Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሆድና የሆድ ነገር

ሆድና የሆድ ነገር

ቀን:

(ክፍል አሥራ ሦስት)

በጀማል ሙሐመድ ኃይሌ (ዶ/ር)

“እንጀራ ካልበላሁ፣ የበላሁ አይመስለኝም”

“እንጀራ ባይኖር ምን መብላት ይቻላል?” ለሚል ሰው፣ “ዳቦ፣ ቂጣ፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ሩዝ…” እያላችሁ እንዳትደክሙ፡፡ ከደከማችሁም ጥፋቱ የራሳችሁ ነው፡፡ “እንጀራ ካልበላሁ፣ ምግብ የበላሁ አይመስለኝም” የሚሉ ስንትና ስንት ሰዎች እንዳሉ አለማወቃችሁ ነው ለዚህ የዳረጋችሁ፡፡

በነገራችን ላይ፣ ከእንጀራ ውጪ የሆነን ምግብ ከበሉ በኋላ “ማጥበቂያ” የሚባለው ስለቀረባቸው እንዳይመስላችሁ፡፡ “ማጥበቂያ” ማለት፣ አንድ ሰው ለምሳሌ ምሳ ወይም እራት ከበላ በኋላ (የበላው ምግብ እንጀራ ሊሆን ይችላል)፣ በተጨማሪነት የሚበላው ምግብ ነው፡፡ ያ ምግብ ዳቦ፣ ቂጣ፣ ቆሎ ወይም ፍራፍሬም ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ ከሰው ቤት (በግብዣ፣ በሠርግ፣ ወዘተ. ምክንያት) በልቶ ከሆነና በደንብ አልጠገብኩም ብሎ ካሰበ ከቤቱ ከተገኘው ምግብ ጥቂትም ቢሆን ይበላል ማጥበቂያ መሆኑ ነው… “ማጥበቂያ” ምግብ ከበላን በኋላ ሆዳችን “ጥብቅ” እንዲል ማለትም፣ ሙልት እንዲል ወይም ሙልት ብሎ እንዲሰማን የምንፈልግ መሆናችንን የሚያመላክት ነው፡፡) 

እናም ሐበሾችን፣ “እንጀራ ካልበላሁ፣ የበላሁ አይመስለኝም” ለማለት ያበቃቸው ነገር፣ ሚስጥሩ ምን ይሆን? ከእንጀራ ውጪ የሆነ ምግብ ሆዳቸው እስከሚሞላ (ማጥበቂያ በማያስፈልገው ደረጃ) ከበሉ በኋላ፣ የበላሁ የማይመስላቸው ሚስጥሩ ምን ይሆን?

“እንጀራን ከልክ በላይ ከመውደዳችን የመነጨ ነው” በማለት የሚቀርበው ምክንያት፣ ጉዳዩን ከላይ ከላይ ከማየት የዘለለ አይሆንም፡፡ ሥረ መሠረቱን ፈንቅሎ የሚያስረዳ ሳይንሳዊ መልስ ሊፈለግለት “ይገባል” ባይ ነኝ፡፡

ሐበሾች ሆዳቸው እስከሚሞላ ድረስ ሌላ ምግብ በልተው ሲያበቁ፣ የበላሁ የማይመስላቸው አብዛኛውን ዕድሜያቸውን እንጀራ ሲበሉ ስለኖሩ፣ ከእንጀራ ጋር የተፈጠረ ልክ የለሽ ቁርኝት ያሳደረባቸው ሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖ ውጤት ይሆን? ወይስ እንጀራ በውስጡ ባለው የተለየ ንጥረ ነገር? ወይም እንጀራ ባለው ጨጓራ ላይ ሄዶ የመጎዝጎዝ ባህሪው? ወይስ በዚህ ሁሉ ድምር ምክንያት ይሆን ሐበሾች ከእንጀራ ጋር ሙጭጭ ያሉትና “እንጀራ ካልበላሁ፣ ምግብ የበላሁ አይመስለኝም” እስከማለት የደረሱት? የመስኩ ባለሙያዎች የዚህን ቅኔያዊ ፍች በሳይንሳዊ መንገድ ቢፈትሹት… 

