙሉ ኃይል ሳይጀመር ቶሎ ሒሳብ ወጣ ወጣ አድርጉ…›› እያለ ወያላው ተሳፋሪዎችን መጠየቅ ጀመረ። ‹‹እንኳን ግብር ደማችንን ለእናት አገራችን ብንሰጥ የማይቆጨን የጀግኖች ልጆች ነን እኮ፡፡ የምን ማስፈራሪያ ነው?›› ብሎ ከጀርባ የተሰየመ ጎልማሳ ሲናገር፣ ‹‹ሁላችንም ያለ በፍቅርና በክብር ብንገብር እኮ ኩራታችን አልነበር?›› ስትል አጠገቡ የተቀመጠች ወጣት ገባችበት። ጎልማሳው መልሶ፣ ‹‹ሌባና አጭበርባሪ የበዛበት የንግዱ ዓለም ብዙዎቹ ተዋንያን ግብር መሰወር፣ ማጭበርበር፣ ከሹማምንት ጋር ተመሳጥረው ኮንትሮባንድ መነገድ፣ አገሪቱ በአጥንቷ እስክትቀር ድረስ መግፈፍ ነው ዋናው ሥራቸው፡፡ መንግሥት ግን እነሱን ባላየ አልፎ እኔና አንቺን ማንቁርታችንን ይዞ መከራ ያሳየናል…›› አላት፡፡ ይኼ ጉዳይ ሳይቋጭ ደግሞ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጡ ጓደኛማቾች ቀጠሉ። ‹‹አንቺ መቼ ዕለት የታሰረ ሰው ልጠይቅ ሄጄ የሆንኩትን ነግሬሻለሁ?›› ስትል ቀጠን ያለችዋ ሞላ ላለችዋ መልከ መልካም ወዳጇ፣ ‹‹ለአንድ ሁለት ቀን አረፍ ብለሽ ውጪ ተባልኩ እንዳትይ?›› ብላ መሳቅ ትጀምራለች። ‹‹እሱ አንድ ነገር ነው። ‹መታወቂያሽ የአገልግሎት ጊዜው ሁለት ቀን አልፎታል› ብሎ ጥበቃው አባረረኝ ብልሽ ታምኛለሽ?›› በማለት ስትነግራት ያቺኛዋ ደግሞ፣ ‹‹እንኳን ቢያባርርሽ ጎሸም ቢያደርግሽም አምንሻለሁ አይዞሽ…›› ተባብለው የተጀመረውን ወግ አቆረፈዱት፡፡ ያናድዳል!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጋቢና የተቀመጡ ተሳፋሪዎች ስለመኖሪያ ቤት ችግር እያወጉ አንዳንድ ይባባሉ ጀመር። አንዱ፣ ‹‹አሁንማ የ40/60 እና የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጉዳይ ተረስቶ ስለሌሎች ፕሮጀክቶች እየተወራ ነው፡፡ እኔ ይህን ሁሉ ዓመት ቆጥቤ የቤት ነገር ወሬው ሲጠፋ ቅዠት ውስጥ ያለሁ እየመሰለኝ ነው፡፡ መንግሥት ቤቶቻችን ለማንም አድሎ ከጨረሰ በኋላ የራሳችሁ ጉዳይ እንዴት ይለናል…›› እያለ ብስጭት አለ፡፡ ድንገት አንዲት ቀጭን ወጣት ከመሀል ወንበር፣ ‹‹የቤታችን ጉዳይማ ተከድኖ ይብሰል ተብሎ ተረሳ እኮ፡፡ እኔማ በኪራይ ቤት መከራ እያየሁ እንዴት እንደሚዘለቅ እንጃ…›› ብላ አንገቷን ደፋ ስታደርግ፣ ‹‹የእኔ አከራይማ ‹እራት በልተሃል? ለሽንት ወጥተሃል?› እያሉ ሲጠይቁኝ አምሽተው ‹አልጋ ውስጥ ነህ?