ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሰው የራሱ የሆነ የፈጠራም ሆነ የቢዝነስ ሐሳብ ይዞ ቢቀርብም ባለው የአሠራር ክፍተት ምክንያት ካለመበት ቦታ ሳይደርስ የሚቀረው ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ በተለይም በአገሪቱ የሚታየው የብድር አሠራር ወይም የኮላተራል ሁኔታ ምቹ ባለመሆኑ የተነሳ በርካታ የፈጠራ ሐሳቦች ከሜዳ እንደቀሩ ይወሳል፡፡ ይህንንም አሠራር ለመቅረፍ መንግሥትም ሆነ ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋሞች እየሠሩ ቢሆንም፣ ችግሩ አሁንም አልተቀረፈም፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ችግር ለመቅረፍና ማኅበረሰቡን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ ዕልባት ሶሉውሽን እየሠራ ይገኛል፡፡ አቶ ነፃነት እራያ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የድርጅቱን ሥራ አስመልክቶ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ዕልባት ሶሊውሽን ዓላማው ምንድነው?
አቶ ነፃነት፡- ዕልባት ሶሉውሽን በዋናነት ዓላማ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የፋይናስ አገልግሎትና የኢኮኖሚ ኢምፓወርመንት (ማብቃት) ተደራሽነት የሌላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ከዘርፉ ጋር ማስተሳሰር ነው፡፡ ድርጅቱም በዋነኛነት ትኩረት አድርጎ እየሠራ ያለው በዲጂታል ኢኮኖሚው ላይ ሲሆን የፋይናስ፣ የገበያ፣ የጤና ዘርፎችን ለማኅበረሰቡ በቴክኖሎጂ ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ እነዚህንም አገልግሎቶች የሚሰጡ ተቋማትንም ሆነ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን ማብቃት ወይም ደግሞ በዚህ ቦታ ላይ ማኅበረሰቡ አገልግሎት በመስጠት የተሰማሩ ተቋማትን በዲታጂል ቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው፡፡ ድርጅቱም ከተቋቋመ ሰባት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በተለይም ይህንን አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮችንና ማይክሮ ፋይናንሶች ማብቃት ላይ ትልቅ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ምን ዓይነት ተግዳሮት ገጥሟችኋል?
አቶ ነፃነት፡- እንዲህ ዓይነት ሥራዎች ሲሠሩ እንደ አፍሪካ ወይም ደግሞ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ላይ የሚታየው አንዱና ዋነኛው ችግር የመሠረተ ልማት አለመሟላት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በገጠራማ ቦታዎች ላይ ችግሩ ሰፋ ያለ ነው፡፡ በተለይ የኔትዎርክ ዝርጋታ በየቦታው ባለመኖሩ ሥራችን ላይ ችግር ፈጥሮብናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አብዛኛው ማኅበረሰብ በቴክኖሎጂ የመጠቀም ደረጃው በሚፈለገው ልክ ስላልሆነ እንቅፋት ፈጥሮብናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚሠሩ ሰዎች ውስን መሆናቸው ሥራችንን ፈታኝ አድርጎብናል፡፡ በተለይም ደግሞ እንዲህ ዓይነት ሥራዎች በሚሠሩበት ጊዜ የፋይናንስ ሥርዓቱ ከብድር ጋር የተያያዘ መሆኑ ችግር ፈጥሮብናል፡፡
ሪፖርተር፡- ተቋማችሁ ከእነማን ጋር ቅንጅት ፈጥሮ እየሠራ ነው?