በባህር ዳር መምህራን ኮሌጅ፣ የፔዳኮጂካል ሳይንስ የአንደኛ ዓመት ተማሪ እያለሁ፣ ለምሳ እንሠለፋለን፡፡ ከምሳ ሰዓት በፊት ቀደም ብለው ከተሠለፉት ተማሪዎቸ መካከል በተለይም ወደ ሠልፉ መጀመሪያ አካባቢ ያሉት (በወቅቱ “የምግብ ሥቃይ” የምንላቸው) አስተናጋጆቹ ሲያቀራርቡ በዕለቱ የሚቀርበውን የምግብ ዓይነት ቀድመው የማየት ዕድል ነበራቸው፡፡ ከኋላ አካባቢ የተሠለፍነው በዕለቱ ለምሳ ወይም ለእራት የቀረበው ምግብ ፓስታ ወይም ማካሮኒ መሆኑን በቀላሉ ነበር የምናውቀው፡፡ እንዴት? ጥቂት የማይባሉት የፊት ተሠላፊዎች ፓስታ ወይም ማካሮኒ ሲቀርብ እንዳዩ፣ በብስጭትና በንዴት እጃቸውን ያወራጫሉ፣ አንዳንዶቹ ራሳቸውን ይይዛሉ፣ ሌሎቹ ፊታቸውን ወደ ኋላ ያዞራሉ፡፡ (እኔ ግን በተቃራኒው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ምናልባት እናቴ አልፎ አልፎ ማካሮኒ እያዘጋጀች ታበላን ስለነበር ሊሆን ይችላል፡፡)…

እ.ኤ.አ. በ2008 ለፒኤች ዲግሪ ትምህርት ህንድ አገር፣ ቪሻካፓትናም ከተማ ወደሚገኘው አንድራ ዩኒቨርሲቲ በሄድኩበት ወቅት፣ ቀድሞን ለትምህርት የሄደውና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቅርብ ባልደረባዬ የነበረው ዝይን እንግዳ ሰው (አሁን ዶ/ር) ምሳ ጋበዘኝ፡፡ ወደ ዶርሙ ሄድኩ፡፡ ሽሮ ወጥ ሠርቷል፡፡ በስስ በስሱ እየተደረገ በአራት ማዕዘን ቅርፅ የተቆረጠ እሽግ ዳቦ አቀረበ፡፡ እሽጉን ፈታና ቁራጭ ዳቦዎችን ከሳህኑ ላይ “ማንጠፍ” ጀመረ በመካከላቸው ክፍተት እንዳይኖር እየታገለ፡፡ ለወጥ ማድረጊያ/ማቅረቢያ ሌላ ዕቃም አላቀረበም፡፡ ነገሩ ግራ ገባኝ፡፡

“ዝይን ምን ማድረግ ነው የፈለከው?” በማለት ጠየቅኩት፡፡

“ዳቦውን አጠጋግቼ ከዘረጋሁት በኋለ፣ ከላዩ ላይ ወጡን ማድረግ ፈልጌ ነው፡፡”

“ለምን?”

መልሱ አጭር ነበር “እንጀራ እንዲመስለን፡፡”…

እዚያው ህንድ እያለን፣ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አብሮኝ ለትምህርት የሄደው መስፍን ተሻገር (አሁን ዶ/ር)፣ ህንዶች በእነሱ ዘንድ ተወዳጅ የሆነ ስስ ቂጣ (ቻፓቲ) የሚጋግሩበትን አነስ ያለ የኤሌክትሪክ ምጣድ ገዛ፡፡ ቂጣም “ቻፓቲም” ሲጋግርበት ትንሽ ከቆየ በኋላ፣ አንድ ቀን ምሳ ጋበዘኝ፡፡ ከቂጣም፣ ከቻፓቲም ራቅ ያለ፣ ወደ እንጀራ መንገድ የጀመረ፣ ሆኖም ከእንጀራ ያልደረሰ ወይም ለመድረስ ትንሽ የቀረው ምግብ አቀረበልኝ፡፡ “ቂጣ” ወይም “ቻፓቲ” እንዳይባል ዓይን አለው፡፡ “እንጀራ” እንዳይባል ዓይኖቹ በደንብ አልወጡም፡፡ በዚህ ላይ ከወደ ሥሩ በመጠኑም ቢሆን የቂጣነት ባህሪና መልክ ነው ያለው፡፡ የቸገረ ነገር!