› ሲሉ ‹አዎ› ካልኳቸው ቆጣሪ ያጠፋሉ…›› ሲል አንዱ ከኋላ እኚያ እናት ቀበል አድርገው፣ ‹‹ምን ሞኝ ናቸው አንተ? ቆጣሪ መለሱ አልመለሱ ደግሞ። መብራት እንደሆነ ድንገት ከጠፋበት ቢመጣ ጠፍቶ አዳሪ ነው፡፡ ድንገት ሲበራ ካደረም ጠዋት ሂያጅ ነው፣ ምስኪን ናቸው…›› ይሉታል። አንዱ ደግሞ፣ ‹‹አሉላችሁ ደግሞ የእኔ…›› ብሎ ሲጀምር ሁሉም ወደ እሱ ዞሩ። ‹‹…በወር በወር መታወቂያዬን ኮፒ ያስደርጉና ይይዛሉ…›› ብሎን ዝም ሲል ግራ ገብቶን ተያየን። ‹‹ፖሊስ ጣቢያ ነው እንዴ የተከራየኸው?›› ብሎ አንዱ ሲሳለቅ ጎልማሳው ግን፣ ‹‹እኮ ለምን?›› ብሎ ሲጠይቀው፣ ‹‹ፀጉረ ልውጥ እንዳልሆን እየሠጉ መሆኑ ነዋ…›› ብሎ መልሶ በገዛ እንግልቱ ልቡ እስኪፈርስ ሳቀ። ህምም…!

‹‹እውነታቸውን ነው፣ ዘንድሮ እኮ ከቋሚ ተሠላፊው የባሰው ተጠባባቂው ነው…›› ብላ ከጎልማሳው አጠገብ እሷም ብትሆን እንደማትለቀው በአግቦ ትነግረዋለች። ‹‹ስንት ዓይነት ኑሮ አለ?›› ብለው ጥቂት አጉረምርመው ደግሞ እናታችን ቀጠሉ። ‹‹አንድ የማከራያት ሰርቪስ አለችኝ። ታዲያ የተከራየኝ ወጣት ነው። እንዲያው ባየሁት ቁጥር አንጀቴ ይንቦጀቦጃል። ሲመሽለት ግን እንዳይሆን ሆኖ ሰክሮ አንዷን አቅፎ ካልገባ አይሆንለትም። ጠዋት መክሬው ማታ  ከሌላኛይቱ ጋር ነው። ነገም ያው ከተነገ ወዲያም እንደዚያው። ብቻ እንደ ግል ቤት ሁሉን የሚችል የለም…›› ብለው ከመናገራቸው ወያላችን፣ ‹‹ፒያሳ ደርሰናል መጨረሻ…›› ብሎ በሩን ከፈተው። በተከፈተው በር ለመውረድ ስንጋጋ የኑሮ ውድነቱ፣ የግጭቱ፣ የተከራይና የአከራይ ብሶታችን፣ የውል አልባው ዘመናችን ፈተናዎች ቀለው ዕፎይ የምንልበት ጊዜ ደጅ የሚጠብቀን እንመስል ነበር። ‹‹ተስፋ ባይኖር ኖሮ ምን ይኮን ነበር? ተስፋ አስቆራጮች እንደ አሸን በሞሉበት ዘመን ተስፋ ሰንቆ መኖር ምንኛ መታደል ነው?›› የሚሉት አዛውንቷ እናት ናቸው ከታክሲው ወርደው የሚቀጥለውን መንገዳቸውን እያመቻቹ፡፡ ያቺ ቀጭን ወጣት ደግሞ፣ ‹‹አይ ማዘር ተስፋና ትዝታ እሹሩሩ በሚባሉበት አገር በወል ሳይሆን በግል ነው ማሰብ፡፡ አለበለዚያ ሁሉም ነገር ተረት ተረት ይሆንብናል…›› ስትላቸው፣ ‹‹የግል ነገራችንን ስናሳድድ ነው አገራችንን መቅኖ ቢስ ያደረግናት፡፡ ይልቁንስ ከእኔነት ይልቅ ለእኛነት እንጨነቅ፡፡ እኛ ለእኛ ማለት ይለመድ…›› እያሉ ሲናገሩ በአንክሮ እያዳመጥናቸው ወደ ጉዳያችን ተበታተንን፡፡ መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት