በገለታ ገብረ ወልድ
የዕለቱን ጽሑፍ በጨዋታ እንጀምር፡፡ “An African Treasury” በተባለ መጽሐፍ ውስጥ ካሉት አጫጭር ታሪኮችና የቅኔ መድበል ውስጥ ከሰፈሩት የጥቁር አፍሪካውያን ጸሐፊዎች ስብስብ ሥራዎች ውስጥ ያገኘሁት “With the lid off” በሚል ርዕስ የሰፈረ ነው፡፡ ጸሐፊው ቶድ ማትሺኪዛ የተባለ ደቡብ አፍሪካዊ ነው፣ እንዲህ ይላል፡፡
አልበርት ቪሌ በምትባል መንደር ለምትገኝ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ እንዲሆን አንድ ነጭ (አውሮፓዊ) ቄስ ተመደበ፡፡ ቄሱ ወጣትና ጎበዝ ሰባኪ ነው፡፡ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ስላሉት ምዕመናን ኃጢያተኝነት ይቆረቆራል፡፡ ከኃጢያት እንዲነፁ ይታገላል፡፡ አብዛኞች ምዕመናን ክልሶች (Colored People) ናቸው፡፡
ዘወትር እሑድ ቄሱ መድረኩ ላይ ይወጣና የመስበኪያ ድጋፉን (Pulpit) በሁለት እጆቹ ጥርቅም አድርጎ ይዞ በየመሀሉ በብርጭቆ የቀረበለትን ውኃ እየተጐነጨ ስብከቱን ይጀምራል፡፡ ‹‹እናንተ ክልሶች ትጠጣላችሁ፣ ሰካራሞች ናችሁ፡፡ እየሰከራችሁ የምትሠሩትን አታውቁም፡፡ በዚህ ዓይነት ገነት እንገባለን ብላችሁ የምትጠብቁት እንዴት ነው? እናንተ ክልሶች ኃጢያታችሁ በዝቶ ጥፋታችሁ ከሰማዩ መንግሥት ትዕግሥት በላይ ሆኗልና ነፍሳችሁ አይማርም፡፡ እናንተ ክልሶች መግቢያችሁ ገሃነም ነው፡፡ የሚጠብቃችሁ የገሃነም እሳትና የማያንቀላፋ ትል ነው፡፡
‹‹እናንተ ክልሶች በትንሳዔ ጊዜም እንደ ከብት በመቃብራችሁ ትቀራላችሁ እንጂ የሰማዩ መንግሥት ገዥ ፊት የሚያቀርባችሁ የለም፡፡ ገነት ሲያምራችሁ ይቅር፡፡ እናንተ ክልሶች ሌቦች፣ ቀማኞች፣ ዝሙተኞች፣ ጨካኞች፣ ሆዳሞች፣ ሸፍጠኞች፣ ከሃዲዎች ስለሆናችሁ ክልሶች በሙሉ ኃጢያተኞች ናቸው፡፡ መጽሐፉ የሚላችሁን አታደርጉምና አታድርጉ የተባላችሁትን ታደርጋላችሁና… ምንትሴ ናችሁና… ቅብጥርሴ ሆናችኋልና ወዮላችሁ…›› እያለ እየዘለፈ ይለፋደድባቸዋል፡፡
ከነጮች ምዕመናን ጋር ተቀምጦ በጥቁሮችና በክልሶች ላይ ሲያላግጥ መዋሉን ክልሶቹ ምዕመናን አውቀዋል፡፡ ክልሶቹ ምዕመናን በዚህ ቄስ የዘወትር እሑድ ስድብና ዘለፋ ተማረሩ፣ ተበሳጩ፡፡ ‹‹ይኼ ነጫጭባ ቄስ አሁንስ አበዛው፣ ዝም ስንለው ጊዜ ‹ልክ ነህ› ያልነው መሰለው እንዴ? ይኼ ብሽቅ…›› ተባባሉና ተሰባስበው ሄዱለት፡፡ ልክ ልኩን ነገሩትም፡፡ ‹‹ስማ አያ ቄሱ ከዛሬ ጀምሮ ‹እናንተ ክልሶች› እያልክ መጥራትህንና ‹ኃጢአተኞች ናችሁ›… ምናምን እያልክ የምታደርገውን ዲስኩር አቁም፤›› አሉት፡፡
‹‹እኛ አንተን ‹ነጩ ነጫጭባው አውሮፓዊው ቄስ› እያልን አልጠራንህም፡፡ እንደምናከብርህ አውቀህ ልታከብረን ይገባል፡፡ የምንፈልግህ ለሃይማኖታዊ ምክርህ እንጂ ለስድብ አይደለም፡፡ ልባችንን በመጽሐፉ ቃል ለማፅናናት መጥተን ‹እናንተ ክልሶች› እያልክ እየሰደብክ ልባችንን አቁስለህ እንድትመልሰን አንፈልግም፣ የምታቆም ከሆነ አቁም፣ እንቢ ካልክ ግን የቁም ሕይወትህን አስከፊና መራራ እናደርግብሃለን፡፡ ሥጋህን ለአሞራ፣ አጥንትህን ለአቧራ እንሰጥልሃለን፡፡ ብታርፍ እረፍ ቅሌታም…›› ብለውት ሄዱ፡፡