ይህን የምላችሁ ግን አሁን ነው፡፡ ያኔማ “ቪሻካፓትናም ላይ እንጀራ ተገኘ” እያልን ነው ያነከትነው፣ እኔም ሆንኩ በሌላ ጊዜ የተጋበዙ ኢትዮጵያውያን፡፡ ሆዳችንም እንጀራ እንደበላ አምኖ፣ በደንብ ሙልት ብሎ ነበር…  

ሰሞኑን አማራ ክልል በነበረው የፀጥታ ችግር፣ ባህር ዳር ከተማ ለሳምንት ያህል ጊዜ ገበያ፣ ሱቆችና ድርጅቶች ተዘጋግተው ነበር፡፡ በመሆኑም የጤፍ ዱቄት ያለቀባቸው ሰዎች እቤት ያላቸውን ማካሮኒ፣ ፓስታና ሩዝ በማብሰል እየበሉ ለመቆየት ተገደዱ፡፡ እናም አንዳንዶቹ (ምሁራን ጭምር) “ፓስታና ማካሮኒ ያስርበናል” ሲሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ “ከሆዳችን አልቆይልን አለ” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ባለፈው ዓመት በሰሜን በኩል በነበረው ጦርነት በበርካታ ወራት ለሚቆጠሩ ጊዜያት ከግብይትና መሰል አገልግሎቶች ርቀው በከረሙት አካባቢዎች ከሚገኙት ሕዝቦች መካከል፣ እንጀራ ማብሰልና መብላት ያልቻሉት ሰዎች ሩዙን፣ ፓስታውን፣ ማካሮኒውን፣ የተገኘውን… ሲበሉ የማስራቡ ነገር፣ ከሆድ ውስጥ አልቆይ የማለቱ ነገር እንዴት አድርጓቸው ይሆን? ነው ወይስ፣ ሰላም ከሰማይ ሲርቅና ተስፋው ሲመነምን “የለመድኩትን እንጀራ ካላመጣችሁ” በማለት የረሃብ ሠራዊት የሚልከው ቀልድ አያውቄው ሆድ፣ ክፉ ቀን ላይ መሆናቸውን አውቆ የሩሃብ ሠራዊቱን አግቶላቸው ይሆን?

ወይስ ደግሞ ከእነ ተረቱ “ቁርጥ ያጠግባል” ነውና አዕምሯቸው እንጀራ እንደማይገኝ ቁርጡን ሲያውቅ፣ “እንጀራ፣ እንጀራ” እያለ “በቅብጠት” ለሚያላዝነው ሆዳቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንጀራ እንደማይገኝ ስላሳወቀው፣ በጉሮሮ ቦይ የተላከለትን በፀጋ በመቀበልና “ተመስገን” በማለት ከቋቱ ላይ በማቆየት ጭምር አርፎ ተቀምጦ ይሆን?

ወይስ ደግሞ እንጀራ በበሉበት ጊዜና እንጀራ ሊያገኙ በሚችሉበት ጊዜ መካከል ያለው ርቀት እየሰፋ በሄደ ቁጥር፣ ማለትም እንጀራ የተበላበት ብቻ ሳይሆን የታየበት ጊዜ ከሳምንታት ወደ ወራት ከዚያም ወደ ዓመት እየተቃረበ በሄደ ቁጥር፣ አቶ ሆድ የነበረው የደነደነ የእንጀራ ፍቅሩ መለዘብ በመጀመሩ፣ በጉሮሮ ቱቦ የወረደለትን ምግብ ከፀጋ በመቁጠር “እንጀራ፣ እንጀራ” የሚል ጩኸቱን አቋርጦ ይሆን? ወይስ ደግሞ…

(በሰሜን በኩል በነበረው የጦርነት ወቅት ዳቦ ካየ ብዙ ወራት ያለፈው ሕፃን፣ “ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋህ?” ሲሉት፣ “ዳቦ መግዛት” ብሎ መመለሱን ስሰማ አንጀቴን በላኝ…) 

ለማንኛውም፣ “ፓስታና ማካሮኒ ያስርበናል” እና “ከሆዳችን አልቆይልን አለ” የሚሉትን ሐሳቦች ትንሽ ፈታ አድርጎ ማየት ያስፈልገናል፡፡ 

እንጀራ ከማሽላ፣ ከገብስና ከሩዝ ዱቄት እንደሚጋገር ሁሉ፣ ከስንዴ ዱቄትም መጋገር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በሳዑዲ ዓረቢያ ጅዳ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፊኖ ዱቄት ብቻ እንጀራ እየተጋገሩ ይሸጣሉ፡፡ እንጀራው ከገብስም ሆነ ከሩዝ ወይም ከሌላ ዱቄት፣ በዚህ ምክንያት ተራብኩ ወይም “ከሆዴ አልቆይ አለኝ” የሚል ሰው አልሰማንም፡፡ ዋናው ነገር እንጀራ ከመሆኑ ላይ ነው፡፡