አቶ ነፃነት፡- ተቋሙ ተጠቃሚ የሚያደርገው ከስደት የተመለሱ ሰዎችና አካል ጉዳተኞችን ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የፋይናንስ አገልግሎቱ ተደራሽ እንዲሆኑ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተለይም ሥልጠና በመስጠትና የዲጂታል ቴክኖሎጂን እንዲጠቀሙ በማድረግ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ከባንኮች፣ ከማይክሮ ፋይናንስ፣ እንዲሁም ከሌሎች ተቋሞች በምን ዓይነት መልኩ ብድር ሊያገኙ እንደሚችሉ መሠረታዊ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ በተለይም ከኅብረት ባንክ፣ ከንግድ ባንክ፣ ከአማራ ባንክና ከሌሎች ባንኮች ጋር ቅንጅት በመፍጠር ያለ ምንም ማስያዣ እነዚህን ሰዎች ብድር እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡ እንዲህ ዓይነት ብድርም በተለያዩ አገሮች ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በእኛ አገርም ቴሌ ብር፣ ሳፋሪኮምና ሌሎች ተቋሞች በአሁኑ ወቅት ምንም ማስያዣ ብድር እያመቻቹ ይገኛል፡፡ በተለይም የፋይናንስ ቴክኖሎጂ በሠለጠነባቸው አገሮች ይህ አሠራር በሰፊው ይታያል፡፡ በተለይም ትንንሽ ብድር ዋስትና አይጠየቅም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ የቢዝነስ አዋጭነት እንጂ ሌላ መሥፈርት የለውም፡፡ ይህም በቀጣይ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊው የሚሠራ ይሆናል፡፡ የትም አገር የብድር አገልግሎት ተግባራዊ የሚደረገው ‹‹የቢዝነስ ሐሳቡ አዋጪ ነው ወይስ አይደለም?›› በሚል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት የብድር ሥርዓት ብዙም አልተለመደም፡፡ የእናንተ ተቋም ወደ እዚህ አሠራር እንዴት ሊመጣ ቻለ?
አቶ ነፃነት፡- በእርግጥ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዓይነት አሠራር በስፋት አልተለመደም፡፡ ነገር ግን በቅርቡ ብሔራዊ ባንክ ይህንን መሠረት ያደረገ መመርያ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ ከዚህም የተነሳ በዚህ አሠራር በርካታ ተቋሞች የሚጠቀሙ ይሆናል፡፡ የእኛም ተቋም በዋናነት ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ለብድር በሚሆን ደረጃ ከሥልጠና ጀምሮ እስከ መጨረሻው ሒደት ድረስ ተበዳሪዎቹ በባንኮች ተቀባይነት እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታዎችን የሚያመቻች ይሆናል፡፡ ተበዳሪዎችም ብድሩንም ከወሰዱ በኋላ በአግባቡ መመለስ እንዲችሉ፣ እንዲሁም ትክክለኛ የሆነ ቢዝነስ እንዲኖራቸው ከገበያ ጋር የማስተሳሰር ሥራ ተቋሙ የሚሠራ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብድሩን በተገቢው መንገድ እንዲመልሱ መከታተል የተቋሙ ዋነኛ ሥራ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ ውስጥ የኮላተራል ብድር የሚያመቻቹ ተቋሞች በርካታ ሆነዋል፡፡ ይህም በሥራ ፈጠራ የተሰማሩ ሰዎች በፋይናንስ ችግር ምክንያት ወደ ኋላ እንዳይጎተቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ እየታየ ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር በተወሰነ መልኩ ቢሆን የሚቀርፍ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ተቋማችሁ ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ምን ያህል ሰዎችን ተጠቃሚ አድርጓል?
አቶ ነፃነት፡- እስካሁን ከ60 ሺሕ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሠራነው በክልሎች በመሆኑ ውጤታማ መሆን ችለናል፡፡ በዚህ መሠረት 80 በመቶ ያህል ብድር የተመቻቸላቸው በክልሎች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ257 በላይ አባላትን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ አበባን ጨምሮ 10 የሚሆኑ ቢሮዎችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?
አቶ ነፃነት፡- የዲጂታል ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን እንገኛለን፡፡ በትምህርት ቤቶች፣ በገጠራማ ቦታዎች በመሄድ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ በተለይም ማንኛውም ሰው ጤናውን በዓመት ሁለት ጊዜ ቼክ የሚያደርግበትን ሁኔታ እየፈጠርን ነው፡፡ በቴክኖሎጂ የታገዘ የጤና አገልግሎትም ተደራሽ ስናደርግ ከ500 በላይ የሕክምና ባለሙያዎች አብረውን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህ መሠረት አራት ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ማድረግ ችለናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሥራዎችንም ስንሠራ ገጠራማ አካባቢዎችን ተደራሽ የምናደርግ ይሆናል፡፡