እነሆ ከዚያች ቀን ጀምሮ ያ ቄስ እሑድ በመጣ ቁጥር ‹‹እናንተ ክልሶች›› ማለቱን ትቶ፣ ‹‹የተወደዳችሁ ወንድሞቼ (My beloved Brethren) ማለት ጀመረ ይባላል፡፡ ደስ አይልም? በጣም እንጂ፡፡ ይህን ያጫወትኳችሁ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡
ወደ ነጥባችን ስንመለስ መንግሥትና የፖለቲካ አንቀሳቃሾች ሁሉ ተው፣ እረፉ ሊባሉ በሚገባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ነጥቦችን ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ቀዳሚው የሰላምና የአገራዊ ደኅንነት ጉዳይ ነው፡፡ በመሠረቱ ግጭት ተፈጥሯዊ ነው፣ ሰላምን ለማረጋገጥም እየተደከመ እንኳን እንዲህ ቀላል መፍትሔ መስጠት አይቻልም፡፡ ያማ ቢሆን በየትኛውም ዓለም ግጭትና ቀውስ ባልተነሳ ነበር፡፡
መገንዘብ የሚያስፈልገው ግን ሰላም ማለት ሁከትን ማቆም፣ ጦርነትና መገዳደልን መግታት ብቻ እንዳሆነ መረዳቱ ላይ ነው፡፡ የሰላምና የዕርቅ ትርጉምና መንገዶች የሚለው የህዝቅያስ አሰፋ መጽሐፍ (ፕሮፌሰር) ገጽ 15 ላይ እንደሰፈረው፣ አገር ሰላምን የሚነሱ ገሃዳዊ ያልሆኑ ዓይነት ሁከቶችን ለመመከት መጋጀት ከመንግሥትም ሆነ ከሕዝብ ይጠበቃል፡፡
‹‹ለምሳሌ ጥቂት ሰዎች ከመጠን በላይ ሀብትና ገደብ በሌለው ሥልጣንና መብት ሲንፈላሰሱ፣ ብዘኃኑ በድህነት፣ በጭንቀት፣ በተስፋ ቢስነት ቀንበር የሚሰቃዩበት ሁኔታ መታየት ከጀመረ አደጋ አለ፡፡ ችግሮቹ ማኅበራዊ ፍትሕ ከሌለበት ወይም ከጎደለበት ሥርዓት ሊወለዱ እንደሚችሉ ተገንዝቦ በእንጭጩ ማስተካከል ያሻል፡፡
‹‹በሌላ አነጋገር ድህነት፣ መገለል፣ ተስፋ መቁረጥ፣ የክብር መዋረድና መብት መነፈግ ከጥይት ይበልጥ ቀስ በቀስ በሚያሰቃይ ሁኔታ ሕይወትን ለማጥፋና ዋጋ ቢስ ለማድረግ ችሎታ አላቸው፡፡ ነገር ግን እንደ ጦርነትና ሌሎች የኃይል ሥራዎች ጉልህ ሆነው በገሃድ አይታዩም፡፡ ሥራቸው የረቀቀና ሥውር ነው፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበረሰብ መዋቅር ላይ የተመሠረቱ ጭቆናና መገለሎች ናቸው ሥርዓታዊ ሁከት ተብለው የሚጠሩት፡፡›› (ገጽ16)
መንግሥትና ፖለቲከኞቻችን በተገቢው እንዲፈትሹ የምሻው ይህንን ዓይነቱን የግጭት መንስዔ ነው፡፡ መሬት ላይ የሚታይን ሀቅ ትቶ ሌላ ምክንያት ከመፈተሽ በፊት፣ በሥርዓቱም ውስጥ ሆነ በግለሰቦች ጥፋት የሚፈጠርን የሕዝብ ምሬት ማስቀረት ወይም መቀነስ ካልተቻለ ሰላምን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ማቃለል ከተቻለ ደግሞ ሕገወጦች፣ ኢመደበኛ ታጣቂዎች፣ የሰላምና የዴሞክራሲ አማራጮች የሚያውኩትን ሕዝቡ ራሱ ይታገላቸዋል፡፡
በእርግጥ በእኛ አገር ሁኔታ ከጥላቻ ትርክት፣ ከፅንፈኝነትና ከተዛባ የብሔር ዕሳቤ በተነሳ ፖለቲካውን መበረዝና ማቆሸሽ ተለምዷል፡፡ ማኅበራዊ ድረ ገጽና ዘመን አመጣሹን የኢንፎርሜሽን መስተጋብር ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የሚጠቀሙና ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ የሚሹ ኃይሎች እንደሚራኮቱ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንንም ቢሆን ለማረም ብርቱ ጥረት መደረግ ያለበት በፖለቲካው መስክ ቢሆን ይመከራል፣ ካለፈም በሕግና ሥርዓት፡፡