የሩዝ እንጀራም ሆነ የስንዴ እንጀራ ሆድ ላይ የሚቆይ ወይም የማያስርብ ከሆነ፣ ፓስታና ማካሮኒ ከስንዴ የሚሠሩ ሆኖ እያለ፣ እነፓስታና ሩዝ ለምን ይሆን ከሆድ ላይ መቆየት የተሳናቸውና በተመጋቢያቸው ላይ ረሃብ የሚለቁበት? ወይስ ነገሩ የሥነ ልቦና ጉዳይ ነው ሆድ መሙላትንና መጥገብን ከእንጀራ ጋር አያይዞ ያደገ ሰው፣ ሌላ ዓይነት ምግብ ሲበላ የለመደውን ዓይነት እርካታ ያጣል? ወይስ ደግሞ ነገረ ሚስጥሩ ከቡኮው፣ በምጣድ ከመብሰልና ጠፍጣፋ ቅርፅ ከመያዝ ላይ ነው ያለው? ወይስ… የመስኩ ምሁራን ቢመራመሩበት አይከፋም፣ ጉዳዩ የምግብ አማራጮቻችንን እንዳናሰፋ ቀፍድዶ ይዞናልና… 

ከበሉ በኋላ ቶሎ ያለመራብ ወይም የምግብ ሆድ ላይ የመቆየት ጉዳይ ከተነሳ፣ ቂጣም ሆነ ገንፎ ሆድ ላይ እንደሚቆይ የሚናገሩ ሰዎች አሉ፡፡ ምሽቱ ዳር ዳር ሲል ወደ ጭማቂ ቤት ጎራ በማለት፣ አንባሻና ዳቦን በአቦካዶ ጭማቂ እያማጉ በልተው ራታቸውን “የሚዘጉ” የአዲስ አበባና የአንዳንድ ከተማ ወጣቶችና ጎልማሶች፣ ይኼ ምግባቸው ሆድ ላይ እንደሚቆይ አምነው ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ለማትሪክ ፈተና ጋምቤላ ከተማ በሄድኩበት ጊዜ የታዘብኩት ተጨማሪ ሀቅ ይኼው ነው አቦካዶ በአብዛኛው በፍሬ ነው የሚሸጠው፡፡ ይቆራረጥና ከዳቦ ጋር በመሆን ቁርስም፣ ራትም ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሆድ ላይ ይቆያል ማለት ነው (?)፡፡

“ዘመናዊው” ምግብ ዳቦ በአቦካዶ ይቅርና ጥንታዊዎቹ ቂጣና ገንፎ እንኳን የረሃብ መድኃኒት ተደርገው አልተቆጠሩም ተረታችን የሚነግረን “እንጀራ ለረሃብ፣ ድንጋይ ለካብ” በማለት ነውና፡፡ (“ወፍከሌ” ከሚባል የገጠር ቀበሌ ወደ ከደሴ ከተማ በእግር ሲኬድ የምትገኝ አንዲት አደገኛ አቀበት አለች በዋዛ የማትገፋ/የማታልቅ፡፡ ስሟ “ምስር ቂጣ” ይባላል፡፡ ቂጣ ከምስር ዱቄት ከተዘጋጀ ሆድ ላይ በመቆየት ምናልባትም እንጀራን ያስንቅ ይሆናል፡፡ ከምስር ዱቄት የተጋገረን እንጀራ ግን ሊያስንቅ አይችልም፡፡ ለምን? ሰውዬው እንጀራ ነዋ!)፡፡

እንደ ገና ወደ ህንድ ገጠመኜ ልመልሳችሁ (“የህንድ ወሬ በዛብን” ባትሉኝ አይደል፡፡) ስድስት ወራት አካባቢ ለሚቆይ ትምህርት በሄድኩበት ወቅት ያጋጠመኝ ነው እ.ኤ.አ. በ1999፡፡ ሁለት ጓደኞች ነበሩኝ ቴጉህ ሀንዴኮ ከኢንዶኔዥያ፣ ዞንጎ ከቡርኪና ፋሶ፡፡ ትምህርቱን ስፖንሰር ያደረገን የህንድ መንግሥት ነበር፡፡ የሚሰጠን ገንዘብ እዚያ ላለ ኑሯችን በቂ ነው፡፡ ሆኖም ዞንጎ በደንብ መቆጠብ ፈለገ፡፡ ምክንያቱን ነገረን፣ “አገሬ ስመለስ ቤት መሥራት አለብኝ፡፡ ደመወዜ ደግሞ ቤተሰቤን ከመቀለብ አያልፍም፡፡”

እናም ዞንጎ በጣም ርካሽ ሆኖ ያገኘውን አትክልትና ፍራፍሬ መመገብን ምርጫው አደረገ፡፡ ከሳምንት በላይ ብዙም አልቆየ፡፡ ቀጭን ሰውነቱ፣ መክሳት ያዘ፣ በቀላሉም ይደክመውና አቅም ያንሰው ጀመረ፡፡ በአጭሩ ልፍስፍስ ብሎ ቁጭ!