ይሁንና መንግሥትን ጨምሮ ፖለቲከኞች የአገር መከላከያ ሠራዊቱንም ሆነ የፀጥታ ኃይሎችን እንደ ብቸኛ ፖለቲካ መፍቻ በማድረግ ወደ ኃይል ዕርምጃ ማስገባትም ሆነ መጋጨትን ልብ ሊሉ ይገባል፡፡ የአገርን ሕዝብ የወል ጠባቂን በየጢሻውና በየመንደሩ እያንከራተቱ ያልተገባ ዋጋ ማስከፈልም ሆነ፣ ንፁኃንን ለጥቃት ማጋለጥም ትክክልና ተገቢ አለመሆኑ መጤን አለበት፡፡
አገር ከፖለቲካም በላይ ነው። የመከላከያ ሠራዊቱ ደግሞ በትዕግሥትና በዲስፒሊን የተገነባና የተደራጀ ኃይል መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱን የቻለ አገር እንደ መሆኑ ቆም ብሎ ከየትኛውም የፖለቲካ ተፅዕኖ ራሱን መጠበቅ አለበት፡፡ ይህ እሳት የሚተፋ ትጥቅ ከአፍ እስከገደፉ የታጠቀ ኃይል ከመላው የአገሪቱ ሕዝቦች የተውጣጣ እንደ መሆኑም፣ ጥራትና ብዛቱ ብቻ ሳይሆን አገራዊ ስሜቱ እንዲዳብርና የመላው ሕዝብ ባለአደራ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
ሠራዊቱ እኮ አገረ መንግሥቱን ከየትኛውም ጥቃት ለመመከቻና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተደራጀ ነው፡፡ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የሰላም አለኝታ የነበረን ሠራዊት የሰላም ጠባቂ ማድረግ ግድ ቢሆንም፣ ዋናውን አገራዊ ተልዕኮ ስቶ እንዲባክን አልፎ አልፎም ለጥቃት እንዳይገለጥ መንግሥት የፖለቲካ መፍትሔን ማስቀደም አለበት፡፡
ይህ እውነታ እየታወቀ አንዳንድ የፖለቲካ ጥያቄ ያላቸውና የውስጥ ምንደኛ የሚባሉ ኃይሎች፣ በውጭ ኃይሎች ገፋፊነትና በፖለቲካ ነጋዴዎች ውንብር ሠራዊቱን ወደ መፎካካርና ማስቆጣት ከመግባት መቆጠብ አለባቸው፡፡ በአገር ወዳዱ ሕዝብም ‹‹ተው!›› ሊባሉ ይገባል፡፡ እንደ አገር የፖለቲካ አለመግባባት ቢኖር እንኳን፣ የፀጥታና የፍትሕ አካላትን በጋራና ገለልተኛ ሚናቸው አክብረን ማስከበር የሁላችንም ግዴታ ሊሆን ይገባል፣ ይታሰብበትም፡፡
በሌላ በኩል የፖለቲካ ተዋንያን ሁሉ አቁሙ መባል ያለባቸው፣ የኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ከሚያጠናክሩ ተግባራት ይልቅ የመነጣጣልና የመባላት ፖለቲካን ማቡካትን ነው፡፡ አሁን የተጀመረው የለውጥ ሐሳብ ከአምስት ዓመታት በፊት ሲቀነቀን የተዳከመውን አገራዊ አንድነት ለማጠናከር ግብ ማስቀመጡ እየተዘነጋ፣ ዛሬ ሁሉም እየተነሳ የጓዳውን ጣጣ ብቻ ሳይሆን ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር የሚያባላውን ትርክት (አንዱ በሌላው ጫማ እየቆመ ከመወዳደር ይልቅ) ሲያበኮና ሲጋግር ማዋል ማደሩ አደብ ሊይዝ ይገባል፡፡ ሕዝቡንም ወደ አልሆነ አቅጣጫ ከመምራት መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ሁሉም የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና እንደ ፌዴሬሽን ምክር ቤትን የመሰሉ አካላት ዋነኛ ተግባራቸው አድርገው መገኘት አለባቸው፡፡ ለነገሩ የትምህርት ተቋማት፣ ሚዲያዎችና የእምነት ተቋማትም ቢሆኑ ከመለያየትና ከመባላት ይልቅ ለአብሮነትና አገራዊ አንድነት ጉልበታቸውን ቢያውሉና ለዴሞክራሲና ለአገር መለወጥ ቢተጉ በጠቀመ ነበር፡፡
እዚህ ላይ ከወራት በፊት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣንና ከኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጋር፣ በትብብር መሥራት የሚያስችለውን የአገራዊ አንድነትና የጋራ እሴቶች ግንባታ ማጠናከሪያ መግባቢያ ስምምነት መፈራረሙ አንድ በጎ ዕርምጃ ነበር፡፡ አገራዊ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑና መሰል መንግሥታዊ አካላትም ከዝግጅት ሸብ ረብ ወጥተው፣ በፍጥነት ወደ ተግባር ሊገቡ ግድ ይላል፡፡ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ካስፈለገም በመተግበር ጭምር፡፡
በወቅቱ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዲማ ዲልቦና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ትነበብ ብርሃኔ ተገኝተው አሁን ያለውን አገራዊ ችግር ያለ ልዩነት በማውሳት መፍትሔው ወደ ተግባር መግባት ነው ማለታቸው በጎ ዕርምጃ ነበር፡፡ ሕዝቡም ግን ጠባችሁ አታጋቡብን፣ አታባሉን፣ አብሮነታችን ላይ ሥሩ ብሎ ሊነሳ ግድ ይለዋል፡፡
ሌላው ቀርቶ ከለውጡ በፊት እንኳን የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአገሪቱ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበትና ፍትሐዊ የሀብት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጀማመራቸው ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ በተገባ ነበር፡፡ እንደ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን፣ የመከላከያ ቀን፣ የባንዲራ ቀን፣ ወዘተ ዓይነቶቹ አገራዊ የጋራ እሴቶች መገንቢያ ሁነቶችን አስቁሞ፣ በየትምህርት ፖሊሲዎች ላይ ማስተካከያ እያደረጉ የተናጠልና የጋራ እሴቶች ማጠናከርን ገትቶ፣ የራስ የራስን ማቀንቀን አገር ሊያፀና አይችልምና ይብቃን፡፡
በወቅቱ የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት መንግሥት ብቻ ሳይሆን ድርጅቶቹ ሚናቸውን ይበልጥ በማስፋት ለአገር ዕድገትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል፡፡ ግን የሕግ ተገዥነት፣ ሕገ መንግሥታዊነት፣ ግጭት አፈታትና የሰላም ግንባታ የትብብሩ መስኮች መሆናቸውን ከመግለጽ ባሻገር በቀውስ ውስጥም ቢሆን ሥራ አለመጀመራቸው ለምን መባል አለበት፡፡ ምን እስኪመጣ ነው የሚጠበቀው?