ቴጉህና እኔ አትክልትና ፍራፍሬ ብቻ መመገቡን ትቶ፣ ኃይል ሰጪና አልሚ ምግቦችን እንዲበላ፣ ካልሆነ ለበሽታም ጭምር ሊጋለጥ እንደሚችል መከርነው፡፡ ቴጉህ ምን ቢለው ጥሩ ነው?

“ሩዝ እየቀቀልክ ብላ፡፡ ሩዝ ሆድ ላይ ይቆያል፡፡” (ልብ በሉ፣ ሐበሾች “እንጀራ ሆድ ላይ ይቆያል” ስንል፣ ኢንዶኔዥያውያን በበኩላቸው “ሩዝ ሆድ ላይ ይቆያል” ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል የእኛ አገር ሰው፣ በኢንዶኔዥያውያን ተቃራኒ፣ “ሩዝ ሆድ ላይ አይቆይም” ይላል፡፡ ምናልባት ኢንዶኔዥያውያን እንጀራ በበሉ “እንጀራ ሆድ ላይ አይቆይም” ይሉ ይሆን?… ይህ ቢሆን እስካሁን ያነታረከን ነገር ቢያንስ በግማሽ “መልስ አገኘ” ማለት ነበር….

ለማንኛውም የዞንጎ ነገር ከተነሳ፣ አንድ ነገር ሁሌ አብሮ ትዝ ስለሚለኝ እሱን ላካፍላችሁ ያው ከሆድ ጋር የተያያዘ ነገር! ኒውደልሂ ውስጥ ተልከስካሽ ውሻዎች ሞልተዋል ልክ እንደኛው አገር፡፡ የሆነ ሰውነቱ ሞላ ሞላ፣ ፈርጠም ፈርጠምጠም ያለ ውሻ ባየ ቁጥር፣ “ይኼ በጣም ምርጥ ነው” ይላል በአፉ ምራቅ እየሞላ፡፡ “ለምን?” ካላችሁ፣ የውሻ ሥጋ ስለሚበሉ፡፡ የውሻ ሥጋ ሆድ ላይ ስለመቆየት አለመቆየቱ ግን አላወራንም…

 ወደ እንጀራችን ስንመለስ ለእንጀራ የተሰጠው ቦታና ክብር ከማጥገብና ሆድ ላይ ከመቆየት ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፡፡ እስቲ “አንድ እንጀራ የጣለውን፣ አምስት እንጀራ አያነሳውም” የሚለውን አባባል ልብ ብለን እንየው፡፡ እዚህ ላይ “እየተሞካሸ” ያለው የእንጀራ ሚና፣ ሆድ ከመሙላትም፣ ረሃብን ከመከላከልም ሆነ ሆድ ላይ ከመቆየትም በላይ ነው፡፡ የንፅፅሩን ጉልበት ልብ በሉልኝ፡፡ ሰውዬን የጣለው አንድ እንጀራ ሲሆን፣ የዚያ አንድ እጥፍ (ሁለት እንጀራ) ወይም ሁለት እጥፍ (አራት እንጀራ) ሊያነሳው አይችልም፡፡ አምስት እንጀራም አያነሳውም፡፡ ምናልባት ሦስት እጥፍ (ስድስት እንጀራ) ያነሳው ይሆናል… (ይህች ብሂል ብዙ “ጉድ” የያዘች ናት፡፡ በሚቀጥለው እናየዋለን፡፡)

እንጀራን አዘውትሮና ሳያቋርጡ መብላት ጠቃሚ መሆኑ ከላይ በቀረበው መንገድ ነው የተገለጸው፡፡ ይህን የማያውቅ አንድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን ያሰለጥን የነበረ ፈረንጅ፣ ሠልጣኞቹ እንጀራ በማዘውተራቸውና ሌሎች ምግቦችን አመጣጥነው መብላት “ባለመቻላቸው” (ባለመፈለጋቸው) የሰውነት ጥንካሬ ማጣታቸውን በማውሳት በምሬት ሲናገር በቴሌቪዥን መስማቴን አስታውሳለሁ፡፡ ምን ማለት ይሆን ያለብን? “አይ የፈረንጅ ነገር!” ወይስ “አይ የእንጀራ ነገር!”፡፡

(በክፍል አሥራ አራት እንገናኝ ኢንሻ አሏህ!)

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው jemalmohammed99@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...