በሦስተኛ ደረጃ መጤን ያለበት ሁሉም የአገራችን ክልሎችና አስተዳደሮች የዴሞክራሲ ምኅዳርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በትጋት ለመቅረፍ መነሳት እንዳለባቸው ግልጽ አቋም ሊያዝ ይገባል፡፡ ለውጡንም ሆነ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡና ችግር ፈጣሪዎች ላይ መጠነ ሰፊ ዕርምጃ እየወሰዱ አገርን መታደግ የመንግሥት ግዴታም መሆን አለበት፡፡ ሙሉ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ከዚህ በላይ ምን ኃላፊነት አለበትና ነው በግልጽ እየታየ ያለን ችግር እያድበሰበሰ ችግሩን በጉልበት ሊገታ የሚመኘው? የውስጡን ትቶ ወደ ውጭስ ሲያማትር የሚኖረው?
እስካሁንም በሙስናና በብልሹ አሠራር ምክንያት በየቦታው በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ከሥራ ከማስወገድ አንስቶ እስከ ደረጃ ማሳነስና ማሰናበት የደረሱ ልዩ ልዩ ውሳኔዎች ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ እውነታው ግን አሁንም የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የእሳት አሎሎ ሆኗል፡፡ የእሳት አሎሎን ደግሞ ማን ታቅፎ መቆየት ይችላል? ከላይ የተወረወረልህን ወይም የተወረወረብህን የእሳት አሎሎ አንተም በተራህ ቁልቁል እየወረወርክ አሽቀንጥረህ ካልጣልክ በቀር፣ መላቀቂያ የለምና ሕዝቡም ሰላማዊውን ትግል ማድረግ አለበት፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ የመልካም አስተዳዳር ብልሽት ችግር ሲነሳ፣ የምናተኩረው በአብዛኛው በጉቦ ላይ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በየምክንያቱ ለስብሰባና ለግብዣ የሚባክኑ ገንዘቦች፣ የመንግሥትን መኪና ለግል ጉዳይ መጠቀም፣ ተገቢ ያልሆነ የውሎ አበል፣ በየመሥሪያ ቤቱ በጥቅማ ጥቅም መልክ ለክበብ፣ ለመስተንግዶ… ወዘተ ለመሳሰሉት የሚባክኑ ገንዘቦች ጉዳይ ላይ የመረረ ትግል መደረግ አለበት፡፡ ምዕመኑ በተሳዳቢው ቄስ ላይ በአንድ ተነስቶ ስድብህን አቁም እንዳለው ሁሉ፣ ዘጋው ሌብነትና መንግሥታዊ አባካኝነትን አቁሙልን ሊል ይገባዋል፡፡
በሌላ በኩል ከለውጡ በፊትም ሆነ በኋላ በየአካባቢው በስፋት እየተነሱ የነበሩና/ያሉ ጥያቄዎችስ መቼ ነው የጋራ መፍትሔ እንዲሰጣቸው የሚሞከረው? ለአብነት ያህል (1) የፊንፊኔ ዙሪያ ፖለቲካ ተግባራዊ ሊሆን ሲል ተቃውሞ መጣ ተባለና ጉዳዩ ቀረ (ተሰረዘ) ተባለ፡፡ እርግጥ ዘግየት ብሎም ቢሆን በሸገር ከተማ ምሥረታና በአዲስ አባባ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ተጠቃሚነት ሊመለስ ተሞክሯል፡፡ (2) የወልቃይትና የራያ የማንነት ጥያቄዎች ግን በፍጥጫና በግጭት ከመለወስ ውጪ መቋጫ አላገኙም፡፡ (3) ብሔር ብሔረሰቦች በፈቀዱበት ቦታ በሰላም የመኖርና የመንቀሳቀስ መብት መቼ ተመለሰ? (4) የትግራይ ኃይሎች፣ የኦነግ ሸኔና አሁን ደግሞ የአማራ ታጣቂዎች የግጭት መነሻ መፍትሔና ቀጣይ ዕጣ ፋንታስ ምንድነው? (5) የብሔራዊ ዕርቅና መግባባት የዘመናት ጥያቄዎችስ በድፍረት ተነስተው ሕዝብ የማይደመጠው እስከ መቼ ነው? ማለት ይገባል፡፡
ሌላው ጥያቄ ‹‹ለወጣቶችና ለሴቶች የሥራ ዕድሎች በበቂ መጠን የለም፡፡ ምን እየተሠራ ነው?›› የሚለው ነው፡፡ ሆን ብለን ካልተውነው በስተቀር አንዱ የህልውና ጉዳይ ይህ ነው፡፡ የሥራ ዕድል ማለት ሁሉም ነገር ማለት ነው፡፡ ገቢ ማግኘት፣ ቤት መከራየት መቻል፣ በቅ ምግብና ልብስ ማግኘት፣ ትዳር መሥርቶና ልጆች አፍርቶ በወግ እያስተማሩ መኖር፣ ወዘተ ማለት ነው፡፡ ሥራ ሲጠፋ ዘረፋ፣ ውንብድና፣ አመፅ እንደሚተኩም የታወቀ ነው፡፡
እውነት ለመናገር አሁን አሁን እየታየ ያለው ነገር ሕዝብን አዳምጦ ብዙኃኑን ባማከለ መንገድ ሕግጋት ከማውጣትና ከመተግበር ይልቅ፣ በድርጅት ወይም በአንድ ወገን ተወካዮች አዲስ ነገር ፈጥሮ ሕዝብ ላይ መጫን እየታየ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በአፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ችግር ከመፍጠሩም ባሻገር ቅቡልነትም ሲያጣ እየታየ ነውና አስተካክሉ ሊባል ይገባል፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ፓርላማ አዋጅ ያፀድቃል፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስችል ደንብ ያወጣል፡፡
ሥራውን የሚያስፈጽመው መሥሪያ ቤት (ተቋም) ደግሞ ደንቡን ለማስፈጸም መመርያ ያዘጋጃል፣ መመርያ ማዘጋጀት ደግሞ ጊዜ የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ አዋጁና ደንቡ መሬት ላይ ሲወርዱ ምን አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ውጤት ሊያስገኙ እንደሚችሉ ከወዲሁ የማወቅ ችሎታን፣ ትዕግሥትን፣ ኃላፊነትንና አርቆ አስተዋይነትን የሚፈልግ ሥራን ቸል ማለት ግን ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ይህን አካሄድ ለማስተካከል ቢያንስ ለማሻሻል አለመሞከርን ተው መባል አለበት፡፡
በአጠቃላይ ፖለቲከኞችና ራሱ መንግሥት እንደ ነገረኛው ሰባኪ ሕዝብ የጠላባቸውን፣ አገር ያልወደደላቸውን ንግግርም ሆነ ተግባር መተው አለባቸው፡፡ መተው ብቻ ሳይሆን የሚበጀውን ትህትናና አገር ወዳድነትም በተግባር ሊያሳዩ ግድ ይላል፡፡ በውሸት፣ በመቀናናት፣ በመስገብግብና በጠላት ማብዘት የሚገነባ አገር ወይም የሚገኝ ብልፅግና እንደሌለ ተገንዘበውም ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ እንሻለን፡፡ ሕዝቡም በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ኃላፊነታችሁን ተወጡ ሊል ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